Saturday, September 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹አንድ ግቢ ውስጥ ያሉ ተቋማት የዝሆን ጠብ መጣላት ስለፈለጉ አብሮ መሥራት አቅቷቸው ፈረንጅ ሲያሳድዱ ይውላሉ›› ይርጉ ገብረ ሕይወት (ዶ/ር)፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የክሊኒካል ሰርቪስ ዳይሬክተር

አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ በስሩ አምስት ተቋማት አሉት፡፡ እነሱም ጥቁር አንበሳ ሆስፒታልና አራቱ የሕክምና፣ የነርሲንግ፣ የፋርማሲና የኅብረተሰብ ጤና ትምህርት ቤቶች ናቸው፡፡ በ1954 ዓ.ም. ግንባታው የተጀመረው ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል አገልግሎት ወደ መስጠት የገባው በ1964 ዓ.ም. አካባቢ ነበር፡፡ በሕዝብ መዋጮ የተሠራ ሲሆን፣ እስከ 1968 ዓ.ም. ድረስ የልዑል መኮንን መታሰቢያ ሆስፒታል ይባልም ነበር፡፡ ልዑል መኮንን የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሁለተኛ ልጅ ናቸው፡፡ ወደ አዳማ ሲሄዱ መንገድ ላይ ባጋጠማቸው የትራፊክ አደጋ ነበር ሕይወታቸውን ያጡት፡፡ ወደ 4.3 ሚሊዮን ብር ከሕዝብ ተዋጥቶ የተሠራው ጥቁር አንበሳ ከ1968 ዓ.ም. በኋላ አሁን የሚጠራበትን ስያሜ ያዘ፡፡ ከተቋቋመ ከስድስት ዓሠርታት በላይ ያስቆጠረው ሆስፒታሉ ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚመጡ ሕሙማንን ያስተናግዳል፡፡ ከባድ ጫና ካለባቸው የጤና ተቋማት መካከል ግንባር ቀደም ሲሆን፣ የሚሰጣቸውን የሕክምና ዓይነቶችና ያሉበትን ተግዳሮቶች በተመለከተ ዶ/ር ይርጉ ገብረሕይወትን ሻሂዳ ሁሴን አነጋግራቸዋለች፡፡

ሪፖርተር፡- ጥቁር አንበሳ ድሮና አሁን የሚሰጣቸው አገልግሎቶች ምን ይመስላሉ? እንዴትስ ያነጻጽሩታል?

ዶ/ር ይርጉ፡- ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ሲመሠረት አጠቃላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር 25 ሚሊዮን አካባቢ ነበር የሚገመተው፡፡ በዚያ ዘመን ዘመናዊ ሕክምናን የመጨረሻው አማራጭ ተደርጎ ነበር የሚታሰበው፡፡ በዛኔ የነበሩ ኢትዮጵያውያን ባህላዊ፣ ሃይማኖታዊ የሕክምና ዘዴዎችን ነበር የሚያዘወትሩት፡፡ ስለዚህም ወደ ሆስፒታሉ የሚመጡ የተገልጋዮች ቁጥር በጣም ውስን ነበር፡፡ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ስምንት ፎቅ ቢኖረውም በወቅቱ አልጋ የነበረው እስከ አምስተኛ ፎቅ ድረስ ብቻ ነበር፡፡ ያኔ ሕንፃው ከበቂ በላይ የሚባል ነበር፡፡ ከስድስተኛ እስከ ስምንተኛው ፎቅ ድረስ ያሉት ክፍሎች ባዶ ነበሩ፡፡ አሁን ያለውን ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ደግሞ ስናይ ብዙ ነገሮች መቀየራቸውን እንታዘባለን፡፡ የሕዝቡ ቁጥርም ከ100 ሚሊዮን በላይ ሆኗል፡፡ ያኔ ከነበረው አልጋ በመቶዎች የሚቆጠሩ ተጨማሪ አልጋዎች አሉት፡፡ ትርፍ የሚባል ቦታ የለውም፡፡ ከታች ከመሬት ጀምሮ እስከ ስምንተኛው ፎቅ ድረስ በአልጋ የተሞላ ነው፡፡ በሕመምተኛ የተጨናነቀ ቦታ ነው፡፡ አሁን ባለን መረጃ መሠረት ባለፈው 2010 ዓ.ም. ወደ ግማሽ ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎችን አክሟል፡፡ በየዓመቱ ወደ ሆስፒታሉ የሚመጡ ታካሚዎች ቁጥርም እያደገ ነው የመጣው፡፡ ለምሳሌ 2007 ዓ.ም. ላይ ወደ 274 ሺሕ ሰዎችን ነበር ያገለገልነው፡፡ በ2008 ዓ.ም. ደግሞ በተመላላሽ ክፍል ብቻ ወደ 309 ሺሕ ሕሙማን አይተናል፡፡ በ2010 ዓ.ም. ወደ 384 ሺሕ ተመላላሽ ሕሙማን ታይተዋል፡፡ እንግዲህ ሌሎች የድንገተኛና ተኝተው የሚታከሙ ዜጎች አሉ፡፡ የእነዚህ ድምር ነው ግማሽ ሚሊዮን የመጣው፡፡

ሪፖርተር፡- ጥቁር አንበሳን ከሌሎች የሕክምና ተቋማት ለየት የሚያደርገው ምንድነው?

ዶ/ር ይርጉ፡-       ጥቁር አንበሳን ለየት የሚያደርጉ ሁለት መሠረታዊ ነገሮች ያሉ ይመስለኛል፡፡ አንደኛው መሠረታዊ ጉዳይ የደሃ ደሃ የሆኑ ድህነታቸው በመንግሥት የተረጋገጠላቸው ሰዎች አገልግሎት የሚያገኙበት ቦታ መሆኑ ነው፡፡ 67 ከመቶ የሚደርሰው ታካሚ የደሃ ደሃ ተብሎ የተመሰከረለትና ከሚኖርበት አካባቢ የድህነት ማረጋገጫ ሠርተፊኬት ይዞ የሚመጣ ነው፡፡ ይህ በራሱ የሚፈጥረው ጫና አለ፡፡ ሁለተኛው ሆስፒታሉን ልዩ የሚያደርገው ጉዳይ በሌሎች ተቋማት የማይሰጡ የሕክምና አገልግሎቶችን መስጠቱ ነው፡፡ ለማሳያ ያህል ሁሉም ዓይነት የካንሰር ሕክምና በአብዛኛው ተሟልቶ የሚገኘው ጥቁር አንበሳ ነው፡፡ ሆስፒታሉ ከ1985 ዓ.ም. ጀምሮ የካንሰር ሕክምና አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡ በሁሉም የሕክምና ዘርፎች በውስጥ ደዌ፣ በሕፃናት፣ በማሕፀንና ፅንስ፣ በቀዶ ሕክምና እንዲሁም በሌሎች የሕክምና መስኮች ልዩ ልዩ የካንሰር ሕክምናዎች ይሰጣል፡፡ ሕክምናውን የሚሰጠው በቀዶ ሕክምና፣ በኬሞቴራፒ፣ በመድኃኒት ወይም በጨረራ ሊሆን ይችላል፡፡ በተለይ የጨረር ሕክምና አገልግሎት የሚሰጠው እዚህ ብቻ ነው፡፡ የቀዶ ሕክምና አገልግሎትን በተመለከተም ጥቁር አንበሳ በዛ ያሉ ልምድ ያላቸው በሳል ሐኪሞች አሉት፡፡ የልብ ሕክምናም በጥቁር አንበሳ ይሰጣል፡፡ አገልግሎቱን የሚሰጠው በተወሰኑ ጊዜያት ከውጭ በሚመጡ ሐኪሞች ብቻ ሳይሆን ባሉት ሐኪሞች በየዕለቱ ነው፡፡ ቀዶ ሕክምናን ጨምሮ የሕፃናት፣ የአዋቂዎች የልብ ሕክምና አገልግሎት ይሰጣል፡፡ በድንገተኛ አገልግሎትም በዓመት እስከ 40 ሺሕ ሰዎች ይታከማሉ፡፡ የአጥንት ሕክምና አገልግሎትም እየሰጠ ይገኛል፡፡ በአጥንት ሕክምና ረገድ ሰው ሠራሽ መገጣጠሚያዎችን የመትከል አገልግሎት የሚሰጥበት ተቋም ነው፡፡ እንግዲህ ጥቁር አንበሳ በአንድ በኩል የደሃ ደሃ የሚባሉ ሰዎችን የሚያክም ተቋም ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በዓይነቱ ለየት ያለ በሌሎች ተቋማት የማይሰጡ አገልግሎቶችን የሚያቀርብ ተቋም ነው፡፡ የዩኒቨርሲቲ ተቋም ስለሆነ በተጓዳኝ የሚሠራቸው ሥራዎች እንዳሉም መዘንጋት የለበትም፡፡ በአገሪቱ ባለው የሰው ኃይል ግንባታ ዘርፍ በጣም ቁልፍ ሚና ይጫወታል፡፡ በቅድመ ምርቃና ድህረ ምረቃ ወደ 6,500 የሚደርሱ ተማሪዎች አሉን፡፡ በድህረ ምረቃ የስፔሻሊቲና ሰብ ስፔሻሊቲ ትምህርት የሚማሩ ብዙ ሰዎች አሉን፡፡ ለተቋማችን ብቻ ሳይሆን በአገሪቱ ለሚገኙ ለሌሎች ተቋማትም ሰዎች እናፈራለን፡፡ ከዚህም ውጪ በምርምሩ ዘርፍ ተሳትፎ እናደርጋለን፡፡ ባለፉት አራት ዓመታት ውስጥ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምርምር በመሥራትና በማሳተም እስካሁን አንደኛ ደረጃ ላይ እንገኛለን፡፡ አገልግሎት የመስጠት፣ የማስተማርና ምርምር የማድረግ ኃላፊነታችንን እየተወጣን እንገኛለን፡፡

ሪፖርተር፡- ሆስፒታሉ የተጣለበትን ኃላፊነት ለመወጣት የሚያበቃው በቂ በጀት ያገኛል ወይ? በጀትስ የሚመደብለት ከየት ነው?

ዶ/ር ይርጉ፡- ድህነት ዜና አይሆንም፡፡ አገሪቱ ችግር አለባት፡፡ የምንኖረው በድህነት ውስጥ ነው፡፡ በድህነት ስንኖር የተለየ ሴክተር ሀብታም የተለየ ደሃ አይሆንም፡፡ ያለውን ችግር ሁላችንም የምንጋራው ነው፡፡ የጥቁር አንበሳን ችግር ከአገልግሎት ፈላጊው ቁጥር አንጻር እንመልከት ካልን ግን ፍላጎትና ግብዓት ላይ ከፍተኛ ያለመመጣጠን አለ፡፡ ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ አገልግሎት ፍለጋ ወደ ጥቁር አንበሳ የሚመጡት ታካሚዎች ቁጥር በአማካይ በየዓመቱ በ20 በመቶ እየጨመረ ነው የመጣው፡፡ ተመጣጣኝ የሆነ ግብዓት በየጊዜው ማግኘት ራሱን የቻለ ፈተና ነው፡፡ ምክንያቱም በጀት የሚተከለው በዓመት አንድ ጊዜ ነው፡፡ በአብዛኛው አይበቃም ይኼ ምንም ድብቅ ነገር የለውም፡፡ መሀል ላይ ወገባችንን እንይዛለን፡፡ አገልግሎት እንዳይቋረጥ፣ ብሶት እንዳይበዛ ለሚመለከተው የመንግሥት አካል እናመለክታለን፡፡ ለምሳሌ መጋቢት ወር ላይ ከፍተኛ የሆነ የበጀት እጥረት አጋጥሞናል፡፡ ተጨማሪ ገንዘብ ለተለያዩ የሕክምና ዘርፎች እንፈልጋለን ብለን ጠይቀናል፡፡ አሁን ባለው አካሄድ ግልጽ ነው እጥረት አለ፡፡ እጥረት ሲኖር ደግሞ ያለንን አቅም አሟጠን ተጠቅመን ጭማሪ የሚያስፈልጋቸው ቦታዎችን ለይተን ጥያቄ የምናቀርብበት አግባብ አለ፡፡ ሌላው ነገር ሕክምና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም ይጠይቃል፡፡ ሁሉም ቴክኖሎጂ ግን ከውጭ አገሮች ነው የሚገባው፡፡ ከ80 በመቶ በላይ የሚሆን መድኃኒትም ከውጭ የሚገባ ነው፡፡ ገንዘቡን ማግኘት ችግር ቢሆንም ገንዘቡ ተገኝቶም ግብዓቱን ማግኘት ሌላ ጫና ነው፡፡ ቴክኖሎጂው ከገባ በኋላም ጠብቆ ማቆየት፣ ሲበላሽ ማደስ ራሱን የቻለ ጫና አለው፡፡ ይኼ ግን የጥቁር አንበሳ ልዩ ባህሪና ችግር ነው ማለት አንችልም፡፡ የጥቁር አንበሳ ልዩ ችግር የሚሆነው ተቋሙ ከጊዜው ጋር እየተራመደ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን የመጠቀም ጉጉት ቢኖረውም በበቂ ማድረግ አለመቻሉ ነው፡፡ ከዚህ በፊት እንግዲህ ሁሉን ሕክምና በጠቅላላ ሐኪሞች እንሰጥ ነበር፡፡ ሁሉ ነገር በጠቅላላ ሐኪም መሰጠት የለበትም ስፔሻሊቲ አገልግሎት መኖር አለበት ብለን እ.ኤ.አ. በ1981 አካባቢ በግንባር ቀደምነት ሰዎችን የማሠልጠን ሥራ ጀመርን፡፡ ስፔሻሊስት ሐኪሞችን ማሠልጠንና መመደብ በራሱ የሚፈልገው ግብዓት አለ፡፡ ስፔሻሊቲ ብቻ ለምን ብለን ደግሞ ወደ ሰብ ስፔሻሊቲ አገልግሎት መሄድ አለብን ብለን እየሄድን ነው፡፡ በዚህ ረገድ ፋና ወጊ የሆኑ ሥራዎች እየሠራን ነው፡፡ ይህም በራሱ የሚጠይቀው ነገር አለ፡፡ እንደምታውቂው የእኛ አገር ላይ የተለያየ አመለካከት ያለው ማኅበረሰብ ነው ያለን፡፡ ለቀላል ሕመም በአገር ውስጥ ባለሙያ እምነት በማጣት ውጭ የሚሄድ አለ፡፡ በፅኑ ታሞ አገልግሎቱ እዚህ ባለመሰጠቱ ለምኖ ገንዘብ ሰብስቦ ውጭ ሄዶ የሚታከምም አለ፡፡ ቀጣዩ ራዕያችን ሰዎች ሕክምና ፍለጋ ወደ ውጭ እንዳይሄዱ ማድረግ ነው፡፡ የልብ ሕክምና አገልግሎት ስንጀምር ለልብ ሕክምና ውጭ ይወጡ የነበሩ ሰዎች አገልግሎቱን እዚሁ እንዲያገኙ በመፈለግ ነው፡፡ የካንሰር ሕክምና በስፋት እንዲኖር ስናደርግ ለሕክምና ለምነው፣ ተበድረው ተለክተው ውጭ የሚሄዱ ሰዎችን ማስቀረት እንችላለን፡፡ የመጀመሪያው ዜጎች በአገራቸው እንዲታከሙ እዚሁ እንዲቀሩ ማድረግ ነው፡፡ ቀጥሎ ግን ጎረቤት አገሮች እዚህ ለሕክምና እንዲመጡ ለማድረግ መሥራት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- አንዳንድ የሕክምና ተቋማት ከፍተኛ የሚባል የገንዘብ አቅም ኖሯቸው የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በተለያዩ አካባቢዎች ዕውን እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ በአገሪቱ ትልቅ ስም ያለው ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ግን በተቋሙ የሚሰጡ አገልግሎቶችን ለመስጠት እስኪቸገር ድረስ የበጀት እጥረት ያጋጥመዋል፡፡ እንዲያውም በጀት የሚሰጠው ዩኒቨርሲቲው እንደሆነ ነው የሚነገረው፡፡ ይህም የስሙን ያህል አቅም እንዳይኖረው እንዳደረገው ይነገራል፡፡ በእዚህ ላይ ምን ይላሉ?

ዶ/ር ይርጉ፡- ተቋሞች በበጀት ማዕከልነት የሚታወቁበት የአሠራር ሁኔታ አለ፡፡ ለምሳሌ የእኔ ተቋም የበጀት ማዕከል ቢሆን ቀጥታ ከፋይናንስ ሚኒስቴር ጋር ግንኙነት ይኖረዋል፡፡ ስለዚህ በጀቴን የማቀርበው ለፋይናንስ ሚኒስቴር ነው፡፡ እንደዚህ ሲሆን መንገዱ አጭር ነው፡፡ በጀት እጠይቃለሁ ለጥያቄው ማብራሪያ እሰጣለሁ፡፡ የተወሰነ ነገር አገኛለሁ፣ ስጨርስ ደግሞ እጥረት አለ ብዬ ተጨማሪ በጀት ላስፈቅድ የምችልበት አጭር መንገድ አለ፡፡ እንደ ዕድል ሆኖ ግን ለጥቁር አንበሳ መንገዱ አጭር አይደለም፡፡ እኛ ቀጥታ የበጀት ማዕከል አይደለንም፡፡ የበጀት ማዕከሉ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ነው፡፡ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሦስት መሠረታዊ ተልዕኮዎች አሉት፡፡ የመጀመርያው ማስተማር ሲሆን፣ ቀጥሎ ምርምርና የኅብረተሰብ አገልግሎት ናቸው፡፡ ስለዚህ በጀት የሚደረግለት በማስተማሩ ዘርፍ በተማሪው ቁጥር፣ ለምርምር አቅም በፈቀደ፣ ከዚያ የተረፈውን ለማኅበረሰብ አገልግሎት ያውላል፡፡ ሆስፒታሉ ያለበት ጫና እየበዛ ሲመጣ ሁኔታው ለኃላፊዎቻችንም እየተሰማቸው ስለመጣ ለማኅበረሰብ የሚባለውን ጨምረን እየወሰድን ነው፡፡ ምናልባት እኛ የበጀት ማዕከል የምንሆንበት አጋጣሚ ቢኖር የተሻለ በጀት ማግኘት እንችል ይሆናል፡፡ ዩኒቨርሲቲው የሚበጀትለት ገንዘብ መጠኑ ባነሰ ቁጥር ድርሻችን ያንሳል፡፡ በሰፋ ቁጥር ደግሞ ይሰፋል፡፡ ልዩነቱ ይኼ ነው፡፡ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ካሉት 350 የሚሆኑ ፕሮግራሞች መካከል 120 የሚሆኑት እኛ ውስጥ ነው ያሉት፡፡ ከነእጥረቱ ከነችግሩ ሕዝብ የሚያገለግል አንጋፋ ተቋም እንደሆነ መሰመር ግን አለበት፡፡

ሪፖርተር፡- የደም ግፊት መለኪያ መሣሪያዎችን ጨምሮ ሌሎች ጥቃቅን የሕክምና ግብዓቶች ሳይቀሩ እንደሚያጥሩ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ ለዚህም ጥቁር አንበሳ ወደ ነበረበት ክብሩ ይመለስ የሚሉ ሐኪሞች መፈክር ይዘው ወጥተው ነበር፡፡ እርግጥ ጥቁር አንበሳ ክብሩ ቀንሷል?

ዶ/ር ይርጉ፡- መቼም እነሱ ድሮ እንደነበረው ለማለት አፈ ታሪክ ሰምተው ካልሆነ በስተቀር አልኖሩትም፡፡ እኛ ግን ኖረነዋል፡፡ ጥቁር አንበሳ እንደነበረ አይደለም፡፡ ከነበረበት በጣም የተሻለ ተቋም ሆኗል፡፡ ከዚህ በላይ በጣም በርትተን መሥራት እንዳለብንም እናውቃለን፡፡ ጥቁር አንበሳ ወደ ድሮ ክብሩ የሚሉ ደግሞ ድሮን አያውቁም፡፡ ድሮ ማለት መቼ መሰለሽ ድሮ ጥቁር አንበሳ የቁስለኛ ሆስፒታል ነበር፡፡ በየትኛውም ጦርነት የተጎዳ ሰው የሚታከምበት ሆስፒታል ነበር፡፡ እሱ ነው የድሮ ክብሩ? እሱን ነው የሚፈልጉት? አሁን ጥቁር አንበሳ ወደ 33 ኬዝ ቲም አሉት፡፡ ድሮ የጨረር ሕክምና አልነበረም፡፡ ድሮ ካርዲያክ ሕክምና አልነበረም፡፡ ድሮ የአጥንት መገጣጠሚያ ሕክምና አልነበረም፡፡ ድሮ የሚሉት የትኛውን ነው? እጥረት አለ? አዎ እጥረት አለ፡፡ ሆስፒታል ውስጥ መሠራት ካለበት የላቦራቶሪ ቴስት ሜኑ 16 በመቶ አይኖርም፡፡ ይኼ የሚደበቅ አይደለም እውነታ ነው፡፡ መድኃኒትን ብንመለከት አቅርቦቱ ከ65 እስከ 70 በ መቶ ነው፡፡ እስከ 35 በመቶ የመድኃኒት እጥረት ያጋጥማል፡፡ መድኃኒትና ሌሎች የሕክምና ግብዓቶች የሚመጡበት ምንጭ ለሁሉም አንድ ነው፡፡ መድኃኒት የሚያሠራጨው የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅርቦት ኤጀንሲ ነው፡፡ ገንዘብ እንኳን አንሰጣቸውም እነዚህን መድኃኒቶች እንፈልጋለን ግዙልንና ከበጀታችን ውሰዱ እንላለን፡፡ ከሚሰጠን በጀት እንገዛለን በጀቱ ያልቃል ያበድሩንና እንቀጥላለን፡፡ ምክንያቱም ስላልከፈልከኝ አላቀርብም ቢለኝ እኔ አገልግሎት ነው ማቋርጠው፡፡ አገልግሎት ሳቆም ሕዝብ ነው የሚጎዳው፡፡ ስለዚህ የተገኘውን ሊሰጡን ይሞክራሉ፡፡ ተቋሙ መሠረታዊ መድኃኒቶችና ግብዓቶች ለማቅረብ ነው የተፈጠረው፡፡ የሆነ ሰውዬ የዚህ ዓይነት ካንሰር አለበት፣ እንዲህ ያለ መድኃኒት ያስፈልገዋል ቢባል ከመሠረታዊ መድኃኒት ዝርዝር ውስጥ መድኃኒቱ ከሌለ ከየትም አያገኝም፡፡ ለምሳሌ እስካሁን መንግሥት የማያቀርበውን የሉኪሚያ መድኃኒት የእኛ ሰዎች ተነጋግረው በጥናት ላይ ተመሥርተው መድኃኒት የሚያቀርቡበት ሁኔታ አለ፡፡ በጣም ውድ የሆነ መድኃኒት ከውጭ በዕርዳታ ያስገባሉ፡፡ ነገር ግን መንግሥት መድኃኒቱን አያቀርብም ከመሠረታዊ መድኃኒቶች ዝርዝር ውስጥ የለም ብለን ዝም ብንል ሰዎች ወዲያው ይሞቱብናል፡፡ ከ1,500 በላይ የደም ካንሰር ያለባቸውን ሕመምተኞች ለማቆየት በዕርዳታ መልክ ስለሚያወጣው ወጪና ስለሚያገኙት መድኃኒት ማንም አውርቶት ግን አያውቅም፡፡

ሪፖርተር፡- ወጪውን የሚችለው ጥቁር አንበሳ ነው?

ዶ/ር ይርጉ፡- ጥቁር አንበሳ አይችልም፡፡ የእኛ ሐኪሞች ከሌሎች ድርጅቶች ጋር ተነጋግረው የእያንዳንዱን በሽተኛ የሕመሙን ሁኔታ እየመዘገቡና እያስረዱ መድኃኒት ይላካል፡፡ በተቋምና ሙያተኛው ጥረት በጣም ብዙ የሚታከሙ አሉ፡፡ ጥቁር አንበሳ ለየት ያሉ ሕክምናዎች የሚሰጡበት ስለሆነ ለየት ያሉ መድኃኒቶች አቅርቦት ከፍተኛ እጥረት አለበት፡፡ እኔ ለጤና ጥበቃ ሚኒስትር እንዴት ነው የምናደርገው ብዬ ደብዳቤ ጽፌያለሁ፡፡ ለምሳሌ አሁን የተለዩ አገልግሎት ከምንላቸው ውስጥ የልብ ሕክምና አንዱ ነው፡፡ ለልብ ሕክምና የሚሆን የግብዓት አቅርቦት ከመንግሥት በኩል የለም፡፡ የመድኃኒትም ሆነ የተለያዩ ግብዓቶች አቅርቦት የለም፡፡ ለምሳሌ ፔስሜከር መንግሥት አይገዛም፣ የመድኃኒት አቅርቦት ኤጀንሲም አይገዛም፡፡ ሰዎች ግን በዕርዳታ መልክ ይሰጡናል፡፡ እንደዚህ እየተባለ ነው አገልግሎቱ እየተሰጠ ያለው፡፡ ሰዎች ያልገባቸው ነገር ወደ ረቂቅ ሕክምናዎች ስንሄድ አገልግሎትና ግብዓት በጣም ውድ እንደሚሆን ነው፡፡ ለምሳሌ የጉልበትና የዳሌ አጥንት መገጣጠሚያ መቀየር ሕክምና የሚጠብቁ ወደ 800 በሽተኞች አሉ፡፡ አንዱን መገጣጠሚያ ለመግዛት በአማካይ ከ80 ሺሕ ብር በላይ ያስፈልጋል፡፡ 800 ሰዎችን ለማከም ወደ 64 ሚሊዮን ብር ያስወጣል፡፡ አንድ የአጥንት ሕክምና ስፔሻሊስት በጣም እጥረት አለ ብሎ ቢያማርረኝ አዎ እጥረት አለ ችግር አለ ምንም ማድረግ አልችልም ነው ምለው፡፡ ምክንያቱም 64 ሚሊዮን ብር ቢኖር ብዙ መሠረታዊ የጤና አገልግሎት አቅርቦቶችን ነው ማሟላበት፡፡ እንግዲህ ሌሎች መሠረታዊ ችግሮች አሉ ላልሽው አዎ አሉ፡፡ የደም ግፊት መለኪያ መሣሪያ ይቸግረናል ለምን አይቸግረንም? የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኦዲት ኮሚቴ ሲመጣ እኮ የጣልነውን የደም ግፊት መለኪያ መሣሪያ ብዛት አሳይተናል፡፡ የእኛ አገር የጨረታ ሥርዓት ዝቅተኛ ዋጋ ካቀረበ እንዲገዛ የሚያዝ ነው፡፡ በዝቅተኛ ዋጋ ጥሩ ጥራት ያለው ዕቃ ማግኘት አይታሰብም፡፡ የሚመሳሰል ነገር ነው የሚሰጠው፡፡ የደም ግፊት መለኪየ መሣሪያ ይገዛል በወሩ ይበላሻል፡፡ በወሩ ይጣላል፡፡ መጋዘን ውስጥ የተከማቸ አለ ምንም የምንደብቀው ነገር የለም፡፡ እናመጣለን እንሰጣለን ይበላሻል፣ ይጠፋል፡፡ የመጀመርያው ነገር ጥራት ላይ ያለው ችግር ነው፡፡ ቀጥሎ ደግሞ የአያያዝ ችግር ነው፡፡ መሣሪያዎች በጥንቃቄ ስለማይያዙ በጣም ጉዳት ይደርስባቸዋል፡፡ ቴርሞ ሜትር እስኪሪቢቶ የሚያህል ነገር ነው፡፡ እዚያ ላይ እንደ መንግሥት ንብረት ቁጥር ጽፈንበት ልንቆጣጠረው አንችልም፡፡ ሰዎች ተዋውሰው በተጠያቂነት ስሜት እንዲጠቀሙ የሚደረግበት ሁኔታ አለ፡፡ ግን በጣም ከባድ ችግር አለ፡፡

ሪፖርተር፡- ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከሳምንት በፊት የሕክምና ባለሙያዎችን ባነጋገሩበት ወቅት የልብ ሕክምና ላይ ከፍተኛ ችግር እንዳለ ተነስቷል፡፡ ችግሩ ሕክምናው እንዲቆም ሊያደርሰው የሚችል የአቅም ጉዳይ መሆኑም ተነስቷል፡፡ ጉዳዩ ምን ያህል አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል ይላሉ?

ዶ/ር ይርጉ፡- የሰማችሁት ነገር እንዳለ ሆኖ ጉዳዩን ያነሳችው ዶክተር እዚህ ኖራ የምናገረውን ነገር ብትሰማ ደስ ይለኛል፡፡ የልብ ማዕከሉ እዚሁ ጥቁር አንበሳ ግቢ ውስጥ ነው ያለው፡፡ ጥቁር አንበሳም የልብ ሕክምና አገልግሎት ይሰጣል፡፡ በአንድ ተቋም ውስጥ ሁለት ትንንሽ ተቋሞች ተፈጥረዋል፡፡ እኔ ይኼንን እንደዚህ ነው የማየው፡፡ እኛ ከእስራኤል፣ ከኮሪያ፣ ከኖርዌይ ጋር ለመተባበር ምንም አይገደንም፡፡ እነዚያም እንደዚያው፡፡ እኛ ግን እዚሁ ተግባብተን ተባብረን መሥራት አንችልም፡፡ ይኼ ለእኔ በጣም የሚያሳዝን ነገር ነው፡፡ አንድ ቅጥር ግቢ ውስጥ ያሉ ተቋማት የዝሆን ጠብ መጣላት ስለፈለጉ አብሮ መሥራት አቅቷቸው ፈረንጅ ሲያሳድዱ ይውላሉ፡፡ ይኼ ነገር መቆም አለበት፡፡ ከዚህ በፊት ጉዳዩን መድረኩ ላይ ያነሳችው ሐኪም፣ የቀድሞ ጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዴኤታ ከበደ ወርቁ (ዶ/ር) እና ሌሎችም ባሉበት ይኼ ነገር ምን መሆን አለበት በሚል ቁጭ ብለን ተነጋግረናል፡፡ ተባብረን የምንፈልገውን ድጋፍ ነው መፈለግ ያለብን ወይስ ተያይተው መሥራት የማይችሉ ተቋሞች ነው መሆን ያለብን በሚለው ጉዳይ ተነጋግረን ኮሚቴ እንዲቋቋምና ያለውን ችግር እንዲያጠና ተስማምተን ነበር፡፡ አምስት ሰው ያለው ኮሚቴ አዋቅረን ሥራ ሊጀምሩ ሲሉ ኮሚቴውን አናውቅም ሌላ አጀንዳ ሊኖረው ይችላል በሚል ጭቅጭቅ ተፈጠረና እንደገና ቁጭ ብለን ተነጋግረን፡፡ ያለው ብዥታ ጠርቶ ኮሚቴውም ሥራ እንዲቀጥል ተማመን፡፡ ሰኔ ወር ላይ የእነሱ አሥረኛ ዓመት ይከበራል በዛኔ የኮሚቴው ሪፖርት እንዲወጣ ተስማምተን ነበር፡፡ መድረኩ ላይ እንደዚያ ባለ መንፈስ መነሳቱ ለእኔ ፍጹም ያልተጠበቀ ነገር ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- ሕሙማን ወደ ጥቁር አንበሳ ሪፈር ሲደረጉ የመረበሽ ስሜት ይታይባቸዋል፡፡ ሆስፒታሉን የመሞቻ ቦታ አድርጎ የማሰብም ነገር አለ፡፡ ይህንን እንዴት ያዩታል?

ዶ/ር ይርጉ፡- ጥቁር አንበሳ ጥቁር አበሳ ይባላል እኮ፡፡ እንግልት አለ፡፡ በፅኑ የታመሙ ሰዎች የሚላኩበት ነው የሚል አመለካከት አለ፣ እንግልት አልነበረም ወይ ብንል እውነት ለመናገር ሕሙማን ይንገላቱ ነበር፡፡ ሰዎች ካርድ ለማውጣት ንጋት 12 ሰዓት ላይ መጥተው፣ ካርድ አንድ ሰዓት ላይ ወጥቶ፣ እስከ 3፡30 ካርድ ተበትኖ፣ ሕክምና አራት ሰዓት ላይ እስኪጀመር ይንገላታሉ፡፡ ለሰባት ሰዓት ቀጠሮ የሚመጣው ንጋት 12 ሰዓት ላይ ነው፡፡ ውኃ አናቀርብም፣ በቂ መፀዳጃ ቤት የለም፣ ማረፊያ ቦታ የለም ብዙ እንግልት አለ፡፡ የሚያክሙት በዘመድ ነው ለሚያውቁት ቅድሚያ ይሰጣሉ የሚል አተያይም ደግሞ አለ፡፡ ስለዚህ አሉ የተባሉትን ችግሮች መቀየር አስፈላጊ በመሆኑ አዲስ አሠራር ዘረጋን፡፡ በትውውቅ ቅድሚያ ያገኛሉ የሚለው ነገር እንዳያሠጋ የካርድ አሠራሩን ኮምፒተራይዝድ አደረግነው፡፡ ሰዎች ቁጥር ነው የሚያወጡት እንጂ ስም አይሰጡም፡፡ የታካሚው መረጃም እንደ ድሮ በካርድ ሳይሆን በኮምፒውተር ስለሚያዝ አሠራሩም ቀልጣፋ ሆኗል፡፡ ሰዎች እንደ ድሮው ነገ ወይም ከነገ ወዲያ እየተባሉ አይደለም የሚቀጠሩት፡፡ በዚህ ቀን ጠዋት ወይም ከሰዓት ተብለው ነው የሚቀጠሩት፡፡ ስለዚህ እንደ ቀድሞው ቀኑን ሙሉ እዚህ አይውሉም ማለት ነው፡፡ ሌላው እኛ ጋር የሚመጣው ከባድ የሕክምና ጉዳይ ነው፡፡ ጥሩ የሕክምና አገልግሎት ባለበት አሜሪካ በጤና ተቋማት የሞት አደጋ እስከ ሁለት በመቶ ነው፡፡ እኛ ጋር ደግሞ አራት በመቶ ነው፡፡ አራት በመቶ ትንሽ ነው ለሚሉት ሳይሆን ካለው ሁኔታ አንጻር ነው መታየት ያለበት፡፡

ሪፖርተር፡- ጥቁር አንበሳ ምን ያህል ሐኪሞች አሉት?

ዶ/ር ይርጉ፡- በአጠቃላይ 3,400 ሠራተኞች አሉን፡፡ 930 ነርሶች፣ 1,100 የሚሆኑ ከጀማሪ እስከ ሰብስፔሻሊስት ሐኪሞች አሉን፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች