Friday, December 8, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

የሕግ የበላይነትን ለማስከበር የመንግሥት ቁርጠኝነት በተግባር መታየት አለበት!

‹‹ከልብ ካለቀሱ እንባ አይገድም›› እንደሚባለው ሕዝብን በሥርዓት  ለማስተዳደር ኃላፊነት የወሰደ መንግሥት ከበድ ያለ ችግር ካላገጠመው በስተቀር፣ የተሰጠውን ኃላፊነት በብቃት ለማከናወን አይቸግረውም፡፡ መንግሥት የሕዝቡን ሰላምና ደኅንነት ለማስጠበቅ ሕግ ማስከበር ተቀዳሚ ተግባሩ ነው፡፡ ሕግ ማስከበር ማለት ደግሞ ሕገወጥነትን መከላከል ሲሆን፣ ለዚህም ሲባል የተቋቋሙ አካላት አሉ፡፡ የሕግ አስከባሪ አካላትን በሥርዓት አንቀሳቅሶ ኃላፊነትን በብቃት መወጣት የግድ ይላል፡፡ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ የብዙዎች ጥያቄ የንፁኃን ሕይወት ለአደጋ ተጋልጦ፣ መንግሥት የሕግ የበላይነትን ለማስከበር ለምን አቃተው የሚል ነው፡፡ መንግሥት ደግሞ የሕግ የበላይነትን ማስከበርና ዴሞክራሲያዊ መብትን ማጣጣም የለውጡ ወቅት ተግዳሮት መሆኑን ይናገራል፡፡ ከዚህም ባለፈ ሕግ ለማስከበር ሲባል እንደ ተለመደው የኃይል ተግባር ውስጥ መግባት ተቀዳሚ አማራጭ መሆን የለበትም ይላል፡፡ ችግሩ እዚህ ላይ ነው ያለው፡፡ መንግሥት ሕግ የማስከበር ኃላፊነቱን የመወጣት ግዴታ ሲኖርበት፣ እያንዳንዱ ዜጋም ሆነ ስብስብ ሕግ የማክበር ግዴታ አለበት፡፡ ዴሞክራሲን ማጣጣም የሚፈልግ ማንኛውም ግለሰብ ሆነ ቡድን መብቱን ሲጠቀም፣ በሌላ በኩል ሕግ የማክበር ግዴታ ይጣልበታል፡፡ መብትና ኃላፊነትን ጎን ለጎን አለማስኬድ ለሥርዓተ አልበኝነት ያመቻቻል፡፡ መንግሥት በሕግ የበላይነት ማስተዳደርና በሕግ መግዛት መካከል ያለውን ልዩነት ማሳየት አለበት፡፡ በዚህ መሠረት መንግሥት ቁርጠኛ ሆኖ ተግባሩን ማከናወን ይጠበቅበታል፡፡

እርግጥ ነው የዴሞክራሲ ምኅዳሩን ለማስፋት ሲባል ባለፈው አንድ ዓመት ብዙ ነገሮች ለቀቅ ተደርገዋል፡፡ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ የሚረዱ በርካታ ተግባራት ተከናውነዋል፡፡ እነዚህ ወሳኝ የሆኑ ዕርምጃዎች ለአገር ዕድገት፣ ሰላምና የወደፊት ዕጣ ፈንታ ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖራቸዋል፡፡ እነዚህን እየተወሰዱ ያሉ ተስፋ ሰጪ ዕርምጃዎች ኢትዮጵያውያን ለአገራቸው ሲሉ መደገፍ ይኖርባቸዋል፡፡ የነገዋ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ አብባ መውጣት የምትችለው፣ እያንዳንዱ ዜጋ በሚያበረክተው አስተዋጽኦ ጭምር ነው፡፡ ከዚህ ውጪ አገርን የቅራኔና የግጭት መራኮቻ በማድረግ ቀይ መስመሩን የሚያልፉ አካላት ሲኖሩ፣ በሕግ የበላይነት አደብ እንዲገዙ ማድረግ የመንግሥት ግዴታ ነው፡፡ በየቦታው ግጭት እየቀሰቀሱ የንፁኃንን ደም የሚያፈሱ፣ የሚያፈናቅሉና ንብረት የሚያወድሙ አካላት በሕግ ካልተጠየቁ ማቆሚያው ይቸግራል፡፡ ሕግን ለራስ ፍላጎት ብቻ የሚጠቀሙ አካላትን ተጠያቂ አለማድረግ ጦሱ ለአገር ይተርፋል፡፡ ሕገወጥነት በሕጋዊነት ላይ የበላይነቱን ከያዘ፣ በሕዝብና በመንግሥት መካከል ሊኖር የሚገባው ጤናማ ግንኙነት ተበላሽቶ የበለጠ ችግር ይፈጠራል፡፡ ይህ ደግሞ ለአገር ህልውና አደገኛ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ስለሕግ የበላይነት ያለው አረዳድ ከተዛነፈ በጣም ቆይቷል፡፡ ሥልጣን በጉልበቱ የጨበጨ አካል የሥልጣኑን ዕድሜ ለማራዘም ሲል፣ በሕግ ስም በርካታ ሕገወጥ ድርጊቶችን ይፈጽማል፡፡ ለሰው ልጆች መመኪያ ሊሆን ይገባው የነበረውን ሕግ ለሕገወጥ ዓላማ ማስፈጸሚያ ያውለዋል፡፡ ንፁኃንን ያጠቃበታል፡፡ የተወሰኑ ግለሰቦችን ወይም ቡድኖችን ዒላማ ለማድረግ አፋኝ ሕጎችን ያወጣል፡፡ ለዚህ በምሳሌነት ከሚጠቀሱ ጉዳዮች መካከል በተለይ ከምርጫ 97 በኋላ የወጡትን የሚዲያ፣ የበጎ አድራጎትና ማኅበራት፣ እንዲሁም የፀረ ሽብርተኝነት ሕጎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ እነዚህን ሕጎች በጉልበት ያወጣው ኢሕአዴግ በርካቶችን ለእስር ከመዳረጉም በላይ፣ ብዙዎች አገር ጥለው እንዲሰደዱ ምክንያት ሆኗል፡፡ የውይይትና የክርክር ባህል እንዳይፈጠር አድርጓል፡፡ ሐሳብን የመግለጽ ነፃነት ደፍጥጧል፡፡ በሁለት ምርጫዎች ዓለም ጉድ እስኪል ድረስ መቶ በመቶ በሚባል ደረጃ ፓርላማውን ጠቅልሎ ተቆጣጥሯል፡፡ እንዲህ ዓይነቶቹ ዓይን ያወጡ ድርጊቶችና ሌሎችም የተፈጸሙት በሕጋዊነት ስም ነበር፡፡ የፍትሕ ተቋማትን በማሽመድመዱም ፍትሕ ሸቀጥ ሆኖ ነበር፡፡ በዚህ ዓይነቱ መላቅጡ የጠፋበት ሥርዓት ውስጥ ስለሕግ የበላይነት መነጋገር ከንቱ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ሕገወጥነት በሕጋዊነት ላይ የበላይነት በመያዙ ነበር በሥርዓቱ ላይ የበርካቶች ደም የፈሰሰበት ተቃውሞ ተነስቶ፣ ከኢሕአዴግ ውስጥ በበቀለው የለውጥ ኃይል አማካይነት የለውጥ ሽግግር የተጀመረው፡፡ እንደ ኢሕአዴግ ሁኔታ ቢሆን ኖሮ የከፋ ችግር ይደርስ እንደነበር አይዘነጋም፡፡ ካሁን በኋላ ወደፊት እንጂ ወደኋላ የለም መባል አለበት፡፡

አሁንም ለውጡ ተቋማዊ ሆኖ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ መሠረት መጣል የሚቻለው፣ በሥርዓት መምራትና መመራት ሲቻል ብቻ ነው፡፡ የሕግ የበላይነትን ጽንሰ ሐሳብ በመረዳት ከዚህ በፊት ያጋጠሙ ችግሮችን መመርመር፣ በሽግግር ሒደት ላይ ባለች አገር አፈጻጸሙ እንዴት መሆን እንዳለበት በዳበረ ውይይት ግንዛቤ መያዝ፣ ነፃነትና ኃላፊነት እንዴት መጣጣም እንዳለባቸው የጋራ አተያይ መፍጠር፣ መብቶችና ግዴታዎች ሊኖራቸው የሚገባው ሚዛናዊ መስተጋብር ላይ፣ ስምምነት ለመፍጠር የሚረዱ ሕጋዊ መሠረቶችን መገንዘብና የመሳሰሉት ያስፈልጋሉ፡፡ ንግግሩ፣ ክርክሩና ድርድሩ በሰላማዊና በዴሞክራሲያዊ መንገድ መከናወን ይገባዋል፡፡ ከንድፈ ሐሳብ በተጨማሪ የልምድ ተሞክሮዎችም መፈተሽ አለባቸው፡፡ በተለይ ባለፈው አንድ ዓመት በተለያዩ ሥፍራዎች ያጋጠሙ ግጭቶች፣ ሞት፣ የአካል ጉዳት፣ መፈናቀልና የንብረት ውድመት መስንዔአቸው በግልጽ መነገር አለበት፡፡ ጥቃት አድራሾችና አስተባባሪዎች ለምን ለፍርድ አልቀረቡም ተብሎ በድፍረት መጠየቅ አለበት፡፡ ‹‹በሽታውን የደበቀ መድኃኒት የለውም›› እንደሚባለው፣ ተሸፋፍነው በሚቀሩ ችግሮች ምክንያት ከፍተኛ ጉዳት መድረሱ ይታወቃል፡፡ ጥቂት ሕገወጦችን ለመሸፈን ሲባል ብቻ ሕዝብ መደቆስ የለበትም፡፡ በግልጽ መነጋገር ሲቻል ብቻ ነው መፍትሔ የሚገኘው፡፡

የፌዴራል መንግሥት፣ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥታት፣ የፀጥታና የደኅንነት አካላትና ሌሎች የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ፈታኝ ሁኔታ ውስጥ እንዳሉ ግልጽ ነው፡፡ ነገር ግን ከአገር ህልውና በላይ ምንም ነገር ስለሌለ፣ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ የመወጣት ግዴታ አለባቸው፡፡ ይህንን በቅጡ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ በተለይ ግጭቶችን በመቀስቀስ የሚታሙ የመንግሥት አስተዳደራዊ መዋቅሮች አመራሮችንና የፀጥታ ኃላፊዎችን መቆጣጠር፣ በፖለቲካ ወጀቡ በመወሰድ ወገንተኛ የሚሆኑትን ነቅሶ መለየት፣ ሥልጣናቸውን ለሦስተኛ ወገን አሳልፈው ሰጥተው ባይተዋር የሆኑትን በፍጥነት ማወቅና ተገቢውን ሕጋዊና አስተዳደራዊ ዕርምጃ መውሰድ፣ በየደረጃው ያሉ የመንግሥት መዋቅሮች መሪዎች ግዴታ ነው፡፡ ሕግና ሥርዓትን በተግባር እንጂ በአዳራሽ ዲስኩር ማስከበር አይቻልም፡፡ የንፁኃን ሕይወት እየተቀጠፈና ንብረት እየወደመ ስለሕግ ማስከበር ሥራና ስለዴሞክራሲ መብት ማጣጣም መነጋገር አይቻልም፡፡ ክልሎች በቁርጠኝነት ከሠሩ የአካባቢያቸውን ችግር መቆጣጠር ይችላሉ፡፡ አስፈላጊ ሲሆን ደግሞ የፌዴራል መንግሥት ዕገዛ አላቸው፡፡ የፖለቲካ ቁርጠኝነት በመጥፋቱ ግን ከባድ ኪሳራ ደርሷል፡፡ ሌላው ቀርቶ የግለሰቦች ድንገተኛ ዕለታዊ ጠብ የብሔር ገጽታ ተላብሶ ንፁኃን ሲገድሉና ንብረታቸው ሲወድም በተደጋጋሚ ታይቷል፡፡ ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት ቢኖር ግን ችግሮች ሲያጋጥሙ በቁጥጥር ሥር ማዋል አያዳግትም ነበር፡፡ በዚህ ሁኔታ ደግሞ ፈጽሞ መቀጠል አይቻልም፡፡ ስለዚህ የሕግ የበላይነትን ለማስከበር የመንግሥት ቁርጠኝነት በተግባር መታየት አለበት!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...

ኦሮሚያ ኢንሹራንስ በግሉ ኢንሹራንስ ዘርፍ ሁለተኛውን የገበያ ድርሻ ለመያዝ ያስቻለውን ውጤት ማስመዝገቡን ገለጸ

ኦሮሚያ ኢንሹራንስ ኩባንያ የባንኮች የጥሬ ገንዘብ እጥረት፣ የመለዋወጫ ዕቃዎች...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለአገልግሎት ሰጪ ተቋማት የደንብ ልብስ አለባበስ የጌጣጌጥና መዋቢያ አጠቃቀም ደንብን ማውጣት ለምን አስፈለገ?

በዳንኤል ንጉሤ በሆቴልና መሰል አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ባለሙያዎች የደንብ ልብስ አለባበስ፣ የጌጣጌጥ አጠቃቀም የገጽታና የውበት አጠባበቅን አስመልክቶ በተዘጋጀው ረቂቅ ደንብ ላይ ውይይት ተካሂዷል፡፡ ረቂቅ ደንቡን ያዘጋጀው...

ትኩረት ለሕዝብና ለአገር ደኅንነት!

ኢትዮጵያ ውስጥም ሆነ በቅርብ ርቀት ባሉ አገሮች፣ እንዲሁም ራቅ ባሉ የአፍሪካና የዓለም አገሮች ውስጥ የሚስተዋሉ ዘርፈ ብዙ ችግሮች የተፅዕኖ አድማሳቸው እየሰፋ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ሌላው...

የአስተሳሰብና የአስተዳደር ዘይቤ ለውጥ ያስፈልጋል!

ኢትዮጵያ ውስጥ ሕዝቡን በጋራ አስተሳስረው የሚያኖሩ በጣም በርካታ ማኅበራዊ እሴቶች አሉ፡፡ እነዚህ ለዘመናት ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲሸጋገሩ የኖሩ እሴቶች አገር ለማቆም ትልቅ አስተዋፅኦ ነበራቸው፣...