አቶ በረከት የእምነት ክህደት ቃል ሲሰጡ አቶ ታደሰ ለሌላ ቀን ተቀጠሩ
ከጥረት ኮርፖሬት ድርጅቶች ጋር በተያያዘ ክስ ተመሥርቶባቸው በእስር ላይ የሚገኙት አቶ በረከት ስምዖንና አቶ ታደሰ ካሳ፣ የፍርድ ቤት ሥልጣንን መሠረት አድርገው ያቀረቡት የክስ መቃወሚያ ውድቅ ተደረገ፡፡
ተከሳሾቹ ለአማራ ክልል መንግሥት ጠቅላይ ፍርድ ቤት ባቀረቡት የክስ መቃወሚያ ላይ እንዳስረዱት፣ የፌዴራል ፍርድ ቤቶች በወንጀል ጉዳይ ያላቸው ሥልጣን በፍርድ ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 25/88፣ 138/91 እና 321/95 ተደንግጎ ይገኛል፡፡ በአንቀጾቹ የተዘረዘሩ ወንጀሎች በየትኛውም የአገሪቱ ክልሎች ተፈጽመው ሲገኙ ዓይተው የመወሰን ሥልጣን ያላቸው፣ የፌዴራል ፍርድ ቤቶች መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡
እነሱን የከሰሳቸው የአማራ ክልል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ዓቃቤ ሕግ ያቀረበባቸው ክሶች ፍሬ ነገሮች የሚካተቱት፣ ከላይ በተጠቀሱት የሕግ ድንጋጌዎች (አንቀጾች) መሆኑን አስረድተዋል፡፡ በመሆኑም የቀረበባቸውን ክስ ፍርድ ቤቱ ለማየት የሚያስችል ሥልጣን እንደሌለው የሚያሳይ መሆኑን አክለዋል፡፡ ተከሳሾች እንዳስረዱት፣ አዋጅ ቁጥር 883/2007 አንቀጽ 6 (ሀ) ከክስና ከምርመራ ጋር በተያያዘ ከአንድ በላይ በሆኑ ክልሎች የሚንቀሳቀሱ ሕዝባዊ ባለሥልጣናት ወይም ሠራተኞች በሚፈጸሙ የሙስና ወንጀሎች፣ የፌዴራል ሥልጣን መሆኑንም እንደሚደነግግ ጠቁመዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በእነሱ ላይ የቀረቡትና ተፈጸሙ የተባሉት ወንጀሎች፣ ከኢትጵያም ድንበር አልፈው በውጭ አገር ጭምር የተፈጸሙ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የውጭ አገር ዜጎችን የሚመለከቱ ወንጀሎችንና በተለያዩ ክልሎች የሚፈጠሩ ወንጀሎች ላይ ዳኝነት የመስጠት ሥልጣን የፌዴራል ፍርድ ቤቶች መሆኑንም፣ አዋጅ ቁጥር 25/88 አንቀጽ 4፣ 9 እና 11 ላይ መደንገጉንም አስረድተዋል፡፡
በመሆኑም ለክልሉ ኮሚሽን ዓቃቤ ሕግ የክስ ምክንያት የሆነው ድርጊት የውጭ አገር ዜግነት ካላቸው ጋር የተፈጸመ መሆኑን ጠቁመው፣ አሜሪካዊ ዜግነት ያላቸው ተከሳሽም በክሱ መካተታቸውን አስታውሰዋል፡፡ በመሆኑም ፍርድ ቤቱ ሥልጣን እንደሌለው አውቆና የክስ ፋይሉን ዘግቶ እንዲያሰናብታቸው ጠይቀው ነበር፡፡ በሌላ መከራከሪያ ሐሳብም መቃወሚያቸውን አቅርበዋል፡፡
የክልሉ ፀረ ሙስና ኮሚሽን ዓቃቤ ሕግ ያቀረበባቸው ክስና ተላልፈውታል ያላቸው ሕግ አዋጅ ቁጥር 881/07 ነው፡፡ ተፈጽሟል ያለው የወንጀል ድርጊት ደግሞ አዋጁ ከመውጣቱ በፊት በመሆኑ፣ የወንጀል ሕግ ወደኋላ ሄዶ የማይሠራ በመሆኑ መዝገቡን ዘግቶ እንዲያሰናብታቸው በድጋሚ ጠይቀዋል፡፡
የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ በበኩሉ ባቀረበው የመቃወሚያ መቃወሚያ እንዳስረዳው፣ ፍርድ ቤቱ ክሱን የማየት ሥልጣን አለው፡፡ ሥልጣኑንም ያገኘው በውክልና ነው፡፡ ወንጀሉ የተፈጸመው በክልሉ መሆኑንና የተመዘበረውም ሀብት የአማራ ክልል ሕዝብ በመሆኑ፣ ክሱ መታየት ያለበት በክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት መሆኑን በመግለጽ የተከሳሾቹ መቃወሚያ ውድቅ እንዲደረግለት ጠይቋል፡፡
የግራ ቀኙን ክርክር የመረመረው የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት እነ አቶ በረከት ያቀረቡት የክስ መቃወሚያ ውድቅ በማድረግ፣ የእምነት ክህደት ቃላቸውን እንዲሰጡ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ በዚህም መሠረት አቶ በረከት ስለተከሰሱበት ክስ በዝርዝር መናገር እንደማይፈልጉ ተናግረው፣ ነገር ግን ምንም ዓይነት ጥፋት እንዳልፈጸሙና ሊጠየቁ እንደማይገባ በመግለጽ የእምነት ክህደት ቃላቸውን ሰጥተዋል፡፡ አቶ ታደሰ ግን ጊዜ እንደሚፈልጉ ተናግረው ግንቦት 5 ቀን 2011 ዓ.ም. የእምነት ክህደት ቃላቸውን እንዲሰጡ ቀጠሮ ተይዟል፡፡