ለወራት የአገራችን ሚዲያዎችን የአየር ሰዓት ያጣበበ ማስታወቂያ፣ የብዙዎችን ትኩረት ስቦ ቆይቷል፡፡ ማስታወቂያው ከሚዲያ ባሻገር፣ የተለያዩ የማስታወቂያ መንገዶችን በመጠቀም ፍዳችንን ሲያበላን ከርሟል፡፡ የማስታወቂያ ሰሌዳዎችን በማጣበብ መልካም ምግባር የሚሰብከውን ማስታወቂያ በምን ይሆን ሲያስነብበንና ሲያብሰለስለን ቆይቷል፡፡ እነዚህን ማስታወቂያዎች አሁንም ድረስ በየሚዲያው እየተመለከትን፣ እያደመጥንና እያነበብን እንገኛለን፡፡ የከተማችን የባቡር ጣቢያዎች ወይም ፌርማታዎች ሳይቀሩ ለዚህ ማስታወቂያ ተፈቅደው ማንነቱን ሳይገልጽልን በቆየው ማስታወቂያ ተሸፍነዋል፡፡ ‹‹ብሩህ ተስፋ ለሚታየው ልባም›› ይላል የማስታወቂያው መልዕክት፡፡ በውስጡም ሌሎች ተስፋ ሰጪ መልዕክቶች ያጀቡት ነበርና ብዙዎቻችን መልካምና አዲስ ነገር ይዞ የሚመጣ ምን ነገር እናይ ይሆን በማለት በልብ አንጠልጣዩ ማስታወቂያ የሚገለጠውን ዕውነት መጨረሻ ለማወቅ ጓጉተን ነበር፡፡
‹‹ብሩህ ተስፋ ለሚታየው ልባም›› ከሚለው ማስታወቂያ ጀርባ ከመልካም ነገር በላይ ምንስ ይጠበቃል? በማስታወቂያው መልካም ምግባር መግለጫ በሆኑ ቃላት የታጀቡ መልዕክቶች ምን ይሆኑ ብሎ ራሱን ያልጠየቀ፣ እርስ በርሱ ያልተነጋገረና ከሰዎች ያልተወያየ የለም ማለት ይቻላል፡፡ ግብረገብነትን ተላብሶ ሲዥጎደጎድ የከረመው መልዕክት ግን የአልኮል መጠጥ ለማስተዋወቅ ነው ብሎ ማን ያስባል፡፡ ማንስ ቢሆን ልባምነትን፣ መልካም ምግባርን በምንም መልኩ ቢሆን ከአልኮል መጠጥ ጋር ለማያያዝ እንዴት ይዳዳዋል፡፡ የልባምነት መገለጫ አገርን የሚጠቅም ተግባርና ጀግንነትን፣ ብልህነትን የሚያፀባርቅ፣ ትጋትና አስተዋይነትን የሚያነግሥ እንጂ ቢራን ማን ልባም ያደርገዋል፡፡ ማስታወቂያውን የሠሩት የሽያጭ ሰዎች ወይም በዘመኑ የግብይት ሥርዓት መሠረት የማስታወቂያ ዘመቻ ቀማሪዎች ልብ ሰቀላው ቢሳካላቸውም የመጨረሻው ግባቸው ግን ውግዘትን ማትረፍ ሆኗል፡፡
አልኮል ለመሸጥ እንዲህ ዕድል ያለ ግነትና ጉሸት ከልክ ያለፈ ሲሆን ጊዜ፣ እንኳንና በሕዝቡ ዘንድ በሕግም ሊያስጠይቅ የሚችልበት አግባብ ተደንግጓል፡፡ የልባምነት ልኬት አልኮል መጎንጨት እንደሆነ መንገር ልቅነትም ነው፡፡ ከአገር አልፎ የውጭው ዜጋ የሚታዘበን ሕዝቦች እየሆንን ያለነው ገደብ ባጡ የመጠጥ ማስታወቂያዎች እኮ ነው፡፡ የነገ ተስፋችን ቢራ በመጠጣት ላይ የተመሠረተ እስኪመስለን ድረስ ነገሩን፡፡
ያጣናቸው በርካታ መልካም መገለጫዎች ቢኖሩንም ይህን ያህል ወርደን መገኘታችን ግን ያሳምማል፡፡ ብርታትና አንበሳነት ቢራ ከመጠጣት እንደሚገኝ ያለ ይሉኝታ ያውም ወጣትና ሕፃናት ሳይገደቡ በሚመለከቱት መስኮትና በየመንገዱ ሲለፈፍልን እንደ ዜጋ ሊቆጨን ይገባል፡፡ የነገ አገር ተረካቢዎችን ለመታደግ የአልኮል ማስታወቂያዎችን በኤሌክትሮኒክስ ሚዲያዎች ማስተዋወቅ መከልከሉ በሕግ በወጣ ማግሥት የዜጎች የነገ ተስፋና ልባምነትን ከቢራ ጭለጣ ጋር አያይዞ ማቅረብ የትኛው የማስታወቂያ ዕውቀትና ክህሎት ሹክ እንደሚላቸው ግራ ያጋባል፡፡ ማስታወቂያ ግነትና ኩሸት አለው፡፡ ሳይንሱም በተወሰነ ደረጃ ይፈቅድለታል፡፡ ከልኩ ሲያልፍ ግን በሽታ ነው፡፡ ይህንን በመጠጥ ኢንዱትስትሪው እያየን ነው፡፡
ብሩህ ተስፋን ለቢራ አደባባይ ሲወጣና በማስታወቂያ ሲያጥለቀለቅ ስናይ ይኼ ነገር ምንድነው? የሚል ጠያቂ ባይጠፋም፣ መንግሥት አካባቢ ዝምታው መብዛቱ ሳያስገርም አይቀርም፡፡ ምናልባት ሕጉ ተፈጻሚ ሊደረግ ጥቂት ጊዜ ስለቀረው ነው ተብሎ ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን እንዲህ ያሉ ቀስ በቀስ የኢትጵያዊነት መገለጫዎችንና በመልካም ጎናቸው የምንጠቀምባቸውን ጉዳዮች በሾርኔ እየተጠቀሙና እየገቡ ሕዝብን የሚያሳስት መልዕክት ማቅረቡ በታወቀና ሕዝቡም ተቃውሞውን በገለጸ ጊዜ፣ እንዲህ ያሉትን ፈር የለሽ ማስታወቂያዎች የመቆጣጠር ኃላፊነት ያለባቸው ተቋማት ምን እየሠሩ ነው? እንላለን፡፡ ሚዲያዎችም የዚህን ማስታወቂያ አካሄድና ሊያስከትል የሚችለውን ተፅዕኖ ተገንዝበውና መዝነው ማዕቀብ ማስቀመጥ ይጠበቅባቸው ነበር፡፡
የቢራ ማስታወቂያዎችን የተመለከተው አዲሱ ሕግ ሥራ ላይ ከመዋሉ በፊት ያለውን ጊዜ እንዳሻው የተጠቀመበት ቢራ አምራቹ ድርጅት፣ እንዲህ ያለውን ተግባር ቸል ማለቱ ለዜጎች ያለውን ደንታ ማጣት ሊያሳይ ይችላል፡፡
ሌላው የምናዝንበት ጉዳይ፣ እንዲህ ባለው የማስተዋወቂያ ሥልት ማስታወቂያውን ያስነገረው ኩባንያ ባለድርሻዎች በኢትዮጵያ ቢዝነስ ውስጥ ለረዥም ዓመታት በጨዋነታቸው የሚጠቀሱ በተለያዩ ውጤታማ ቢዝነስ መስክ ዕውቅናም ተቀባይነትም ያተረፉ ሆነው ሳለ፣ ዛሬ ላይ እንዲህ ባለው ደረጃ ራሳቸውን ማቅረባቸው ጭምር ነው፡፡ ነገሩ ከራስ በላይ ነፋስ እንዳይመስልባቸው ያስብቡበት፡፡
የዚህ ማስታወቂያ እንቆቅልሽ ከተፈታ በኋላ የኅብረተሰቡ ግብረ መልስ በቁጭትና በንዴት የታጀበ እንደሆነም እያዩ ነው፡፡ ቢራዬን ጠጡልኝ ለማለት ስንት የማስታወቂያ ሥልት እያለ፣ ይህንን መንገድ መምረጥ ተገቢ እንዳልነበረም ተመልካቾች እየገለጹ ነው፡፡ ችግሩ ማስታወቂያውን እንዲህ ባለው መንገድ እንዲሠራለት ዲዛይን ያደረገው ኩባንያ ላይ ብቻ የሚተው አይደለም፡፡ ማስታወቂያውን ለማስተጋባት ራሳቸውን በፊት አውራሪነት ያስቀመጡ ማስታወቂያ ነጋሪዎችም በዜጎቻቸው ላይ ቀልደዋል፡፡ የቀረበውን ዓይነት የቢራ ማስታወቂያ ማቅረብ ተገቢ አይደለም ብለው መሞገት ሲችሉ፣ ፍራንካው በልጦባቸዋል፡፡ ቢራን በዚህ መንገድ ለመግለጽ ድምፃቸውን ያከራዩ ምሥላቸውን ለቢራው ያዋሉ ሁሉ ተወቃሾች ናቸው፡፡
በእርግጥ ገበያውን ለመቀላቀል ቀልብና ልብ የሚስብ ማስታወቂያ ማስነገር የሚጠበቅ ቢሆንም፣ ኃላፊነት በተሞላበት መልኩ መሥራት እየተቻለ እንደሙያተኛም ሐሳብ በማቅረብ ከትችት የሚያድን ማስታወቂያ መሥራት እየተገባ፣ ሁሉም ንብርብር መሆናቸው ተገቢ አይደለምና ለቀረው ጊዜም ቢሆን ዕርምት መውሰድ ይጠበቅባቸዋል፡፡
ማስታወቂያ ነጋሪና አስነጋሪዎች አነጋጋሪ ማስታወቂያ ሠርተናል ብለው ልባቸውን በሐሴትና በስኬት ሞልተውት ይሆናል፡፡ ብሩ ተስፋ ማለት ቢራ መጠጣት ነው ብሎ እንዲያስብ፣ በረባ ባልረባው ሆድ የሚብሰውን ሁሉ ቢራ ጠርሙስ ሥር እንዲገኝ የሚያማልል አካሄድም ጭምር ውስጡ ያለበት አካሄድ መልካም ተግባር ካለመሆኑም በላይ፣ ደንበኛ ለማፍራት ፈር የለቀቀ ዘዴ ሆኖም ይገኛል፡፡
ስለዚህ የማይገናኙና በባህሪይ የማይተዋወቁ ነገሮችን በማዋሃድ ዜጎች የተሳሳተ ምልከታ እንዲኖራቸው ያደረገው ማስታወቂያ አሁንም እንዲታረም ካልተደረገ ነገም ሌሎች በዚሁ መንገድ ያልታሰበ ጥፋት ሊያመጡ ይችላሉና ጉዳዩ ችላ መባል የለበትም፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ ከሳምንታት በኋላ ተግባራዊ የሚሆነው ሕግ ከመምጣቱ በፊት አንዳንድ የቢራ ፋብሪካዎች የማስታወቂያ ሥልታቸውን ቀይረው፣ በየመንገዱ ሰውነታቸውን አጋላጭ ልብስ ለብሰው ቢራ ሲያስተዋውቁ መታየታቸው አሁንም የቢራ ፋብሪካዎች የማስታወቂያ ሥነ ምግባር ላይ ተጨማሪ ማዕቀቦችን የሚፈልጉ ይመስላሉና የማስታወቂያው ጉዳይ ‹‹እንኳን ዘንቦብሽ እንዲሁም ጤዛ ነሽ›› የሚለውን አባባል የሚያስታውሰን ዓይነት ጨዋ ዜጋ ለመፍጠር አቀበት የሆነብንን መንገድ ሰማይ ቧጥ ያደረገዋልና ኧረ በሕግን ጠበቅ እናድርግ፡፡