ሰላም! ሰላም! አንዱ መጣና ‹‹ከሜሲና ከሮናልዶ ማን ይበልጣል?›› ብሎ አፈጠጠብኝ። ማን ይበልጣል ልበለው? ማንን እንደሚያስበልጥ በምን አውቃለሁ? አሁን እስኪ ቁስ አካል ከሰው በበለጠበት ዘመን ሰው ከሰው በለጠ አልበለጠ ምን ፋይዳ አለው እያልኩ ተጨነቅኩ። ካልነገርከኝ ብሎ ሰቅዞ ሲይዘኝ እንደ ምርጫ ቦርድ ገለልተኛ ካልተሆነ በቀር ምርጫው ለተመራጩም ለተሸናፊውም እንዳልጠቀመ አስታውሼ “ይለፈኝ” አልኩት። ‹ስንቱን አሳለፍኩት?› አለ መሐሙድ አህመድ። ቆይ ግን እንዲህ በፍርኃት ዘለዓለም ዓለማችን አጣብቂኝ ምርጫ ውስጥ እየገባን በይለፈኝ የመምረጥ ዕድላችንን የምናሳልፈው እስከ መቼ ነው? ልብ አድርጉ! ከክርስቲያኖ ሮናልዶና ከሊዮኔል ሜሲ ማን ይበልጣል ዓይነቱን ምርጫ ማለቴ ነው። ደግሞ ልክ እንደ ፖለቲካ ምርጫ አስታውሳችሁ ወደ ሌላ ነገር እንዳትገቡ አደራ። ታዲያላችሁ በአንድ ወቅት ሙሰኛ አፀዳለሁ በሚል ቀዳሚ አጀንዳ አዲስ ፕሬዚዳንት በመረጠችው በናይጄሪያ፣ በሜሲና በሮናልዶ አድናቂዎች መካከል በተነሳ የእኔ ይበልጣል የእኔ ይበልጣል አተካራ ታናሹ ታላቁን ገደለው ሲባል መስማቴን አስታውሳለሁ። የእኛ ኳስ ሁኔታ ያላማራቸው የምርጫ ተወዳዳሪዎች የኳስ ደጋፊዎችን ከስታዲየም አካባቢ አጠፋለሁ ብለው ብቻ ሲወዳደሩ እንዳንሰማ እንጂ ሌላውስ ሌላ ነው!
ይህንን ዓይነቱን ወሬ ስቃርም ኪሴ እየተመናመነ ሲመጣ እንጀራዬን ፍለጋ ከቤት ወጣሁ። ባሻዬም መንገድ ሲያገኙኝ፣ ‹‹ልጅ አንበርብር አደራ አሁንም ጠንቀቅ እያልክ። የዘመኑ ሰው እንደሆነ የሚያስመርጥህንም የሚመርጠውንም አላውቅ ብሏል፤›› ካሉኝ በኋላ፣ ‹‹ለመሆኑ ሜሲና ሮናልዶ አፍሪካውያን ናቸው?›› ብለው ጠየቁኝ። አንዱ ደቡብ አሜሪካዊ አንዱ አውሮፓዊ እንደሆነ ስነግራቸው፣ ‹‹አይ አፍሪካ ምናለበት ዛሬ እንኳ የራሷን ሰዎች ሐሳብ፣ ዝናና ክብር አነፃፅራ ብትጋደል?›› ብለውኝ ተጓዙ። አሁን ይኼን ጉድ ሜሲም ሮናልዶም ቢሰሙ ኳስ ማንከባለል እርግፍ አድርገው ትተው ገዳም አይገቡም ትላላችሁ? ለነገሩ ያንን ያህል ክፍያ የሚፈጽም ዓለም እያለላቸው ምን ይሁነኝ ብለው ገዳም ይመኛሉ፡፡
መቼም እንደ መፍረድ ቀላል ነገር የለም። ‹ከበሮ በሰው እጅ. . .› ይላል ያገሬ ሰው። ‹. . .በሰው እጅ ያምር ሲይዙት ያደናግር›። ድሮ ነበር እንጂ በከበሮ መደናገር ዛሬ በሰው እጅ ስናየው እያደናገረን ያለው ገንዘብ ብቻ ሆኗል። ‘ከየት? እንዴት? ትናንት የማኪያቶ እኔ እየከፈልኩለት?’ የሚያስብለን አንዳንዱ ‘ኦቨርናይት’ የሚያሳየው ይባላል እንዴ? ከበሮንማ ገንዘብ ይኑር እንጂ ከፍሎ ማስደለቅ ይቻላል። አይቻልም እንዴ? አስደላቂዎችን እዩ ከተጠራጠራችሁ። ጊዜው ተቀይሯላ። ‹ገንዘብ፣ ገንዘብ፣ ገንዘብ። ገንዘብ. . .› ካለ ጠፈር ላይ ‹ቫኬሽን› አለ። ዕድሜ ለገንዘብ። አሁን ይኼን ሁሉ ያመጣሁት መፍረድ ቀላል ነው ብዬ ነው አይደል? አዎ። ልብ ብላችሁ ስሙኝ ታዲያ። መቼም በፕሮፓጋንዳ ጋጋታ ልባችሁን ከሚጠቧችሁ ‹ዳያስፖራም ሆኑ ላሜቦራ› ፖለቲከኞች የእኔ ይሻላችኋል። ለራስ አልቆርስ ብለን ዳቦው እያለቀ ጠኔ ገደለና!
እንግዲህ ለሰው ልጅ የውድቀቱ ሁሉ መነሻው ቁንፅል እውቀት ነው ይባላል። ደግሞም እውነት ነው። ባይሆን ኖሮ ምልክቶቹን አናይም ነበር። ከምልክቶቹም አንዳንዶቹ በአርሰናልና በማንቸስተር ዩናይትድ ለሻምፒዮንስ ሊግ ባለማለፍ ምክንያት ትዳር ማፍረስ፣ በሜሲ ይበልጣል ሮናልዶ ፀብ ቀስቅሶ ሕይወት ማጥፋት፣ አድለው የጨረሱትን ቤት መልሶ ለማን ነው ያስረከብኩት እያሉ ቆጠራ፣ የፌስቡክ ኮሜንቶች ስድብና ዛቻ፣ በመልሶ ማልማት የለማውን አፍርሶ መልሶ ማልማት፣ ወዘተ. ብዙ ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል። ታዲያ የጥፋቱ ጥፋት የሚብሰው ትንሽ ማወቃችን ሳያንሰን፣ ከእኛ በላይ የለም ብለን አገር ይያዝልኝ ስንል መዋላችን ጭምር ነው። ለምሳሌ በቀደም፣ ‹‹ኧረ ይኼ ልክ አይደለም፤›› ይለዋል አንድ ሠራተኛ የአንድ ሀብታም ቅንጡ አውቶሞቢል ጎማ እየቀየረ። ቀያሪው እኮ ሠራተኛው ነው። ያ አፈር አይንካኝ ባዩ ሀብታም ፌስቡክ ላይ ከዘጠና ሰዎች ጋር ቻት እያደረገ በመሀል በመሀል ‹‹ገልብጠው! . . . የለም! . . . አሁን ነው የምታስረው?›› እያለ ጣልቃ ይገባል። እኔ ኮንዶሚኒየም ቤት ላሻሽጥ ደንበኛዬን እየጠበቅኩ ቆሜ እታዘባለሁ። ሥራዬ ብለው ከታዘቡ እኮ ስንት ያለ ቦታው የተቀመጠ ዕቃ ይታዘባሉ መሰልዎ!
አያለሁ ብያችኋለሁ። ጎማው ተገልብጦ ነው የታሰረው። ሠራተኛው የሚያደርገው ጠፍቶት ከባለቤቱ አላውቅም ብሎ ዝም ብሎ ገጥሞታል። በዚያ ላይ ቡሎኖቹን በጣም አታጥብቅ ስለተባለ እንደነገሩ ሰካክቷቸዋል። ባለመኪናው ጎማው ገጥሞ ብቻ ሲያይ ሰላሳ ብር ወርውሮለት ሊያሽከረክር ገባ። በዚህ ቅፅበት ሃምሳ ሜትር ርቀት ላይ ሙሽራ እስኪመስል ሽቅርቅር ብሎ የለበሰ ጎልማሳ ጥጉን ይዞ ሽንቱን ይሸናል። አንድ መንገደኛ፣ ‹‹ምናለበት እንደ አለባበስህ አስተሳሰብህን ብታሳምረው?›› ብሎት አለፈ። ‹‹አንተ አትሸናም? በመንፈስ ነው የምትኖረው?›› ጎልማሳው እየተሳደበ ሳይጨርስ ያ ፊት ለፊቴ ቆሞ የነበረ መኪና በቅጡ ያልተገጠመውና ያልታሰረው ጎማ በሮ ሹፌሩ የሚያደርገው ጠፍቶት ሲደነባበር፣ መሪውን ወዳልሆነ አቅጣጫ አዞረውና ጎልማሳው ላይ ወጣ።
እዚያው በዚያው ዓይኔ እያየ ጎልማሳው በዚያው አንቀላፋ ብላችሁ ታምኑኛላችሁ? የነገሮችን አነሳስ ሳይ ስለቆየሁ ደንግጬ ራሴ ሲዞር፣ ለወሬ ከተሰበሰበው ሰው መሀል አንዱ በቦታው ላልነበረ ሰው ትዕይንቱን ሲያብራራ እሰማለሁ። ‹‹እንዲህ ሆኖ እንዲያ ሲሆን አሽቀንጥሮ ቢጥለው አስፋልቱ አናቱን ተርትሮ ጣለው፤›› ይላል። “እና ሞተ?” ይጠይቃል ሰሚው ደንግጦ። ‹‹እና ሊቀርለት ነው? ድብን ነዋ፤›› አይለውም? ‘አንተ እንዴት እንዲህ ይባላል?’ የሚለው ሰው ካለ ብዬ ስጠባበቅ፣ ደንበኛዬ ደረሰና ተያይዘን ወደ ጉዳያችን ሄድን። ኋላ ለባሻዬ ነገሩን ከመጀመርያው እስከ መጨረሻው አብራርቼ ሳጫውታቸው ያ በኩራትና በተበቃይ ድምፀት ሞቱን ያረዳ የነበረ መንገደኛ ገርሟቸው ምን ቢሉኝ ጥሩ ነው? ‹‹አንበርብር ተፈራርተንና የሚጀምርልን አጥተን ነው እንጂ ያላበደ የለም ዘንድሮ፤›› አሉኝ። ሁሉን እናውቃለን እያልን በሁሉ ነገር ከከሰርን ዘንዳ ድሮስ ሊቀርልን ኖሯል ባሻዬ!
ታዲያላችሁ ባሻዬ እንደ ቀልድ የተናገሩት ነገር እያደር ይከነክነኝ ጀመር። አብሬያቸው የምውላቸውን ሰዎች ባህሪና አነጋገር መታዘብ ጀመርኩ። ‹‹በተለምዶ ዕብደት የምንለው የአዕምሮ ሕመም በአገራችን ቢበዛም በባህላዊ ማስታመሚያ መንገድ ስላለው እንጂ፣ ውጭ ቢሆን መንግሥት ዛሬ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ሳይሆን ይገነባ የነበረው የአዕምሮ ሕሙማን ማዕከል ነበር፤›› የሚለኝ ደግሞ ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ነው። እሱ ደግሞ የማይለው የለም። ‹‹እንዴት? ምንድነው ባህላዊ ሕክምናው?›› ብዬ እጠይቃለሁ። ‹‹አለማመን ይባላል። እሱ እኮ ተቆጪ ነው። እሱ እኮ ተናዳጅ ነው። እሱ ሲናገር እንዳመጣለት ነው፣ ለዛሬ ለነገ አይልም። አብሾ አለበት። ሰይጣናም ናት. . . ምን የማንለው አለ? የአዕምሮ ሕመም በሽታ እንደሆነ አናውቀውም፣ ስለዚህ አናምነውም። ለዚህ እኮ ነው ሕግ መጣስ፣ ሌብነት፣ ክፋት፣ ስስት፣ ዘረኝነት፣ አስመሳይነት፣ አድርባይነትና መሰል ድርጊቶች ሥርዓታችን ሙሉ ለሙሉ ፍሬ እንዳያፈራ ያደርጉታል፡፡ ሃያ ሰባት በመቶ የምንሆነው ወፈፌዎች ዋናው ችግራችን ይኼ ነው፤›› ብሎ የእኔንም ችግር አረዳኝ።
የሁላችንንም የሚባል ችግር በሚገባ ካዳመጥኩት በኋላ ተሻለ ሲባል እያደር በጉልበት እንጂ፣ በፀባይና በሐሳብ ብልጫ ተሠርቶ የማይኖርባት አገር እየሆነች የመጣችው አገሬ አሳዘነችኝ። ‹‹በነውር ጀምረን በነውር መቋጨት እስከ መቼ እንዲያጨነግፈን እንደምንፈቅድ አላውቅም፤›› ብዬ ያሻሻጥኩት ኮንዶሚኒየም ቤት ባለቤት ኮሚሽኔን ሊሰጠኝ ቢደውል አላነሳ አልኩ። እንደ ዝና እንደ መታወቂያ የደፋናቸው ባህሪያትና መለያዎች ከትዕግሥትና ከጥበበኝነት ይልቅ ለምን ጉልበት ተኮር ሆኑ? ማን እንደ እኛ ደመ ሞቃት? ማን እንደእኛ አትንኩኝ ባይ? ማን እንደ እኛ የጀግና አገር? መሸሽ የማያውቅ የማይሸነፍና መሰል የብሔራዊ ስሜት መገለጫ ስሞች ዕውን ከአዋቂነት፣ ከአስተዋይነትና ከጥበበኝነት የፈለቁ ናቸው? ወይስ ከግትርነት? እያልኩ እንደ ባለዕዳ ስብከነከን ቆይቼ ወዲያው ረስቼው ገንዘቤን ልቀበል በረርኩ። ኋላ የምበላውና የቤት ኪራይ የምከፍለው ሳጣ በሐሳብ ተወጥሬ ዜብራ ላይ ልገጭና ልሙት ታዲያ?! ዜብራ ላይ የሚሻገሩ ቀርፋፋ ተሻጋሪዎች በሐሳብ የናወዙ ቤት አልባ ናቸው ሲባል ስለሰማሁ ነው ይቅርታ!
በሉ እንበተን እስኪ። ከዚህ በላይ ተሰብስቦ ማሽሟጠጥ የአገር ልማት ማደናቀፍ ነው። እስኪ አንዳንዴ ሥራ ባንፈጥር ወሬ እየቀነስን ልማቱን እናግዝ? ልላችሁ ስል የባሻዬ ልጅ ደውሎ አቋረጠኝ። “ምንድነው?” ስለው፣ ‹‹ፈጥነህ ድረስ እኔና አንተ የምንመራው ስብሰባ አለ፤›› አለኝ። ከራሴ በላይ አጥብቄ ስለማምነው ተነካክቶ አያነካካኝም እያልኩ ፈጥኜ ደረስኩ። ጉዳዩን ሲያስጨብጠኝ ‘የሠፈራችን ወጣቶች ሥራ ፈጠራ ከሌላ ሠፈር ወጣቶች ሥራ ፈጠራ ጋር ሲነፃፀር በእጅጉ ወደኋላ መቅረቱን’ አጫወተኝ። ‹‹ታዲያ እኔና አንተን ብቻ ምን አገባን?›› ስለው፣ ‹‹መንግሥት የሚናገረው ነገር ሁሉ የመንግሥት ንብረትና ራዕይ እየመሰለ ልማቱን ስለጎተተው በእናንተው አንደበት አበረታቱዋቸው፤›› ተብሎ ነው አለኝ። እያቅማማሁ ሺሕ ወጣት ወዲያ፣ እኔና የባሻዬ ልጅ ወዲህ ሆነን ተቀመጥን። ‹‹ይኼ ሁሉ ወጣት ሥራ የለውም?›› ብዬ ግሮሰሪ ያለሁ መስሎኝ ልቀደድ ስል፣ ‘ኧረ እንዳታስበላኝ አንተ ሰውዬ’ በሚል ቁንጥጫ መዘለገኝ። እውነት እውነት እላችኋለሁ በልጅነቴም እንዲያ ያለ ቁንጥጫ አላጋጠመኝም። ታዲያ ይኼን እያየሁ የመናገር ነፃነቴ ተጨቆነ ብል፣ ትግሉን ከወዳጄ የባሻዬ ልጅ ልጀምር ነው ማለት ነው? ጉድ ነው!
በአጭሩ የሥራ ፈጠራ ተነሳሽነታቸው ለምን ዝቅተኛ እንደሆነ ወጣቶቹ አስረዱ። አንዱ ቆፍጣና ወጣት ተነስቶ፣ ‹‹የልብስ ስፌት መኪናን የፈለሰፈው ሰው የሞተው ታርዞ፣ በብርድና በቁር ኩርትም ብሎ ነው። እእ . . . ራዲየም የተባለውን ጨረር በምርምር ያገኘችውና የኖቤል ተሸላሚ መሆን የቻለችው ሜርኩሪ የሞተችው ጨረሩ ባደረሰባት አደጋ ነው። ስለተመጣጣኝ ምግብና ለሰውነታችን ስለሚኖረው ዓይነተኛ ጥቅም ለመጀመርያ ግዜ በመጽሐፍ ያሳተመውም የምግብ ተመራማሪ ምሁር የሞተው በተመጣጠነ ምግብ እጥረት ነው። ታዲያ እኛ ይኼን ሁሉ እያወቅን በፈጠራ ላይ ጊዜ የማናጠፋው መኖር ስለምንሻ ነው፤›› ብሎ ሲቀመጥ ገረመኝ። የፖለቲከኞችን ቢጨምርበት ጥሩ ነው፡፡ ሌላው የገረመኝ የሰጣቸው ምሳሌዎች እውነት መሆን በባሻዬ ልጅ ሲረጋገጥ እንጂ በወጣቶቹ ድምዳሜ አልነበረም።
ወዲያው የባሻዬ ልጅ ‘በካውንተር አታክ’ ስለቶማስ ኤድሰን ጨለማ ፈሪነት፣ ስለኦሊቨር ራይት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት አለማጠናቀቅ፣ ወዘተ. ብዙ ምሳሌ ደርድሮ በማሱት ጉድጓድ ያልወደቁ ስመጥር ተመራማሪዎችን ዘርዝሮ አሳመናቸው። የአንተ ድርሻ ምን ነበር? አላችሁኝ። አለማወቄን አውቄ ዝም ብሎ ማዳመጥ ነዋ። ዘንድሮ እኮ የበጠበጠን ያለ ዕውቀት ሲከፋ ደግሞ በቁንፅል ዕውቀት አገር ካላተራመስን፣ ሁሉንም ነገር ካልመራን፣ የሚታወቀውንም የማይታወቀውንም ካልተነተንንና መንጋ ካላግተለተልን ባይነት ሆኗል። ከስብሰባው በኋላም እኔና የባሻዬ ልጅ ወደ ተለመደችዋ ግሮሰሪያችን አምርተን የተሰበሰብነው በዚሁ ዙሪያ ነው። አገር ደህና ሰው የሌላት ይመስል የወፈፌዎች መጫወቻ እንዳትሆን እስኪ እናንተም ጨከን ብላችሁ ተነጋገሩበት። ትንሽ እሳት ጫካ ታነድ እንዳይሆን፣ ትንሽ ዕውቀት አገር ታፈርስ እንዳይተረት እንወያይበት። አለበለዚያ ዓረም ይወረናል! መልካም ሰንበት!