Friday, April 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትየእግር ኳስ ደጋፊዎች የሁከት ምንጭ

የእግር ኳስ ደጋፊዎች የሁከት ምንጭ

ቀን:

እግር ኳስ ፉክክር ያለበት፣ ማሸነፍ መሸነፍና በአቻ ውጤት መለያየት ባህሪያቱ ቢሆኑም፣ በዚያው መጠን የተመልካቾችን ስሜት የሚያነሳሳ፣ በዓለምም ሆነ በአገር አቀፍ ደረጃ ተወዳጅ እየሆነ የመጣ ስፖርት ነው፡፡ ይህም የስፖርቱ ጠቀሜታ ከመዝናኛነት ያለፈ ፋይዳ እንዲኖረው መነሻ ሆኖታል፡፡ በዋናነትም የማኅበረሰብ ትስስርን ለማጠናከር፣ እንዲሁም በተለያዩ ምክንያቶች ተራርቀው የነበሩ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ማቀራረብና ሰላም ለመፍጠር ትልቅ የፖለቲካ መሣሪያ ብቻ ሳይሆን በኢኮኖሚያዊ ፋይዳውም የጎላ ሚና እየተጫወተ ይገኛል፡፡

ለዚህ ከባለድርሻዎቹ መካከል ተመልካቾችና ደጋፊዎች የእግር ኳሱ ዓብይ አካል ሲሆኑ፣ ለተጫዋቾች ሥነ ልቦናዊ ጉልበትና በፕሮፌሽናል የእግር ኳስ ዓለም ውስጥ የክለቦች የሀብት ምንጭ ናቸው ተብሎ ይታመናል፡፡ በተለይ ደግሞ እንዲህ እንደ አሁኑ በማዘውተሪያዎችና መሰል አካባቢዎች ሰላም ሲታወክ እግር ኳሱ የፍቅር መሠረትና ወዳጅነትን የበለጠ ለማጠናከር በኢትዮጵያ ጥቅም ላይ ያልዋለ ዘርፍ መሆኑ የሚናገሩ ሙያተኞች አሉ፡፡ በኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ በስፖርት ሳይንስ መምህርነት ለ12 ዓመታት ያህል አገልግሎት የሰጡ፣ በአሁኑ ወቅት በመቐለ ዩኒቨርሲቲ በስፖርት ማኔጅመንት የዶክትሬት ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ የሚገኙት አቶ የማነ ጎሳዬ ይጠቀሳሉ፡፡

‹‹ዛሬ ዛሬ ይህ መሆኑ ቀርቶ የተወሰኑ የእግር ኳስ ደጋፊዎች ያልተገባ ባህሪይ በአገራችን የሰላም መደፍረስ ምክንያት እየሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ በዝግመት ላይ ያለውን ስፖርት አዳክሟል፣ ውድድሮች በሚካሄዱባቸው አካባቢዎች ለሚገኙ የማኅበረሰብ ክፍሎችም ሥጋት ሆኗል፤›› የሚሉት አቶ የማነ፣ ለክስተቱ ‹‹ስሜት ነው›› የሚል ሽፋን በመስጠት በማዘውተሪያዎች ሰላምን በማደፍረስ ረገድ ጠብ አጫሪነትን በማነሳሳትና በተዋናይነት የሚሳተፉበት ሥርዓት አልበኝነት ሥር እየሰደደ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ለዚህ ፌዴሬሽኑም ሆነ ሌሎች አካላት ችግሩ እንዳይፈጠር ወይም ከተፈጠረም በኋላ ለማስወገድ አማራጭ ሊሆኑ የሚችሉ ሁሉንም ዕርምጃዎች ከመውሰድ መዘግየታቸው ለችግሩ መዝለቅ አስተዋፅኦ ሳያበረክት እንዳልቀረም አቶ የማነ ያምናሉ፡፡ እየተፈጠረ ያለውና በስፖርቱም ላይ የተጋረጠው አደጋ በሁሉም መመዘኛ ‹‹አሳሳቢ፣ ፀረ ሰላምና ፀረ ስፖርት ነው›› በሚል ሚያዝያ 14 እና 15 ቀን 2011 ዓ.ም. የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ ከሰላም ሚኒስቴርና ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በሸራተን አዲስ የተዘጋጀው የውይይት መድረክ ጠንካራ ጎኖች ያሉትን ያህል ክፍተቶችም እንደነበሩበት ይናገራሉ፡፡

በውይይቱ ከተነሱት መልካም ጎኖች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከእግር ኳሱ ጋር ግንኙነት ያላቸው ባለድርሻ አካላት ማለትም አሠልጣኞች፣ የእግር ኳስ ዳኞች፣ የክለብና የክልል ስፖርት አመራሮች፣ የዩኒቨርሲቲ ስፖርት ሳይንስ ምሁራን፣ የስፖርት አካዴሚ ተወካዮችና ሠልጣኞች፣ ጋዜጠኞችና የክለብ የቦርድ አመራሮች፣ ማኅበራትና የማኅበራት ተወካዮች ተሳትፈዋል፡፡ ለውይይት መነሻ እንዲሆን የተለያዩ ክፍሎች ተወካዮችና ምሁራን ባቀረቧቸው ጽሑፎች በችግሩ መንስዔዎችና መፍትሔዎች ላይ ጠቃሚና መሠረታዊ ጭብጦች መነሳታቸው ጭምር ያምናሉ፡፡

በዋናነትም በፌዴራልና በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ተወካዮች በሁከት ምክንያቶች፣ ተግዳሮቶችና መፍትሔዎች ላይ ያቀረቡት፣ በትምህርት ቤቶች ስፖርትና ዜግነት በመቅረፅ ሒደት ላይ መሠረታዊ ችግሮችና ቁልፍ መፍትሔዎችን የጠቆሙት  ሌሎች ምሁራኖች ያነሷቸው ሐሳቦች ተወስደው በተግባር ሊውሉ እንደሚገባ፣ የእግር ኳስ ደጋፊዎች ያልተገባ ባህሪይና መንስዔዎች ተብለው የተለዩ ችግሮችና የመፍትሔ ሐሳቦች ላይ ማተኮር እንደሚገባ፣ ጊዜን በአግባቡ ለመጠቀም ከመድረክ መሪው የተወሰዱ ዕርምጃዎችና ከመደበኛው ውይይት ውጪ በየዕረፍት ጊዜያቱ የሚተዋወቁ ሰዎች ተገናኝተው በጉዳዩ ዙሪያ እንዲወያዩ ዕድል መስጠቱ በጠንካራ ጎኑ እንደሚወስዱት ተናግረዋል፡፡

ክፍተቱን በሚመለከት ከመድረኩ ስያሜ እንደሚጀምር የሚያምኑት አቶ የማነ፣ የውይይቱ ዓብይ አጀንዳና ለመድረኩ የተመረጠለት ርዕስ ‹‹የስፖርታዊ ጨዋነት ምንጮች›› የሚል መሆኑ፣ ይህንኑ መነሻ በማድረግ ውይይቱ ያተኮረው፣ ስለ ‹‹ስፖርታዊ ጨዋነት ምንጮች›› ሳይሆን ስለስፖርታዊ ጨዋነት መጓደል ምክንያቶች ላይ እንደነበር ይናገራሉ፡፡

በአገሪቱ እግር ኳስ የተፈጠረውና ‹‹ደጋፊ ተብዬ›› ሥርዓት አልበኞችና የተለየ ድብቅ ዓላማ ያነገቡ ፖለቲከኞች የሚተውኑበትን የጥፋት ትዕይንት፣ ከስታዲየም ወጥቶ በሰውና በንብረት ላይ ጉዳትና ውድመት እየደረሰ ባለበት በዚህ ወቅት፣ ‹‹የስፖርታዊ ጨዋነት መጓደል›› ተብሎ ሊገለጽ በተገባ ነበር ሲሉ አቶ የማነ ያሰምሩበታል፡፡ ችግሩ በተጨባጭ ሰማይ ጥግ ደርሶ እያለ ‹‹ማሽሞንሞን አያስፈልግም›› የሚሉት አቶ የማነ፣ በተለያዩ ጥናቶች እንደተረጋገጠውና የዓለም አቀፍ ስያሜው እንደሚያመለክተው በኢትዮጵያ በእግር ኳሱ የሚታየው ያልተገባ ባህሪይ ሳንፈራው ‹‹ሁከት›› አሊያም ‹‹ጋጠ ወጥነትና ሥርዓት አልበኝነት እንበለው፤›› ይላሉ፡፡

ድርጊቱን በተገቢው ስያሜ አለመጥራት፣ ችግሩን ላለመለየትና ወደ መፍትሔው ላለመሄድ ግርዶሽ ይሆናል ብለው የሚያምኑት አቶ የማነ፣ ‹‹ስያሜ ድርጊትን ይገልጻል፣ የችግሩን ምንጮችና መፍትሔዎችንም ለመመርመር አቅጣጫ ያመላክታል፣›› ባይ ናቸው፡፡

በመድረክ አመራሩ በኩል በጉልህ የሚታይ ክፍተት ያሉት ሙያተኛው፣ ከተሳታፊዎች ሐሳቦች እንዲቀርቡ የሚጋብዝና የሚያበረታታ እንዳልነበረ፣ ይባስ ብሎ የመድረክ አመራሩ ‹‹ካልተስማማችሁ አዳራሹን ለቅቄ እወጣለሁ›› ከማለት ባሻገር ከጥያቄው ጋር ምንም ግንኙነት የሌለውን የግል ማንነትን ማንፀባረቅ፣ ከውይይት መድረኩ ዓብይ ዓላማ ጋር ፍፁም የተቃረነ እንደነበርም ያስረዳሉ፡፡

በዓለም አቀፍ እግር ኳስ ማኅበር (ፊፋ) ስፖርታዊ ጨዋነት ማለት ‹‹መከባበር›› ማለት መሆኑ፣ በኢትዮጵያ በእኛ እግር ኳስ ደጋፊዎች ሁከትና ሥርዓት አልበኝነት ዋናው ቁልፍ ምክንያት ግን አለመከባበር፣ መናናቅ፣ ራስ ወዳድነትና ምንም ሳይለፉ ውጤት በግርግር ከመፈለግ እንደሚመነጭ ልብ ማለት እንደሚገባ ያምናሉ፡፡

‹‹ከጊዜ ወደ ጊዜ መልካም ማኅበራዊ እሴቶቻችን በመሸርሸራቸው ምክንያት ዜጋ እርስ በርሱ፣ ሰው በመሆኑ ብቻ የማይከባበርበት፣ አንዱ ሌላውን የሚንቅበትና የማያዳምጥበት አገር በዓለም ላይ ቢኖር ኢትዮጵያ ብቻ ትመስለኛለች፤›› ብለው እንደሚያምኑ የሚናገሩት አቶ የማነ፣ በዚህ አሳሳቢ ችግር ላይ ለመወያየት በተዘጋጀው መድረክ ላይ ከመድረክ መሪው ሲንፀባረቁ የነበሩት ንግግሮች ተገቢነታቸው እምብዛም ነበር፡፡

ስለችግሩ መንስዔና መፍትሔ ከማኅበራዊ ሳይንስና ከሥነ ልቦና አንፃር ሲተነተን ደግሞ፣ ‹‹…በቃ በቃ፣›› የሚሉ አስተያየቶች እየተሰጡ ጠቃሚ ሐሳቦች ሲቆራረጡ ነበር፡፡ በዚህም የተነሳ ተደጋጋሚ ቅሬታዎች በጫጫታ መልክ ሲቀርቡ፣ ‹‹ስትፈልጉ ጥላችሁ ውጡ፤›› ብሎ ማለት ችግሮቹን ከተለያየ አቅጣጫ ተመልክቶ መፍትሔው ላይ ቁርጥ ያለ አቋምና ውሳኔ ላይ ከመድረስ ይልቅ መልካም ነገር የያዘውን መድረክ ዋጋ የሚያሳጣ ስለመሆኑ ጭምር ይናገራሉ፡፡

ሌላው ክፍተት ሲሉ የተናገሩት ደግሞ፣ ‹‹በውይይቱ ወቅት በአብላጫው ሐሳብ አቅራቢዎች በኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ የስፖርታዊ ጨዋነት መጓደል አሁን አሁን የተፈጠረ ክስተት እንደሆነ፣ ዋና ምክንያቶቹም የዘርና የጥላቻ ፖለቲካ፣ እንዲሁም የተወሰኑ ክለቦች ስያሜና ምልክት ዘርን የሚገልጹ መሆናቸው ብቻ ተደርጎ መገለጹ ተገቢ አልነበረም፡፡ በእርግጥ እነዚህ ምክንያቶች የነበረውን ችግር መልኩን ቀይረውታል፣ በጣምም አባብሰውት እግር ኳስ የማኅበረሰብ ትስስር ማጠናከሪያ ሳይሆን፣ የመለያያ ሥጋት ሆኖ እንዲታሰብ አድርገውታል፤›› ብለው እንደሚያምኑና ችግሩም በሰዎች አስተሳሰብ ውስጥና ሰዎች ማንነታቸውን ከሚደግፉት ክለብ ጋር ማያያዛቸው የክለባቸውን ሽንፈት የማንነት ሽንፈት አድርገው በማሰባቸው እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡

የተመልካቾች ያልተገባ ባህሪይና በውድድር ሜዳዎች ለረዥም ዘመን የተለመደው አለመከባበር፣ ራስ ወዳድነት፣ ምንም ሳይለፉ ውጤት ማምጣት የሚሉትና ሌሎችም ዝንባሌዎች አሁን የመጣ ነውን? ሲሉ የሚጠይቁት አቶ የማነ፣ ‹‹ተቃራኒ ተጨዋቾችን፣ አሠልጣኞችንና ደጋፊዎችን ማንኳሰስ፣ በፀያፍ ስድብ ማዋረድ፣ አለፍ ሲልም መደባደብ፣ የውድድር ዳኞችን ማዋከብ፣ ማስፈራራት፣ ማጥቃት፣ የተጨዋቾች በእያንዳንዱ የዳኞች ውሳኔ ላይ መነጫነጭና ትንቅንቅ መፍጠር፣ ወዘተ የዛሬ ክስተት አይደለም፡፡ ሥር የሰደደና የእግር ኳሱ አንዱ መገለጫ ነው፡፡ በሌላው ዓለም እንደምናየው በኢትዮጵያ የእግር ኳስ ጨዋታ ለመመልከትና ለመዝናናት ቤተሰቡን ይዞ አዲስ አበባ ስታድየም የሚገባ አለ? እውነቱን እንነጋገር ከተባለ ጋጠ ወጥነትና ብልግና አንብበን ሳይሆን የማዘውተሪያዎች የየዕለት ክስተቶች ከሆኑ ውለው ያደሩ አይደሉምን?›› ብለው ችግሩ ለዘመናት የኖረ ስለመሆኑ ጭምር ያብራራሉ፡፡

የማኅበረሰብ መልካም እሴቶች ተቃርኖ የእግር ኳስ አካል አድርጎ ማሰብና ያለዚህ ስፖርቱ ውበት እንደሌለው አድርጎ መሳል በሰፊው እየተለመደ መሆኑን የሚናገሩት አቶ የማነ፣ የማኅበረሰብ መልካም እሴቶች ተቃርኖ ባህሪይ በቸልታ ሊታይ እንደማይገባ፣ ይህ የሰብዕና መዛባት ከ15ኛው የዕድሜ ዘመን ጀምሮ የሚከሰትና የሌሎችን መብት በመጣስ የሚገለጽ እንደሆነም ያስረዳሉ፡፡

በሙያተኛው እምነት ይህ ሥር የሰደደና እርስ በርስ አለመከባበር፣ ግለኝነት ላይ የተመሠረተ ያልተገባ የእግር ኳስ ተዋናዮች ባህርይ፣ የዛሬውን የዘርና የጥላቻ ፖለቲካን ለማስተናገድ እጅግ የዳበረ ለም መሬት ነው፡፡

ከዚህ በፊት ተራ ፀያፍ ስድብ በስታዲየም ተወስኖ የነበረው ሁከት አሁን በዘርና በጥላቻ ስድቦች ተተክቶ ወደ ውጪ መውጣቱን የሚናገሩት አቶ የማነ፣ ‹‹የመጀመርያዎቹ ተራና ፀያፍ ስድቦች ግለሰቦችን (ዳኞች፣ አሠልጣኞች፣ ተጫዋቾች፣ ደጋፊዎች) ያዋርዱና ያንኳስሱ ነበር፡፡ የአሁኑ ግን የሚነካው ማንነትን ስለሆነ ማኅበረሰብን ከማኅበረሰብ ለማጋጨት ለሚፈልጉ አካላት ምቹ አጋጣሚ ሆነላቸው፣ በእግር ኳሱ ቤተሰብ ዘንድ የበፊቱ ጋጠ ወጥነት ፖለቲካው ስላልገባበት መልካም እግር ኳሳዊና የእግር ኳስ ውበት እንደሆነ አድርጎ መግለጽና የአሁኑ ችግር ደግሞ ገና አሁን የተፈጠረ እንደሆነ አድርጎ ማሰብ ፍፁም ስህተት ነው፤›› ይላሉ፡፡

ችግሩም በውይይቱ ተደጋግሞ እንደተነሳውና ሁሉም ግንዛቤ እንደጨበጠበት የፖለቲካው ጣልቃ ገብነትና የክለቦች ስያሜ ብቻ አለመሆኑ ነው ብሎ መደምደምም አግባብ እንዳልሆነ ይናገራሉ፡፡ ሙያተኛው እግር ኳሱን መነሻ አድርጎ የሚስተዋለው ሁከትና ሥርዓት አልበኝነት፣ ‹‹ለመንስዔውም ሆነ ለመፍትሔው በሣይንስ የተደገፈ ጥናት ማድረግ ነው፤›› ብለው ያምናሉ፡፡

ሁሉም ቦታ የሚሰጡት አስተያየቶች በተግባር ከሚታዩትና ከተሰሙት ነገሮችና ከሌሎች አገሮች የጥናት ግኝቶች በመነሳትና በአብዛኛው ግምታዊ እንደሆነ፣ የችግር ምንጭና መፍትሔው በባህሪይው ጭምር ለየት እንደሚል ያስረዳሉ፡፡ የችግሩን ምንጭ ከሥር መሠረቱ ማጥናት ካልተቻለ ደግሞ የሚወሰዱን ዕርምጃዎች እንዴት ውጤታማ ማድረግ ይቻላል? ሲሉም ይጠይቃሉ፡፡

በሸራተኑ የውይይት መድረክ ከመነሻው ጥናታዊ ጽሑፍ ሊቀርብ ይገባል የሚል ጥያቄ ቀርቦ እንደነበር የሚያወሱት ሙያተኛው፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በቅድሚያ ጉዳዩ የሚመለከተው ነበርና የሰጠው ምላሽ ‹‹ተጠንቷል አስፈላጊ ነው ተብሎ የሚወሰድ ከሆነ ይቀርባል›› ቢልም የቀረቡት ጽሑፎች የጥናት ውጤቶች ሳይሆኑ በተያያዥ ጉዳዮች ላይ ለውይይት የሚሆኑ የመነሻ ሐሳቦች እንደነበሩም ያስረዳሉ፡፡

ፌዴሬሽኑ አገራዊ ተቋም እንደመሆኑ፣ ለመመለስ ያህል ‹‹ተጠንቷል›› ማለት እንዳልነበረበት የሚናገሩት አቶ የማነ፣ ይህም ጥናት ላይ ተመሥርተን ለማኅበራዊና ሌሎች ችግሮቻችን ሣይንሳዊ መፍትሔ ለመስጠት ያለን ዝንባሌ አነስተኛ መሆኑ ነው፡፡ ምክንያቱም ይህ ሒደት ተመጣጣኝ ጊዜና ግብዓት ስለሚጠይቅ ወደ መፍትሔው በአቋራጭ ቶሎ መድረስን ታሳቢ ስለሚያደርግ እንደሆነም ያስረዳሉ፡፡

ለችግሮቻችን የምንወስዳቸው የመፍትሔ ዕርምጃዎች ለዘለቄታው፣ ‹‹መድኃኒት የማይሆኑን ለዚህም ሊሆን ይችላል፤›› የሚሉት ሙያተኛው፣ በሁሉም መስክ ‹‹….ሌሎች ለመድረስ የፈጀባቸውን ጊዜ እኛ በአጭር ጊዜ ውስጥ….›› የሚለው ፈሊጥ እንደማያዋጣ፣ ምንም ሀብት ሥራ ላይ ሳይደረግ ለችግሮች ሁሉ መፍትሔ በአቋራጭ የሚገኝ ከሆነ ሌሎች ማኅበራዊ ችግሮቻቸውን ለመፍታት የሚሄዱበትን መንገድና ርቀት የጅልነትና ያለማወቅ እንዲም ሲል በዘርና በጥላቻ ፖለቲካ ተዘፍቆ እያለ ‹‹እኛ በአስተሳሰብ ከእነሱ ልቀን የተገኘን ስለሆነ ነው›› ማለት ይህ ድንቅ ነገር ካልሆነ ምን ሊባል ይችላል? በማለት ይጠይቃሉ፡፡

ለደጋፊዎች ያልተገባ ባህሪይ ሁሉም በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በደረጃ አስተዋጽኦ ሲኖረው፣ ክለቦች የአንበሳውን ድርሻ እንደሚወስዱ ያምናሉ፡፡ ይሁንና በውይይት መድረኩ ላይ ይህ ሁከት የሚመለከተው ሁሉ ‹‹የወይራ ቀንበጥ የያዘች እርግብ ሆኖ ነው የቀረበው፤›› የሚሉት አቶ የማነ፣ ሁሉም አገር የሚያውቀውን ሀቅ ‹‹እኔ የለሁበትም፣ አይመለከተኝም፤›› እያለ የሚክድ ከሆነ ‹‹እንዴት መፍትሔ ይገኛል?›› በማለት ይጠይቃሉ፡፡

በሁሉም መስክ ‹‹ሰዎች በውስጣችን የምናስባቸው፣ በአደባባይ የምንናገራቸውና በተግባር የምንፈጽማቸው ነገሮች ፍፁም መለያየታቸው እዚህም እዚያም ለሚፈጠሩና በቀላሉ ለመፍታት ፈታኝ ለሆኑ ችግሮቻችን ምክንያት ይሆኑ እንዴ?›› በማለት አስተያየታቸውን የሚያጠቃልሉት አቶ የማነ፣ በጥባጭ ወይም አስበጥባጭ ሦስት ሰብዕና ሲኖረው፣ ሕዝብ ሲቆጠር የሚቆጥረው አካልና ቁመና በመሆኑ እንጂ ሰብዕና ቢቆጠር ኖሮ፣ ‹‹የኢትዮጵያውያን ቁጥር ሦስት መቶ ሚሊዮን ሳይገባ ይቀር ነበር? የችግሩ መፍትሔ መጀመሪያ ስህተትን መቀበል፣ ለማስተካከል ቃል መግባትና ወደ ተግባር መቀየር ነው፤›› ይላሉ፡፡       

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...