Sunday, April 14, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የግብርና ኢንቨስተሮች ላጋጠሙዋቸው ችግሮች ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምላሽ እንዲሰጡ ጠየቁ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ የግብርና ኢንቨስትመንት አልሚዎች ማኅበራት በእርሻ ኢንቨስትመንት እያጋጠሙ ያሉ ችግሮች ዘላቂ መፍትሔ እንዲያገኙ የሚጠይቅ ደብዳቤ፣ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ላኩ፡፡ ከቀናት በፊት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የተላከው ደብዳቤ፣ በኢትዮጵያ የእርሻ ኢንቨስትመንት የሚያጋጥሙ ዋና ችግሮች ዝርዝር ማብራሪያና የመፍትሔ አቅጣጫ የያዘ ነው፡፡

 

አልሚዎቹ ሰላምና ፀጥታ ባለመኖሩ እያጋጠሙዋቸው ያሉ ዘርፈ ብዙ ችግሮች፣ የመልካም አስተዳደር ተግዳሮቶች፣ የፖሊሲ መለዋወጥ፣ እንዲሁም የድጋፍ ማዕቀፎች በአግባቡ ተግባራዊ አለመሆናቸው የሚያጋጥሟቸው ችግሮች እንደሆኑ በደብዳቤው ዘርዝረዋል፡፡

 

መስኩን ስኬታማ እንዲያደርጉ የተዘጋጁ የድጋፍ ማዕቀፎች በአግባቡ ተግባራዊ አለመደረጋቸውን፣ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የብድር ፖሊሲ ተለዋዋጭነት፣ ዘርፉን የማይመጥን ከፍተኛ ወለድ፣ ኃላፊነት የጎደለውና አድሏዊ አሠራር እንዳለ የኢንቨስተሮቹ ደብዳቤ ያትታል፡፡

አልሚዎች ላቀረቡት መሬት የሚመጥን በቂ የፋይናንስ አቅርቦት ማግኘት ላይ ችግር መኖሩ፣ የእርሻ መሬት ከተረከቡ በኋላ ብድር የሚከፈልበት በቂ የዕፎይታ ጊዜ አለመኖር፣ በተፈጥሮና በፀጥታ ችግር ምክንያት ለሚፈጠሩ የምርትና የንብረት ውድመቶች የኢንሹራንስ ሽፋን አለመኖር፣ ግብርናውን በቴክኖሎጂ ለማዘመን የሚደረግ ድጋፍ አለመኖር፣ የገበያ ትስስር አለመኖር፣ የምርጥ ዘርና የኬሚካል አቅርቦት አለመኖርና የድጋፍ ማዕቀፎች በአግባቡ ተግባራዊ አልሆኑም የሚሉት ከተነሱት ነጥቦች መካከል ናቸው፡፡

ከፀጥታ ችግር ጋር በተያያዘም ሰፋፊ የእርሻ ኢንቨስትመንቶች እያጋጠሟቸው የሚገኙ ውስብስብ ችግሮችን በደብዳቤው ዘርዝረዋል፡፡ በጋምቤላና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች በቅርቡ ንብረታቸው የተዘረፈባቸው ኢንቨስተሮች መኖራቸውን፣ ከአጎራባች አገሮች ድንበር አቋርጠው የሚገቡ ቡድኖች በእርሻቸው ላይ ጉዳት እንደሚያደርሱ፣ በተደጋጋሚ ጊዜ መንገድ ስለሚዘጋ ምርትና ሠራተኞችን እንደ ልብ ማንቀሳቀስ ችግር መሆኑን፣ እንዲሁም በአርሲና በባሌ አካባቢዎች በፀጥታ ችግር ምክንያት ከስምንት ሺሕ ሔክታር በላይ የእርሻ መሬቶች እንደማይለሙ፣ በከፊል ለደረሰባቸው የንብረት መቃጠልና ዘረፋ ካሳ ሳይከፈል መዘግየቱን ኢንቨስተሮቹ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በላኩት ደብዳቤ አስታውቀዋል፡፡

አልሚዎች ወደ ሥራ ከገቡ በኋላ የፖሊሲና የመመርያ መለዋወጥ፣ ፍትሐዊ ያልሆነ የመሬት ሊዝ፣ ኃላፊነት በጎደለው መንገድ አልሚዎችን በጅምላ በመፈረጅ በኢንቨስትመንት ላይ ጉዳት ማድረስ፣ በአገር አቀፍ ደረጃ ለሁለት ዓመታት ብድር እንዲቆም መደረጉ ኢንቨስተሮቹን እየጎዱ ካሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ተብለው በአቤቱታው ከሰፈሩ ጉዳዮች መካከል ተጠቃሽ ናቸው፡፡

ራሳቸው ባልፈጠሩት ምክንያት የሊዝ ውል ማሻሻያና ብድር የሚፈልጉ አፋጣኝ ምላሽ እንዲያገኙ፣ በዕውቀት ላይ የተመሠረተ በአንድ ማዕከል የሚመራ አካል እንዲቋቋም፣ የተዘጋጁ የድጋፍ ማዕቀፎች፣ ፋይናንስ፣ ፀጥታ፣ ገበያና የግብዓት አቅርቦት በበቂ መጠን እንዲኖሩ፣ በኃላፊነት መጓደል ምክንያት ለሚደርሱ ኪሳራዎች የሚመለከታቸው ሁሉ የጥቅምና የኪሳራ ተጋሪ የሚሆኑበት አሠራር እንዲኖር፣ በሚያጋጥሙ አደጋዎች ለሚደርሱ ጉዳቶች ካሳ መክፈልና ልዩ የማበረታቻ ድጋፎች እንዲኖሩ የሚያሳስቡ ሐሳቦችን በደብዳቤያቸው አካተዋል፡፡

የደቡብ ሳግላ ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ሥራ አስኪያጅ አቶ ደመወዝ ካሳሁን፣ አልሚዎቹ በተለያዩ ጊዜያት ለሚመለከታቸው አካላት ደብዳቤ ማስገባታቸውን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ሥልጣን ላይ ከነበሩበት ጊዜ ጀምሮ ደብዳቤ ማስገባታቸውን፣ ከዚህኛው ጋር ለሦስተኛ ጊዜ ለጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ መላካቸውንና እስካሁን ግን ምላሽ አለመገኘቱን አስረድተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች