Saturday, December 2, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

የፖለቲካ ፓርቲዎች ከቅጥፈት ፖለቲካ ተላቀቁ!

ግማሽ ክፍለ ዘመን ያህል እያስቆጠረ ያለው የፖለቲካ ፓርቲዎች ጉዞ በአመዛኙ፣ ከዴሞክራሲያዊነት ጋር የተጣላ እንደሆነ ብዙዎችን ያስማማል፡፡ የኮሙዩኒስት ርዕዮተ ዓለም እንከተላለን ብለው እርስ በርስ ከተፋጁት የዘመነ ቀይ-ነጭ ሽብር የፖለቲካ ፓርቲዎች ጀምሮ፣ የብዙዎቹ መሠረታዊ ችግር የዴሞክራሲን መሠረታዊ መርሆዎች ጠንቅቆ አለመረዳት ነው፡፡ እንዳለመታደል ሆኖ እንጂ የፖለቲካ ፓርቲዎች እኮ የፖሊሲ አማራጮች ማመንጫ ናቸው፡፡ የሕዝብ አስተያየትና ፍላጎት የሚሰበሰብባቸውና አገር የሚመሩ ሰዎች የሚገኙባቸው ተቋማት ናቸው፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተለያዩ ሐሳቦች በነፃነት የሚንሸራሸሩባቸው ነፃ መድረኮችም ናቸው፡፡ የተለያዩ ዓላማዎችን የሚያራምዱ ግለሰቦችም ሆኑ ስብስቦች በነፃነት የሚደራጁባቸው ናቸው፡፡ ግልጽነት፣ ተጠያቂነትና ኃላፊነት የሚባሉት ጽንሰ ሐሳቦች በስፋት የሚስተጋቡባቸውም ናቸው፡፡ በውስጠ ዴሞክራሲ የበለፀጉ ስለሆኑም የተለያዩ ሐሳቦች ይስተናገዱባቸዋል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች በንድፈ ሐሳብም ሆነ በተግባር አንድ ለመሆን ከፍተኛ ፍጭት ተደርጎ፣ አሸናፊው የበላይ የሚሆንባቸው ጠንካራና በዲሲፕሊን የተገሩ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች በዚህ ዓይነቱ ቁመና ላይ ለመገኘት ዝግጁ ናቸው? ዘመኑን ከማይመጥን የቅጥፈት ፖለቲካ በመላቀቅ አገር ለመምራት ብቃት አላቸው? ሌሎችም ጥያቄዎች መነሳት አለባቸው፡፡

 

በኢትዮጵያ ከ100 በላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች በመኖራቸው የብዙዎች መነጋገሪያ ሆነዋል፡፡ ይህ ቁጥር በቅርቡ በተጀመረው ቢጤ ለቢጤ የመሰባሰብ ሒደት በተወሰነ ደረጃ ሊቀንስ ይችላል ተብሎ ይታሰባል፡፡ እያለ እያለ ደግሞ ጥቂት ጠንካራ የፖለቲካ ፓርቲዎች ይኖራሉ ተብሎም ተስፋ አለ፡፡ ምናልባት ይህ ተስፋ ከተሳካ ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያዊያን ብሩህ ጊዜ ይመጣ ይሆናል፡፡ አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ግን የፖለቲካ ፓርቲዎች ከምንም ነገር በፊት ዴሞክራሲን በውስጣቸው መለማመድ አለባቸው፡፡ ዴሞክራሲን ሳይኖሩት ዴሞክራት ነኝ ብሎ መደስኮር ፋይዳ ቢስ መሆኑ በተደጋጋሚ ታይቷል፡፡ ‹ለምንወደውና ለሚወደን ሕዝብ› እየተባለ በሕዝብ ስም መነገድ በዚህ ዘመን አያዋጣም፡፡ ብዙዎቹ የፖለቲካ ፓርቲዎች የመሥራቾቻቸው ወይ የአደራጆቻቸው የግል ንብረት መሆናቸው ፀሐይ የሞቀው ሀቅ ነው፡፡ ከዚህ ዓይነቱ ስስታምነት ውስጥ በመውጣት ፓርቲዎችን የአባላት ማድረግ ይቅደም፡፡ ስያሜዎቻቸውም ሆነ ይዘታቸው የኢትዮጵያን ተጨባጭ ሁኔታ ያማከለ ይሁን፡፡ በስመ ርዕዮተ ዓለም አለኝ አሠላለፍን በማሳመር ‹ሶሻል ዴሞክራት፣ ሊበራል፣ አብዮታዊ ዴሞክራት…› እያሉ አገራዊ ሁኔታን መግፋት ዓላማ ቢስ ያደርጋል፡፡ ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ጉዞ ማድረግ የሚቻለው አገራዊ ባህርይን ተላብሶ ዴሞክራሲያዊነትን በመደረብ እንጂ፣ ጊዜውን በማይመጥን ቅጥፈት አይደለም፡፡

የዴሞክራሲ መርሆዎችን ተረድቶ ለተግባራዊነታቸው ቁርጠኛ መሆን የሚችል የፖለቲካ ፓርቲ የአባላቱን ንቃተ ህሊና ያዳብራል፡፡ ወቅታዊ ሁኔታዎችን በመተንተን ለቀጣዩ ዕርምጃው ራሱን ያዘጋጃል፡፡ በአባላቱና በአመራሩ መካከል የሐሳብና የተግባር አንድነት እንዲኖር ሁሌም ለውይይት በሩ ክፍት ነው፡፡ ከሐሜት፣ ከአሉባልታና ከሸፍጥ የጠራ ሥርዓት በመዘርጋት ግልጽነትንና ተጠያቂነትን ያዳብራል፡፡ በተለያዩ መስኮች የፖሊሲ ሐሳቦችን ለማመንጨት የሚያስችሉ ባለሙያዎችንና ተመራማሪዎችን ከጎኑ ያሠልፋል፡፡ የሚያቀርባቸው የፖሊሲ አማራጮች የመራጮችን ልብ የሚያማልሉ እንዲሆኑ ከፍተኛ ጥረት ያደርጋል፡፡ በአጠቃላይ ከልማዳዊ ድርጊቶች ተላቆ ለዘመናዊ አስተሳሰቦችና ተግባራዊ ዕርምጃዎች ቅድሚያ ይሰጣል፡፡ አባላቱም በየደረሱበት ሥፍራ ተጨባጭ፣ አሳማኝና ተቀባይነት ያላቸው የደረጁ ሐሳቦች ከማንፀባረቅ አልፈው በእንቅስቃሴያቸው ጭምር አርዓያ መሆን አለባቸው፡፡ በጥራዝ ነጠቅ ዕውቀት እየተመሩ ተፎካካሪን ጠላት አድርገው የሚስሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለኢትዮጵያ በፍፁም አያስፈልጉም፡፡ ዕውቀት አልባ ፖለቲከኝነትና ራዳር የሌለው መርከብ አንድ ናቸው፡፡ በተለመደው የሸፍጥና የቅጥፈት መንገድ ላይ መመላለስ ተቀባይነትን ያሳጣል፡፡ ተቀባይነትን ያጣ የፖለቲካ ፓርቲ ደግሞ እንኳን ዓላማውን ሊያሳካ ህልውናውም ያጠራጥራል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በዜግነትና በብሔር ፖለቲካ ላይ የተለያዩ አስተያየቶች እየተደመጡ ነው፡፡ እነዚህ ሁለት አስተሳሰቦች የራሳቸው ባለቤቶች አሏቸው፡፡ ነገር ግን ሁለቱን ልዩነቶች ጎን ለጎን ማስኬድ እየተቻለ፣ የተቃርኖ መፈልፈያ ማድረግ ደካማነት ነው፡፡ የዜግነትና የብሔር ፖለቲካ የተለያዩ አደረጃጀቶችንና ርዕዮተ ዓለሞችን ይጠይቃሉ ወይ? በዴሞክራሲያዊ ማዕቀፍ ውስጥ የዜግነት ወይም የብሔር ችግሮችን መፍታት ያቅታል ወይ? ሁለቱን ተፎካካሪ ጉዳዮች በተቃርኖ በማቧደን ለምን መሠረታዊ ቅራኔ ይፈጠራል? በዴሞክራሲያዊ ማዕቀፍ ውስጥ ሁለቱም ተፎካካሪ ሐሳቦች በነፃነት መስተናገድ ይችላሉ፡፡ ምክንያቱም ሁለቱም በየጎራቸው ደጋፊዎች ስላሏቸው፡፡ ወሳኙ መራጩ ሕዝብ ስለሆነ ፖለቲከኞች በሐሳብ ለመብለጥ ይዘጋጁ፡፡ አንዱን አጥፍቶ ሌላውን ማልማት አይቻልም፡፡ የኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታም አንዱን ጥሎ ሌላውን አንጠልጥሎ ሳይሆን፣ ለሁለቱም አስተሳሰቦች ሰፋ ያለ ምኅዳር መክፈትን ያስችላል፡፡ የተለያዩ አስተሳሰቦች በነፃነት የሚስተናገዱበት ሥርዓት ዴሞክራሲ ነው ከተባለ፣ የሁሉም ችግር መፍትሔ ዴሞክራሲ ብቻ ነው፡፡ ለዚህም ነው ‹ዓይንህን አልይ› ከሚል የሸፍጥ ፖለቲካ በመላቀቅ ዴሞክራሲን መላበስ የሚያስፈልገው፡፡ ዴሞክራሲን ሳይኖሩት ስያሜ ላይ እንደ ሰሌዳ ለጥፎ መንጎማለል ፋይዳ የለውም፡፡ ለኢትዮጵያም አያስፈልግም፡፡

ኢትዮጵያ የጠንካራ ነገር ግን የጥቂት የፖለቲካ ፓርቲዎች አገር እንድትሆን በርትቶ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግና አጋሮቹ በአንድነት አንድ ወጥ ትልቅ አገራዊ ፓርቲ ለመመሥረት በዝግጅት ላይ ናቸው፡፡ ሰሞኑን ሰባት የፖለቲካ ፓርቲዎች አንድ ትልቅ ፓርቲ መሥርተዋል፡፡ በአምስት ፓርቲዎች ውህደት ሌላ ፓርቲ ለመመሥረት ዝግጅቱ ተጠናቋል፡፡ ሌሎችም በዚህ መሠረት ጠንካራ ፓርቲዎች ያደራጃሉ ተብሎ ይታሰባል፡፡ እንዲህ እያለ ወደፊት ሁለት ወይም ሦስት የፖለቲካ ፓርቲዎች ብቻ በአገሪቱ ፖለቲካ ምኅዳር ውስጥ ቢኖሩ፣ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ከኋላቀርነትና ከአዝጋሚነት ይላቀቃል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከአኩራፊዎች መሰባሰቢያነትና ከግለሰቦች የንግድ ድርጅትነት ይላቀቃሉ፡፡ ቢጤ ለቢጤ እየተፈላለጉ በጥንካሬ ሲደራጁ፣ ለዓመታት የዘለቀው የቅጥፈት ፖለቲካ ይከስማል፡፡ በስመ ፖለቲከኝነት የሚያጭበረብሩ ደግሞ እንደ በፊቱ የሚያላግጡበትና የሚፈነጩበት ምኅዳር አይኖርም፡፡ የራሳቸው ዓላማና ግብ የሌላቸው ለማሳሳቻነት የሚፈለጉ ቡድኖች ሥፍራ አያገኙም፡፡ ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት ዓላማና ግብ ይዘው በጥንካሬ የተደራጁ ጥቂት የፖለቲካ ፓርቲዎች እንጂ፣ ምርጫ በደረሰ ቁጥር እንደ ግሪሳ ለአጃቢነት ብቅ ብለው የሚበተኑ ተላላኪዎችን አይደለም፡፡ እነዚህ የቅጥፈት ፖለቲካ ውጤቶች ስለሆኑ አያስፈልጉም፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከቅጥፈት ፖለቲካ መላቀቅ አለባቸው!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...

ሀብቱንና ትርፉን እያሳደገ የቀጠለው አዋሽ ባንክ

አዋሽ ባንክ በአዲስ አበባ ከተማ አዲስ ዋና መሥሪያ ቤት...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ድጋፍና ተቃውሞ እኩል ይስተናገዱ!

ኢትዮጵያ ውስጥ ለረዥም ዓመታት ለመንግሥት ከሚቀርቡ ጥያቄዎች መካከል አንዱ የመብት መከበር ጉዳይ ነው፡፡ ዜጎች ተፈጥሯዊም ሆኑ ሕጋዊ መብቶቻቸው እንዲከበሩላቸው ለመንግሥት ጥያቄ ሲያቀርቡ፣ ጥያቄው የቀረበለት...

ፖለቲካዊ ችግሮች ፖለቲካዊ መፍትሔ ይፈለግላቸው!

መንግሥት ከኦነግ ሸኔ ጋር በታንዛኒያ ዳሬሰላም ከተማ ሲያካሂድ የነበረው ንግግር ያለ ውጤት መጠናቀቁን ካስታወቀ በኋላ፣ በኦሮሚያ ክልልም ሆነ በሌሎች ቦታዎች ሰላም ለማስፈን የነበረው ተስፋ...

ኢትዮጵያን ከግጭት ቀጣናነት ማላቀቅ የግድ ነው!

ፍሬ አልባ ፖለቲካዊ ልዩነቶች ወደ ግጭት እያመሩ ለአገርና ለሕዝብ የማያባራ መከራ ሲያቀባብሉ፣ ከትናንት ስህተቶች ለመማር ፈቃደኛ ያልሆኑ ፖለቲከኞችና ተከታዮቻቸው በእሳት ላይ ቤንዚን እያርከፈከፉ ጠማማ...