በገብረ ፃድቃን ገብረ ትንሳዔ (ሌፍተናንት ጄኔራል)፣ በታደሰ በርሄ (ብርጋዴር ጄኔራል) እና በመስፍን አማረ (ብርጋዴር ጄኔራል)
በአገራችን ኢትዮጵያ የነበረው የአስተዳደር ዘይቤ ከተለወጠ አንድ ዓመት ሞልቶታል፡፡ በሕገ መንግሥቱ መሠረት ደግሞ በየአምስት ዓመቱ የሚደረገው ምርጫ አንድ ዓመት ቀርቶታል፡፡ ባለፈው አንድ ዓመት የፖለቲካ ምኅዳሩ መስፋቱ፣ የፖለቲካ እስረኞች መፈታታቸው፣ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል መልካም ግንኙነት መፈጠሩና የጦርነት ዳመና መገፈፉ ጥሩና የሚደገፉ ሥራዎች ናቸው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ አንድ ዓመት ለቀረው ምርጫ ግልጽና የማያሻማ ውሳኔ አለመኖሩና በዚህ መሠረት በቂ ዝግጅቶች አለመካሄዳቸው፣ በገዥው ፓርቲ ውስጥ ባሉት የፖለቲካ ድርጅቶች መካከል የሐሳብና የአሠራር ልዩነቱ ጤናማ መሆኑን ጥያቄ ውስጥ መግባቱ፣ ኢኮኖሚው በሚያሠጋ ሁኔታ ውስጥ መሆኑ፣ ዜጎች በሚሊዮኖች መፈናቀላቸውና በማንነታቸው ምክንያት ለከፍተኛ ጥቃት (የሞት የንብረት ውድመት) መዳረጋቸው፣ ሰላም፣ መረጋጋትና የሕግ የበላይነት በአገሪቱ አለመስፈኑ፣ የወጣቶች የሥራ አጥነትና የፖለቲካ ተሳትፎ ጊዜውን ጠብቆ የሚፈታበት ተስፋ አለመኖሩ፣ በጠቅላላ የተጀመረው የሽግግር ሒደት በተሻለ ውጤት ለማጠናቀቅ የሚያስችል ፍኖተ ካርታ አለመኖሩና ይባስ ብሎም አስፈላጊነቱ ጥያቄ ውስጥ መግባቱ፣ አገራችን እጅግ አሳሳቢ በሆነ የፖለቲካ ሁኔታ ውስጥ እንድትገኝ አድርጓታል፡፡
በዚህ ላይ ደግሞ የተቃዋሚው የፖለቲካ ጎራ እጅግ የተበታተነ ከመሆኑም በተጨማሪ፣ ብዙዎቹ እንደ አማራጭ በግልጽ ለሕዝብ ያቀረቡት አገራዊ የፖለቲካ ፕሮግራምና የምርጫ ማኒፌስቶ መኖሩን አናውቅም፡፡ እነዚህ ሁኔታዎች በድምር አገራችንን በከፍተኛ የፖለቲካ ቀውስ ውስጥ እንድትገባ አድርገዋታል፡፡ እነዚህ (የተጠቀሱትና ያልተጠቀሱም ይኖራሉ) ስትራቴጂካዊ አደጋዎች አገራችንን ወደ ማትወጣው ማጥ ሊከቷት ይችላሉ፡፡ ስለዚህ በቀረው አጭር ጊዜ በከፍተኛ መረባረብ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል አቅጣጫና አገራዊ አቅማችን ያገናዘበ የሥራ ቅደም ተከተል መያዝ ይገባል የሚል ሐሳብ አለን፡፡ የዚህ ጽሑፍ አላማም በዚሁ በአገራችን ጉዳይ ላይ በሚደረጉ ውይይቶችና መፍትሔ የማፈላለግ እንቅስቃሴ አስተያየታችንን ለመስጠት ነው፡፡
- መነሻችን
- አገራዊ ሁኔታ
አገራችን ኢትዮጵያ የምትገኝበት የፖለቲካ ሁኔታ ስንል በቅርቡ (ከ2008 ዓ.ም.) በኋላ ያለውን ይበልጥ ደግሞ፣ ባለፈው አንድ ዓመት ያለውን ሁኔታ መነሻ በማድረግ ነው የምንመለከተው፡፡ ከቀጣይ ዕርምጃዎቻችን አንፃር ዋናው ጉዳይ ይህ በመሆኑ፡፡ ያለፍንበት ታሪካዊ ጉዞ ለአሁኑ ሁኔታችን ተፅዕኖ የለውም ብለን ሳይሆን (የተለያዩ ትርክቶች መኖራቸው እንደተጠበቀ ሆኖ)፣ ይህ ጽሑፍ የታሪክ ጽሑፍ ባለመሆኑ ዋናው ትኩረታችን አሁን ከደረስንበት የፖለቲካ ምዕራፍ በአገራችን ሰላምና ዴሞክራሲ ከማስፈን አንፃር (እንዴት ብንቀጥል ይሻለናል በሚለው ሐሳብ) ላይ አስተያየታችን ግልጽ ለማድረግ ነው፡፡ ከአንድ ዓመት ወዲህ የመጣው ለውጥ ከመከሰቱ በፊት በኢሕአዴግ የሚመራው የአገራችን የፖለቲካ አስተዳደር የፌዴራል ሥርዓቱ ከሚጠይቀውና የሥርዓቱ መሠረት ከሆነው፣ በተለይ ደግሞ እንደ አገራችን በመሳሰሉ ብዙኃነትን ማስተናገድ በሚገባቸው አገሮች የግድ መኖር የነበረበትን ሰፊ ዴሞክራሲያዊ ምኅዳር በጣም እየጠበበ በሕገ መንግሥቱ በተቀመጡ የቡድንም ሆነ የግለሰብ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ መብቶችን አጋጣሚው ሲከሰት እየደፈጠጠ፣ ፖለቲካዊ ልዩነቶችን በሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ መንገድ ሳይሆን በፀጥታዊ አስተዳደራዊ መንገድ እየፈታ ኅብረተሰቡን አሸማቆና አድርባይ አድርጎ ማስተዳደርን እንደ ፖሊሲ ሲጠቀም የነበረ አስተዳደር ነበር፡፡ በሕገ መንግሥቱ የተቀመጠውን ፌዴራላዊ አስተዳደር አሀዳዊ አስተዳደር በሚመስል ሁኔታ አማክሎ፣ በክልሎች ጉዳይ ጣልቃ እየገባ ሲያስተዳድር የነበረ ነው፡፡ ለኢሕአዴግ ዴሞክራሲ በተለያዩ የፖለቲካ ኃይሎች መካከል የኃይል ሚዛናቸውን መሠረት ያደረገ ድርድር፣ ከዚህ አልፎ ደግሞ ተአማኒነት ባለው ሕዝባዊ ምርጫ የሚሰጥ የሕዝብ ውሳኔ ውጤት ሆኖ በቀጣይነት እያደገ ሥር እየሰደደ የሚሄድ ሒደት ሳይሆን ሰጪና ተቀባይ ያለው፣ ሰጪው ለሱ የሚጠቅመውንና የፈቀደውን የሚሰጥ፣ ተቀባይ ደግሞ አሜን ብሎ የተሰጠውን ያህል ብቻ ተቀብሎ በፀጋ የሚኖር አድርጎ የሚያስብ አስተሳሰብ ነው ሲሠራበት የነበረው፡፡ በጽሑፍና በንግግር የሚባለው ሌላ ሊሆን ይችላል፡፡ በተግባር የታየው ግን የተገለጸው ነው፡፡ ይህ ደግሞ መቀጠል አልቻለም፣ የለውጡ መነሻ ይህ ነው፡፡
ይህ ከላይ የታየው ሁኔታ ኅብረተሰቡ ውስጥ በፍትሕ መጓደል ወይም አድልዎ፣ የመልካም አስተዳደር ዕጦት፣ ፍትሐዊ ያልሆነ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት፣ መብቱን ለመጠየቅ የሚፈራና የተሸማቀቀ ኅብረተሰብ፣ ራሳቸውን ከሕግ በላይ አድርገው እንደፈለጋቸው የሚያደርጉ የመንግሥት የሥራ አስፈጻሚ አካላትን መረን የለቀቀና ለፓርቲው ታማኝ ነን እስካሉ ድረስ ጠያቂ የሌላቸው በየደረጃው የተሰገሰጉ የመንግሥት ባለሥልጣናት ለመንግሥትና ለሕዝብ ሀብት ምዝበራና ብክነት ምክንያት ሆነዋል፡፡ ፓርቲና መንግሥት ልዩነታቸው ጠፍቶ አንድ የሆኑበት፣ የመንግሥት መሠረታዊ ተቋማት (ሕግ አውጭው፣ ሕግ ተርጓሚውና ሥራ አስፈጻሚው) በሥራ አስፈጻሚው ብቻ እንደፈለገ የሚዘወሩበት፣ የሕዝብ ተመራጮች ለሕዝባቸው ባላቸው ተቆርቋሪነትና ተጠያቂነት ሳይሆን ለፓርቲው ባላቸው “ታማኝነት” የሕዝብ ውክልና አግኝተዋል እየተባለ የሚመረጡበት፣ ከዚህ ሲያልፍም ምርጫ የሚጭበረበርበት ሁኔታ ውስጥ ነው የነበርነው፡፡ ይህ መለወጥ ነበረበት፣ የለውጡ አስፈላጊነትም ከዚህ አንፃር ነው መለካት ያለበት፡፡ ውጤቱም ይህንን ሁኔታ ማስተካከል መሆን አለበት ብለን እናምናለን፡፡
ለውጡ የመጣው በኅብረተሰቡ ውስጥ መጠኑና ግፊቱ ቢለያይም፣ በሁሉም የአገራችን አካባቢዎች በተቀሰቀሰ የሕዝብ ቁጣ ነው፡፡ ጠንካራው የሕዝብ አመፅ በኦሮሚያና ቀጥሎም በአማራ ክልሎች የነበረ ቢሆንም፣ በትግራይና በሌሎች ክልሎችም ውስጥ የነበረው የሕዝብ ቁጣና በተለይ የወጣቶች ተቃውሞ ቀላል አልነበረም፡፡ ይህ የሕዝብ ቁጣና ምሬት ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግን ራሱን እንዲፈትሽ በማስገደድ፣ በፓርቲው ውስጥም የለውጥ አስፈላጊነትንና ለውጥ ለማምጣት የሚፈልግ ኃይል እንዲወጣ ምክንያት ሆነ፡፡ ይህ የኅብረተሰቡ ከፍተኛ ተቃውሞና በፓርቲው ውስጥ የተፈጠረው የለውጥ ኃይል በቅንጅት ለውጡን አመጣ፡፡ ለውጡ የነበረውን መንግሥት በኃይልና በአመፅ ጠራርጎ ለማስወገድ በሚፈልጉ የአመፅ ኃይሎችና ለውጡን ከውስጥ ለማምጣት የመንግሥትን ሥልጣን በመቆጣጠር ለማምጣት በሚፈልጉ ኃይሎች ቅንጅት የመጣ ነው፡፡ ይህ ለውጡ የመጣበት ሁኔታ እስካሁን ድረስ ለውጡን በማስተዳደር (Manage) ላይ ተፅዕኖው ይታያል፡፡ በሁለቱም ኃይሎች መካከል ውጥረት ያለ ይመስላል፡፡ አሁንም የለውጡ አካሄድና ሊያስመዘግባቸው በሚፈለጉ ውጤቶች ላይ የሁለቱም ኃይሎች ፍላጎቶች ውጥረት ውስጥ ያሉ ይመስላል፡፡ የዚህ ዋና መገለጫው በየስብሰባው የሚሰነዘሩት ሐሳቦችና በተለይ ደግሞ ኢሕአዴግ ውስጥ ያለው ሁኔታ ነው፡፡
በአገር ደረጃ የተቀሰቀሰው ቁጣና የለውጥ ፍላጎት በአመፅና በነውጥ ቢጠናቀቅ ኖሮ፣ በአገራችን አንዣብቦ የነበረው የፖለቲካ ሥጋትና ይህም ሊያስከትል ይችል የነበረው አደጋ እጅግ ከፍተኛ ይሆን ነበር፡፡ አገራችን አሁን ባለችበትና ከለውጡ በፊት በነበሩት ጊዜያት፣ በነውጥ ሥልጣን ላይ የነበረውንና ያለውን አስተዳደር በመጠራረግ ተሸክማ እንደ አገር መቀጠል ትችል ነበር ወይ ተብሎ ሲጠየቅ መልሱ እጅግ አጠራጣሪ ነው፡፡ አስተዳደሩን በጠቅላላ በነውጥ ከመጠራረግ በመለስ በመጣው ለውጥ እንኳን እንደ አገር ሁኔታውን ተሸክመን ማለፍ እየከበደን መሆኑ በግልጽ እየታየ ነው፡፡ ነውጥ ቢከሰት የመንግሥት መዋቅሮችና የኢኮኖሚ አውታሮች በከፍተኛ ደረጃ ይወድሙ ነበር ብቻ ሳይሆን፣ ከፍተኛ ደም መፋስስና የንብረት መውደም ይደርስ ነበር፡፡ አገር እንደ አገር የመቀጠል ዕድሏ የጨለመ ይሆን ነበር፡፡ ይህ ሳይሆን መቅረቱና ለውጡ በመጣበት መንገድ መከሰቱ (የማይቀር ለውጥ ስለነበረ) እንደ ተሻለ ሁኔታ ማየቱ ተገቢ ነው፡፡ ይህ ሲባል ለውጡ በመጣበት መንገድ የጠፋ ሕይወትና የወደመ ንብረት፣ በሕዝብ ላይ የደረሰ የአካልም ሆነ የሥነ ልቦና ጥቃት አልነበረም ማለት አይደለም፡፡ አሁንም ቢሆን ያለው የፖለቲካ ሁኔታ አያሳስብም ማለትም አይደለም፡፡ በጣም አሳሳቢ ነው፡፡ ግን አሁን በአንድ አገር ውስጥ ሆነን የመንግሥት መዋቅር ተጠቃሎ ሳይፈራርስ የሕይወትና የንብረት ጉዳቱን ተሸክመን ችግሩን ለመፍታት እየሞከርን እንገኛለን፡፡ ይህ ቀላል ጉዳይ አይደለም፡፡
አገራዊ የፖለቲካ ቀውሱ አሁን ካለበት ደረጃ የባሰ እንዳይሆን አስተዋጽኦ ያደረጉ ምክንያቶች አሉ፡፡ በኢትዮጵያ ሕዝቦች መካከል የነበረውና ያሉት የረጅም ጊዜ አብሮ መኖር፣ መከባበር፣ በሃይማኖት፣ በባህል፣ በጋብቻና በሌሎችም ብዙ ገመዶች የተሳሰረ መሆኑ የአደጋውን መጠን ከተከሰተበት በላይ እንዳይሆንና ወደ ጠቅላላ የእርስ በርስ መፋጀት እንዳያድግ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በተለያዩ ታሪካዊ ወቅቶች በበጎም በክፉም ጊዚያት በጋራ የሠራቸው፣ የተጋፈጣቸው፣ አገራችንን እንደ አንድ አገር ለረጅም ጊዜ እንድትቆይ ያደረጉ ክስተቶች በሕዝቡ ውስጥ የፈጠሩት ሰብዓዊነትና አንድነት አደጋውን በእጅጉ ቀንሶታል፡፡ ችግሮች በተፈጠሩበት አካባቢ ገሚሱ ሲገድል ገሚሱ ያድናል፡፡ ሌላው ሲዘርፍ ገሚሱ ይከለከላል፡፡ ይህ ሁኔታ ባይኖር ኖሮ ሲነዛ በነበረው የጥላቻ ፕሮፓጋንዳ ሕዝቡ እርስ በርሱ ይተላለቅ ነበር፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የትግራይ ሕዝብ አደጋውን ካስተዋለ በኋላ በውስጡ ያሉትን ችግሮችና ልዩነቶች አቆይቶ፣ እንደ ሕዝብ እየመጣብኝ ነው ብሎ ያመነበትን አደጋ ለመከላከል በአንድነትና በፅናት ቆሟል፡፡ የትግራይ ሕዝብ ይህንን በማድረግ እስካሁን ለአደጋው ሳይጋለጥ ዘልቋል፡፡ ሌላው እዚህ ላይ ሳይጠቀስ መታለፍ የሌለበት ትልቅ ጉዳይ፣ በጠቅላላው የአገርን ሰላም በማስጠበቅ በኩል ትልቅ ድርሻ የነበረው የአገር መከላከያ ሠራዊት ነው፡፡ ይህ የመንግሥት ተቋም በተቻለ መጠን ሕገ መንግሥቱን መሠረት በማድረግ ችግሮች በተከሰቱበት አካባቢዎች እየገባ ፀጥታ እንዲከበር፣ ሕዝብ እንዲረጋጋና ሰላም እንዲመለስ ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ የሠራዊቱ አባላት በተቻለ መጠን ከወገንተኝነት በመፅዳት አገርንና ሕገ መንግሥትን ባያስቀደመና በጥሩ ዲሲፕሊን ለሠሩት ሥራ ሊመሰገኑ ይገባል፡፡ አገሪቱንም ከባሰ ጉዳትና መፈራረስ ታድገዋል ብለን እናምናለን፡፡
እነዚህ ከላይ ያየናቸው ሁኔታዎች በአገራችን የተከሰተው ቀውስ ከደረሰበት ደረጃ እንዳይባባስ ትልቅ ድርሻ የተጫወቱ ክስተቶች፣ በሕዝቦች ውስጥ ያሉ እሴቶችና የመከላከያ ሠራዊታችን ለኢትዮጵያ ሕዝቦች ፍላጎትና ለሕገ መንግሥቱ ታማኝ መሆን፣ ለወደፊትም አገራችን ከፖለቲካው ቀውስ ለመውጣት በምናደርገው ጥረትም በተገቢው መንገድ ከተጠቀምንባቸው ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖራቸዋል ብለን እናምናለን፡፡ አሁን የምንገኝበትን ሁኔታ ስናይ ደግሞ የአገሪቱን የፖለቲካ ሥልጣን እስካሁን ድረስ ተቆጣጥሮ የነበረው የኢሕአዴግ አራቱ ብሔራዊ የፖለቲካ ድርጅቶች ውስጥ የአስተሳሰብና የአሠራር አንድነት የጠፋ መሆኑን ኃላፊዎቹ በየአጋጣሚው ሲገልጹ እንሰማለን፡፡ በጠቅላላ ጠፍቷል እንዳንል አንዳንዴ ብቅ እያሉ የተለወጠ ነገር የለም ስለሚሉን፣ አሁንም አገሪቱ በኢሕአዴግ ገዥ ፓርቲነት ስም እየተዳደረች ነው፡፡ ከዚህ አልፎ ግን ድርጅቱ የቆመላቸው አስተሳሰቦች እንደ አብዮታዊ ወይም ልማታዊ ዴሞክራሲ፣ ብሔር ብሔረሰቦችን መሠረት ያደረገው ፌዴራላዊ የፖለቲካ አስተዳደር አወቃቀር፣ የመንግሥት በኢኮኖሚ ዕድገት ያለው ሚና ላይ ልዩነቶች እንዳሉ በግልጽ ባለፈው ጉባዔ ታይቷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የፖለቲካ ድርጅቶቹ የነበራቸውን ድርጅታዊ አሠራር ማለትም ጊዜውን የጠበቁ ስብሰባዎችና በዚህ መሠረት የሚወሰኑ ውሳኔዎች እንደተለመደው እየሄዱ ያሉ አይመስሉም፡፡ በአንዳንድ ውሳኔዎች ላይ ልዩነቶች አሉ (ለምሳሌ በማንነትና የወሰን ማካለል ኮሚሽን ጉዳይና በፓርቲው ውህደት ላይ)፡፡ ጠቅለል ባለ ሁኔታ ድርጅቶቹን አስተሳስረው የነበሩት የፖለቲካ አስተሳሰቦች በተለይ አሁን በሥራ ላይ ያለው ሕገ መንግሥትና ከዚህ የሚመነጨው የአስተዳደር አከላለል፣ ድርጅቱ ሲከተለው የነበረው የፖለቲካዊ ኢኮኖሚ አስተሳሰብ (Developmental State) እና በውስጣዊ አሠራራቸው ላይ ችግሮች አሉ፡፡ ይህ ማለት ስትራቴጂካዊ አመራሩ ውስጥ ከፍተኛ ችግር ተፈጥሯል ማለት ነው፡፡
በዚህ ሁሉ መሀል ደግሞ በገዥ ፓርቲና በውስጡ ባሉ ድርጅቶችም ግልጽ ሆኖ የወጣናለሕዝብ በይፋ የተነገረ የፖለቲካ አስተሳሰብ የለውጥ አጀንዳና አካሄድ የለም፡፡ በኢሕአዴግ ውስጥ ሆነው የቆየውን አስተሳሰብ የሚቃወሙ ድርጅቶች በአንዳንድ አጋጣሚዎች ተቃውሞአቸውን ይገልጻሉ እንጂ በተደራጀ መንገድ በሌላ አማራጭ ሐሳብ ለመተካት እንደሚፈልጉ በግልጽ አልወጣም፡፡ ይህ ሁኔታ የኢትዮጵያን የፖለቲካ ሁኔታ በንቃት ለሚከታተለው የኅብረተሰብ ክፍል (አሁን ደግሞ ይህ ከፍል ቁጥሩ እጅግ ተበራክቷል) በየአጋጣሚው ከሚደመጡ የኃላፊዎች ንግግሮች ብቻ እንዲገምት አስገድዶታል፡፡ ይህ በሚገባ ታስቦበት የሚደረግ የሚመስል የግልጽነት መጓደል (Deliberate Ambiguity) አሁን በአገራችን ላለው የፖለቲካ አለመረጋጋት እያስከተለ ያለው ጉዳት ከፍተኛ ነው፡፡ ለውጡን ተከትሎ በውጭ አገር የነበሩ የፖለቲካ ድርጅቶች ወደ አገራቸው ገብተዋል፡፡ ይህ አሠራር ሕግና ሥርዓት የተከተለ ባይሆንም፣ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች ወደ አገር ቤት መግባታቸው የሚደገፍ ነው፡፡ በአገር ውስጥ ሆነው ሲያጋጥሙዋቸው የነበሩ ችግሮችን እየቻሉ ሲታገሉ የነበሩ የፖለቲካ ድርጅቶችም ሁኔታው አሁን ተመቻችቶላቸዋል፡፡ ይህ ሁኔታ የኢትዮጵያ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ማዕከሉ አገር ውስጥ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ ይህ ጥሩና የሚደገፍ ነው፡፡ እነዚህ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገር ሆነው ሲታገሉ የነበሩ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ በጋራም ይሁን በተናጠል በሚገባ የታሰበበትና የተጠናቀረ በአገራችን መከተል ያለብን የአገረ መንግሥት ግንባታ (State Building) አቅጣጫ የሚያሳይ አስተሳሰብና የአስተዳደር አወቃቀር በግልጽ ለሕዝብ በይፋ አላወጡም፡፡ ይህ በዋናነት በጥላቻ ፖለቲካ ብቻ ተዘፍቆ የነበረ የፖለቲካ ኃይል ከነበረበት አዙሪት ወጥቶ፣ የተለየና ረጅም ርቀት ያማተረ የአገረ መንግሥት ግንባታ ፕሮግራም አውጥቶ ለሕዝብ ይፋ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ ከዚህ አንፃር አሁንም በተለያዩ አጋጣሚዎች የፓርቲ ኃላፊዎች ከሚሰጡዋቸው የተቆራረጡ መግለጫዎች በዘለለ፣ የአገረ መንግሥት ግንባታ እንቅስቃሴው የሚመራበት አቅጣጫ በአገር ውስጥ ሰላም ለማስፈን የሚያስችል፣ የአገሪቱን ኢኮኖሚ አሁን ካለበት ችግር የሚወጣበት፣ በቀጣይ ደግሞ ዕድገት የሚያሳይበት፣ የአገር አስተዳደር ሥርዓቱ በጥልቀትና በስፋት ተዘርዝሮ የፓርቲ ፕሮግራምና የምርጫ ማኒፌስቶ ሆኖ፣ ኢሕአዴግ አሁን እየተከተለው ካለው የተለየ መሆኑን በማሳየት ለመራጩ ሕዝብ መቅረብ አለበት፡፡ ይህንን እስካሁን ድረስ አላየንም፡፡ እዚህም ላይ ከፍተኛ የስትራተጂካዊ አመራር ችግር ያለ ይመስለናል፡፡
ይህ ሁኔታ በድምር የሚያሳየን የሕዝቦች የለውጥ ፍላጎት ከፍተኛ እንደሆነ ነው፡፡ ግን ለውጡ እንዴት ይቀጥላል? ምን የተሻለ አማራጭ ይመጣል? ወይም ካለፈው የፖለቲካ አስተዳደር ምኑ ይሻላል? የሚለው ሕዝብን በሚያሳምን መንገድ በግልጽ አልወጣም፡፡ ይህ ደግሞ ከፍተኛ የፖለቲካ አለመረጋጋትና ቀውስ አስከትሏል፡፡ ከባድ የሰላምና መረጋጋት ዕጦት አለ፡፡ ሕዝቦች እየተፈናቀሉ ነው፡፡ በማንነት ጥያቄ ላይ ተመሥርተው እርስ በርሳቸው እየተፋጁ ነው፡፡ ሁኔታው ለዚህ መፍትሔ የሚያስቀምጥ ስትራተጂካዊ አቅጣጫ አስቀምጦ በፍጥነትና በከፍተኛ ኃላፊነት፣ በውጤታማነት መንቀሳቀስን ይጠይቃል፡፡ አሁን ያለው የፖለቲካ ቀውስ ቀስ በቀስ የአገራችንን ኢኮኖሚ በከፍተኛ ደረጃ እየጎዳው ነው፡፡ የውጭ አገር ባለሀብቶች አገራችን ውስጥ መዋዕለ ንዋያቸውን ለማፍሰስና ራሳቸውን ጠቅመው አገራችንና ሕዝባችን ለመጥቀም የነበራቸው ተነሳሽነትና ፍላጎት እንደቀነሰ መገመት ይቻላል፡፡ የአገር ውስጥ ባለሀብቱም አዳዲስ ሥራ ፈጣሪ ኢንቨስትመንት ማድረግ ይቅርና ቀደም ብለው በሥራ ላይ የነበሩ ድርጅቶች በውጭ ምንዛሪ እጥረት ከፍተኛ ችግር ውስጥ እንደሆኑ ይታወቃል፡፡ በመንግሥት ደረጃም ትልልቆቹ ፕሮጀክቶች ባለፈው ዓመት የሥራ እንቅስቃሴያቸውን እንዲያቆሙ ተገደዋል፡፡ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው (በአሁኑ ጊዜ ትልቁ ሥራ ፈጣሪ) በከፍተኛ ችግር ውስጥ እንዳለ ይታወቃል፡፡ እነዚህ የኢኮኖሚ ችግሮች ቀስ በቀስ ወደ ፖለቲካ ችግር ይቀየሩና የሥራ አጡ ብዛት፣ የዋጋ ንረቱት፣ የዕቃዎች አለመገኘት፣ የኑሮ ውድነት፣ ተጠራቅመው የፖለቲካ ቀውሱን ይበልጥ በማባባስ ለመመለስ አስቸጋሪ ወደ ሆነበት ደረጃ እንዳይገፉት ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ እነዚህ ሁኔታዎች በተናጠልና እርስ በርሳቸው በመደጋገፍ የሚፈጥሩት ችግር አገራችንን ወደ ከፍተኛ ቀውስ ውስጥ እየከተታት ነው፡፡
በዚህ የሽግግር የፖለቲካ ቀውስ ውስጥ ባለንበት ሁኔታ የውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት፣ በተለይ በኤርትራው መሪ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ደላላነት ከመካከለኛ ምሥራቅ አገሮች ጋር የሚደረገው ግንኙነትና ፕሬዚዳንት ኢሳያስ በአገራችን ጉዳይ ላይ ያላቸው አሉታዊ ሚና፣ የራሳችንን ችግሮች በራሳችን እንዳንፈታ ሌላ ተጨማሪ ችግር ሆኖ የሚያባብስ ሁኔታ እየፈጠረ ነው፡፡ እዚህ ላይ መግለጽ የምንወደው ጉዳይ በኤርትራና በኢትዮጵያ መካከል ሰላም መውረዱ፣ በተለይ ደግሞ በሁለቱ ወንድማማች ሕዝቦች መካከል ሰላም መፈጠሩና የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ወደ ከፍተኛ ደረጃ እንዲጎለብት ሁኔታዎች መመቻቸታቸውን ከልብ እንደግፋለን፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ በመንግሥታቱ መካከል የሚደረገው ግንኙነትና ስምምነት ደግሞ በየደረጃው ጊዜውን እየጠበቀ የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላትና የፖለቲካ መሪዎች እየተወያዩበት፣ እያመኑበት፣ ውሳኔ እየሰጡበት፣ ከዚሀ ቀጥሎም ጊዜውን ጠበቆ ለሕዝብ የሚገለጽበት አካሄድ መከተል ይገባል፡፡ ከሁሉም በላይ የውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት የአገራችንን የአሁንና የወደፊት አገራዊ ጥቅሞች የማይጎዳና አደጋ ውስጥ የማይከት፣ አሁን ካለንበት የፖለቲካ ቀውስ ተጨማሪ ቀውስ የማይፈጥርና በሕዝቦች ንቁ ተሳትፎ በዕርጋታና እየተጠና የሚደረግ መሆን ይኖርበታል፡፡
ከፍ ሲል ሲገለጹ ከነበሩ ችግሮችና ተግዳሮቶች በተጨማሪ መታሰብ ያለበት ጉዳይ የአገራችን ተቋማዊ መዋቅር፣ አሁን በለውጡ ምክንያት (በሽግግሩ ዘመን) እንዲሸከም እየተገደደ ያለው በጠቅላላው ሳይፈራርስ መሸከም ይችላል ወይ የሚለው ጉዳይ ነው፡፡ የአገራችን መንግሥታዊ መዋቅሮች በየጊዜው እየተጨፈለቁና እየፈረሱ እንደገና እንዳዲስ ለመገንባት ጥረት እየተደረገ፣ በዚህ ሒደት ጠንካራ አቅም ያላቸው መንግሥታዊ መዋቅሮችን መፍጠር ቀላል ያልሆነ ተግዳሮቶችና ችግሮች ባሉበት ወቅት ነው ለውጡና ሽግግሩ እየተካሄደ ያለው፡፡ አሁን ደግሞ በዚህ ባልጠነከረው የመንግሥት መዋቅር በጣም ብዙ የተደራረቡ ሥራዎችን በአጭር ጊዜ ለመፈጸም እየተፈለገ ነው፡፡ መንግሥታዊ መዋቅሩና አጠቃላይ የአገራችን የፖለቲካ ሥርዓት መዋቅር፣ እነዚህን ተደራራቢ ብዙ ሥራዎች በአጭር ጊዜ ተሸክሞ መፈጸም ይችላል ወይ ተብሎ መጠየቅ ያለበት ጉዳይ ይመስለናል፡፡
ከዚህ አንፃርም ስናይ አሁን በአገራችን ውስጥ ከዚህ ቀደም ሲደረጉ ከነበሩት ምርጫዎች ለየት ያለና ተአማኒነት ያለው፣ በአግባቡ የተደራጀ የፖለቲካ ፍላጎቶቻችንን ከሞላ ጎደል ሊያሳካ የሚችል ምርጫ በሕገ መንግሥቱ መሠረት ለማካሄድ የቀረን ጊዜ አንድ ዓመት ብቻ ነው፡፡ ለዚህ የሚደረገው ዝግጅት እጅግ ከፍተኛና ሁሉንም የመንግሥት አካላትና የኅብረተሰቡን ድጋፍና እንቅስቃሴ የሚጠይቅ ነው፡፡ ለዚህ የሚደረግ ዝግጅት ለምሳሌ የሕዝብ ቆጠራ፣ ተፈናቃዮችን ወደ ነበሩበት የመመለስና ኑሯቸውን ማስተካከል፣ ሰላምና መረጋጋት ማስፈን፣ ኢኮኖሚው እንዲነቃቃ ማድረግ፣ የገዥው ፓርቲና የተቃዋሚ ፓርቲዎች የምርጫ ዝግጅትና እንቅስቃሴ፣ ምርጫው በውጤታማነት እንዲከናወን መደረግ ያለበት አስተዳደራዊና ሎጂስቲካዊ ዝግጅት፣ ወዘተ እጅግ ብዙ ናቸው፡፡ እነዚህን በተገቢው መንገድ ማካሄድ የሽግግር ወቅቱ ዋነኛ ሥራዎች መሆን አለባቸው፡፡ ከዚህ አልፎም የመንግሥት የዕለት ተዕለት ተጨማሪ ሥራዎችም አሉ፡፡ በዚህ ሁኔታ የፖለቲካ ቀውሱን የሚያባብሱ፣ ባልተደራጀና በሩጫ የሚከናወኑ ሥራዎች ከተጨመሩበት ውጤቱ ያማረ አይሆንም፡፡ ስለዚህ ግልጽ ሆነ የሥራ ቅደም ተከተል ወጥቶ የአገሪቱ የፖለቲካ መዋቅር ሊሸከም በሚችለው ሁኔታ እየተመዘነ ቢሠራና ፕሮግራም ቢወጣ የተሻለ ውጤት ይኖረዋል ብለን እናምናለን፡፡ ለማጠቃለል በአገራችን ባለፉት 27 ዓመታት ዓለም የመሰከረለት ከፍተኛ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ለውጦች ተመዝግበዋል፡፡ በዚህ መስክ ውጤታማ የሆነ እንቅስቃሴ የተደረገ ቢሆንም፣ በሌላ በኩል ደግሞ የፌዴራል ሥርዓቱ አስኳል ከሆነው ከፖለቲካ አመራሩ በኩል የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ላይ ከፍተኛ ችግሮች እንደነበሩ፣ ሕገ መንግሥቱ በተግባር እየተጣሰ መቆየቱ፣ የኢኮኖሚውና የማኅበራዊ ልማቱም በፍትሐዊ ተጠቃሚነት ላይ ጥያቄና ጥርጣሬ ይነሳበት እንደነበረ ይታወቃል፡፡ በእነዚህ ጥያቄዎች መነሻነት ለውጥ የመጣበት ሁኔታ ላይ እንገኛለን፡፡ በለውጡና በሽግግሩ ሒደት ደግሞ በርካታ የተወሳሰቡ ለረጅም ጊዜ የቆዩ ፖለቲካዊ፣ ኦኮኖሚያዊና የፀጥታ ችግሮች እየተነሱ አጠቃላይ የፖለቲካ ሥርዓቱ (ገዥው ፓርቲም ሆነ ተቃዋሚዎችን የሚያጠቃልል ነው) እነዚህን ችግሮች ለመፍታት እየተጋፈጠ ያሉበት ሁኔታ ላይ እንገኛለን፡፡ ይህ ሁኔታ ግልጽነት ያለው ስትራቴጂካዊ አቅጣጫ፣ መዳረሻና ብቃት ያለው አመራር ይፈልጋል፡፡ ይህ ስትራቴጂካዊ አቅጣጫ በግልጽ ለሕዝብ ቀርቦ፣ ሕዝብ አውቆትና እየተቸው በልፅጎ እንዲወጣ (የገዥው ፓርቲ ሆነ የተቃዋሚዎች) ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ ውጪ እንዲሁ በደመ ነፍስ የሚደረግ እንቅስቃሴና የተወሰኑ የፖለቲካ ልሂቃን የእርስ በርስ መነታረክ ወይም መስማማት ብቻውን እንደ መፍትሔ መውሰድ ካሉብን ችግሮች ጋር አይመጥንም ብለን እናምናለን፡፡
በአንድ አገር ያሉ የተለያዩ የፖለቲካ አማራጮች በልሂቃን ይጠነሰሳሉ፡፡ ከዚያ በኋላ ግን የፓርቲ ፕሮግራሞች ሆነው ሕዝቡን አሳትፈው ተግባር ላይ ይውላሉ፡፡ የፖለቲካ ልዩነቶች በሰፊ ውይይትና ድርድር ይበለፅጋሉ፣ ይዳብራሉ፡፡ በመጨረሻ ግን ልዩነቶቹ በግልጽ ወጥተው በሕዝብ በምርጫ ውሳኔ ያገኛሉ፡፡ የዳበረው ሰላማዊውና ሕጋዊ (ከጉልበት በመለስ) የሚደረግ የፖለቲካ ሽግግር መንገድ ይህ ነው፡፡ አሁን ከፊታችን ተደቅኖ ያለውን የፖለቲካ ሁኔታ በተገቢው መንገድ ከተጠቀምንበት፣ አገራችን ትክክለኛውን የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ትጀምራለች፡፡ ይህ ደግሞ በሒደት በቀጣይ ምርጫዎች እየጎለበተ ይቀጥላል፡፡ ይህ ሲሆን አሁን ያለውን ሁኔታ ወደ ትልቅ ፀጋ መቀየር ይቻላል፡፡ ተመራጩም ይህ ነው፡፡ ይህ ሳይሆን ቀርቶ ግልጽነት በጎደለው፣ ስትራቴጂካዊ አማራጮች በሚገባ ተደራጅተው ለሕዝብ ምርጫ ሳይቀርቡና ወጉ በማይታወቅ ሁኔታ ከቀጠለ ግን ውጤቱ ያማረ አይሆንም፡፡ በለውጥና በሽግግር ውስጥ አለን እያልን ከመተማመን ይልቅ ጥርጣሬው እያየለ፣ ሰላምና መረጋጋት ጠፍቶ ኢኮኖሚው እየሞተ ከቀጠለ ደግሞ አገራችንን ወደማትወጣው አዘቅት እንከታታለን ብለን እናምናለን፡፡ ያሉን አማራጮች እነዚህ ናቸው፡፡ አሁን በአገራችን ያለውን የፖለቲካ ቀውስ ለመፍታት ዋናው መንገድ ተአማሚነት ያለው ምርጫ በሕገ መንግሥቱ መሠረት ማካሄድ ነው፡፡ ይህ ሰላማዊ ሒደት ሕጋዊ ሽግግሩን ያጠናክራል፡፡ በአገራችን ሊካሄድ እየታሰበ ያለው ምርጫ ሰላማዊና ሕጋዊ የሽግግር ምርጫ በመሆኑ ክብደቱ ከፍተኛ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም እጅግ በጣም አሳሳቢ የሆነ የፖለቲካ ሁኔታ ውስጥ ሆነን የሚደረግ ምርጫ በመሆኑ ሚዛኑ ከፍተኛ ነው፡፡ ይህንን ጉዳይ በኋላ ላይ ዘርዘር አድርገን እናየዋለን፡፡ ከዚያ በፊት ግን ምንም እንኳን እስካሁን ድረስ የተገለጸው ሁኔታ ትግራይንም የሚመለከት ቢሆንም፣ የቅርብ ጊዜ በአገራችን የነበረውንና እስካሁንም ድረስ ያለውን ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባትና እኛም እንደ ግለሰቦች የዚሁ ብሔር ተወላጆች በመሆናችን የሚመለከተን ስለሆነ፣ ትግራይ ውስጥ ያለውን ሁኔታ በተመለከተ ጥቂት ነገሮችን እንላለን፡፡
1.2. ትግራይ ውስጥ ያለው ሁኔታ
በአገር ደረጃ ሲዘረዘር የነበረው ፖለቲካዊ ሁኔታ በትግራይ ውስጥ የተለየ አይደለም፡፡ ሕገ መንግሥቱ የሚያጎናፅፋቸውን መብቶች የትግራይ ሕዝብም ሊጠቀምባቸው የሚያስችል ሁኔታ አልተፈጠረም፡፡ ሕገ መንግሥቱ ተግባር ላይ ሲውል አልነበረም፡፡ ግን ደግሞ ለዚህ ሕገ መንግሥት መመሥረት ከፍተኛ ዋጋ ከፍሏል፡፡ ይህ በመሆኑም ለውጡ ከመምጣቱና ወደዚህ የሽግግር ምዕራፍ ከመግባታችን በፊት፣ ትግራይ ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች የሕዝብ ሰላማዊ ተቃውሞ ነበር፡፡ የትግራይ ወጣቶች በማኅበራዊ ሚዲያው የለውጥ ፊታውራሪዎች ነበሩ፡፡ ስለለውጥ ጽፈዋል፣ ታግለዋል፡፡ ለውጡ ሲመጣም የትግራይ ሕዝብ በደስታ ነው የተቀበለው፡፡ ለውጡ በመጣ ማግሥት የነበረው የሕዝቡ ደስታ በግልጽ የታየና ከፍ ያለ ነበር፡፡ ከዚህም ጋር ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ወደ ትግራይ ሄደው ባደረጉት ንግግር የተንፀባረቀው የሕዝብ የደስታ ስሜት የዚህ ማሳያ ነው፡፡ በኋላ ላይ ግን ለረጅም ጊዜ ሆን ተብሎ ሲሠራበት የነበረው የጥላቻ ፖለቲካ (በጊዜው በቂ ምላሽ ይሰጠው ስላልነበረ)፣ ከዚህ ጋርም ተያይዞ በተወገደው አስተዳደር ውስጥ በፌዴራል ከፍተኛ የሥልጣን ቦታዎች የነበሩ የትግራይ ተወላጅ የሆኑ የሕወሓት አባላት በሥራ ላይ በነበሩበት ወቅት አደረጉት ለሚባለው ጥፋት፣ የትግራይን ሕዝብ በጠቅላላ በዚያ ዓይን በሚመዝን የጥላቻ ፖለቲካ ተለውሶ የተካሄደው የመንጋ ፖለቲካ ሕዝቡን በአጠቃላይ ሥጋት ውስጥ ከቶታል፡፡
ይህ ጉዳይ በጥላቻ ንግግር ብቻ የቆመ አልነበረም፡፡ የትግራይ ተወላጆች በያሉበት ከፍተኛ የሕይወትና የንብረት ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ በእርግጥ ይህ ክስተት በማንኛውም የአገራችን ዜጎች ላይ በአገር ደረጃ የደረሰ ከፍተኛ ጉዳት ነው፡፡ አሁን ግን የምንናገረው ስለትግራይ ነው፡፡ በትግራይ ተወላጆች ላይ ከደረሰው የአካልና የማቴርያል ጉዳት በተጨማሪ፣ ከፍተኛ የሆኑ የሥነ አዕምሮና በማንነታቸው እንዲሸማቀቁ ያለሙ የፕሮፓጋንዳ ሥራዎች ተሠርተዋል፡፡ ከእነዚህ ጥቂቶቹን ለመግለጥ ያህል፣ “ደርግ የወደቀው በኢሕአዴግ ትግል ሳይሆን በራሱ ነው” የሚለው፣ ከ60 ሺሕ በላይ ሕይወት ተከፍሎበት ለተመዘገው ለውጥ መስዋዕትነት ለከፈለው ኅብረተሰብ ይህ አባባል ትልቅ ቁስል ነው የሚፈጥረው፡፡ “የ27 ዓመታት የጨለማ ዘመን፣ የቀን ጅቦች፣ ፀጉረ ልውጥ በአካባቢያችሁ ተከታተሉ”፣ “ትግርኛ ተናጋሪ” እየተባለ የተሠራው ዶኩመንተሪ ፊልም፣ ወዘተ. የትግራይና የአማራ ክልሎችን የሚያገናኝ መንገድ ተዘግቶ ንብረት እየተዘረፈ የፌዴራል መንግሥት ዝም ብሎ መቆየቱ፣ በአቶ ኢሳያስና በዶ/ር ዓብይ ሲደረጉ የነበሩ ትግራይን ያገለሉ የሚመስሉ የተለያዩ ግንኙነቶች፣ በአማራ ክልል እየተስፋፋ በመጣው የግዛት ይገባኛል ጥያቄና ይህንን ጉዳይ በኃይል ለመፍታት ዝግጅት የሚመስል ሰፊ የማስታጠቅና የማደራጀት እንቅስቃሴ፣ በትግራይ ሕዝብ ላይ እንደ ሕዝብ ያነጣጠረ “የጥቃት ዘመቻ” የሕዝቡን ሥጋት ከፍ ወዳለ ደረጃ አድርሶታል፡፡ የትግራይ ሕዝብም ይህ ጉዳይ በጥቂት ጥፋት ሠርተዋል ተብለው በተጠረጠሩ የሕወሓት መሪዎች ላይ ብቻ ሳይሆን በትግራይ ሕዝብ ህልውና፣ ማንነትና ክብር ላይ ያነጣጠረ አደጋ ነው የሚል ግንዛቤ ወስዶ ከዚህ አንፃር ተንቀሳቅሷል፡፡ ይህ ሁኔታ አገራዊ የፖለቲካ ቀውሱን ለመፍታት አስቸጋሪ አድርጎታል፡፡
በአገራችን ከረጅም ጊዜ ጀምሮ ሆን ተብሎ ሲሠራበት በቆየውና በለውጡ ዋዜማና ከለውጡ በኋላም እየተጠናከረ በመጣው በትግራይ ሕዝብ ላይ ካነጣጠረ የጥላቻ የፖለቲካ ዘመቻ አንፃር፣ የትግራይ ሕዝብ ሌላውን ነገር ሁሉ አሳድረን አንድነታችንን አጠናክረን የመጣብንን አደጋ በጋራ ሆነን እንከላከል ማለቱ ተገቢ ነው፡፡ ሆኖም የትግራይ ሕዝብ አንድነቱ ይበልጥ የሚጠነክረውና የሚመጣበትን ማንኛውንም አደጋ ከየትኛውም አቅጣጫ በብቃት መከላከል የሚችለው፣ በውስጡ ያሉትን ፖለቲካዊ ችግሮች በመፍታት ለአንድነቱና ለውስጣዊ ጥንካሬው ደልዳላ መሠረት ሲኖረው ነው፡፡
ትግራይ ውስጥ አሁን በጉልህ የሚታይ ሁኔታ አለ፡፡ በአንድ በኩል ከትግራይ ውጭ ከመሀል አገር በተለይ ከአማራ ክልልና ከኤርትራ፣ በተናጠልም ሆነ በቅንጅት ጥቃት ሊመጣብን ይችላል የሚል ሥጋት አለ፡፡ ይህንን ሊመጣብን የሚችለውን ጥቃት በአንድነት ቆመን እንመክት የሚል አስተሳሰብ አለ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ይህን ጥቃትና በአንድነት የመመከት አስፈላጊነት ተቀብሎ፣ ግን ደግሞ አንድነታችን እንዲጠናከርና ዘላቂነትና ጠንካራ ፖለቲካዊ መሠረት እንዲኖረው በዋናነት የፖለቲካ ችግሮቻችንን በፍጥነት እየፈታን የበለጠ እንዘጋጅ የሚል አስተሳሰብ አለ፡፡ የዝግጅታችን ዋናው ትኩረት ፖለቲካዊ ችግሮቻችንን ፈጥነን በመፍታት ጠንካራ ፖለቲካዊ መሠረት ያለው አንድነት መገንባት መሆን አለበት፡፡ ከትግራይ ውጭ የሚመጣብንን ጥቃት በአስተማማኝነት መመከት የምንችለውና ማንኛቸውንም ችግሮች መቋቋም የሚያስችለን፣ በውስጣዊ ጥንካሬያችን የሚመሠረተው በትግራይ ውስጥ ለራሳችን ብለን በምናደርገው ፖለቲካዊ ለውጥ መሆን አለበት፡፡ የዝግጅታችን ዋነኛው ባህሪ የሚለካው በርካታ ከፍተኛ ብቃት ያላቸውን፣ በተለይም የተማረ ወጣት የኅብረተሰብ ክፍል የሕወሓት አባልና ደጋፊ ባለመሆኑ ብቻ ከፖለቲካዊ ሥርዓቱና ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሊያበረክት ከሚችልበት ሥራ በማግለል ላይ የተመሠረተውን የፖለቲካ ምኅዳር መቀየር መሆን አለበት፡፡ ከዚህ ጋር ደግሞ በአገር አቀፍ ደረጃ የምናምንበት መርህ ላይ የተመሠረተ ስትራቴጂካዊ ዝምድና በአገራችን ካሉ የፖለቲካ ኃይሎች ጋር በመፍጠር፣ ይህንን ማጠናከርና በአገራችን ለሚደረገው የአገረ መንግሥት ግንባታ የራሳችንን አስተዋጽኦ ስናደርግ ነው፡፡
ከላይ የተገለጸውን አስተሳሰብ ለማሳካት አሁን በትግራይ ውስጥ የሚደረገው ለውጥ ሁሉን አሳታፊና ጠንካራ ክልላዊ መንግሥት በመመሥረት ላይ ያተኮረ መሆን ይኖርበታል፡፡ ለውጡ ሕወሓት እንደ የፖለቲካ ድርጅት ጠነከረም ደከመም የትግራይ ሕዝብ ሁኔታ በሕወሓት መዳከምና መጠንከር ብቻ የሚወሰን ወደማይሆንበት ደረጃ ማሸጋገር መሆን አለበት፡፡ ይህ ደግሞ የሚሳካው መንግሥትና የፖለቲካ ድርጅት ሲለያዩ ነው፡፡ ተአማኒነት ባለው ምርጫ ያሸነፈ የፖለቲካ ድርጅት ያሸነፈውን ያህል ሥልጣን የሚጋራበት፣ ሕዝቡ የተለያዩ አማራጮችን እንዲቀርቡለት የሚያደርግ የክልሉ መንግሥታዊ መዋቅር ተፈላጊውን ቅርፅ ይዞ (ሕግ አውጭ፣ ሕግ ተርጓሚ፣ ሥራ አስፈጻሚ ሆኖ)፣ እነዚህ የመንግሥት አካላት አንፃራዊ ነፃነታቸውን ጠብቀው አንዱ ሌላኛውን እየተቆጣጠረ መንግሥት የሕዝብን መብት የሚያስጠብቅለት ሥርዓት መትከል ይገባል፡፡ ይህ ሲሆን ፍትሕ ቀስ በቀስ ይረጋገጣል፡፡ ሕዝብ አድልዎ የሌለበት ግልጋሎት ያገኛል፡፡ የመንግሥትና የሕዝብ ሀብት ብክነት በእጅጉ ይቀንሳል፡፡ መገናኛ ብዙኃን አንፃራዊ ነፃነት ይኖራቸዋል፡፡ በክልሉ ከመልካም አስተዳደር መጓደልና አድልዎ የሚመነጭ የፖለቲካ አለመረጋጋት ይቀንሳል፡፡ የሕዝቡ አንድነት ይጠናከራል፣ ሰላም ይሰፍናል፡፡ የአገር ውስጥም ሆነ የውጭ ኢንቨስትመንት ይበልጥ ይሳባል፡፡ ኢኮኖሚው ቀስ በቀስ እየተጠናከረ በማይታጠፍ መንገድ ያድጋል፡፡ ጠንካራ ክልላዊ መንግሥት የመመሥረት ጉዞአችን በተሳካ ሁኔታ በተፈጸመ ልክ፣ የፖለቲካ ልዩነቶች ችግር መሆናቸው ቀርቶ ፀጋ ይሆናሉ፡፡ ለኢኮኖሚያዊ ዕድገትና ለሰላም መሠረት ይሆናሉ፡፡ ገዥው ፓርቲም በከፍተኛ የፖለቲካ እንቅስቃሴና ትግል ውስጥ ስለሚጠመድ ራሱን እየሞረደና ይበልጥ እየጠነከረ የተሻለ አመራር በመስጠት አሸንፎ ለመውጣት፣ በሐሳብም በአደረጃጀትም የበለጠ ብቃት እንዲኖረው በቀጣይነት ይዘጋጃል፡፡ አሁን እንዳለው በአስተዳደራዊ መንገድ እየተቆጣጠሩ ሥልጣን በመያዝ በስብሶ መቀመጥ ይቀራል፡፡ ይህንን ለማምጣት ለውጥ ያስፈልጋል፡፡
በትግራይ የፖለቲካ ሥርዓት ለውጥ የሚመጣው የትግራይን ሕዝብ ጥቅምና መብቶችን መሠረት አድርጎ፣ ከራሱ ከትግራይ ሕዝብ ውስጥ ሲመነጭ ነው፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ከተለያዩ አቅጣጫዎች በገንዘብና በሥልጣን ኃይል፣ ከራሱ ከሕዝቡ ያልበቀለና በሕዝቡ ተቀባይነት የሌለው “ለውጥ” በሕዝቡ ላይ ለመጫን የሚደረግ ሙከራ እንዳለ ይሰማል፡፡ ይህ በትግራይ ሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት እንደማይኖረው እንተማመናለን፡፡ ቀደም ብሎ እንደተገለጸው ትግራይ ውስጥ ፖለቲካዊ ችግሮች አሉ፡፡ እነዚህን ፖለቲካዊ ችግሮች በውስጣችን ታግለን እንፈታቸዋለን፡፡ ከትግራይ ውጭ ባሉ ኃይሎች የሥልጣንና የገንዘብ ማባበያነት በተፅዕኖ የሚመጣን “ለውጥ” ግን የትግራይ ሕዝብ በከፍተኛ ደረጃ ሊቃወም ይገባል፡፡ ምክንያቱም ከሕዝብ ውስጥ የማይመጣና ከውጭ በተፅዕኖ የሚመጣ ለውጥና ይህንን እናሳካለን የሚሉ “የለውጥ” ደላላዎች ሁሉ፣ ከሁኔታዎች ጋራ በመለዋወጥ ቀጣይ አደጋ ውስጥ ስለሚከቱን ነው፡፡ ችግሮቻችንን አይፈቱም፡፡ ይልቁንስ ይበልጥ ያባብሱታል፡፡ ለተጨማሪ የተወሳሰበ ችግር ያጋልጡናል፡፡ ስለዚህ የፖለቲካ ሕይወታችንን ራሳችን መቆጣጠር ይኖርብናል፡፡ ከየትኛውም አቅጣጫ በሥልጣን ሆነ በገንዘብ አማካይነት ለውጥ አመጣለሁ የሚል ኃይል ነገ ገንዘቡን ወይም ሥልጣኑን የሚሰጠው ኃይል ሲጠፋ ለሌላ ጌታ ያድራል፡፡ ጌታው እስካለ ድረስ ደግሞ የጌታውን በሽታ በሙሉ ይዞልን ይመጣል፡፡ ኪሳራው ከባድ ነው፡፡ በፅናት እንቃወመው፡፡ ማምጣት የምንፈልገውን ለውጥ ሕዝባችን ያለ ምንም የውጭ ተፅዕኖ ራሱ ታግሎ ማምጣት አለብት፡፡
በመሀል አገር ከለወጡ ጋር ተያይዞ የተፈጠረ የፖለቲካ ሁኔታ የትግራይን ሕዝብ ላይ የህልውና አደጋ ለመከላከል አንድነትን ማጠናከር ተገቢ ነው፡፡ ነገር ግን እኛ እየሞትንና እየደማን ከሚገባን በላይ ከፍተኛ ዋጋ እየከፈልን የምንጠብቀውና የምንከላከለው የኢትዮጵያ አንድነት መኖር የለበትም፣ የራሳችንን ጉዳይ ብቻ እናከናውን የሚል አመለካከት በተለይ በወጣቱ ክፍል ጎልቶ መምጣት ጀምሯል፡፡ ይህ የብሔርተኝነት አስተሳሰብ በመሀል አገር በተፈጠረ የጥላቻ ፖለቲካ የተገፋፋ ሆኖ፣ ከዚህ በተጨማሪ ሕወሓት ትግራይንና የትግራይን ሕዝብ የሚገባቸውን ትኩረት አልሰጠም ከሚል አስተሳሰብም ይነሳል፡፡ ሕወሓት ዋናው ሥራውን መሀል አገር ማልማት ላይ ብቻ በማድረግ ድርጅቱና የትግራይ ባለሀብቶችም ትግራይን ረስተው መሀል አገር እንዲሠፍሩ በማድረግ የትግራይን ሕዝብ ከድተዋል፣ ኃላፊነታቸውን ረስተዋል የሚል እሳቤም ይጨመርበታል፡፡
አሁን የትግራይ ከልላዊ መንግሥትና ሕዝብ የሚያስተሳስረው ዋናው ጉዳይ የመጣብንን የህልውና አደጋ በጋራ ተባብረን እንከላከል፣ ሁለተኛው ደግሞ በከባድ መስዋዕትነት በሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ያረጋገጥነውን መብት እናስጠብቅ፣ እንከላከል በሚሉት ጉዳዮች ላይ ነው፡፡ ግን ደግሞ ሕገ መንግሥቱ በተግባር ይጣስ ነበር ብቻ ሳይሆን፣ አሁንም (መጠነኛ መሻሻል ያለ ቢሆንም) ትግራይ ውስጥ ሕገ መንግሥቱን የሚፃረሩ ተግባራት እየተፈጸሙ ነው፡፡ ሕወሓት ያልፈቀደው አስተሳሰብ በትግራይ መገናኛ ብዙኃን አይተላለፍም፡፡ የወረዳና የዞን አመራሮች፣ የፓርላማ አባላት፣ የቢሮ ኃላፊዎች ገሚሶቹ ተመራጮች ገሚሶቹ ተሿሚዎች ከሕወሓት ፈቃድ ውጪ በመንግሥት የሥራ ኃላፊነት አይመደቡም፣ አይመረጡም፡፡ እነዚህ የመንግሥት ሥራ አስፈጻሚዎች (ተሿሚዎችም ሆነ ተመራጮች) ተጠሪነታቸው ለሕወሓት ነው፡፡ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ተጠሪነታቸውና የሥራ ኃላፊነታቸው፣ ኃላፊ ሆኖ በላያቸው ለተሾመ የመንግሥት ባለሥልጣን ወይም ለመረጣቸው ሕዝብ መሆን ነበረበት፡፡ አሁን ባለው ልምድና አሠራር የሚሾም ብቃት ይኑረውም አይኑረውም የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ነው፡፡ ይህ አሠራር ደግሞ መንግሥትና ፓርቲው እንዳይለያዩ ከማድረጉም በላይ፣ በመንግሥት አካላት መኖር የነበረበትን (Check and Balance) በማጥፋት በዴሞክራሲያዊ ማዕከልነት እንዲተካ ያደርጋል፡፡ የሕዝብ ተመራጮች ተጠሪነታቸው ለመረጣቸው ሕዝብ መሆን ይቀርና ለፖለቲካ ድርጅቱ ይሆናል፡፡ ስለሆነም ችግሩ ሥርዓታዊ (Systemic) ነው፡፡ እንዲሁ አንዳንድ ነገሮችን በመነካካት በሂስና ግለሂስ የሚሻሻል አይደለም፡፡
ለምሳሌ የትግራይ የመገናኛ ብዙኃን ኃላፊ ሆኖ የሚሾም የመንግሥት ባለሥልጣን ለሕወሓት ባለው ታማኝነት እየተመዘነ፣ ወይም ደግሞ ባለው የኔትወርክ መተሳሰር እየተመረጠ ነው፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ደግሞ የድርጅቱ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል የሆነ ሰው ነው፡፡ ይህ ሰው ማንም ይሁን ማን በዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት እየተመራ የፓርቲ ታማኝነቱን ማረጋገጥ ይጠበቅበታል፡፡ የሕዝቡ እሮሮና የተለያዩ አማራጭ አስተሳሰቦች “ጠላቶቹ” ናቸው፡፡ ስለዚህ በሙሉ አቅሙ ይዋጋቸዋል፡፡ በመሆኑም የአስተሳሰብ ልዩነቶችን ለማስተናገድና ሕዝብ በመረጠው አስተሳሰብ ዙሪያ እንዲሰባሰብ አይፈቅድም፡፡ ድርጅቱ ያቀረበውን ሐሳብ ብቻ እንዲጋት ይታገላል፡፡ አስፈላጊ መስሎ ሲታየውም አስተዳደራዊ ዕርምጃ በመውሰድ ችግር የመሰለውን አስተሳሰብ ማስወገድ ይፈልጋል፡፡ በአስተሳሰብና በአሠራር ልዕልና ማሸነፍ ከበድ ያለና ከፍተኛ ጥረት የሚጠይቅ ስለሚሆን አቋራጩን ይመርጣል፡፡ በዚህ መንገድ የሚሠራ መንግሥት የአስተሳብ ልዩነትም እያለ ብዙኃኑ በመረጡት መንገድ የሚተዳደር የፖለቲካ ሥርዓት አይገነባም፡፡ ሁሉም ሕዝብ በተለያዩ ጉዳዮች ሁልጊዜ ተመሳሳይ አስተሳሰብ መያዝ አይችልም፡፡ ማድረግ የሚቻለው የሐሳብ ልዩነቶችን በሰላማዊ ውይይትና ዕውቀት ላይ ተመሥርቶ አስተሳሰቡን በማብሰል፣ በመጨረሻም ብዙኃኑ ያመኑበትን ተግባር ላይ በማዋል ማጠናቀቅ ነው፡፡ ይህ በአገር፣ በክልል ደረጃ የተለያዩ አማራጮችን የሚያቀርቡ የፖለቲካ ቡድኖች በነፃ ሐሳባቸውን ለሕዝብ አቅርበው የሚወዳደሩበት፣ በነፃና ተአማኒነት ባለው ምርጫ መቋጫ የሚያገኙበትን አሠራር ተግባራዊ በማድረግ ይፈታል፡፡ አሁን ትግራይ ውስጥ መካሄድ ያለበት ለውጥ ዴሞክራሲውን ማስፋትና የተስተካከለ ወደ ሕዝብ የቀረበ የሕዝብን ብሶት የሚሰማ መንግሥት መመሥረት ላይ ያተኮረ መሆን አለበት፡፡ እነዚህ በተደጋጋሚ የሚገለጹት የመልካም አስተዳደር መመዘኛዎች ቀስ በቀስ በአስተማማኝ ሁኔታ ተግባራዊ የሚሆኑት፣ ዴሞክራሲው ሰፍቶ ወደ ሕዝብ የቀረበና ለሕዝብ ተጠሪ የሆነ መንግሥት ሲመሠረትና ሲጠናከር ነው፡፡ ይህ ማለት ደግሞ ለምሳሌ ከሥራ አስፈጻሚው ተነፃፃሪ ነፃነት ያለው የሕግ ተርጓሚና ሕግ አውጪ ሲኖር፣ ለሕዝብ ወቅታዊና ፈጣን ግልጋሎት የሚሰጥ ቢሮክራሲ፣ ለሕዝብ ተጠሪነት ያለው በሕዝቡ በቀጥታ ወይም በወከላቸው አባላት የሚመረጥ የወረዳ አመራር፣ የከተማ ከንቲባ፣ የፓርላማ አባል ሲኖር ነው፡፡ በድርጅት የሚመደብ የወረዳ አመራር፣ የከተማ ከንቲባ፣ በድርጅት ምልመላ የሚመረጥ የፓርላማ አባል ተጠሪነቱ ለፖለቲካ ድርጅቱ እንጂ ለመረጠው ሕዝብ ሊሆን አይችልም፡፡
በድርጅቱ የውስጥ አደረጃጀት መሠረት በስትራቴጂካዊ ጉዳዮች ላይ እንዲያተኩር ኃላፊነት የተሰጠው የሕወሓት የፖለቲካና የድርጅት ቢሮ የትግራይ ሕዝብ የወደፊት ዕድገት፣ ሰላምና ዴሞክራሲ የሚጠናከርበትና የሚሰፋበት ይበልጥ ሕዝብን በሚጠቅም ስትራቴጂካዊ አቅጣጫ ጉዳዮች ላይ መጠመድ ነበረበት፡፡ ነገር ግን ዋነኛ የሥራ ድርሻውን ትቶ የወረዳና የዞን ኃላፊዎች፣ የፓርላማ ተመራጮች መመልመልና ማሰማራት ዋና ሥራው ሆኗል፡፡ በእነዚህ የዕለት ተዕለት ሥራዎች (Operational and Administrative) ራሱን ይጠምድና ስትራቴጂካዊ ጉዳዮችን ማሰብ አይችልም፡፡ እነዚህ አስተዳደራዊ ጉዳዮች ሥልጣንን በሰዎች ኑሮና ሕይወት ላይ ለመወሰን ስለሚጠቅሙ፣ በሰዎች ዓይን ሥልጣን የሚያጎናፅፉ ስለሆኑ ይመቻሉ፡፡ ከዚህ መውጣት አያስመኙም፡፡ ግን ደግሞ ይህ አሠራር ከሕገ መንግሥቱ እምነትና አስተሳሰብ ውጭ ብቻ ሳይሆን፣ ሕዝቡ የተሻለ አማራጭ እንዳይኖረውና (የአስተሳሰብ፣ የአሠራር፣ የአመራር ብቃት ያላቸው) ጠንካራ ሰዎች እንዳይወጡ እንደ ልጓም ሸብቦ የያዘ አሠራር ነው፡፡ ይህ በትግራይ ሕዝብ ላይ የተጫነ ትልቅ ፖለቲካዊ ችግር ነው፡፡ ይህ ችግር ሊፈታ ይገባል፡፡ የለውጡ እንቅስቃሴ ከተጀመረ ወዲህ የሕወሓት አመራሮች በተከላካይነት መንፈስ ነው ያሉት፡፡ በመጀመርያ አካባቢ ለምን እንዲህ ሆነ ላይባል ይችላል፡፡ እስካሁን ድረስ ከማዕከላዊ መንግሥትም ሆነ ከሌሎች የተለያዩ አቅጣጫዎች ምን ይመጣብን ይሆን እያሉ ራሳቸውን ከማዕከላዊ መንግሥት ፕሮግራሞችና አሠራሮች ያገለሉ በሚመስል ሁኔታ በተከላካይነት መቀመጥ ግን ፈጥኖ መለወጥ ያለበት ጉዳይ ነው፡፡ ይህ ሁኔታ በቅርቡ በሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ ከተወሰኑ ውሳኔዎች አንፃር ስንነሳ እየተሻሻለ የመጣ ይመስላል፡፡ ይህ መሻሻል ተጠናክሮ መቀጠል አለበት እንላለን፡፡ መሻሻሉን ያየንባቸው ጉዳዮች በቀጣይ አገራዊ ምርጫ ላይ የተወሰደው ውሳኔ፣ የኢሕአዴግ ድርጅቶችን ውህደት በተመለከተ ቅድመ ሁኔታውን መሠረት በማድረግ የተወሰነው ውሳኔ፣ በሕገ መንግሥቱ መከበር ላይ ያለው አቋም (ይህንን በአርአያነት በትግራይ ተግባራዊ ማድረግ የሚገባቸው መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ) በአገር ደረጃ ሕገ መንግሥቱ ይከበር የሚለው አቋም በግልጽ ለሕዝብ ይፋ አድርገዋል፡፡ በጥቅሉ ሲታይ ደግሞ በአገሪቱ አሳሳቢ የፖለቲካ ጉዳዮች ላይ አቋም በመውሰድ ኅብረተሰቡ እንዲያውቀው በማድረግና አስፈላጊውን ትግል ለማድረግ መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል፡፡ ይህ መጠናከር ያለበት ጅምር ነው እንላለን፡፡
እዚህ ላይ መነሳት ያለበት ጉዳይ የትግራይ ክልላዊ መንግሥትና ገዥው ድርጅት ሕወሓት ዋናው ሥራቸው፣ ትግራይን በተገቢው መንገድ መምራትና ማስተዳደር ነው፡፡ ይህ ማለት በትግራይ መልካም አስተዳደር፣ ዴሞክራሲና ሰላም ሰፍኖ በዚህ ሳቢያ ደግሞ ጠንካራ ኢኮኖሚያዊ ልማት እንዲመዘገብ ማስቻል ነው፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ትግራይ የኢትዮጵያ አካል ስለሆነችና በአገራችን ኢትዮጵያ የሚደረገው ክፉም ሆነ በጎ ነገር ትግራይንም ስለሚመለከትና በትግራይም ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ስላለው፣ ሕወሓትም እንደ ነባር ተሞክሮ ያለው ድርጅት የአገራችንን የፖለቲካ ቀውስ በመፍታት ላይ የራሱ ድረሻ ስላለው ገንቢ በሆነ መንገድ መሳተፍ ይገባዋል፡፡ ትግራይ ላይ ብቻ በመጠመድ የኢትዮጵያን ይቅርና የትግራይን ችግር መፍታት አይቻልም፡፡ ስለሆነም ሕወሓት አሁን በአገራችን በሚነሱ መሠረታዊ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የፀጥታ ጉዳዮች ላይ አገራችን ከገባችበት ቀውስ ለመውጣት የሚያስችለን ስትራቴጂካዊ አቅጣጫና አተገባበሩ ላይ ጉልህ አስተዋጽኦ በማድረግ መሳተፍ ይኖርበታል፡፡ ይህንን ተሳትፎውንም ጊዜና ሁኔታውን ባገናዘበ መንገድ አስፈላጊ መስሎ ሲታየው ለኢትዮጵያ ሕዝቦች ማሳወቅ ጠቀሜታ ይኖረዋል፡፡
- በአገር ደረጃ ያሉን አማራጮች
የአገራችን ፖለቲካዊ ሁኔታ አሁን ከሚገኝበት ተነስተን ወደፊት ለማስቀጠል ሁለት አማራጮች ያሉን ይመስለናል፡፡ አንደኛው አማራጭ ለውጡን በኃይል ከላይ ወደ ታች በመጫንና አሁን ሥራ ላይ ያለውን ሕገ መንግሥት ሕገ መንግሥታዊ ባልሆነ መንገድ የፖለቲካ ፍላጎትን ለማስፈጸም መሞከር ነው፡፡ ይህ ከተለያዩ የፖለቲካ ኃይሎች በተለይ ደግሞ “አሀዳዊ አስተዳደር”፣ “ጂኦግራፊያዊ የፌዴራል አከላለል” እንከተላለን የሚል ፖለቲካዊ አስተሳሰብ ያላቸው የፖለቲካ ኃይሎች ይህንን አካሄድ የሚመርጡ ይመስላል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ አሁን በሥልጣን ላይ ያለው በኢሕአዴግ ድርጅታዊ አሠራር ወደ ሥልጣን የመጣው ኃይልም፣ አንዳንድ ዕርምጃዎቹና በተለያዩ ጊዜያት የሚሰጣቸው መግለጫዎች የዚህ አሰተሳሰብና አማራጭ ደጋፊ ይመስላል፡፡ ሁለተኛው አማራጭ ደግሞ እስካሁን ድረስ በሥራ ላይ ያለውን ሕገ መንግሥት በመከተልና ይህንን መሠረት በማድረግ፣ በቀጣይ ምርጫ በሚረጋገጥ የሕዝብ ፖለቲካዊ ፍላጎት መሠረት የሕዝብ ውክልና (Mandate) ይዞ ለውጡን ወደፊት መግፋት የሚል ነው፡፡ ይህንን አስተሳሰብ አሁን ያለውን ማንነት መሠረት ያደረገውን ፌዴራላዊ ሥርዓት የሚደግፉ ኃይሎች የሚጋሩት ነው፡፡ የመጀመርያውን አማራጭ የሚደግፉ ቀደም ብሎ እንደተገለጸው የመጣውን ለውጥ በኃይል በአመፅ አምጥተነዋል የሚሉ ኃይሎች (በአገር ውስጥ የነበሩም ሆነ ከአገር ውጭ በለውጡ ምክንያት ወደ አገር የገቡ የፖለቲካ ኃይሎች) አሁን ያለው ለውጥ ሕገ መንግሥቱን በመጠራረግ በኃይል ወይም ሕገ መንግሥታዊ ባልሆነ መንገድ የሽግግር ጊዜውን ማጠቃለል ይፈልጋሉ፡፡ የሚበልጡት የኦሮሞና የሌሎች ብሔርተኛ ድርጅቶች አቋማቸው ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ተከትሎ በሕዝብ ምርጫ ለውጠን መደገፍ ወደሚለው ያመዘነ ይመስላል፡፡ ስለሆነም ሕገ መንግሥቱን ጠራርገን እናስወግድ በሚለው አስተሳሰብ ውስጥ የሚካተቱ አይመስልም፡፡
ይህ ሕገ መንግሥቱን በመጣስ ለውጥ ለማምጣት የሚደረገውን ጥረት በአገራችን እየተበራከቱ የመጡ ፅንፈኛ የብሔረተኛ አስተሳሰብ ያላቸው የፖለቲካ ድርጅቶችም ይገፉበታል፡፡ እነዚህ ኃይሎች የ“ይዋጣልን” የፖለቲካ አስተሳሰብ በመከተል፣ አገሪቱን ወደከፋ ችግርና ቀውስ ለመክተት የሚንቀሳቀሱ ይመስላል፡፡ በየአከባቢው የሚነሱ አነስተኛ ችግሮችን ከማንነት ፖለቲካ ጋር በማያያዝ፣ ችግሮችን የማባባስና የኅብረተሰቡን አስተሳሰብ በአጭር ጊዜ የመመረዝ ችሎታ አላቸው፡፡ በመሆኑም እስካሁን ድረስ የፈጠሩት ችግርም ይሁን ለወደፊትም የሚፈጥሩት ችግር ቀላል አይደለም፡፡ መነሻቸው ለየብቻ ቢሆንም እነዚህ የ“አሀዳዊ አስተዳደር” የፖለቲካ አራማጆችና ፅንፈኛ ብሔርተኞች ሕገ መንግሥቱን በመጣስ ለውጥ ማምጣት ላይ ግን ይገናኛሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በዚሁ ሕገ መንግሥቱን በመጣስ ለውጥ ማምጣት ላይ በአቶ ኢሳያስ የሚመራው የኤርትራ መንግሥትም ተመሳሳይ አቋምና እንቅስቃሴ አለው፡፡ ይህ የውጭ ኃይል ሕገ መንግሥቱንና ሕገ መንግሥቱን ለመተግበር የሚያስችሉትን የመንግሥት ተቋማት በመጠራረግ ለውጥ በፍጥነት እንዲመጣ ይፈልጋል፡፡ ይህ አስተሳሰብ ለኢትዮጵያ ሕዝቦች ካለው “ቀና ፍላጎት” የሚነሳ አይደለም፡፡ የራሱን የአቶ ኢሳያስን የሥልጣን ዘመን ለማራዘምና የአገረ ኤርትራ ግንባታ ፕሮጀክት ለማሳካት በማሰብ ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱን መሠረት ያላደረገና የጣሰ የለውጥ አካሄድ ሕጋዊና ሰላማዊ ፖለቲካ ለውጥ ማምጣት አያስችልም ብቻ ሳይሆን፣ አገሪቱን እስከ መበታተን ሊያደርስ የሚችልና ምን ሊያስከትል እንደሚችል ለመተንበይ የሚከብድ፣ ከማንኛውም ኃይል ቁጥጥር ውጪ የሆነ ሁኔታ በመፍጠር ወደማንወጣው አዘቅት ይከተናል የሚል አስተሳሰብ አለን፡፡
ሁለተኛው አማራጭ አሁን በሥራ ላይ ያለውን ሕገ መንግሥት መሠረት በማድረግ፣ ቀስ በቀስ ሕጋዊና ሰላማዊ ለውጥ ማምጣት የሚፈልጉ ኃይሎች አሉ፡፡ እነዚህ ኃይሎች በዚህ ጥቅል አስተሳሰብ ውስጥ ሊጠቃለሉ የሚችሉ ቢሆንም፣ በመካከላቸው ልዩነቶች የሉም ማለት አይደለም፡፡ የሕገ መንግሥቱ መሠረታዊ ይዘት ሕይወቱ የሚባለው ዴሞክራሲያዊ መሆኑን በመገንዘብ በሕገ መንግሥቱ ያሉት የግለሰብ፣ የቡድን፣ የማኅበረ ኢኮኖሚያዊ መብቶች በሙሉ ተግባራዊ እንዲሆን፣ ራስን በራስ ማስተዳደር የሚባለው አስተሳሰብ ደግሞ የክልሎቹ አቅም እስከፈቀደ ድረስ ሕገ መንግሥቱን መሠረት አድርጎ ይህንን ሳይጥስ፣ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ እንዲሆን የሚፈልጉና ለዚህ የሚታገሉ ኃይሎች አሉ፡፡ እነዚህ ኃይሎች ከላይ የተገለጸውን ሁኔታ መሠረት በማድረግ፣ እንደ አገር ደግሞ የአገራችንን አንድነትና አገራዊ ጥቅም የሚያስጠብቅ፣ በመፈቃቀድና በእኩልነት የተመሠረተ አንድነትን የሚያጠናክር ሒደት እንዲበረታታና እንዲጠናከር ይፈልጋሉ፡፡ ሕገ መንግሥቱን እንደ ከለላ እየተጠቀሙ ፀረ ዴሞክራሲ የሆነ ተግባራቸውን መቀጠል የሚፈልጉ ኃይሎችም አይታጡም፡፡ ዋናው ኃይል ግን የሕገ መንግሥቱን መሠረታዊ ባህርይ (ዴሞክራሲያዊ መሆን) ጠብቆ ለውጡን በሰላማዊና በሕጋዊ መንገድ ማስቀጠል የሚፈልገው ኃይል ነው፡፡ ከለውጡ በፊት የነበረው የፖለቲካ አስተዳደር ዋናው ችግር ደግሞ፣ የፌዴራል ሥርዓቱ ዋነኛ ባህርይ የሆነው ዴሞክራሲያዊ የመሆን ይዘቱን ማጥፋት ነበር፡፡ ይህንን መመለስ ይገባል፡፡ እንደተገለጸው የግለሰብ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብት መጠበቅ አለበት፡፡ የሕዝቦች፣ የብሔር ብሔረሰቦች የክልል መስተዳድሮች ሥልጣናቸው ተጠብቆ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ መደረግ አለበት፡፡ የክልል መስተዳድሮች ሕገ መንግሥቱን ተከትለውና ይህንን ጠብቀው እስከ ሄዱ ድረስ ጥፋት ቢሠሩም፣ የራሳቸው ኃላፊነትና ከሕዝባቸው ጋር ሆነው የሚያወራርዱት ሒሳብ መሆኑ ታውቆ ከጥፋታቸው እየተማሩ እንዲያስተካክሉ ዕድሉን መስጠት ይገባል፡፡ የሕዝቦች በኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ መስኮች የመልማት መብታቸው የአገሪቱ አቅም በፈቀደ መጠን በየጊዜው እየዳበረ የሚሄድ ሆኖ መጠበቅ አለበት፡፡ እነዚህን መብቶች የሚጥስ አካሄድ ድሮም ዘንድሮም ትክክል አይደለም መባል አለበት፡፡
- የትኛውን አማራጭ እንምረጥ?
ከላይ ሲዘረዘር ከመጣው ሐሳብ ግልጽ እንደሆነ የምንገምተው፣ አሁን ባለው የአገራችን ሁኔታ በሥራ ላይ ያለውን ሕገ መንግሥት ተከትለን ይህንኑ መሠረት አድርገን ለውጡን በሰላማዊና በሕጋዊ መንገድ እናስኪደው የሚለውን መንገድ ነው የምንመርጠው፡፡ ይህንን ሐሳብ የማይቀበሉና ሕገ መንግሥቱን በሆነ መንገድ በመጣስ (ሕዝባዊ አመፅ፣ በሌላም ሕገ መንግሥታዊ ያልሆኑ አማራጮች) ለውጡን ማጠናቀቅ የሚፈልገሉ ኃይሎች እንዳሉ እናውቃለን፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን አሁን ያለው ትርክት በመንግሥት መገናኛ ብዙኃንም ሆነ በማኅበራዊ ሚድያ የበላይነት ያለው የአሀዳዊ አገረ መንግሥት ግንባታ አስተሳሰብ ይመስላል፡፡ እነዚህ አማራጭ አስተሳሰቦች ማለትም ብሔር ብሔረሰቦችን መሠረት ያደረገው በማንነት ላይ የተመሠረተ የፌዴራል ሥርዓትና የአሀዳዊ አገረ መንግሥት ግንባታ ላይ መሠረት ያደረገው የፖለቲካ ሥርዓት ግንባታ አሁን ገና ብቅ ያሉ አማራጮች አይደሉም፡፡ በአገራችን ሁለቱም የአገረ መንግሥት ግንባታ አስተሳሰቦች ተሞክረዋል፡፡ ኢሕአዴግ ሥልጣን ከመቆጣጠሩ በፊት በአገራችን የነበረው የአገረ መንግሥት ግንባታ አካሄድ አሀዳዊ መንግሥት የመገንባት ሒደት ነው የነበረው፡፡ ይህ በሕዝቦች አመፅ ተወግዷል፡፡ ቀጥሎም በኢሕአዴግ መሪነት ብሔር ብሔረሰቦችን መሠረት ያደረገ የአገረ መንግሥት ግንባታ ሒደት ተጀምሮ አሁን ያለንበት ደረጃ ላይ እንገኛለን፡፡
የእነዚህ ሁለት አማራጮች ደጋፊ የፖለቲካ ቡድኖች በከፍተኛ ደረጃ ሐሳባቸውን ቀምረውና ተደራጅተው ለሕዝብ እንደ አማራጭ ቀርበው በሰላማዊ መንገድ አንዱ አሸንፎ፣ ሌላው ደግሞ ተቃዋሚ ሆኖ ተአማኒነት ባለው ምርጫ እንድንሸጋገር መደረግ አለበት እንላለን፡፡ የአሀዳዊ አገረ መንግሥት ግንባታ ፖለቲካ አራማጆች የተበታተኑ እንደሆኑ እናውቃለን፡፡ ግን በአስተሳሰባቸው የሚቀራረቡት ተሰባስበውና ራሳቸውን አደራጅተው፣ ሐሳባቸውን በሚችሉት አቅም አደራጅተው ለምርጫ ይዘጋጁ፣ ይወዳደሩ፡፡ በማንነት ላይ የተመሠረተ ፌዴራል ሥርዓት ፖለቲካ አራማጆች ደግሞ እንዲሁ ያድርጉ፡፡ በዚህ ሒደት የብዙ ኃይሎች መፈራረስና መሰባሰብ (Realignment) ሊኖር እንደሚችል እንገምታለን፡፡ በሰላማዊና በሕጋዊ መንገድ የሽግግሩን መድረክ በውጤት ለመዝለቅ የተሻለውና በአገራችን የአገረ መንግሥት ግንባታ ሒደት የፖለቲካ ሥርዓቱን በሕዝቦች ፍላጎት ላይ የተመሠረተ እንዲሆን የሚያስችለው አማራጭ ይህ አካሄድ ይመስለናል፡፡
የአገራችን የፖለቲካ ቀውስ በሰላማዊና በሕጋዊ መንገድ መፍታት ከቻልን፣ በአገራችን እያንዣበበ ያለውን አደጋ በመከላከል ሰላም እንዲሰፍን እናደርጋለን ብቻ ሳይሆን፣ በአገራችን ለዘመናት በይደር የቆየውን የፖለቲካ ትራንስፎርሜሽን ሒደት ለማካሄድ መሠረቱን እንጥላለን ማለት ይሆናል፡፡ ይህ ደግሞ እጅግ ከፍተኛ ሥራና ውጤት ነው፡፡ ከዚህ በመነሳት አሁን ያለው የፖለቲካ አመራር ዋነኛ ሥራው፣ የተጀመረውን ለውጥ የፖለቲካ ትራንስፎሜሽን ለማምጣት በሚያስችል መሠረት ላይ ማስቀመጥ ቢሆን ይመረጣል፡፡ የፖለቲካ ትራንስፎርሜሽን በግልጽ ከተቀመጡ ግቦች አንፃር በማስቀመጥ፣ ከእነዚህ ግቦች ዋናውና መሠረታዊው ጉዳይ ቀጣዩን ምርጫ በሕገ መንግሥቱ መሠረት ተአማኒነት ባለው መንገድ በወቅቱ እንዲከናወንና ይህንን ለማድረግ የሚያስችሉ ሁሉም ዓይነት ዝግጅቶች ማከናወን መሆን አለበት ብለን እናምናለን፡፡ ከዚህ ጋር ጎን ለጎን አሁን ያለው ገዥ ፓርቲ በሕገ መንግሥቱ በተሰጠው ሥልጣን ብቻ እንዲወሰን፣ ማለትም ማንኛውም በሥልጣን ላይ ያለ መንግሥት የሚሠራቸውን የቀን ተቀን ሥራዎች ሰላምና መረጋጋት እንዲከበር፣ ሁሉም ዓይነት የመንግሥት ግልጋሎቶች ለዜጎች በተሟላ መንገድ መስጠትና ኢኮኖሚውን እንዲያንሰራራ ማድረግ ላይ ቢያተኩር ይመረጣል እንላለን፡፡
ተቃዋሚ የፖለቲካ ኃይሎችም ዋናው ትኩረታቸው ከአንድ ዓመት በኋላ በሚደረገው ምርጫ ለማሸነፍ፣ ሰፊ ሰላማዊ የፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ማድረግ ላይ ቢያተኩሩ፡፡ ይህ ማለት ራሳቸውን ማደራጀት፣ ማሰባሰብ፣ የምርጫ ማኒፌስቶ ማዘጋጀት፣ ሲመረጡ የሚሠሩዋቸውን ፕሮግራሞች በሰፊው በሰላማዊ መንገድ ለሕዝብ ማቅረብ፣ ለዚህ የሚመጥን የሎጂስቲክስ ዝግጅት ማድረግ ላይ ቢያተኩሩ ለአገራችን የፖለቲካ ትራንፍርሜሽን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖራቸዋል፡፡ ይህ ሒደት በሕዝቡ ላይ ተስፋ አጭሮ እንቅስቃሴው በሙሉ ወደ ሰላማዊ ፖለቲካዊ ውድድር እንዲያተኩር ግጭቶች መፈናቅሎች እንዲቆሙ፣ ሰላም እንዲሰፍን፣ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ብለን እናምናለን፡፡ በአጠቃላይ በቀረችን አንድ ዓመት አገራችንን መጠነ ሰፊ ወደ ሆነ የምርጫ ፖለቲካ ማዕበል እናስገባት እንላለን፡፡
4. ቀጣይ ዕርምጃዎች (የፖለቲካ ፍኖተ ካርታ)
4.1 ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ማክበርና ማስከበር
ይህ ተግባር አሁን ያለው ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት መብታችንን ያስጠብቅልናል የሚሉና በአገራችን ሰላማዊና ሕጋዊ ለውጥ ለማምጣት የሚፈልጉ ኃይሎች ሁሉ ሊፈጸሙት ይገባል፡፡ አሁን ባለው የአገራችን ሁኔታ የአገረ መንግሥት ግንባታ ሒደት በምን ዓይነት የፖለቲካ አስተሳሰብ መመሥረት አለበት የሚለውን የፖለቲካ መሠረታዊ አቅጣጫ ላይ በግልጽ የወጣ ልዩነት እየታየ ባለበት ወቅት፣ በማንነት ጉዳይ ላይ በተመሠረተ ዴሞክራሲያዊ ፌዴራላዊ ሥርዓት የአገረ መንግሥት ግንባታ የሚያምኑ ኃይሎች ሙሉ አቅማቸውን በማስተባበርና በመካከላቸው ሁኔታው የሚጠይቀውን ዝምድናና ቅንጅት መሥርተው በቀጣዩ ምርጫ አሸንፈው እንዲወጡ ሰፊ የዝግጅት ሥራ ይጠይቃቸዋል፡፡ እነዚህ ኃይሎች አሁን ተበታትነው በተናጠል ነው እየተንቀሳቀሱ ያሉት፡፡ ይህ ሁኔታ መለወጥ አለበት፡፡ ከዚህ አንፃር አሁን ያለው ሕገ መንግሥት ለሕዝቦች የሚያጎናፅፈውን መብት በተገቢው መንገድ በመግለጽ፣ ቀደም ብለው የተፈጠሩ ችግሮችና ድክመቶች እንዴት እንደሚታረሙ በማስቀመጥና ሕገ መንግሥቱን አስተሳሰብ እንደ ማሰባሰቢያ በመጠቀም አቅማቸውን ሰብሰብ ማድረግ ይኖርባቸዋል፡፡
ከዚህ አንፃር ገዥው ፓርቲ ያለው ድርሻ ከፍተኛ ነው፡፡ ምርጫው ሕገ መንግሥቱ በሚፈቅደው መሠረት ወቅቱን ጠብቆ እንዲካሄድ መወሰንና በውሳኔው መሠረት መንቀሳቀስ ይገባል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ግልጽ የሆነ አቋምና ውሳኔ አለማድረግ (Default)፣ ማለትም ውሳኔዎች በሁኔታዎች አስገዳጅነት እንዲደረጉ መፍቀድ ሰላማዊና ሕጋዊ የለውጥ ሒደት እንዳይኖር ሆን ብሎ እንደ መፍቀድ መሆኑ መታወቅ ይኖርበታል፡፡ ተቃዋሚ የፖለቲካ ኃይሎችም ይህንን ሕገ መንግሥታዊ ጉዳይ ተከትለው በቀጣዩ ምርጫ ሙሉ ዝግጅት እንዲያደርጉ መጋበዝ፡፡ ከሕገ መንግሥቱ ውጪ የሆኑ በተለይ ደግሞ ከቀጣዩ ምርጫ ጋር በቀጥታ ያልተያያዙ ጉዳዮችን ከምርጫው በኋላ እንዲሠሩ ማቆየት፣ ይህ አስተሳሰብ በገዥው ፓርቲ ውስጥ ልዩነት የሚፈጥር ከሆነም ልዩነቱ በግልጽ ወጥቶ አንድ መልክ እንዲይዝ ማድረግ፡፡ በዚህ ሳቢያም ፈጥኖ ለምርጫው በሚደርስ ሁኔታ የፖለቲካ ኃይሎች አደረጃጀት እንዲፈጠር ሁኔታዎችን ማመቻቸት፡፡ በሐሳቡ የማይስማሙ የኢሕአዴግ አባል የፖለቲካ ድርጅቶች ካሉም ከኢሕአዴግ ውጪ ካሉ የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር ተቀናጅተው ራሳቸውን ለቀጣዩ ምርጫ ማዘጋጀት ስለሚችሉ፣ አሁን እጅግ አሳሳቢና አንገብጋቢ እየሆኑ የመጡ ጥያቄዎች እንደ የአዲስ አበባ አስተዳደርና የሲዳማ ክልል የመሆን ጥያቄና የመሳሰሉት ሕገ መንግሥቱን መሠረት ተደርጎ በሕዝብ ምርጫ እንዲወሰን ማድረግና ሁኔታዎችን ፈጥኖ ማመቻቸት፡፡ እነዚህን የመሳሰሉትንና ሌሎች ጥያቄዎች ሊፈቱ የሚችሉበትን የውሳኔ አቅጣጫ አስቀምጦ ለሕዝቡ ግልጽ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ አሁን አገሪቱን እየመራ ያለው ኃይል ዋና ሥራው ሕገ መንግሥቱን ማክበርና ማስከበር፣ በዚህ መሠረት ተአማኒነት ያለው ምርጫ እንዲካሄድ ሁኔታዎችን ማመቻቸት፣ ሰላም፣ የሕዝቦችን መብትና ደኅንነት ማስጠበቅ ማለትም የሕግ የበላይነት እንዲከበር ማድረግ፣ ማንኛውም በሰላማዊ መንገድ በውድድርና በሕዝብ ምርጫ የፖለቲካ ሥልጣን መያዝ የሚፈልግ ኃይል ሕግና ሥርዓት ተከትሎ ያለ ምንም ተፅዕኖ የሚወዳደርበት፣ ከዚህ ውጪ በኃይል የሚደረግ ማንኛውንም እንቅስቃሴ ግን እንደ ወንጀል እየታየ ተገቢው ዕርምጃ የሚወሰድበት፣ አገር ወደ ሥርዓተ አልበኝነት ሳትገባ በሰላማዊ የፖለቲካ ውድድር የሽግግሩን ወቅት የምናጠናቅቅበት ሁኔታ የመፍጠር ኃላፊነት አለበት፡፡
4.2. የቀጣዩን አገራዊ ምርጫ ተዓማኒነት ማረጋገጥ
ይህ በቀጣይ የሚደረግ አገራዊ ምርጫ በአገራችን ታሪክ እጅግ በጣም ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል፡፡ በተፈለገው ጥራትና ተአማኒነት ከተካሄደ ደግሞ የአገራችንን የፖለቲካ ሥርዓት ሽግግር በተደላደለ መሠረት ላይ እንዲቀመጥ ማድረግ ያስችላል፡፡ ከዚህ የበለጠ ሌላ ፖለቲካዊ ተግባር ስለማይኖር፣ በቀረን አንድ ዓመት ውስጥ በሕገ መንግሥቱ መሠረት ውጤቱ ያማረ እንዲሆን አሁን በሥልጣን ላይ ያለው ኃይልና ሌሎች የፖለቲካ ኃይሎች ለዚህ ውጤት መሥራትና መዘጋጀት አለባቸው እንላለን፡፡ ይህ በአገራችን ታሪክና የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ እንደ አንድ ታሪካዊ ወቅት (Milestone) ታሪካዊ ፍፃሜ፣ የተለያዩ የፖለቲካ ኃይሎች ፍላጎታቸውን ማሳኪያ በማድረግ እንደገና አገሪቱን ችግር ውስጥ እንዳይከቷት መሥራት ይኖርብናል፡፡ አገራዊ ምርጫውን እንደ ቁልፍ ሥራ በመውሰድና ተገቢውን ዝግጅት በማድረግ ተአማኒነት ያለው ምርጫ ከተካሄደ፣ ከምርጫው በኋላ ምርጫውን ተከትሎ የሚመጣውንም ትርምስ ማስወገድ ወይም በከፍተኛ ደረጃ መቀነስ ያስችላል፡፡ ይህ ሒደት ከዚህ ቀደም በነበረው ብልሹ አሠራር ምክንያት ጠፍቶ የነበረውን የአገራችን የፖለቲካዊ ሥርዓት ተአማኒነቱን መመለስ ላይ ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡ አሸናፊው ብቻ ሳይሆን የተሸነፈውም ሽንፈቱን በፀጋ ተቀብሎ የፓርላማ መቀመጫውን ይዞ ትግሉን እየቀጠለ ለሚቀጥለው ምርጫ ይዘጋጃል፡፡ ይህ ሁኔታ ሕዝብ በመንግሥት ላይ ያለውን እምነት በመጨመር ለተሻለ ሰላምና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት መነሻ ይሆናል፡፡
በቀጣዩ ለሚደረገው አገራዊ ምርጫ በተገቢው መንገድ ለማካሄድ እንቅፋት ሊሆኑ የሚችሉ ከወዲሁ መፈታት ያለባቸው በርካታ ጉዳዮች አሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ጎላ ጎላ ያሉትን ለመጥቀስ ተፈናቃዮች ወደ ቀዬአቸው ተመልሰው ሰላማዊ ኑሮአቸው እንዲቀጠሉ ማድረግ፣ በአገር አቀፍ ደረጃ ያለውን ያለ መረጋጋት ተገቢውን ዕርምጃ በመውሰድ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን ማድረግ፣ የሕዝብ ቆጠራ ማካሄድ ወይም በነበረው ምርጫው እንዲካሄድ መወሰን፣ የፖለቲካ ኃይሎች የምርጫ ሐሳባቸውን (ማኒፌስቶ) አዘጋጅተው በስፋት በሰላማዊ መንገድ እንዲንቀሳቀሱ ማስቻል፣ ሰፊ የሆነ የምርጫ አደረጃጀትንና የሎጂስቲክስ ሥራዎችን ማዘጋጀትና የመሳሰሉ በርካታ ሥራዎች አሉ፡፡ የመንግሥትና የገዥው ፓርቲ ዋናው ትኩረትና ተቀዳሚ ተግባሩ ይህ መሆን አለበት፡፡ በጠቅላላ አገሪቱን ወደ ሰፊ የምርጫ ወቅት የፖለቲካ እንቅስቃሴ በማስገባት ፖለቲካዊ ሽግግሩን ባማረ ውጤት እንዲጠናቀቅ መሥራት አለበት፡፡ ይህ የምርጫ እንቅስቃሴ ትግራይም ውስጥ በስፋት መካሄድ ይኖርበታል፡፡ በተለይ በድርጅታዊ አሠራር የድርጅት ካድሬ ብቻ እየተመለመለ ለፓርላማ አባልነት (ለክልል ወይም አገራዊ)፣ ለወረዳ አስተዳዳሪነትና ለከተማ ከንቲባነት የሚደረገው አሠራር መቅረት አለበት፡፡ በየአካባቢው ያለ ሕዝብ ከውስጡ ከነዋሪዎች የተሻለ ፍላጎቴን ይወክሉልኛል፣ አስተሳሰቤን ይጋራሉ የሚላቸውን ተጠሪነታቸው ለመረጣቸው ሕዝብና አካባቢ የሆነ የሕዝብ ተወካዮች (የድርጅቱም ካድሬም ሊሆኑ ይችላሉ ሕዝብ እስካመነባቸው ድረስ) እንዲመርጥ ሁኔታዎችንና አሠራሩን ሊስተካከል ይገባል፡፡
4.3. የመንግሥታዊ ተቋማትን ተዓማኒነት ማረጋገጥ
በሕዝብ ዘንድ ተአማኒነት ያለው ምርጫ ማካሄድ ከብዙ ጠቀሜታዎቹ አንዱ፣ የመንግሥታዊ ተቋማትን ተአማኒነት ከፍ እንዲል ማድረጉ ነው፡፡ በተጭበረበረ ምርጫ የሚመረጥና የሥራ አስፈጻሚው ታዛዥ የሆነ የሕግ አውጭ በሕዝብ ዘንድ ተአማኒ ሊሆን አይችልም፡፡ በሥራ አስፈጻሚው መልካም ፈቃድ የእሱ ታዛዥ በመሆኑ የሚቋቋም የፍትሕ ሥርዓት፣ በሕዝብ የታመነ የሕዝብን መብት የሚያስጠብቅ የሥራ አስፈጻሚውን የሕግ ጥሰት የሚከላከል በሕዝብ የሚከበርና ተአማኒነት ያለው መሆን አይችልም፡፡ ተአማኒነት ባለው ምርጫ የሚቋቋም ከተቃዋሚዎች በርከት ብለው የተወከሉበት የሕግ አውጭ (ፓርላማ) ከተቋቋመ የሥራ አስፈጻሚው ታዛዥ የመሆን ዕድሉ ይጠባል፡፡ ስለዚህ ለሕግ አውጭ ተጠሪ የሆነ ከሥራ አስፈጻሚው አንፃራዊ ነፃነት ያለው የሕግ ተርጓሚ ደግሞ የተሻለ ሥራ አስፈጻሚውን የመቆጣጠር አቅምና ፍላጎት ይኖረዋል፡፡ የአንድ ፓርቲ የሥልጣን ሞኖፖል ስለማይኖር፡፡ ይህ ደግሞ ቀስ በቀስ በተዋረድ የመንግሥት ተቋማትን ተአማኒነት እየዳበረ እንዲሄድ መሠረቱን ይጥላል፡፡ አሁኑ ምርጫ በተገቢው መንገድ ከተመራ የተጀመረው ለውጥ ሰላማዊና ሕጋዊ ይሆናል ብቻ ሳይሆን፣ በአገራችን ለሚደረገው የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ትልቅ መሠረት ይጣላል፡፡ የተረጋጋች ኢትዮጵያ እንድትኖር የጎላ ድርሻ ይኖረዋል፡፡ ከእነዚህ ከላይ የተገለጸው ተአማኒነት ያለው ሕገ መንግሥቱን መሠረት ያደረገ ዋነኛ ሥራ ጎን ለጎን የአገሪቱ ኢኮኖሚ ለከፋ አደጋና ጉዳት እንዳይዳርገን ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡ የአገራችን ኢኮኖሚ አሁን ከደረሰበት ደረጃ በታች እንዳያሽቆለቁልና ትንሽም ቢሆን ነፍስ እንዲዘራ ለማድረግ ዋናው ሥራ ሰላም፣ የተረጋጋና ተስፋ የሚጣልበት ሊተነበይ የሚችል (Predictable) የፖለቲካ ሥርዓት እንዲኖር ማድረግ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ከላይ እንደተገለጸው ተአማኒነት ያለው ምርጫ በማካሄድ አድርጎ የሚመጣ ትራንስፎርሜሽን ዕውን ይሆናል ብለን እናምናለን፡፡ ከዚህ ጋር ጎን ለጎን ከፖለቲካ ሥራው ባልተናነሰ ሁኔታ፣ የኢኮኖሚው ጉዳይ ራሱን የቻለ በከፍተኛ ትኩረት የሚመራ እንቅስቃሴ ያስፈልገዋል ብለን እናምናለን፡፡
5. ማጠቃለያ
አገራችን በከፍተኛ የፖለቲካ ሽግግርና ቀውስ ውስጥ ትገኛለች፡፡ ይህ ሁኔታ የወቅቱን ሙቀት እያዩ፣ በዕለት ተዕለት ሥራና የጊዜውን ጥያቄዎች በማየትና ለመፍታት በመጠመድ አይፈታም እንላለን፡፡ አሁን በአገራችን እየታየ ያለው የፖለቲካ ሁኔታ እንደ ከፍተኛ ፀጋና መልካም አጋጣሚ በመጠቀም፣ የአገራችንን ፖለቲካዊ ሥርዓት ወደ ተደላደለ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለማሸጋገር እጅግ ሰፊ ዕድል አለ ብለን እናምናለን፡፡ ከዚህ አንፃር ስናየው መነሻ የምናደርጋቸው ታሳቢዎች አሉ፡፡ አንደኛው የአንድ አገር ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ በአንድ ምርጫ ብቻ አይፈጸምም፡፡ ማድረግ የሚቻለው ለቀጣይ ዕድገቱ መሠረቱን ማስቀመጥ ብቻ ነው፡፡ ይህ ደግሞ መደረግ የሚችለው በሰላማዊ ሕጋዊ መንገድ ብቻ ነው፡፡ በኃይል በጉልበት ወይም ሕጋዊውን አሠራር በመጣስ አይመጣም፡፡
መጪውን ወቅቱን የጠበቀ ምርጫ በተመለከተ የተለያዩ አስተያየቶች እንሰማለን፡፡ የሐሳቦቹ ማጠንጠኛ በቂ ዝግጅት አድርገን ችግራችንን በአስተማማኝነት የሚፈታ ተአማኒነት ያለው ምርጫ ለማካሄድ ፖለቲካዊ ዝግጅት ያስፈልጋል፣ ለዚህ ደግሞ ጊዜ ይጠይቃል፣ ስለሆነም ምርጫው በተቀመጠለት ጊዜ ላይካሄድ ይችላል የሚል ነው፡፡ በአገራችን ያሉትን የፖለቲካ ችግሮች በአንድ ምርጫ ብቻ እንደሚፈቱ የሚያስብ ፖለቲከኛ ካለ የዋህ ይመስለናል፡፡ በአንድ የምርጫ ወቅት ሊደረግ የሚችለው በተለይ እንደ አገራችን በመሳሰሉ በሽግግር ውስጥ ያሉ አገሮች ውስጥ ቀጣይ የሚገነባው የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት፣ የአገረ መንግሥት ግንባታውን ተጠናክሮ እያደገ የሚሄድ መሠረት ላይ ማስቀመጥ ብቻ ነው፡፡ ይህ ማለት ቀጣይነት ያለው ሰፊ ሥራ እንዳለ በመገንዘብ የአገሪቱ የፖለቲካ ኃይሎች በዋናነት የሚስማሙበት ጊዜው የፈቀደውን ያህል ተአማኒነት ያለው፣ በቀጣይነት ደግሞ እያደገ የሚሄድ የፖለቲካ ሥርዓት ማስቀመጥ ላይ ያተኩራል ማለት ነው፡፡ ይህ ከሆነ አሁን የተሸነፈ የፖለቲካ አስተሳሰብ ራሱን ይበልጥ አደራጅቶ ከአምስት ዓመት በኋላ ተወዳድሮ ሊያሸንፍ ይዘጋጃል ማለት ይሆናል፡፡ በቂ ዝግጅት (የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የምርጫ ኮሚሽን አደረጃጀት፣ የምርጫ ሥርዓት ዝርጋታ፣ ሰላምና መረጋጋት አለመኖር፣ ወዘተ.) ተብሎ የምርጫ ጊዜውን ከሕጉ ውጪ ማራዘም ሕገ መንግሥቱ የመጣስና ሕገወጥ የመሆኛው አንድ መንገድ ነው፡፡ ይህ ደግሞ በራሱ ሁኔታ በ(Default) የሚመጣ ከሆነ፣ አሁን ልንጠቀምበት የምንችለውን መልካም አጋጣሚ በማሳጣት መገመት ወደማንችለው ውጥንቅጥ ውስጥ ይከተናል፡፡ የምርጫ ዝግጅቶችን ሟሟላት በአገር ደረጃ ስናየው በቁጥጥራችን ያለ ነገር ነው፡፡ ጉድለቶች ቢኖሩትም የሽግግር ምዕራፉን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ያበቃናል፡፡ ይህ ስትራቴጂካዊ ፍፃሜ ነው፡፡ ይህንን መልካም አጋጣሚ ተጠቅመን የተጓደሉብንን በቀረው ጊዜ ሟሟላት እንችላለን፡፡ ከዚህ ውጪ የሚኖር አማራጭ ግን ሁኔታዎች ከቁጥጥራችን ውጭ ሆነው እንደ አገር ልንወጣው ወደማንችል አዘቅት ሊከተን ይችላል ብለን እናስባለን፡፡
ምርጫውን በተቀመጠለት ጊዜ ለማካሄድ ከወሰንን በቀረን አንድ ዓመት ገደማ አገሪቱን ወደ ሰፊ “የምርጫ ፖለቲካ”፣ ማለትም ሰላማዊና ሕጋዊ ሰፋፊ የፖለቲካ ውይይት በማስገባት፣ በሰላማዊና ሕጋዊ መንገድ ለፖለቲካዊ ሥልጣንና ለቀጣይ የአገረ መንግሥት ግንባታ የራሱን አስተዋጽኦ የሚያደርገውን ኃይልና በአቋራጭና በግርግር ሥልጣን ለመያዝ ሁሉንም ዓይነት መንገዶች (ሕጋዊውንም፣ ሕገወጡንም) መጠቀም የሚፈልግ ኃይል ለመለየትና በወጉ ለማስተዳደር ይመቻል፡፡ ይህ ደግሞ ሰላምና መረጋጋትና የሕግ የበላይነት እንዲሰፍን አስተዋጽኦ ያደርጋል፡፡ የአገሪቱ የወደፊት ጉዞና አቅጣጫ የሚተነበይ (Predictable) ያደርገዋል፡፡ ይህ በዓለም አቀፍ ግንኙነት ተአማኒነትን በማትረፍ ለኢኮኖሚው መነቃቃት አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡ የሕዝቡንም በሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ መንገድ ያለ ተፅዕኖ የፖለቲካ ምርጫውን እንዲያስተካከል፣ የፖለቲካ ንቃቱ ከፍ እንዲል፣ የአገሩንና የራሱን ፖለቲካዊ ሕይወት ይበልጥ እንዲቆጣጣር ያስችለዋል፡፡ የሽግግር ሒደቱ በጠንካራ መሠረት እንዲገነባ ያስችላል፡፡ በቀጣይ ምርጫ ልናሳካው የምንመኘውና ማሰብ ያለብን ግብ የፖለቲካ ሽግግሩ በሰላማዊና ሕጋዊ መንገድ፣ ለቀጣይ የአገረ መንግሥት ግንባታ ሰፊ መደላድል መፍጠር ላይ መሆን አለበት እንላለን፡፡ መቼም አሁን በአገራችን የሆነ ምርጫ ሲደረግ የተጭበረበረና አንድ ፓርቲ ብቻ ሙሉ በሙሉ የሚቆጣጠረው ፓርላማ ይኖራል ብሎ መገመት አይቻልም፡፡ የተለያዩ የፖለቲካ ኃይሎች በሕጋዊና በሰላማዊ መንገድ ተመርጠው ፓርላማ ውስጥ መቀመጫ መያዛቸውና የአገራችን ፓርላማ መሠረታዊ የአገራችን የፖለቲካ ልዩነቶች ክርክር የሚደረግበት፣ ሕዝቡ በቀጣይ የተለያዩ አማራጮችን የሚያይበትና የሚዘጋጅበት፣ መንግሥትና ፓርቲ የሚለያዩበት፣ የመንግሥት ዋነኛ አካላት (ፓርላማ፣ ሕግ ተርጓሚውና ሥራ አስፈጻሚው) አንፃራዊ ነፃነታቸውን አረጋግጠው በሥራ አስፈጻሚው የማይታዘዙበት ሁኔታ በመፍጠር ቢጠቃለል እንኳን፣ ይህ ከቀጣይ ፖለቲካዊ ትራንስፎርሜሽን አንፃር ከፍተኛ ውጤት ነው፡፡ ስለዚህ ለፖለቲካ ሽግግሩ ተገቢውን ትኩረት እንስጥ እንላለን፡፡ እናመሰግናለን!
ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊዎቹ ከዚህ ቀደም በተለያዩ ወቅቶች የኢሕአዴግ ምክር ቤትና የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት የነበሩ ሲሆን፣ ከደርግ ውድቀት በኋላ በተቋቋመው የአገር መከላከያ ሠራዊት በከፍተኛ አመራርነት አገልግለዋል፡፡ ጽሑፉ የእነሱን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected], [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡