Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየግዥ ሥርዓቱ የሚፈትናቸው የመድኃኒትና ሕክምና መሣሪያዎች

የግዥ ሥርዓቱ የሚፈትናቸው የመድኃኒትና ሕክምና መሣሪያዎች

ቀን:

ለተለያዩ የመንግሥት ሕክምና ተቋማት መድኃኒቶችና የሕክምና መሣሪያዎችን በወቅቱ ለማቅረብ ቢመከርም በተለያዩ ምክንያቶች አቅርቦቱ በቂ አይደለም፡፡ ለዚህም ከግዥው ሥርዓት ጋር የተያያዙ ችግሮች በቀደምትነት ይነሳሉ፡፡ ተቆጣጣሪው ባለሥልጣን መድኃኒቶችን ለመመዝገብ ሰፊ ጊዜ መውሰዱም መድኃኒት እንደ ልብ እንዳይገኝ ማድረጉ ይነገራል፡፡  

 

የጤና ሚኒስትር አሚር አማን (ዶ/ር) እንደተናገሩት፣ ከግዥ ሥርዓት ጋር ላለው ችግር ለመንግሥት ሕክምና ተቋማት መድኃኒትና የሕክምና መሣሪያ እየገዛ የሚያቀርበው አንድ መንግሥታዊ ኤጀንሲ ብቻ መሆኑ የራሱን አሉታዊ ተፅዕኖ ፈጥሯል፡፡ ኤጀንሲው ግዥውን የሚያካሂደው እንደ ማንኛውም ሸቀጥ ለእያንዳንዱ ጥያቄ ጨረታ እያወጣ፣ በየዓመቱም ቢያንስ 170 ጨረታዎችን የሚያወጣ መሆኑ ችግር ፈጥሯል፡፡

ጨረታውም በተጠየቀ ጊዜ የሚወጣና የሚጠየቀው አነስተኛ መሆኑ፣ አንድ ጨረታ እስከሚወጣ፣ እስከሚጠናቀቅና እስከሚመዘገብ ድረስ ከስድስት እስከ 18 ወራት መፍጀቱ መድኃኒቱ እስካልተመዘገበ ድረስ ኤጀንሲው ማቅረብ አለመቻሉ በአገር ውስጥ የመድኃኒት እጥረት እንዲከሰት ያደርጋልም ብለዋል፡፡

ችግሩን ከግምት በማስገባት በመድኃኒትና የሕክምና መሣሪያዎች ግዥ አቅርቦት ላይ አንዳንድ የማሻሻያ ዕርምጃዎች እንደተወሰዱ፣ ከተወሰዱትም ዕርምጃዎች መካከል አንደኛው መንግሥትን በማስፈቀድ የሕክምና መሣሪያዎች ግዥና አቅርቦት ላይ ያተኮረ የማዕቀፍ ግዥ ዘንድሮ መጀመሩ እንደሚገኝበት ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡   

በማዕቀፍ ግዥው መሠረት አምስት የአውሮፓና የአሜሪካ ታዋቂ የላቦራቶሪ ማሽን አምራች ፋብሪካዎች ተጋብዘው በሦስት ማለትም ሲቢሲ፣ ኬሜስትሪና ግሎኬሜትሪ በተባሉ የሕክምና ማሽኖች አቅርቦት ተከላና ጥገና ላይ ስምምነት ተደርግል፡፡

በስምምነቱ መሠረት ፋብሪካዎቹ ለ500 ጤና ተቋማት የሚውሉና ከፍ ብለው የተጠቀሱትን ማሽኖች በነፃ እንደሚያቀርቡ፣ እንደሚተክሉ፣ እንደሚጠግኑ ወይም በአዲስ እንዲተኩ አለበለዚያ መንግሥት ካስጠገነ ካሳ እንደሚከፍሉ ከስምምነት ተደርስል፡፡

ሚኒስቴሩ ወይም መንግሥት ሪኤጀንቶችን ለሦስት ዓመት ከፋብሪካዎቹ እንደሚገዛ በስምምነቱ ላይ የተጠቀሰ ሲሆን፣ መሣሪያዎቹም በ50 ጤና ተቋማት ውስጥ ተተክለዋል፡፡ በቀጣይም በ450 ጤና ተቋማት ውስጥ ይተካላል፡፡ የተተከሉት መሣሪያዎች ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምሩ ዶ/ር አሚር አሳውቀዋል፡፡  

እንደ ሚኒስትሩ ማብራሪያ ይህ ዓይነቱ የሕክምና መሣሪያዎች አቅርቦት ወጪ ቆጣቢ ከመሆኑም ባሻገር፣ በብዙ ሚሊዮን ብር ይገዙ የነበሩ ማሽኖችን በነፃ ለማግኘት አስችሏል፡፡ ሪኤጀንቶችንም በብዛት መግዛት አስችሏል፡፡ በአጠቃላይ ለግዥና ለጥገና ይውል የነበረው ወጪ ቀንሷል፡፡

የተጠቀሱትን የሕክምና መሣሪያዎች ቀደም ባሉት ዓመታት በጨረታ እየተገዙ ወደ አገር ውስጥ እንደሚገቡ፣ ለእያንዳንዱም ሪኤጀንት እንደሚገዛ፣ አንዳንዴ ደግሞ የሪኤጀንት እጥረት እንደሚያጋጥም፣ ማሽኖቹም ዘወትር እንደሚበላሹ ብልሽቱንም ለመጠገን የመለዋወጫ ዕቃ መግዛት ግድ እንደሆነ፣ በዚህም የተነሳ ከሚያገለግሉበት ይልቅ በብልሽት፣ በመለዋወጫና በሪኤጀንት እጥረት ያለ ሥራ የሚቆሙበት ጊዜ ይበዛ እንደነበር ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡

በመድኃኒት አቅርቦት በኩል የገጠሙ ችግሮችን ለመፍታት እንደ ብቻኛ አማራጭ ተደርጎ የተወሰደው አገሪቱ ከሚያስፈልጋት መድኃኒቶች መካከል 80 ከመቶ ያህሉን በዓለም ታዋቂ ከሆኑ የመድኃኒት አምራቾች ለማግኘት የሚያስችል የኮንትራት ውል መፈረሙን ሚኒስትሩ አብስረዋል፡፡

በዚህም መሠረት አገሪቷ የሚያስፈልጋትን መድኃኒቶች ጨረታ ሳታወጣ ለሦስት ዓመታት ያህል ከአምራቾች በተጠየቁ ቁጥር እንደሚያቀርቡ ዶ/ር አሚር ተናግረዋል፡፡  

መድኃኒቶችን ለማስገባት ከስድስት ወራትና ግፋ ቢል ደግሞ ከአንድ ዓመት በላይ የሚፈጀውን መጓተት ለማስቀረት የምግብ፣ መድኃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን አወቃቀሩን በመቀየር በምግብና መድኃኒት ላይ ብቻ ትኩረት አድርጎ እንዲሠራ፣ ለዚህም ዕውን መሆን በቴክኖሎጂና በሪፎርም እንዲታገዝ ተደርጓል፡፡ ስያሜውም የምግብ መድኃኒት አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን እንዲባል መደረጉን ሚኒስትሩ ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

ቀደም ባሉት ዓመታት አንድ መድኃኒት ለመመዝገብ በአማካይ ከስድስት ወርና ከዚያም በላይ ይፈጅ የነበረውን ጊዜ በአሁኑ ሰዓት በ14 ቀናት ውስጥ ማጠናቀቅ እንደተቻለና ወደፊት ደግሞ ወደ ስድስት ቀናት ለማውረድ እንደታቀደም አመልክተዋል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ በአሁኑ ሰዓት ወደ 40 የሚጠጉ የካንሰር መድኃኒቶች አገር ውስጥ ማቅረብ ተችሏል፡፡ መድኃኒቶቹ ግዥ ከሚያስፈልገው ወጪ መንግሥት 95 ከመቶ ያህሉን የደጎመ ሲሆን፣ የአንዷ መድኃኒት ዋጋም 8.5 ዶላር መሆኑን ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...