ሦስተኛው የኢትዮጵያ የግብርና፣ ምግብና መጠጥ ማቀነባበሪያ ቴክኖሎጂ እንዲሁም ፕላስቲክ ኅትመትና ማሸጊያ የንግድ ትርዒት ከግንቦት 1 እስከ ግንቦት 3 ቀን 2011 ዓ.ም. በሚሊኒየም አዳራሽ ተካሂዷል፡፡
ለሦስት ቀናት የቆየው ሦስተኛው ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒት ከ18 በላይ አገሮች፣ ከ148 በላይ ዓለም አቀፍ የንግድና ቴክኖሎጂ መሪዎች እንዲሁም የሥራ ፈጣሪዎች ተሳትፈውበታል፡፡
የጀርመኑ የንግድ ትርዒት አዘጋጅ ፌርትሬድና አገር በቀል አጋሩ ፕራና ኤቨንትስ በትብብር ሆነው ያዘጋጁት ይህ የንግድ ትርዒት በፈረንሣዩ የምግብ ማቀነባበሪያ ቴክኖሎጂዎች ዓለም አቀፍ ትብብር (ADEPTA)፣ በጀርመን የዓለም አቀፍ ትብብር (GIZ)፣ በጀርመን ኢንጂነሪንግ ፌዴሬሽን (VDMA)፣ በጀርመን ግብርና ማኅበር (DLG)፣ በቻይና የንግድ ኤጀንሲዎች፣ በኔዘርላንድ የአፍሪካ ቢዝነስ ካውንስል (NABC)፣ በቱርክ መንግሥት ትብብርና በጣሊያን የንግድ ኤጀንሲ (ITA) የታገዘ ሲሆን፣ በአገር ውስጥ በኩልም በግብርናና የተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር፣ የምግብ፣ መጠጥና የፋርማሲዩቲካልስ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ልማት ኢንስቲትዩት ድጋፍና ዕውቅናን አግኝቷል፡፡
በዚህ ዓውደ ርዕይ በብሔራዊ ደረጃ ለመጀመርያ ጊዜ የተሳተፉት አገሮች ጀርመን፣ ኔዘርላንድስና ቱርክ ሲሆኑ፣ ቻይና፣ ፈረንሣይና ጣሊያን ተሳትፏቸውን አጠናክረዋል፡፡
ትኩረቱን በግብርና፣ ምግብና መጠጥ ማቀነባበርና የተቀነባበሩ ምርቶች ላይ እንዲሁም የተቀነባበሩ ምግብና መጠጦች አስተሻሸግና የማሸጊያው ኅትመት ጥራት ላይ ያደረገው ይህ ዓውደ ርዕይ፣ ኢትዮጵያ ከአገሮቹ ጋር ያላትን ቢዝነስ ለቢዝነስ ግንኙነት ያጠናክራል ያሉት አቶ ሰለሞን ታደሰ የኢትዮጵያ ምግብ፣ መጠጥና ፈርማሲዩቲካል ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ናቸው፡፡
ካቻምና ኢትዮጵያ በአገር ውስጥ ያላት የምግብ ገበያ ከአራት ቢሊዮን ዶላር በላይ ያስመዘገበች ሲሆን፣ ወደ ውጭ የምትልካቸው የምግብ ምርቶችም 2.2 ቢሊዮን ዶላር ማስገኘታቸውን መረጃዎች አሳይተዋል፡፡