Thursday, November 30, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ንግድ ባንክ ለወለድ ነፃ አገልግሎት አምስት የሸሪዓ አማካሪዎችን ሰየመ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እየሰጠ የሚገኘውን ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎትን ለኅብረተሰቡ ተደራሽና ተዓማኒ ለማድረግ ጄይላን ከድር (ዶ/ር) ሰብሳቢ፣ ሼክ ሙሐመድ ሐመዲን ምክትል ሰብሳቢ፣ ኑር አብዲ (ተባባሪ ፕሮፌሰር) መሐመድ ዜይን፣ ኡስታዝ አወል አብዱል ወሀብን በአባልነት የሸሪዓ አማካሪ አድርጎ መሰየሙን አስታወቀ፡፡

በወለድ ምክንያት ከባንክ አገልግሎት ርቀው የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ተደራሽ ለማድረግና ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ለአገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት የበኩሉን ዕገዛ እንዲያደርግ የሸሪዓ ሕግ አማካሪ ኮሚቴ መሰየሙ ታውቋል፡፡

በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከወለድ ነፃ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ኑሪ ሑሴን ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በዓለም ላይ የሸሪዓ ሕግ በሁለት ይከፈላል፡፡ የመጀመርያው በፈጣሪ ሕግ ሰው የሚገዛበትና የሚያስተምርበት (ኢባዳት) ሕግ ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ የማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ መርህን የያዘ (ሙአመላክ) ሕግ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የባንክ አገልግሎትም ከኢኮኖሚ ጋር የተገናኘ በመሆኑ በሁለተኛ ሙአመላክ ሕግ ሥር የሚወድቅ፣ ከአጠቃላይ የቢዝነስ ሥራዎች ጋር የተገናኘና እንዴት መሠራት እንዳለበት የሚገልጽ በመሆኑ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክም የሚሰጠው ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ከዚህ ሕግ ጋር የተያያዘ መሆኑን አቶ ኑሪ ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም ከዚህ ዘርፍ ጋር ዕውቀት ያላቸውና ኅብረተሰቡን ማስተማር የሚችሉ፣ የባንክ ባለሙያዎችንም ስለአሠራሩና ስለሥራቸው እየተከታተሉ ምክር በመስጠት አገልግሎቱን ከፍ የሚያደርጉ አማካሪዎች በማስፈለጋቸው፣ አምስቱ ከፍተኛ ልምድና ዕውቀት ያላቸው ሰዎች መሰየማቸውን አስረድተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት እየሰጠ የሚገኘው የሸሪዓ ሕግን ተከትሎ ስለሆነ፣ የግድ የባንክ ባለሙያ ባይሆንም የሸሪዓ ሕግ ዕውቀት ያለው ሰው አስፈላጊ መሆኑን አቶ ኑሪ ገልጸዋል፡፡ በየትኛውም ዓለም ያሉት ባንኮች የሚያስቀምጡት ባለሙያን እንደሆነ ጠቁመው፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክም እስካሁን ባለሙያ አለመሰየሙንና ማንኛውም ጥያቄ ሲነሳ ግብዓት የሚሰጥ ባለመኖሩ ዕውቀት ያላቸውንና በዘርፉም ግብዓት መስጠት የሚችሉ ባለሙያዎችን መሰየም አስፈላጊ በመሆኑ፣ አምስቱ ሰፊ ልምድና ዕውቀት ያላቸው ግለሰቦች መሰየማቸውን ገልጸዋል፡፡  

ቢዝነስ የሚሠሩ ተቋማት እንዴት የሸሪዓ ሕግን አክብረው እንደሚሠሩ፣ ባንኩ ለሚሰጣቸው አገልግሎቶች ማሟላት ያለበትን መሥፈርቶች፣ መፈቀድ፣ መከልከል ያለባቸውን፣ መከበር እያለባቸው የተጣሱትን በሚመለከት ምክር እንደሚሰጡና ሕጉ የሚለውን ተከትለው አገልግሎቱ እንዲሰጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያደርጉ የታመነባቸው መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግና ባንኩ የያዘውን ዕቅድ ለማሳካት ዕውቀታቸውንና ልምዳቸውን ተጠቅመው እንደሚሠሩም ያላቸውን እምነት አቶ ኑሪ ተናግረዋል፡፡ አቶ ኑሪ ሰፊና የካበተ ልምድ ያላቸው የባንክ ባለሙያ ሲሆኑ፣ ከሁለት ወራት በፊት ከኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ ወደ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መምጣታቸው ይታወሳል፡፡       

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች