በተስፋዬ ጎይቴ
ከ1990ዎቹ አጋማሽ በኋላ በአገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ የመረጃ ነፃነት አዋጅን (Freedom of Information Act) የማርቀቅ የአምስት ዓመታት ያህል እንቅስቃሴ እንደተደረገ አስታውሳለሁ። እንዲህ እንዳሁኑ ወቅት ማለት ነው። አዋጁ በፓርላማ ፀድቆ ቢወጣም ትግበራው ግን በድፍረት ስላልተሄደበት፣ በርካታ ስንክሳሮች የበዙበት ሆኖ ቆይቷል። የሕጉ ይዘትም አሁን ባለው የአገራችን የለውጥ አስተሳሰብ በርካታ ክፍተቶች የታዩበት እንደሆነ ይነገራል፡፡ ይሁንና አገሪቱ ይህ ሕግ እንዲኖራት ለማድረግ በወቅቱ የተደረገውን ጥረት ማድነቅ ግን የጨዋ ደንብ ነው ብዬ አምናለሁ። ምክንያቱም የአስተሳሰብ ሚዛናዊነት ምንጊዜም ቢሆን ስንቃችን መሆን ስላለበት ነው።
መረጃ ጠይቆ የማግኘት መብት (Access to Information) በዓለም ላይ በእንጭጭ ደረጃም ቢሆን ከተጀመረ 240 ዓመታት ያህል አስቆጥሮ ነው ወደ እኛ አገር ብቅ ያለው። ነገር ግን ዕርምጃው የዘገየ ቢመስልም በመስኩ ከአያሌ የአፍሪካ አገሮች ቀዳሚ መሆናችንንም ልብ ይሏል። ሕጉ አሁን እንደገና እየተረቀቀ መሆኑን እየሰማን ነው። ታዲያ የቀድሞው ጉድለት በምንም ሁኔታ እንዳይደገም ካለፈው አዋጅ አረቃቀቅና አፀዳደቅ ሒደት ምን እንማራለን? የጋራ ድንጋጌዎችን ሳይጨምር በ29 ያህል አንቀጾች የተዋቀረው የቀድሞው አዋጅ ከመሠረቱ እንዲቀየር ያስገደዱ በይዘቱ ላይ የታዩበት የጎሉ ህፀፆች ምን ነበሩ? ለምን? በመስኩ የዳበረ ልምድ ካላቸው አገሮች ተሞክሮ ምን እንማራለን? ከአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ጋር የሚጣጣመው ዓይነት የሕግ ማዕቀፍስ የትኛው ነው? በዚህ ወቅት እነዚህንና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን ልብ ብሎ ማየቱ ከተደጋጋሚ ክፍተት ይታደገናል ብዬ አምናለሁ። ስለዚህም ነው በዚህ ጽሑፌ ጥቂት ነጥቦችን ላነሳ የተደፋፈርኩት።
ወደ ኋላ መለስ ብለን ስንቃኝ በዓለም ላይ በፋና ወጊነቱ የሚታወቀው የፕሬስ ነፃነት ሕግ (Freedom of The Press) እ.ኤ.አ. በ1766 ፀድቆ በሥራ ላይ የዋለው በስዊድን ነው። ቀጥላ ፈረንሣይ በ1789 ዓ.ም. ተመሳሳይ ድንጋጌ አውጥታለች። የሒደቱን አዝጋሚነት ልብ በሉ። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌ አንቀጽ 19 (Article 19) ተብሎ የሚታወቀው ወርቃማ ክፍል፣ ‹‹እያንዳንዱ ሰው የፈለገውን አመለካከት የመያዝና ሐሳቡን የመግለጽ መብት አለው። ይህ መብት እያንዳንዱ ሰው የፈለገውን አመለካከት ያለ ማንም ጣልቃ ገብነት የማራመድ፣ መረጃ የማግኘት፣ የመያዝና ለሌሎች በማናቸውም መንገድ የማስተላለፍ (የማሠራጨት) መብትን ያካትታ፤›› ይላል። ይህ መሠረታዊ ድንጋጌ በርካታ አገሮች ዘግይተውም ቢሆን፣ ከፕሬስ ነፃነት በማስፋት የሰዎችን በመንግሥት አካላት (Public Bodies) እጅ የሚገኙ መረጃዎች ጠይቆ የማግኘት መብት የሚያረጋግጡ ሕጎችን እንዲያወጡ ግፊት ፈጥሯል።
ለምሳሌ ስካንዲኔቪያዊቷ ፊንላንድ እ.ኤ.አ. በ1951፣ የበለፀገችቷ ልዕለ ኃያል አሜሪካ በ1966፣ ምዕራብ አውሮፓዊቷ ፈረንሣይ በ1978፣ የኮመንዌልዟ አውስትራሊያ፣ ካናዳና ኒውዚላንድ በ1982፣ የመረጃ ነፃነት ሕግ አውጥተዋል። የሚገርመው ነገር ታላቋ እንግሊዝ ግን ሕጉን ያወጣችው ከእነዚህ ሁሉ አገሮች ዘግይታ ነው። በአኅጉራችንም ደቡብ አፍሪካ ሕጉን ያወጣችው እ.ኤ.አ. በ2001 እንደሆነ ሰነዶች ያረጋግጣሉ። ዛሬ ስዊድን፣ አሜሪካ፣ እንግሊዝ፣ ከአፍሪካም ደቡብ አፍሪካን የመሳሰሉት በዚህ ሕግ ዝግጅትና አተገባበር በምሳሌነት ይነሳሉ። በተለይ ለትግበራው ቅድመ ዝግጅት ሰፊ ጊዜ ወስደው መደላድሉን አሟልተው ከመፍጠር አንፃር፣ ከእነዚህ አገሮች ልንማር የምንችላቸው ሰፋፊ ጉዳዮች ያሉ ይመስለኛል። ባለፈው የአገራችን የመረጃ ነፃነት አዋጅ አረቃቀቅ ሒደትም ከእነዚህ አገሮች የተወሰኑ ልምዶች እንደተወሰዱ መረጃዎች ይጠቁማሉ።
ዴቪድ ባኒሳር የተባሉ ዕውቅ ምሁር በአንድ ወቅት ባቀረቡት ጥናት እንዳመለከቱት ከሆነ፣ የመረጃ ነፃነት ሕግ ያላቸው የዓለም አገሮች ጥናቱ በቀረበበት ወቅት ከ50 አይበልጡም ነበር። ነገር ግን ጉዳዩ እያደር በብዙ አገሮች ፓርላማዎች መነጋገሪያ አጀንዳ እየሆነ መምጣቱ አልቀረም። ምሁሩ ከ30 በላይ የሚሆኑ ተጨማሪ አገሮች ሕጉን ለማውጣት በዝግጅት ላይ እንደነበሩና አብዛኞቹ የአውሮፓና የእስያ አገሮች ወደ ዴሞክራሲ ሽግግር ላይ ስለሆኑ፣ ንፋሱ ወደተቀሩትም አገሮች በፍጥነት እየገሰገሰ እንደሆነ ጠቁመው ነበር። ዛሬ የእኝህ ምሁር ጥናታዊ አስተያየት በዓለም ላይ በተጨባጭ እየታየ ነው።
ከዛሬ 20 ዓመታት በፊት አገሪቱን ያስተዳደሩት የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ለፓርላማቸው ከተናገሩት ዕንቁ የሆነ መልዕክት ውስጥ የሚከተለው ቃል ሁሌም በዘርፉ ሰዎች ይጠቀስላቸዋል። ‹‹የቆየው (ያረጀውና ያፈጀው) የሚስጥራዊነት ባህል ሊሰበር የሚችለው ለሕዝቡ የማወቅ መብቱ ሲከበርለት ብቻ ነው። ይህ የማወቅ መብት ደግሞ መረጃ በማግኘት ላይ የተመሠረተ ነው፤›› ብለዋል።
መረጃ ማለት በማንኛውም ዓይነት ቅርፅ የተቀናበረ ማንኛውም ሰነድ (Information Recorded in Any Form) ማለት መሆኑን ከንባባችን እንገነዘባለን። ሰነድ ማለት ደግሞ በማንኛውም አካልና በማናቸውም ጊዜ የተፈጠረ (የተዘጋጀ) መሆኑን ጽሑፎች ያመላክታሉ። ከዚህ አንፃር መረጃ በራሱ ኃይል ነው፣ አቅም ነው። የዕውቀትና የሥልጣኔ፣ የሀብት፣ የአቅምና የዕድገት ምንጭና መገለጫም ነው። አገሮች የመረጃ ሽፋናቸው መስፋት የዕድገታቸውን ግስጋሴ ብቻ ሳይሆን፣ የዴሞክራሲና የመልካም አስተዳደር የዕርምጃቸውንም መጠን ያሳየናል። ከዚህ አንፃር አገራችን የመረጃ ነፃነት ያልተከበረባት አገር ሆና መቆየቷ ሁለንተናዊ ዕድገቷ ላይ ያሳደረውን ጥብቅ የሆነ አሉታዊ ተፅዕኖ መገንዘብ አያዳግትም። የዜጎች/የሰዎች መረጃ የማግኘት መብት ሳይከበር የዴሞክራሲን ፈለግ እየተከተልኩ ወይም መልካም አስተዳደርን እያሰፈንኩ፣ የበለፀገ ሥርዓት እየገነባሁ ነው ማለት ከቶውንም የሚታሰብ አይደለም። የዚህ ጽሑፍ ዋነኛ መነሻም ይኼ ፅንሰ ሐሳብ ነው።
ከዚህም በመነሳት በአገራችን ቀደም ሲል በፀደቀው የመረጃ ነፃነት አዋጅ አረቃቀቅና የትግበራ ዝግጅት ሒደት እዚህም እዚያም ተነስተውና አከራክረው የነበሩ መሠረታዊ ጉዳዮችን በዚህ ጽሑፍ ማንሳቱ፣ ተሞክሮው አሁን ለሚዘጋጀው የሕግ ረቂቅ መጠነኛም ቢሆን አስተዋጽኦ ይኖረዋል የሚል ፅኑ እምነት አለኝ። የተነሱት አከራካሪ ጉዳዮች እጅግ በርካታ ስለነበሩ ሁሉንም ማንሳቱ ሊያስቸግር ይችላል። ለናሙና ያህል ግን በቀላሉ ሊታለፉ የማይችሉትንና የተወሰኑትን ተሞክሮዎች መጠቋቆሙ ለቀጣዩ ሥራ የሚያግዝ ይሆናል ብዬ አምናለሁ።
አዋጁ እንዴትና በማን ይረቀቅ? እነማን ቀረብ ያለ ሙያና ልምድ አላቸው? አጠቃላይ ፕሮጀክቱ እንዴት ይመራ? የየትኞቹን የዓለም አገሮች የአረቃቀቅና የትግበራ ተሞክሮ እንውሰድ? ለምን? ቡድኖችን ወደ ውጭ እንላክ ወይስ የውጭ ባለሙያዎችን ወደዚህ እናምጣ? አዋጁ ምን ይዘት ይኑረው? ምን ምን ክፍሎችና አንቀጾች ይኑሩት? የመገናኛ ብዙኃንና የመረጃ ነፃነት ሕጎች ለየብቻቸው ራሳቸውን በቻሉ አዋጆች ይውጡ ወይስ በአንድነት ይጣመሩ? አገራችን ካለችበት ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር ሚስጥራዊ መረጃዎችን የሚመለከቱ ጉዳዮች ለቀቅ ይደረጉ ወይስ ይጥበቁ? ለአገራችን ሰላምና ለሕዝባችን ደኅንነት የሚበጀው የትኛውን መንገድ ብንከተል ነው? እነዚህ ሚስጥራዊ መረጃዎች በአዋጁ ውስጥ ሰብሰብ ተደርገው ይቀመጡ ወይስ በጣም ይዘርዘሩ? የትኞቹ ጉዳዮች ደንብና መመርያ ይውጣላቸው? የመረጃ ነፃነትን የያዘውን የሕጉን ክፍል ማን ያስፈጽመው? እንደ አንዳንድ አገሮች የመረጃ ነፃነት ኮሚሽን ቢቋቋም ይሻላል ወይስ ለመስኩ ቀረብ ያለ ተልዕኮ የተሰጠው ተቋም ደርቦ ይያዘው? (ይህ እስከ መጨረሻው ያነጋገረ ጉዳይ ነበር)።
በመንግሥት አካላት እጅ የሚገኙ መረጃዎች ለሰዎች ሁሉ ክፍት ይሁኑ ወይስ ለኢትዮጵያውያን ዜጎች ብቻ? የመረጃ ክፍያ ወሰን እንዴት ይሁን? የቅሬታ ሥርዓቱ ምን ምን ደረጃዎች ይኑሩት? የተለያዩ የጊዜ ገደቦች በምን ያህል ስፋትና ጥበት ይቀመጡ? መረጃ የመስጠት ግዴታ በአስፈጻሚ አካላት ላይ ብቻ እንዲያተኩር ገደብ ይደረግ ወይስ እንደ አንዳንድ አገሮች ሕግ አውጪውንም፣ ሕግ አስከባሪውንም፣ ሕዝባዊ ተቋማትንም ቢያካትት ይሻላል? የመረጃ መስጠቱ ወይም የመረጃ ጥያቄዎችን የማስተናገዱ ሥራ በየመሥሪያ ቤቱ ከላይ እስከ ታች በማን ይሠራ? በሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች ተደርቦ ይሠራ ወይስ ሌሎች ራሳቸውን የቻሉ የመረጃ ኦፊሰሮች ይመደቡለት? ለትግበራ ዝግጅት ምን ያህል ጊዜ ይበቃል? ለዚህ ጉዳይ የየትኛውን አገር ተሞክሮ ብንወስድ ይሻላል? ቅድመ ዝግጅቱ ባይጠናቀቅ ለመጠባበቂያ ስንት ዓመት ይያዝለት? ሚስጥራዊ ሰነዶችን በደረጃ ከፋፍሎ በእርግጥም ሚስጥራዊ ናቸው ብሎ የማፅደቁ ሒደት ምን ይምሰል? የሚሉና የመሳሰሉ ነበሩ።
በአረቃቀቁ ሒደት የተነሱት ጥያቄዎች አጥጋቢ መልስ ቢያገኙም ባያገኙም፣ ከየአቅጣጫው መነሳታቸው ግን አልቀረም። የተለያዩ ኃይሎች ከቀላል እስከ ከባድ የሆኑ የልዩነት አስተሳሰቦችን አራምደዋል። ገዥው ፓርቲ የእኔ መንገድ ትክክል ነው፣ ምንም እንከን የለበትም ሲል ተፎካካሪ ፓርቲዎችና የግል ሚዲያዎችን ጨምሮ ከመንግሥት ወጣ ያሉ ኃይሎች ደግሞ አዋጁ ክልከላ (ገደብ) የበዛበት ነው፣ ዴሞክራቲክ አይደለም፣ አሳታፊ አይደለም፣ የይስሙላ ነው፣ ቢፀድቅም የውሸት ነው፣ መቼም ቢሆን ተግባራዊ አይሆንም፣ ኢሕአዴግ በኢትዮጵያ የመረጃ ነፃነት አለ በማለት ኅብረተሰቡንና የውጭ አካላትን ለማደናገርና የሥልጣን ጊዜውን ለማራዘም የሚጠቀምበት ዘዴ ነው፣ ወዘተ. በማለት በወቅቱ የማይሰነዝሩት ትችትና ወቀሳ አልነበረም። ለምሳሌ በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር የማሠልጠኛ ማዕከል አዳራሽ በተካሄደ አንድ የውይይት መድረክ ላይ የነበረው እሰጥ አገባ እስካሁን ድረስ ከሁሉም በላይ ከፊቴ ድቅን ይላል። ታዲያ የተነሱት ትችቶች ዝም ብለው ሟርት አይደሉም። እውነትም አዋጁ በምንም ዓይነት ተግባራዊ አይሆንም እንዳሉት ቃሉ ተፈጸመ።
ለማንኛውም የማርቀቁ ሒደት ሰፋ ያለ ጊዜ ወስዶ ተጠናቀቀ። እንግሊዝን የምታህል የበለፀገች የአውሮፓ አገር፣ ከአኅጉራችንም ተጠቃሽ የሆነችው ደቡብ አፍሪካ፣ ሌሎችም አገሮች ሕጉን ለማርቀቅ ዓመታት ወስዶባቸዋል። ከነበረው ንትርክና ተሞክሮው በፍፁም ለኢትዮጵያ አዲስ ከመሆኑ አንፃር በጊዜ ረገድ የአገራችን ተሞክሮ በጣም የሚያስከፋ ነበር ብዬ አልገምትም።
በዚህም ሒደት ከእየ አቅጣጫው ከቀረቡት ግብዓቶች በመነሳት ረቂቁ መጀመሪያ የነበረበት ይዘት በመጨረሻ ሲታይ፣ ከግማሽ በላይ አንቀጾች ተቀይረዋል ወይም ተሻሽለዋል። ወደ እያንዳንዱ ጉዳይ መግባት የዚህ ጽሑፍ ዓላማ አይደለም። ይሁን እንጂ ያኔ ይነሱ የነበሩት ጥያቄዎች ዛሬም መነሳታቸው አይቀሬ ነውና አርቃቂዎቹም መንግሥትም ትኩረት ሊሰጡበት ይገባል። አሁን በአዋጁ ላይ እየተደረጉ ያሉትን ለውጦች አንድ ሁለት ብሎ ቆጥሮ በተጨባጭ ማሳየት ያስፈልጋል። ያለበለዚያ ያለፈው ሁሉ አይጠቅመንም፣ ሁሉንም ነገር በአዲስ መልክ እንሥራው የሚል የወረት አባዜ እንዳይመስልብንና ለትችት እንዳያጋልጠን ብርቱ ጥንቃቄ ቢደረግ ጥሩ ነው።
ምንም እንኳን አዋጁ በርካታ ችግሮች ቢኖሩበትም፣ በወቅቱ የገዥው ፓርቲ ከፍተኛ ሹማምንትና አርቃቂዎቹ ሕጉ ዴሞክራቲክና አሳታፊ (Participatory) እንደሆነ ለማሳየት የማያደርጉት ጥረት አልነበረም። ተሸፋፍነው ቢተኙ ገላልጦ የሚያይ አምላክ አለ እንደሚባለው ሆነና ዛሬ የተለወጠ አስተሳሰብ መጥቶ ህፀፆቹ ሁሉ አንድ ሁለት ተብለው መቆጠር ጀመሩ። ነገ ከነገ ወዲያ በአዲሱ አዋጅ ላይም እንዲህ ዓይነት የጥያቄ ጋጋታ እንዳይመጣ ሰከን ብሎ ማየት ያስፈልጋል።
የማርቀቁ ሥራ ሲጀመር ጀምሮ ገዥው ፓርቲ በፕሮጀክቱ አስተባባሪነትና የሕጉ መሪ አርቃቂ (Chief Draughtsman) አድርጎ በመረጣቸው ሹማምንት ላይ በርካታ ጥያቄዎች ይነሱ ነበር። በሥራው ላይ አንዳንድ የዘርፉ ባለሙያዎች የተሳተፉ ቢሆንም፣ በአረቃቀቁ ሒደት ዙሪያ የተኮለኮሉት ከፍ ያሉ የመንግሥት ሰዎች የሚሰጧቸው ኢሕአዴጋዊ አቅጣጫዎች ለተፈጠረው አለመተማመን አንዱ መነሻ ነበር። ሌላው ጉዳይ ደግሞ ሕዝቡ በአጠቃላይ በፓርቲው ላይ ከነበረው ከፍተኛ ጥላቻ የተነሳ (በ1997 እና በ1998 የታዩት ክስተቶች ለጥላቻው በቂ ማስረጃ ናቸው) ቀድሞስ ቢሆን ከኢሕአዴግ ምን ጥሩ ነገር ይጠበቃል የሚለውም ጉዳይ እንደተለመደው ሌላው የጥርጣሬ ምንጭ ነበር። የሆነ ሆኖ በዋነኛነት የእንግሊዝ፣ የደቡብ አፍሪካና የአሜሪካ ልምዶች ተቃኝተዋል።
ቶቢ ማንዴልን የመሳሰሉና በዓለም ላይ አንቱ የተባሉ የዘርፉ ምሁራን በረቂቁ ላይ ጊዜ ወስደው አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። ሐሳባቸው ቢካተተም ባይካተትም የተለያዩ የፖለቲካ ኃይሎች፣ የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች፣ የተለያዩ ፓርቲዎችን የወከሉ የፓርላማና የካቢኔ አባላት፣ የሕግ ሙያተኞችና ሌሎችም ምሁራን ዛሬም እንደሚደረገው መድረኮች እየተዘጋጁላቸው ገንቢም ሆነ አፍራሽ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። ሥጋቶቻቸውን አንሸራሽረዋል። የአቅማቸውንና የአቋማቸውን ያህልም መንግሥትን መክረዋል።
አዋጁ እንደ ምንም ሆኖ ከፀደቀ በኋላ ወዲያውኑ የትግበራውን ዝግጅት የሚያስተባብር ባለሥልጣናትን ያካተተ አንድ ዓብይ አገር አቀፍ ግብረ ኃይል ተቋቁሞለታል። ማስፈጸሚያ ደንቦችንና መመርያዎችን በማርቀቅ፣ በተለያዩ ደረጃዎች የግንዛቤ ማስጨበጥ (የሥልጠና) ሥራዎችን በማከናወን፣ የሰው ኃይል በመመልመል፣ የአሠራር ሥርዓት በመዘርጋት፣ ወዘተ. አዋጁን እንዲያስፈጽም ሥልጣን የተሰጠውን የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋምን በሙያ የሚያግዝ አገር አቀፍ የቴክኒክ ኮሚቴም ተደራጅቷል። ይህ በማስረጃ የተደገፈ እውነት ነው። ሁሉንም ነገር መኮነን አይቻልም። የቄሳርን ለቄሳር የክርስቶስን ለክርስቶስ መስጠት ያስፈልጋል።
ኮሚቴው ከሚመለከታቸው ተቋማት የተውጣጡ ልዩ ልዩ ባለሙያዎችን ያቀፈ ነበር። በዚህ የዝግጅት ጊዜ በዓብይ ግብረ ኃይሉ ቁጥጥር ሥር ሆኖ የተወሰኑ ደንቦችና መመርያዎች በቴክኒክ ኮሚቴው ተሞካክረዋል። የማሠልጠኛ ሰነድ ተዘጋጅቶ ለየክልሎቹና ከተማ አስተዳደሮቹ የምክር ቤትና የካቢኔ አባላት (በየክልላቸው)፣ ለመንግሥትና ለግል መገናኛ ብዙኃንና ለኮሙዩኒኬሽን ኃላፊዎችና ባለሙያዎች፣ ለፌዴራል አስፈጻሚ አካላት ሥራ አስኪያጆችና ለመሳሰሉት ጉዳዩ በቅርብ ለሚመለከታቸው በአዋጁ፣ በደንቦቹና በመመርያዎቹ ይዘትና አተገባበር ላይ የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥልጠና በቴክኒክ ኮሚቴው አባላት ተሰጥቷል። ይኼ ሥራ የትግበራው ዝግጅት ወሳኝ ተግባር ተደርጎ ተወስዶ ነበር። የፌዴራልና የክልሎች ኃላፊዎች የጋራ የትግበራ መድረክም ተቋቁሞ፣ በአዲስ አበባና በድሬዳዋ ከተሞች ሁለት ዙር ጉባዔዎች ተካሂደዋል። አሁንም ቢሆን አዋጁ ከተራቀቀ በኋላ የሰው ኃይል ምልመላ፣ ምደባ፣ የሥልጠናና የአቅም ግንባታ ሥራዎች በተለየ ትኩረት ሊሠሩ እንደሚገባቸው ሊዘነጋ አይገባውም። ነጥቡም የተነሳው ለዚሁ ነው።
በአዋጁ ላይ የተቀመጠው የትግበራ ዝግጅት የሁለት ዓመታትና ለፓርላማው ቀርቦ የተፈቀደው የመጠባበቂያ (ተጨማሪ) የአንድ ዓመት ጊዜ ተጠናቀቀ። ይሁንና የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ግን በእነዚህ ሦስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ቀደም ሲል በአዋጅ ቁጥር 211/92 ከተቋቋመበት በአስፈጻሚ አካላት የሚፈጸመውን የአስተዳደር በደል መከላከልና መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን የማድረግ ሥራ፣ በተጨማሪ የመረጃ ነፃነት ሕጉን የማስፈጸም ግዙፍ ሥራ በአግባቡ ለማከናወን የሚያስችል አስተማማኝ ሁለንተናዊ አቅም አልተገነባለትም። ስለሆነም ተቋሙ ጥይት የሌለው ሽጉጥ ዓይነት ሆነ። ተቋሙ ተጠሪ የሆነለት የተከበረው የሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤትም አዋጁ በታቀደው መንገድ ተሟልቶ ተግባራዊ እንዲሆን በሁሉም ረገድ የተሟላ ዕርምጃ እንዲወሰድ አላደረገም።
በአንድ በኩል የመንግሥት አስፈጻሚ አካላት እምብዛም የማይፈልጉትን፣ አንዳንዶቹም ባለሥልጣናት የአስተዳደር በደል አድርሰው ሲጠየቁ ያላግባብ ፊት ለፊት የሚጋፈጡት መሥሪያ ቤት፣ የተቋቋመበትን አዋጅ በአጥጋቢ ሁኔታ ሳያስፈጽም ተደራቢ ግዙፍ ተልዕኮ ተሰጠው። የማስፈጸሚያ በጀት፣ የሰው ኃይልና መዋቅሩ ግን በአስፈጻሚው እጅ ስለሆነ ውጤታማ ሊያደርገው የሚችል ምቹ የመሮጫ ሜዳ አልተዘጋጀለትም። ከመቋቋሙ ጊዜ ጀምሮ “ጥርስ የሌለው አንበሳ” ሲባል የነበረው ተቋም ሌላ ከፍተኛ ኃላፊነት ተደርቦለት አቅሙ ሳይገነባ ይበልጥ ጥርስ እንዳይኖረው ሆነ። በወቅቱ በአዋጁና በደንቦቹ ውስጥ የሠፈሩትን ጉዳዮች ለማስፈጸም ቀላል የማይባሉ ውዝግቦች ነበሩ።
የእዚህ ጽሑፍ ዋነኛ ሐሳብ አሁን በሚረቀቀው አዋጅ ይዘትና ትግበራ ላይ ያለፉት አሉታዊ ክስተቶች ተመልሰው እንዳይመጡ አስተማማኝ መሠረት መጣል ይኖርበታል። የማያወላውል ተቋማዊ ዋስትና ያስፈልጋል ለማለት ነው። ያለበለዚያ ስንገነባ ስንንድ ጠብ የሚል፣ ወንዝ የሚያሻግር ነገር ሳንሠራ መሽቶ ይነጋል፣ ዓመታት ያልፋሉ፣ ሥራ ትተን ላልሠራናቸው ሥራዎች ወይም ለተፈጠሩት ክፍተቶች ሰበብ ፍለጋ ስንዋትት እንኖራለን። ይህ ልምድ በእጅጉ መኮነን ብቻ ሳይሆን፣ መወገድም ያለበት የተዛባ የአገራችን ባህል ነው። በሕዝብ ላይ የሚሠራ ቅጥፈትም ነው። ቅጥፈት ደግሞ የትም እንደማያደርስ ከኢትዮጵያውያን በላይ የተገነዘበው የለም። ያለፈውን ለመኮነን ካለፈው የበለጠ ማውራት ሳይሆን የተሻለ ነገር ሠርቶ በተጨባጭ ማሳየት ያስፈልጋል።
በሌላ በኩልም ጥንቃቄ የሚያስፈልገው ሌላ ዓብይ ጉዳይ አለ። በአንድ ክልል፣ ዞን ወይም ወረዳ የመንግሥት አስፈጻሚ አካል እጅ የሚገኝ የሆነ መረጃ ተፈልጎ ሲጠየቅ የዘር፣ የፆታ፣ ወይም የሃይማኖት ጉዳይ የሚነሳ ከሆነ አደጋው ከባድ ነው። የመረጃ ነፃነት የየትኛውም ማኅበረሰብ፣ ሃይማኖትና ፆታ አባል የሆነ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ያልተሸራረፈና ያልተበላለጠ እኩል መብት መሆኑ መታወቅ አለበት። መሥፈርቱን አሟልቶ እስከቀረበ ድረስ ማለት ነው። ለአንዳንዱ ዜጋ መሥፈርቱን ባያሟላም መንገዱ ቀላል የሚሆንበትና ለሌላው ደግሞ በመሥፈርት ሰበብ መንገዱ አባጣ ጎርባጣ የሚሆንበት ሁኔታ በፍፁም እንዳይኖር መደረግ ይኖርበታል።
አሁን የተያዘው ለውጥ ፅኑ መንፈስም ይኸው ነው። ከአንድ ክልል የመጣ የሌላ ቋንቋ ተናጋሪ የሆነ ኢትዮጵያዊ አሁን በአንዳንድ የፍትሕ ተቋማት ዘንድ እንደሚታየው ዓይነት የመስተንግዶ ልዩነት ወይም ኢፍትሐዊነትና አድሎአዊነት፣ በመረጃ ነፃነትም ጥያቄ አከባበር ላይ የዚህ ክልል ተወላጅ ወይም የዚህ ብሔረሰብ ቋንቋ ተናጋሪ አይደለም በሚል መብቱን የሚጋፋ ነገር እንዳይኖር አዋጁ ብርቱ ጥንቃቄ ማድረግ አለበት። ሰዎች ሁሉ በሕግ ፊት እኩል ናቸው የሚለው መርህ የሚጣስበት ሁኔታ ካለ፣ ሰዎች ሁሉ የመረጃ ነፃነት መብታቸው እኩል መከበር አለበት የሚለው መርህ ሊጣስ የሚችልበት ዕድል ላለመኖሩ ምንም ማረጋገጫ የለንም። ይህንን የምለው እስከ ዛሬ ከነበሩትና አሁንም ካልተወገዱት አዝማሚያዎችና የመብት ጥሰቶች በመነሳት እንጂ በግምት አይደለም። በርካታ ኢትዮጵያውያን ለውጡ ከመሪዎቻችን አላለፈም፣ ወደታች አልወረደም፣ በየአካባቢው የሚታየው ጉድፍ ከቀድሞው እምብዛም የተሻለ አይደለም፣ በአንዳንድ አካባቢዎች እንዲያውም የተባባሰ ነው የሚሉት ከእነዚህ ሁሉ ጉዳዮች በመነሳት ነው።
አገራችን በመሠረተ ልማት ዝርጋታ በተለይም በመገናኛ አውታሮች ልማት ረገድ ተጠቃሽ ዕርምጃ እያሳየች ነው። ይሁንና በተለይ በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ከእየ መንደሮቹ ወደ ቀበሌ፣ ከእየ ቀበሌዎቹ ወደ ወረዳ፣ ከእየ ወረዳዎቹ ወደ ዞን የሚያደርሱ መንገዶችን በማሟላት ረገድ ገና ብዙ እንደሚቀረን ግልጽ ነው። ምኞቱና ተስፋው ቢኖርም ከአገራችን የኢኮኖሚ አቅም አንፃር በተለይ በአርብቶ አደር አካባቢዎች ችግሩን ለመፍታት የተወሰኑ ዓመታትን ሊወስድ እንደሚችል መገመት ይቻላል። ስለዚህ በተለይ ከመሀል በጣም በራቁ ዳር አገሮች መረጃ ጠይቆ የተከለከለ ዜጋ፣ ቅሬታውን/አቤቱታውን በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ በእየ ደረጃው አቅርቦ ምላሽ ለማግኘት የጊዜ ውስንነት እንዳይኖር ሁኔታውን ማየት ያስፈልጋል።
ተበዳዮች የኑሮ ደረጃቸው ዝቅተኛ ከሆነ የመጓጓዣ ገንዘብ፣ የጉዞ ስንቅ፣ ወዘተ. ላይኖራቸው ይችላል። ስለዚህ ዕንባቸውን ወደ ሰማይ ረጭተው ቤታቸው እንዳይቀመጡ መፍትሔ ማስቀመጥ የግድ ይላል። ቅሬታ ወይም አቤቱታ ለመሥሪያ ቤቱ የበላይ ኃላፊ በጽሑፍ ማቅረብ ሲባል ለገጠር ቀበሌ ሊቀመንበር ወይስ ለወረዳው አስተዳዳሪ? ይኼ ሁሉ በማያሻማ መንገድ መቀመጥ ይኖርበታል። ተበዳዩ ማንበብና መጻፍ የማይችል ከሆነ ቅሬታውን በማመልከቻው ቅጽ ላይ የመረጃ ነፃነት ኦፊሰሩ ሊሞላለት እንደሚችል ይታወቃል። ይሁንና ለምሳሌ እንደ አፋር፣ ሶማሌ፣ ወዘተ. በመሳሰሉት ክልሎቻችን አሁን ባለው ሁኔታ በእየ ቀበሌው አስተዳደር ውስጥ በበቂ ሁኔታ ማንበብና መጻፍ የሚችሉ የመረጃ ኦፊሰሮችን መመደብ ይቻል ይሆን ወይ? በቂ አቅም እስኪገነባ ድረስ ምን መደረግ አለበት? የሚለው ጉዳይ ሁሉ አብሮ መታየት አለበት።
በሌላ በኩልም እንዳለመታደል ሆኖ ዛሬ ከአፄ ቴዎድሮስ ወይም ከዳግማዊ አፄ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት በሰፋ ሁኔታ የአገራችንን የመከላከያና የደኅንነት ሚስጥሮች በስፋት የሚያውቁ፣ በሆነው ባልሆነው እየከፋቸው ስሜታቸው በገነፈለ ቁጥር የሚደርሰውን የከፋ ጉዳት በመገንዘብም ሆነ ባለመገንዘብ የደኅንነታችንንና ሰላማችንን ሊያናጉ የሚችሉ እጅግ ብርቱ የሆኑ የአገሪቱን ሚስጥሮች አሳልፈው ሊሰጡ የሚችሉ ዜጎች ያሉባት አገር ሆናለች። ስለዚህ የመከላከያና ደኅንነት ሚስጥሮች ምን ያህል መጥበቅና መላላት አለባቸው የሚለው ጉዳይ በጥልቀት ሊታይ የሚገባው መሆኑ ግድ ነው። በጣም ሲጠብቅ አዋጁን የይስሙላ ያደርገዋል። በጣም ሲላላ ደግሞ በደኅንነታችን ላይ ክፍተት ይፈጥራል የሚሉ ወገኖች ስላሉ በጥንቃቄ ቢታይ።
በአገራችን የሚዲያ ኢንዱስትሪው ገና ድክ ድክ በማለት ላይ እንደሚገኝ ይታወቃል። ባለፈው አንድ ዓመት የለውጥ ጉዟችን ለመገናኛ ብዙኃን የአብዮት ዘመን ሆኖ ቆይቷል። አገር አጥፊና ሕዝብን አተራማሽ ከሆኑት አንዳንድ ግድየለሽና ዓላማ ቢስ ማኅበራዊ ሚዲያዎች በስተቀር፣ ጤነኛውና ሚዛናዊው ሚዲያ ይብዛም ይነስ የተወሰነ ብርሃን በርቶለታል። ይሁንና ኢንዱስትሪውን ይበልጥ የሚያቀጭጭና በመንግሥትና በሕዝብ መካከል እንደ ድልድይ መሸጋገሪያና ዓይንና ጆሮ ሆነው እንዳይሠሩ መሰናክል የሚሆኑ የመንግሥት አካላት ቁጥር ደግሞ ቀላል እንዳልሆነ፣ ቢያንስ ከሰሞኑ በአገራችን የዓለም የፕሬስ ቀን በዓል ሲከበር የወጡት በርካታ መረጃዎች አብነት ናቸው። ትንሽ ጠብ የሚል ጥሩ ሥራ ሠርቶ ሚዲያዎች እንዲያቆላጵሱት የሚፈልግ ሹመኛ ግዙፍ ስህተት ፈጽሞ ጋዜጠኞች ሊያነጋግሩት ሲጠይቁ በሩን ብቻ ሳይሆን፣ ስልኩን ጭምር ይዘጋል። በዚህ ዓይነት ሺሕ ጊዜ ምርጥ የሆነ የመረጃ ነፃነት አዋጅ ቢኖረን ከላይ እስከ ታች የተመደቡትን ሹመኞች አስተሳሰብ መቀየር ካልቻልን አዋጁ በራሱ ወረቀት ብቻ ሆኖ ይቀራል። የለውጡ መሪዎች በዚህ ጉዳይ ላይ የማያወላውል ቁርጠኛ አቋም ሊኖራቸው የሚገባ ይመስለኛል።
የለውጡ ሒደት ግማሽ ፀጉር ግማሽ መላጣ፣ አንዱ ቦታ ነጭ ሌላው ጋ ጥቁር፣ ደጋ ላይ ንፁህ ቆላ ላይ ቆሻሻ እንዳይሆን ቆሻሻውን ሁሉ ከታች ጀምረን እስከ ላይ ወይም ከላይ ጀምረን እስከ ታች ማፅዳት ይኖርብናል። ቆሻሻው የልብስ ወይም የሰውነት ቆሻሻ ሳይሆን የአስተሳሰብ እድፍ ስለሆነ፣ በእንዶድም ሆነ በሳሙና እስኪነፃ ድረስ ታሽቶ በደንብ መታጠብና መፅዳቱ መረጋገጥ አለበት ብዬ አስባለሁ። ያለዚያ ብዙ ጊዜ ብዙዎች እንደሚሉት ታችኞቹ ላይ አቅማችንን እያሳየንና በታችኞቹ አካላት ላይ ብቻ እያሳበብን፣ ፅዳቱ ላይኞቹን በለሆሳስ የሚያልፋቸው ከሆነ ለለውጡ ኃይሎች ትልቅ ክፍተት ነው።
እውነት እንነጋገር ካልን በየመድረኩ ላይ ተደጋጋሚ የለውጥ ደጋፊነትና የሕዝብ ተቆርቋሪነት ዲስኩር ከሚያሰሙን ባለሥልጣናት ስንቶቹ ለውጡን የሚያምኑትን ሃይማኖት ያህል ያምኑበታል ብሎ መጠየቁ ተገቢ ነው። አንዳንዶቹ ባለሥልጣናት ለሹመት ሲታጩና ሲቀርቡ ለእኔ ይኼ ቦታ አይገባኝም/አይመጥነኝም የሚሉበት ሁኔታም መለመድ ያለበት መሆኑ ይታየኛል። ያለበለዚያ ያለአቅማቸው አንድ ኩንታል ጤፍ እንደማሸከምና ተንገዳግደው እንዲወድቁ ማድረግ ይሆናል። ውድቀቱ ደግሞ የግለሰብ ብቻ አይደለም። የተቋም፣ የፖለቲካ ሥርዓትና የአገር ውድቀት ነው። በመሆኑም አዋጁ ያረጀውን ቤት ቀለም የመቀባት ዓይነት ሳይሆን የሚቻል ቢሆን፣ በአስተማማኝ ሁኔታ የማደስ ካልሆነና ታድሶ በአስተማማኝ ሁኔታ ሊያገለግል የማይችልበት ዕድሉ ሰፊ ከሆነ ደግሞ በበቂ አሳማኝ ምክንያት እንደገና አፍርሶ መገንባት የግድ ይሆናል።
ከፍ ብሎ ለማመልከት እንደተሞከረው ወቅቱ በኢትዮጵያ ታሪክ ከምንጊዜውም የከፋ ቂመኝነት የገነነበት ሆኗል። ባለሥልጣኖቻችንም ሆኑ ሚዲያዎቻችን፣ ምሁራኖቻችንም ሆኑ የሃይማኖት አባቶቻችንና እናቶቻችን ቂመኝነትና ዘረኝነት እንደ ሰደድ እሳት አገር አጥፊ፣ እንደ ሚሳይል ሕዝብ ጨራሽ መሆኑን በየቀኑና በእየ ሰዓቱ ይነግሩናል። ነገር ግን እነዚህ አካላት ሁሉ በእውነት ከዚህ መጥፎ አስተሳሰብ የተላቀቁ ናቸው ወይ? ይህ ካልሆነስ በአንዳንድ አካባቢዎች ለሚቀጣጠለው እሳት ክብሪት እንዲጫር የሚያደርገው፣ ወጣቱን የሚያነሳሳው፣ ከኋላ የሚገፋውና የሚበክለው ማነው ብሎ መጠየቁ ደግሞ የግድ ይሆናል። ከኋላችን እየመጣ ያለው ትውልድ እየሄደ ያለው እኛ ባሳየነው መንገድ፣ በከፈትንለት ቀዳዳ ፈለጋችንን ተከትሎ ነው። ስለዚህ እየሄድንበት ያለው መንገድ ልክ ነው ወይ ብሎ ጣትን ወደ ራስ መጠቆም ተገቢ ነው።
ያለችን አንዲት አገር ናት። ቢከፋንም ቢደላንም፣ ብንደሰትም ብናዝንም፣ ብናድግም ብናንስም፣ ብናገኝም ብናጣም አገራችን ኢትዮጵያ ናት። ሲመቸንና ሳይመቸን እንደፈለግን የምንቀያይራቸው ሁለትና ሦስት ወይም አስርና ሃያ አገሮች የሉንም። አገር ለሙቀትና ለብርድ ጊዜ እየቀያየርን የምንለብሰው ልብስ፣ በፆምና በፍስክ ጊዜ እንደ ሁኔታው የምንመገበው ምግብ ዓይነት አይደለችም። ኢትዮጵያ ተወልደን ያደግንባት፣ ሐዘናችንንና ደስታችንን ያየንባት፣ ምንም ትሁን ምን ምንጊዜም ልንከዳት ወይም ልንከፋባት የማንችል እናታችን ናት። ‹አበው አዲስ እረኛ ከብት አያስተኛ› የሚሉት ብሂል ዝም ብሎ የተባለ አይደለም። በቅርቡ ወደ ሥልጣን ወንበር የመጡ ሹመኞች አንዳንዶቹ ወይም ብዙዎቹ ማለት ይቻላል ከቀድሞዎቹ ብዙም የተማሩ አይመስለኝም።
ከራስህ ውድቀት ከመማር ከሌሎች ውድቀት ተማር የሚባለውንም መስማት አይፈልጉም። ሌሎች ሲፈጽሙት ያየኸውን ጥፋት አንተም ደግመህ አትፈጽም ነው ጉዳዩ። እሳት እንዴት እንደሚፈጅ እየታየ እኔን እስከሚፈጀኝ ብሎ መዘናጋት ተላላነት ነው። ሕዝቡን ሲያሰቃዩ የኖሩ ባለሥልጣናትን በእየ መድረኩ ስናወግዝ እየዋልንና እያደርን እኛም ያንኑ ብልሽት የምንደግመው ከሆነ፣ ነገም ያለፉት ሰዎች ዕጣ ፈንታ ሊደርሰን እንደሚችል ለአፍታም ቢሆን መዘንጋት የለብንም። ስለዚህም አዋጁ እንዲህ ዓይነት ጥፋቶችን በሚፈጽሙ የመንግሥት አስፈጻሚ አካላት ላይ ስለሚወሰደው ዕርምጃ ዋስትና ሊሰጡ የሚችሉ ጠበቅ ያሉ አንቀጾች ሊኖሩት ይገባል።
የአሁኑ ጠቅላይ ሚኒስትራችን የወቅቱ መንግሥት በቀጣይ በተቋማት ግንባታ ላይ የተለየ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሠራ በተደጋጋሚ ሲናገሩ ይሰማል። ይሁንና ሥራው ከብዙዎቹ ሥራዎች ቀድሞ መሠራት ያለበት ነው። ለሌሎችም ቀጣይ ሥራዎች ያግዛል። በበኩሌ የለውጡ አስተሳሰብ በደሙ፣ በአጥንቱና በሥጋው በአጠቃላይ በሁለመናው ላይ እንደሰረፀና የአገርና የሕዝብ ኃላፊነት በፅኑ እንደሚሰማው ዜጋ አባባሉ ለውጡ ተቋማዊ አይደለም፣ በአደረጃጀት ላይ የረባ ሥራ አልተሠራም፣ የሚታዩት እንቅስቃሴዎች እሳት የማጥፋት ዓይነት ይመስላሉ፣ ወዘተ. በሚል በእየ ቦታው ለሚነሱት ጥያቄዎች የማስተንፈሻ ወይም የማስታገሻ መልስ ለመስጠት ነው የሚል ቅንጣት ያህል ጥርጣሬ የለኝም። ሊሆንም አይችልም። ከሆነ ግን በጭራሽ አያዋጣም። ኪሳራው ዛሬ ላይታየን ይችላል እንጂ ነገ ይደርሳል። ስለዚህ በምንም ዓይነት እንዳለፉት መንግሥታት ዓይነት ለጥያቄዎች ፈጣን ምላሽ ያለመስጠት አካሄዶች መታረም አለባቸው።
ከታች ከቀበሌ ደንብ አስከባሪ ጀምሮ እስከ መጨረሻው የአገሪቱ የሥልጣን አካል ድረስ በፍፁም የማይጠበቅ አስተሳሰብ ነው። ለጋራ አገራችን ምንም አይጠቅማትም። ‘ከእኛ ወዲያ ፉጨት አፍ ለማሞጥሞጥ ነው’ እንዲሉ ብዙ ነገር ዓይተናል። ለሕዝቡ እኔ ብቻ ነኝ የማውቅለት፣ የሕመሙ ፈውስ እኔው ብቻ ነኝ ብለን የምናስብ ዘመነኛ ሹመኞች ካለፉት መሰሎቻችን ተምረን፣ ሕዝብንና የሕዝብን ፍላጎት ለማክበር የተለየ ጥረት ማድረግ ይኖርብናል ከማለት ያለፈ የምለው ነገር የለኝም። ለዚህ ደግሞ የመረጃ ነፃነት አዋጅ ሰፊ ድርሻ አለው።
የመረጃ ነፃነት ማለት ሕዝቡ ስለሚሠሩለት አገልግሎት መስጫዎች (የትምህርትና የጤና ተቋማት፣ መንገዶች፣ የንፁህ የመጠጥ ውኃ፣ የትራንስፖርት አገልግሎቶች፣ ወዘተ.) ገና ከፕሮጀክቱ ጥናት ጀምሮ የተሟላ መረጃ የማግኘት፣ ባገኛቸው መረጃዎች ላይ ተመሥርቶ አስተያየቱን ያለምንም ገደብ የመስጠት፣ አጥኚዎችም በመንግሥት እጅ የሚገኙ ሰነዶችን ቢቻል ያለክፍያ በነፃ አግኝተው ለሕዝብ ጥቅም በሥራ ላይ የማዋል ጉዳዮችን ሁሉ ያካትታል። የውኃ ቦኖ ተሰብሮ ቢቆም ለምን ተሰበረ ወይም ለምን አገልግሎቱን አቋረጠ ብሎ የመንግሥት አካላትን በመጠየቅ፣ መረጃ የማግኘትና መብትን የማስከበር ጉዳዮችን ይጨምራል። የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ መጓተትና የፍትሐዊ ክፍፍል ጥያቄ ካለ ለምን እንዲህ ሆነ ብሎ መጠየቅና የሚያረካ መረጃ ማግኘት፣ የዜጎች መብት ስለሆነ አዲሱ አዋጅ ወይም ማስፈጻሚያ ደንቦቹ እነዚህን ጉዳዮች ሁሉ በማያከራክር መንገድ በግልጽ ማስቀመጥ ይጠበቅበታል ብዬ አምናለሁ።
የመንግሥት ትምህርት ቤቶች ተማሪዎችን የሚቀበሉባቸው መሥፈርቶች፣ የፈተናዎቻቸውን ውጤት ትክክለኛነት፣ የሕክምና ተቋማት ሕሙማንን ተቀብለው የሚያስተናግዱባቸው አካሄዶች፣ በከተሞች በአጠቃላይ ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎቶች የሚመሩበት ሁኔታ በተመለከተ መገናኛ ብዙኃን ወይም አጥኚዎች ወይም ግለሰቦች መረጃ ጠይቀው የማግኘት መብታቸው ያለገደብ እንዲከበር አዋጁ ትኩረት መስጠት ይኖርበታል የሚል እምነት አለኝ። ለዚህም በመስኩ ስኬታማ የሆኑ የሌሎች አገሮችን ተሞክሮዎች ቀምሮ፣ በልካችን አሰፍቶ፣ እንዲስማማን አድርጎ ማካተቱ ተገቢ ይሆናል። ለመንግሥትና በመስኩ ለተሠማሩ ባለሙያዎች ሁሉ ብርታቱን እንዲሰጣቸው ፅኑ ምኞቴ ነው።
ውድ አንባቢያን! የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ እ.ኤ.አ. በ2004 ዓ.ም. በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ‹‹የመረጃ ነፃነት መከበር የአገራችን አንዱ ወቅታዊ አጀንዳ›› በሚል ርዕስ በ27 ተከታታይ ክፍሎች ዓመቱን ሙሉ ጽሑፎቹን ለአንባቢያን ሲያቀርብ ቆይቷል። የሰዎች መረጃ ጠይቆ የማግኘት መብት ከፍተኛ ጥንቃቄንና ግንዛቤን የሚሻ የሁላችንም የጋራ ጉዳይ ነው። ይህንኑ በመገንዘብ በመረጃ ነፃነት ጽንሰ ሐሳብና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ያለውን ግንዛቤ ለማሳደግ እንዲረዳ ሰነዱ ለአስተባባሪዎቹ፣ ለተግባሪዎቹ፣ ለኅብረተሰቡም ጭምር እንደማጣቀሻ እንዲያገለግል ወጥ ሆኖ ተደራጅቷል።
ቢታተምና ቢሠራጭ አንዳች ፋይዳ ይኖረዋል የሚል ሐሳብ ከዚህም ከዚያም በመቅረቡ፣ በ2005 ዓ.ም. በ200 ገጾች የተደራጀው ይኸው የመረጃ ነፃነት መጽሐፍ ረቂቅ የኅትመት ብርሃን ሳያይ በየስፖንሰሮቹ እጅ እንደሚገኝ በዚህ አጋጣሚ መግለጽም ተገቢ ይመስለኛል። አሁንም ጸሐፊው ይህንን እንደ ማኑዋል ሊያገለግል የሚችል የተደራጀ ሥራ ለሚመለከተው አካል ሕጋዊ በሆነ መንገድ ከክፍያ ነፃ ለመስጠትና በጥቅም ላይ እንዲውል ለማድረግ ዝግጁ ነው። እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን ሁሉ ይጠብቅ። አገራችን ልታድግ የምትችለው ተቀራርበን ስንወያይ ያለንንም አስተዋጽኦ ስናደርግ ነው። መነቋቆር ምን ያህል እንደጎዳን ቁስሉ ተሰምቶን ሁላችንም የተጀመረው ለውጥ ደጋፊዎች እንድንሆን ፀጋውን ይብዛልን።
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡