Thursday, December 1, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  የሳምንቱ ገጠመኝየሳምንቱ ገጠመኝ

  የሳምንቱ ገጠመኝ

  ቀን:

  ባለፉት ሃምሳ ዓመታት ዕድሜዬ ማንነቴን እጅግ እንድጠራጠር ያደረገኝ አጋጣሚ የተፈጠረው ባለፈው ሳምንት ውስጥ ነበር፡፡ በስፖርት ከዳበረው ቁመናዬና ውስጤን ከሚሰማኝ ፍፁማዊ ጤንነት አንፃር አንድም ጊዜ ቢሆን ስለራሴ ተጠራጥሬ አላውቅም ነበር፡፡ አኗኗሬ፣ አመጋገቤ፣ የዘወትር የስፖርት እንቅስቃሴዬ፣ ከማናቸውም ዓይነት ሱሶች ነፃ መሆኔና ደስተኝነቴ፣ ጤንነቴንም ሆነ አካላዊ ይዞታዬን እንድጠራጠር አድርገውኝ አያውቁም፡፡ ይልቁንም በራሴ ሁኔታ ስለምደሰት ሁሌም ኮራ እላለሁ፡፡ ባለፈው ሳምንት ባጋጠመኝ ምክንያት ግን የሚጎድለኝ ነገር እንዳለ ተረዳሁ፡፡ ይህ ጉድለት ደግሞ የእኔ ብቻ ሳይሆን የአብዛኞቻችን እንደሚሆን እርግጠኛ ነኝ፡፡ የሚገርመው እርግጠኛ ባልሆን ነበር፡፡

  ለብዙ ዓመታት በተለያዩ አጋጣሚዎች አራት ኪሎ፣ ፒያሳ፣ ካዛንቺንስ፣ ብሔራዊ ቴአትርና ሜክሲኮ አካባቢ የማየው አንድ ሰው በቀደም ዕለት ጠጋ ብሎኝ ሰላም አለኝ፡፡ ይህ ሰው ምንም እንኳ አለባበሱ ፅዱና ዝምተኛ ቢሆንም፣ የአዕምሮ ሕመምተኛ መሆኑን ሰምቻለሁ፡፡ በቀደም ዋቢ ሸበሌ ሆቴል አጠገብ ድንገት ፊት ለፊት ስንገናኝ ፈገግ እያለ መጥቶ ሰላምታ ካቀረበልኝ በኋላ፣ ‹‹ዛሬ አብረን ምሳ ብንበላ ምን ይመስልሃል?›› ሲለኝ ደንገጥ አልኩ፡፡ ወዲያው ግን፣ ‹‹እሺ አብረን መብላት እንችላለን፤›› ብዬው ወደ አንደ ታዋቂ ሬስቶራንት አመራን፡፡

  ሬስቶራንቱ ገብተን አረፍ እንዳልን ፈጣኑ አስተናጋጅ ትዕዛዝ ሊቀበለን ሜኑ ይዞ መጣ፡፡ ይኼኔ አብሮኝ ያለው ይህ ሰው ሜኖውን እያየ ከቆየ በኋላ ሳቅ አለ፡፡ ‹‹ምን ያስቅሃል?›› ስለው፣ ‹‹ገንዘባችን እንዲህ ረክሷል እንዴ?›› አለኝ፡፡ እኔም፣ ‹‹ችግር የለም እኔ እጋብዝሃለሁ የምትፈልገውን እዘዝ፤›› አልኩት፡፡ ‹‹የአንተ ገንዘብ ቢሆንስ ያው መውጣቱ አይደል?›› ብሎ ፓስታ አዘዘ፡፡ እኔም የምፈልገውን አዝዤ ምግባችንን መጠባበቅ ጀመርን፡፡ ምግባችን እስኪመጣ ድረስ ፀጥታውን ለመስበር በማሰብ፣ ‹‹ለብዙ ጊዜ ስንተያይ አታናግረኝም ነበር፡፡ ዛሬ እንዴት አናገርከኝ?›› በማለት ጨዋታ ስጀምር ሳቅ እያለ፣ ‹‹ምነው ጨነቀህ እንዴ?›› አለኝ፡፡ ‹‹ኧረ በፍፁም ለጨዋታው ያህል ነው፤›› በማለት ስመልስለት፣ ‹‹እንብላና እናወራለን፤›› ብሎኝ ከኪሱ ማስታወሻ አውጥቶ ማንበብ ጀመረ፡፡

  ምግባችን መጥቶልን እየበላን ሳለ፣ ‹‹የዚህ ቤት ምግብ ከድሮ ጀምሮ በጣም ይጣፍጣል፡፡ በዚህ ላይ ደግሞ ለብዙ ዓመታት እጅግ ደስ በሚያሰኝ ሁኔታ ደረጃቸውን ጠብቀው በመጓዛቸው ያስደስቱኛል፡፡ የእኛ ሰው እኮ ምግብ ቤት በከፈተ ሰሞን ንጉሥ አድርጎህ ካላመደህ በኋላ ይቀልድብሃል፤›› እያለ ሲስቅ፣ ይህ ሰው ተሽሎት ይሆን በማለት ማሰብ ጀመርኩ፡፡ ይህ ሰው የዛሬ 32 ዓመት ገደማ አራት ኪሎ ሳይንስ ፋኩሊቲ የአራተኛ ዓመት የፊዚክስ ተማሪ ሆኖ ነው ትምህርቱን በአዕምሮ ሕመም ምክንያት ያቋረጠው፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በቤተሰቦቹ ሥር እየተዳደረ ከተማውን ሲያካልል ይውላል፡፡ ሰውን ሳያናግር ብቻውን እያወራ ስለሚሄድ ብዙዎች ያውቁታል፡፡

  ‹‹አሁን አሁን ሳይህ ደህና ትመስላለህ፣ ተሽሎሃል ማለት ነው?›› አልኩት፡፡ ሳቅ እያለ እያየኝ፣ ‹‹አይ አይመስለኝም!›› አለኝ፡፡ ‹‹ይኼው በደንብ እያወራኸኝና ስለምግብ ቤቱም አስተያየት ስትሰጠኝ እኮ ፍፁም ጤናማ ሆነህ ነው፤›› በማለት ሙግት ቢጤ አስተያየት አቀረብኩለት፡፡ ጭንቅላቱን እየወዘወዘ፣ ‹‹ቤተሰቦቼም አንተ እንደምትለው ይላሉ፡፡ ነገር ግን ሁላችሁም ተሳስታችኋል፤›› ብሎኝ ኮስተር አለ፡፡ ‹‹ለምን?›› በማለት በፍጥነት ጥያቄ አቀረብኩለት፡፡ ‹‹ለምን ማለት ጥሩ ነው፡፡ ሰማህ በፊት የማንንም ሰው ወሬ አልሰማም ነበር፡፡ ማንም አፍጦ ቢያየኝ እኮ ከራሴ ጋር ብቻ ነበር የምነጋገረው፡፡ አሁን ግን እናንተ ተሽሎታል በምትሉት ነገር ውስጥ ስገኝ ግን መበሳጨትና መናደድ ጀመርኩ፡፡ የሰዎችን ንግግርና ሁኔታ ማመዛዘን ስጀምር እረበሽ ጀመር፡፡ ለመሆኑ ይህንን ዓይነቱን አኗኗር እንዴት ችላችሁት ትኖራላችሁ?›› ሲለኝ ደነቀኝ፡፡

  ‹‹ለመሆኑ ምን እየሰማህ ነው?›› ስለው፣ ‹‹ወጣቱ፣ ጎልማሳው፣ አዛውንቱ፣ ሀብታሙ፣ ደሃው፣ ምኑ ልበልህ ሁሉም ያማርራል፡፡ ስለምግብና ስለመኖሪያ ቤት ችግር፣ ስለፍትሕ ዕጦት፣ ስለመብት አለመከበር፣ ስለግብር መብዛት፣ ስለቢሮክራሲ፣ ስለመንገላታት፣ ስለኤሌክትሪክ መጥፋት፣ ስለውኃ መቋረጥ፣ ስለዘረኝነት፣ ስለብዙ ችግሮች በየሄድኩበት እሰማለሁ፡፡ ተስፋ የቆረጡ ወጣቶች፣ የራባቸው የሚመስሉ አሮጊቶችና ሽማግሌዎች፣ የቆሸሹና የተራቡ ሕፃናት በየሄድክበት እያየህ እንዴት ጤነኛ ነኝ ትላለህ? ሁሌም ብሶት የሚያሰማ ኅብረተሰብ ውስጥ እየኖርክ ይኼን የመሰለ ምግብ ስለበላህ የምትረካና ስኬት የሚሰማህ ከሆነ፣ ከአንተ ይልቅ ልብሱን ጥሎ ያበደ ወፈፌ ይሻላል፤›› ሲለኝ አስበረገገኝ፡፡

  ምሳችንን ጨርሰን ቡና እየጠጣን ሳለ፣ ‹‹አየህ የእኔ ወንድም እኔ ጤንነት የሚሰማኝ አንተና ቤተሰቦቼ በምትሉት መንገድ ሳይሆን፣ ይህንን ሁሉ ጉድ ሳላይና ሳልሰማ ነው፡፡ እናንተ ደግሞ ከተራራ የገዘፉ በርካታ ስህተቶች ውስጥ ሆናችሁ፣ በጊዜያዊ ምቾታችሁና በአለባበሳችሁ እየረካችሁ በቅዠት ዓለም ውስጥ ትኖራላችሁ፡፡ የገዛ ወገናችሁን ደም እያፈሰሳችሁ ትመፃደቃላችሁ፡፡ ሕፃናትንና አቅመ ደካሞችን አፈናቅላችሁ ሜዳ ላይ ከበተናችሁ በኋላ ስለሰላም ታወራላችሁ፡፡ የአገሪቱን የተፈጥሮ ስጦታዎች በመጠቀም ሀብታም መሆን እየተቻለ፣ ምስኪኑን ሕዝብ በድህነት አሳሩን ታሳዩታላችሁ፡፡ ዕብሪት በተሞላበት ንግግራችሁ መግባባት አቅቷችሁ፣ አገሪቱን ለማውደምና ሕዝቡን ስደተኛ ለማድረግ ትተራመሳለችሁ… ›› እያለ የገዛ ራሴን ከንቱ መኩራራት አፈራረሰብኝ፡፡ ራሴን እስክጠራጠር ድረስ ይህ ተናግሮ የማያውቅ ሰው ልክ ልካችንን ሲናገር ገረመኝ፡፡ እናንተስ ምን ተሰማችሁ? ሌሎችን ወፈፌ ስንል እነሱ ግን እንዲህ በልጠውን ልካችንን ሲነግሩን አናሳፍርም?

  (ዮናስ አክሊሉ፣ ከአምስት ኪሎ)

  spot_img
  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  [በተቋሙ ሠራተኞች የተወከሉ አንድ ባልደረባ ሚኒስትሩን ለማነጋገር ቀጠሮ ይዘው ወደ ቢሯቸው ገቡ]

  ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም ሰላም ... ተቀመጥ! አመሠግናለሁ ክቡር ሚኒስትር!...

  የጉራጌ ዞን ጥያቄና የክላስተር አደረጃጀት የገጠመው ተቃውሞ

  መንግሥት የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል አካል የነበሩ ዞኖችንና...

  አዋሽ ባንክ ካፒታሉን ወደ 55 ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ያስገደደው ምክንያት ምንድን ነው?

  ባለፈው ቅዳሜ ጠቅላላ ጉባዔውን ያካሄደው አዋሽ ባንክ የ43 ቢሊዮን...

  አቢሲኒያ ባንክ ካለፈው ዓመት የ127 በመቶ ብልጫ ያለው ትርፍ በማግኘት አዲስ ታሪክ አስመዘገበ

  አቢሲኒያ ባንክ ከቀደሚ የሒሳብ ዓመት የ127 በመቶ ብልጫ ያለው...