የታክስ ከፋዮች ያቀረቡትን የራስ ታክስ ሥሌት ማስታወቂያ ለማሻሻል የሚቀርብ ጥያቄን ተቀብሎ ለማስተናገድ ዕገዛ ያደርጋል የተባለው መመርያ በገቢዎች ሚኒስቴር ይፋ ተደርጓል፡፡
በገቢዎች ሚኒስቴር በቅርቡ ከወጡ መመርያዎች መካከል አንዱ የሆነው ‹‹ታክስ ከፋዩ ያቀረበውን የራስ ታክስ ሥሌት ማስታወቂያ እንዲሻሻል ስለሚፈቀድበት ሁኔታ ለመወሰን የወጣ መመርያ ቁጥር 144/2011›› ከዚህ ቀደም ይታዩ የነበሩ ክፍተቶችን ጠቅሷል፡፡
ማንኛውም ታክስ ከፋይ ራሱ አሥልቶ ያቀረበውን የራስ ታክስ ሥሌት ማስታወቂያ የታክስ ባለሥልጣኑ ሲፈቅድለት ሊያሻሽል እንደሚችል በአዋጁ የተደነገገ በመሆኑና የራስ ታክስ ሥሌት ማስታወቂያ ለማሻሻል በታክስ ከፋዩ ማመልከቻ ሲቀርብ፣ ማሻሻያው ስለሚፈቅድበት ሁኔታ ግልጽ አሠራር ለማስቀመጥ የወጣ መመርያ እንደሆነ ተመልክቷል፡፡
ታክስ ከፋዩ በራሱ ውሳኔ ባቀረበው የታክስ ሥሌት ማስታወቂያ ላይ የተገለጸውን የታክስ መጠን በመጨመር ወይም በመቀነስ ወይም ሌላ ለውጥ በማድረግ የሚያቀርበው መመርያ የማሻሻያ ጥያቄው እንዴት እንደሚስተናገድም አንቀጾችን አካቷል፡፡
ይህ ቢካተትም ሚኒስቴሩ በራሱ አነሳሽነት የተሻሻለ የታክስ ሥሌት ማስታወቂያ ለታክስ ከፋዩ ሊሰጠው የሚችልበት ክፍልም አለው፡፡ የታክስ ሥሌት የሚሻሻልበትን ምክንያት ሲያስቀምጥም ታክስ ከፋዩ በራሱ (በራሱ ሒሳብ ባለሙያ) ያዘጋጀው የታክስ ሥሌት እንዲሻሻልለት ሲያመለክት፣ በሚከተሉት ምክንያቶች ሚኒስቴሩ ሊያሻሽላቸው የሚችልባቸውን ዝርዝር ጉዳዮች ያሰፈረ ነው፡፡
የታክስ ሥሌት ሊሻሻል የሚችልባቸው ምክንያቶች ተብለው ከተጠቀሱት ውስጥ የድምር ስህተት ሲኖር፣ የአጻጻፍ ስህተት ሲያጋጥም የማሻሻያ ጥያቄው ይስተናገዳል፡፡ ከዚህም ሌላ ከሒሳብ መደብ አመራረጥ ጋር የተያያዘ ስህተት ሲኖር፣ የጆርናል ምዝገባ ስህተት ሲኖር፣ ሒሳብ ወደ ሌጀር ሲተላለፍ የተከሰተ ስህተት ሲያጋጥም፣ ከሒሳብ ማስተካከያ ጋር የተያያዘ ስህተት ሲያጋጥም፣ በሒሳብ መዝገብ ላይ ሳይመዘገብ የተዘለለ የገቢና ወጪ ሰነድ ሲኖር፣ ወይም የመጨረሻ ሀብት ቆጠራ አያያዝ ስህተት ሲኖር፣ የሒሳብ አያያዝ ዘዴ ስህተት ሲያጋጥምም የታክስ ሥሌት እንዲሻሻል እንደ ምክንያት ሊቀርቡ የሚችሉ ናቸው፡፡
በታክስ ሕጉ የተደነገገው እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ተቋሙ የውጭ ኦዲተሮችን የኦዲት ሪፖርት ሲመረምር ባገኘው ግኝት መሠረት የሚደረግ ማስተካከያ ሲያጋጥም፣ ሦስተኛ ወገን በሚሰጠው ማረጋገጫ ወይም በፍርድ ቤት በሚሰጥ ውሳኔ መሠረት በሒሳብ መዝገቡ ላይ ማስተካከያ ማድረግ ሲያስፈልግም ለማሻሻያው ምክንያት ሆኖ ሊቀርብ ይችላል፡፡ በታክስ ሕግ ያልተፈቀደ ወጪ በተቀናሽነት በመያዙ ምክንያት የተፈጠረ ስህተት ሲኖር ሊያሻሻልና ጥያቄው እንደ ምክንያት ሊቀርቡ የሚችሉ ናቸው፡፡ የግልና የንግድ ሒሳቦች በመቀላቀላቸው የተፈጠረ ስህተት ሲያጋጥም፣ በታክስ ማስታወቂያ ቅጽ ላይ የአመዘጋገብ ወይም የአገላለጽ ስህተት ሲያጋጥም፣ በታክስ ወይም በተለይ በኤክሳይዝ ታክስ ሒሳብ አያያዝ ላይ የማምረቻና አስተዳደራዊ ወጪዎች ተፋልሰው ባልተገባ ቦታ ላይ ተመዝግበው ሲገኙ ጥያቄውን ለማስተናገድ ይችላል፡፡
ከእነዚህ ከተዘረዘሩት ምክንያቶች የተለየና በሚከፈለው የታክስ መጠን ላይ ለውጥ ሊያስከትል የሚችል አሳማኝ ምክንያት ሲያጋጥም፣ ሥራ አስኪያጁ የራስ ታክስ ሥሌት ማሻሻያ እንዲደረግ ሊፈቅድ እንደሚችልም መመርያው ጠቅሷል፡፡
በሌላ በኩል ግን በግብር ዘመኑ በከፍተኛ የሥጋት ደረጃ የተመደበ ታክስ ከፋይ የሚያቀርበው የታክስ ሥሌት ማሻሻያ ጥያቄ ተቀባይነት አይኖረውም፡፡
የራስ ታክስ ሥሌት እንዲሻሻል የሚቀርብ ማመልከቻ መሟላት ይገባቸዋል ብሎ ካስቀመጣቸው ነጥቦች ውስጥ ታክስ ከፋዩ ያቀረበው የራስ ታክስ ሥሌት ማስታወቂያ እንዲሻሻልለት በሚያቀርበው ማመልከቻ ላይ የታክስ ሥሌቱን ለማሻሻል ምክንያት የሆኑትን ጉዳዮች በዝርዝር መጥቀስ አለበት ይላል፡፡ ታክስ ከፋዩ ያቀረበው የታክስ ሥሌት ማሻሻያ ጥያቄ ማመልከቻው ከቀረበበት ቀን በፊት ባሉ አምስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ በነበሩ የራስ ታክስ ሥሌቶች ላይ ለውጥ የሚያመጣ ከሆነ የሁሉም ዘመናት የታክስ ሥሌት ማሻሻያ በአንድነት ሊያቀርብ የሚችልበት ዕድል የሚሰጥ መመርያ ነው፡፡
በራስ ታክስ ሥሌት ላይ ማሻሻያ እንዲደረግ የሚቀርበው ማመልከቻ ለውጡን የሚያሳይ ሆኖ ይዘቱ የታክስ ሥሌት ማሻሻያ እንዲደረግ የተጠየቀበትን የታክስ ጊዜና ዓይነት፣ ማሻሻያ የሚረግበትን ጉዳይና ምክንያቱን፣ ማሻሻያ እንዲደረግበት የተጠየቀው ጉዳይ የሚያስከትለው የገንዘብ ወይም ሌላ ለውጥ፣ በሚሻሻለው የታክስ ሥሌት የተገለጸው የታክስ መጠን ወይም ወደፊት የሚሸጋገር ኪሳራ ወይም በብልጫ የተከፈለ የግብዓት መጠን የሚገልጽ መሆን አለበት፡፡
ከራስ ታክስ ሥሌት ማስታወቂያ እንዲሻሻል የሚቀርበው ማመልከቻ ከማሻሻያ ምክንያቶቹ ጋር አስፈላጊ ከሆኑ ሰነዶች ጋር ተያይዞ መቅረብ እንደሚኖርበትና ማመልከቻው የሚቀርብበት ጊዜም ታክስ ከፋዩ የራስ የታክስ ሥሌት እንዲሻሻል ለሚኒስቴሩ የሚያቀርበው ማመልከቻ የራስ የታክስ ሥሌቱን ማስታወቂያ ካቀረበበት ቀን ጀምሮ ባሉት አምስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ እንዲሆን ይጠይቃል፡፡
የገቢዎች ሚኒስቴር በዚህ መመርያ መሠረት የራስ ታክስ ሥሌት ማሻሻያ እንዲደረግበት የሚቀርብለትን ማመልከቻ ተቀብሎ ከተቀበለበት ቀን ጀምሮ ባሉት 120 ቀናት ውስጥ መርምሮ ውሳኔ የሚሰጥ መሆኑንም በመመርያው ተደንግጓል፡፡
ሚኒስቴሩ የቀረበለትን የራስ ታክስ ሥሌት ማሻሻያ ጥያቄ ተቀብሎ ማሻሻያው እንዲደረግ ወይም ማመልከቻውን ውድቅ በማድረግ ሊወስን እንደሚችልም አመልክቷል፡፡
የውሳኔው አሰጣጥም ሚኒስቴሩ፣ በቀረበለት ማመልከቻ መሠረት የራስ ታክስ ሥሌት ማሻሻያ እንዲደረግ የፈቀደ እንደሆነ የታክስ ሥሌቱን በማሻሻል ለታክስ ከፋዩ የተሻሻለውን የታክስ ሥሌት ማስታወቂያ በአዋጁ በተወሰነው ጊዜ ውስጥ ይልክለታል፡፡ የቀረበውን ራስ ታክስ ሥሌት ማሻሻያ ጥያቄ ያልተቀበለው እንደሆነ ያልተቀበለበትን ምክንያት በመግለጽ በጽሑፍ ለታክስ ከፋዩ ያሳውቀዋል፡፡
የተሻሻለ የራስ ታክስ ሥሌት ማስታወቂያ በድጋሚ ለማሻሻል ሲፈለግም፣ ሚኒስቴሩ ታክስ ከፋዩ ባቀረበው ጥያቄ መሠረት የራስ ታክስ ሥሌት እንዲሻሻል ወስኖ የተሻሻለውን የራስ ታክስ ሥሌት ማስታወቂያ ለታክስ ከፋዩ ከሰጠ በኋላ ለታክስ ከፋዩ የተሻሻለ የታክስ ሥሌት ማስታወቂያ ከመስጠት እንደሚያግደውም ይጠቁማል፡፡
የታክስ ሥሌት ማሻሻያ የሚከለልባቸው ሁኔታዎች ሚኒስቴሩ የመጀመርያ የታክስ ሥሌት ማስታወቂያ ከሰጠ በኋላ ወይም ኦዲት በመደረግ ሒደት ላይ የሚገኝ ከሆነ፣ ታክስ ከፋዩ የሚቀርበው የራስ ታክስ ሥሌት ማሻሻያ ጥያቄ ተቀባይነት እንደማይኖረው የሚጠቅስ ነው፡፡ ከዚህም ሌላ አንድ ጊዜ የታክስ ሥሌት ማሻሻያ እንዲደረግ ጥያቄ የቀረበበት የራስ ታክስ ሥሌት በድጋሚ ማሻሻያ እንዲደረግበት ጥያቄ ሊቀርብበት እንደማችልም መመርያው ያመለክታል፡፡