Wednesday, June 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ልብ አድርቁ በዝቶ ተደነጋገርን!

እነሆ መንገድ። ከሃያ ሁለት ወደ ካዛንቺስ ተሳፍረናል። ጎበዛዝት በለዘዘ ስሜት ጎዳናው ላይ ውር ውር ይላሉ። አርጋጅና አንጓች በሰው ቁስል እንጨት እየሰደዱ ያስቸግራሉ፡፡ የዋህ ሕፃናት በእርግብ ልቦናቸው ለጋ ደመና አምነው ንዳድ ይዳፈራሉ። የነገን ማወቅ አይደለም መገመት የሚችል ጠፍቶ፣ ትናንትን መገንዘብ ቀርቶ ማስታወስ ታክቶ፣ ወላጅ እንደ መካን በትርጉም የለሽ ጉዞ ያዘግማል። ቀሪን ለገረመው ሟች ይስቅለታል። የዘንድሮ ክረምትና መንገድ ‹አፌን በዳቦ› የሚያሰኝ ነው። ‹‹እስኪ ጠደፍ ጠደፍ አትበይ የት ለመድረስ ነው?›› ትላለች አንዲት ዘብነን ብላ የምትጓዝ ወይዘሮ ናት፡፡ ጠደፍ ጠደፍ ባዩዋ አላየቻት ኖሮ ስትዞር ዓይን ለዓይን። ‹‹አንቺ! አንቺ! . . . ›› ተባብለው መሀል መንገድ ላይ ሲተቃቀፉ፣ መታቀፍ የናፈቀው ነጠላ ነፍስ ሁላ ዳር ይዛችሁ አትተቃቀፉም እያለ ወረደባቸው። ጎዳናው ዘሎ ሰው አናት ላይ ጉብ በማለት የሞላ ልምድ አለውና ወያላው ፊት አገኘሁ ብሎ፣ ‹‹ቀነስ አድርጉት በሏቸው። ደግሞ ኋላ በዚህም ግብር ክፈሉ ሊሉን ይችላሉ እኮ?›› ሲል እንሰማዋለን። ‹‹ብንባል እኛ . . . አንተ ምንህ ይነካል? አርፈህ አትጮህም?›› አለችው አንደኛዋ ወይዘሮ። የእርጎ ዝንቡ ብዛት አላነጋግራቸው ማለቱ ሁለቱንም አራስ ነብር አድርጓቸዋል።

 

‹‹እሺ አሁን ትገባላችሁ አትገቡም? ዝናብ እየመጣ ነው . . . ›› ወያላው ለስለስ ብሎ ወደ ሥራው ሲመለስ ‹ቅደሚ. . . ቅደሚ. . .› ተባብለው ወይዛዝርቱ ተሳፈሩ። ወዲያው የተሳፋሪዎች ቁጥር ወደ አሥራ ስምንት አደገ። ‹‹አይበቃም ሾፌር?›› ጋቢና የተሰየመ ልጅ እግር ሲነጫነጭ፣ ‹‹አንተ ምን አገባህ? ቦታ ከያዝክ በኃላ ምንህ ተነክቶ ነው የምትገላምጠኝ?›› ብሎ ሾፌሩ ትርፍ ተናገረው። ‹‹ትርፍ ተጭኖም፣ ትርፍ ተወርቶም፣ ትርፍ በሌለበት ጎዳና በአፍ ብዙ ባንጎዳዳ ምን ይመስላችኋል . . . ? አርፋችሁ አትታጨቁም? አይ እኛ እንደ ንግድ ሚኒስቴር ፈቃድ እስኪመለስ አንጠብቅም እናወርደዋለን . . . ›› ሲል ወያላው፣ ተሳፋሪዎች እንዳልሰሙ ሆነው ማዶ ማዶ እያዩ መስማማታቸውን በዝምታ አፀደቁ። ድሮም ዝምታ ነው ሰውን ያደነዘው ብንል እኮ ሰደቡን የሚለን ይኖራል!

ጉዟችን ጀምሯል። “ኧረ እናንተ ሰዎች ዛሬ ተገልብጠን ጉድ እንዳንሆን፤” ትላለች። “ከአቅም በላይ የተጫኑትንና የተጫነባቸው ይጭነቃቸው እንጂ ብንገለበጥ ባህር አይበላን። በምላስ የተላሰ የመሰለ አስፋልት ላይ ነው ፈልሰስ የምንለው። በበኩሌ አብዛኞቻችን ከምንተኛበት ፍራሽ ይኼ አስፋልት የተሻለ ሳይመቸን አይቀርም፤” ይላል መጨረሻ ረድፍ የተሰየመ ጎልማሳ፡፡ “በበኩሌ አማሟቴ ነው የሚያስጨንቀኝ። እንዳልሆን ሆኜ ማለፌ ሳያንስ ቢቻል አገር፣ ባይቻል ሠፈር፣ በእንባ እንዳይራጭልኝ በመኪና አደጋ መሞት አልፈልግም። ከመኪና አደጋና ከዘንድሮ የመፈናቀል ስደት ሜዲትራንያን በስንት ጣዕሙ . . . ” ስትል መሀል ረድፍ አንዲት ባለሻሽ፣ “ሞት መቼም ልማዱን ዓይተው፣ ግን ከተለመደ ሞት ያልተለመደው በልጦ በረሃና ባህር ለበላው እንደምናዝነው፣ በመኪና አደጋ በየቀኑ የሚያልቀውን ሕይወት ያቃለልነው መስሎ ይታየኝ ነበር። አሁን ግን ለካ ሌላም አለ እናንተ። ይኼ ግጭት የሚሉት ነገር፡፡ ይልቁን ‹ተጠንቀቅ! ቀን እንዳይጥልህ› እያልን ቀን እንዳይጥለን ስንዋደቅ ቀን እኛ ላይ ይውደቅ? እኔ እኮ ዘንድሮ አንዱን ከአንዱ መለየት ከበደኝ፤” እያለች አንደኛዋ ወይዘሮ ትናገራለች።

“እሱ ሳይሆን ቁም ነገሩ ቋሚ ቆሞ ሲሄድ ሁሉን የምር አድርጎ በልቶ ለማይጨርሰው ሀብት እህት ወንድሙን አስለቅሶ፣ ሕዝብና መንግሥት አናክሶ ሳያስበው ማለፉ ነው። በረባ ባልረባው ክልትው እያልን ሞት በጥጋብ ተሸሽጎ በሚናጠቀን ክፉ ቀን ልብ መግዛት ያቃተን ሚስጥሩ አይገባኝም፤” አለች ወይዘሮዋ። “ደላላችን በዝቶ ነዋ። ምን እናድርግ? ከመሠረታዊ እስከ የቅንጦት ምኞታችን ያለ ገንዘብ ምንም ናችሁ የሚሉንን የመብት ታጋይ ነን የሚሉንን መቋቋም ከበደን። ይኼው ነው! ታዲያ በዚህ መሀል ሰው መሆን ትርጉሙ ቢጠፋብን ይገርማል? ፍትሕ ስንል ያለ ስም፣ ያለ ዝና፣ ያለ ሥልጣን፣ ያለ ብሔር መጠጋጋት የለም ካሉን፣ የትዳር አጋሮች ያለ ጥሪት ዝንብህን እሽ የማይሉ ከሆነ፣ ጨዋታው ‘እሺ ለአንድ ራሴ ሠርቼ ልኑር’ ስንል እሱም ቢሆን ቡድን ያስፈልገዋል ሲባል ከሰማን ወይም ካየን፣ ግራ እንደተጋባን ሞት ቢቀድመን ምን ይገርማል? አሟሟታችን ቢከፋስ ይደንቃል?” ብላ አንዷ አነበነበች። “እኔ በቀጣዩ ምርጫ ተወዳዳሪ መሆን ብችል በዕጩነት ቀርቤ ምን እንደምል ታውቃለህ? ‹‹ሰው እንዲረጋጋ ጫት በነፃ አድላለሁ፤›› የሚለኝ ከጎኔ የተቀመጠ ተሳፋሪ ነው። አንዳንዱ ሰው ምን እንደሚያወራም አላስተውል አለ እኮ እናንተ! ይኼ ያልታረመን ሐሳብ ‘ፖስት’ እና ‘ሼር’ የማድረግ አባዜ እኮ ነው!

ወያላችን ሒሳብ መቀበል ጀምሯል። “በይ ነገርኩሽ ዝም ብለሽ ትሄጂ እንደሆን ሂጂ ነገር አታምጪ፤” ሙሉ ቀሚሷን እስኪሸፍን ነጥላ ያጣፋችውን ነጠላ ደጋግማ የምትጎትት ወይዘሮ ታወራለች። “አንቺ ደግሞ ይኼንን ገንዘብ ብለሽ ነው። እንካ ጫኝ አውራጅ የእሷን ሒሳብ . . . ” ትላለች ወዳጇ። ሲያዩዋቸው መንትዮች ይመስላሉ። ወያላው ‘ጫኝ አውራጅ’ መባሉ አስከፍቶታል። እናም ነገር ጎንጉኖ፣ “እኔን ነው?” አላት። ዝርዝር ብሮች ይዘው ወደ እሱ የተዘረጉትን እጆች በጥርጣሬ እየተመለከተ። “ታዲያ ሌላ ‘ጫኝ አውራጅ’ አለ?” ደገመችለት ሞንዳሊት። “ምነው እናንተ መርካቶ ያላችሁ መሰላችሁ?” አጉረመረመ ወያላው። “ምን አልክ? አንቺዬ አንዲህ እንደ ቀበሮ እያነፈነፉ የሰው መብት እየተጋፉ፣ ነገ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብታችን ተገደበ ብለው መንግሥትን ሲያሙ ግን አይገርሙሽም?” ተባብለው ሲያበቁ ሒሳብ ከፋይ መልሷን ተቀብላው ፊቷን አዞረች።

ወያላው ዓይኑ እንደ ቀላ፣ “መቁጠሪያ በመያዣቸና በመቁረቢያቸው ዘመን እየተላከፉ ልበ ደንዳናነታችንን ያባብሳሉ፤” ብሎ በሩን ሲዘጋ ሾፌሩ፣ “ባልሰማ ባላየ ማለፍ ነው። አለበዘሊያ አንተም እንደ አምባገነን መሪዎች የንሰሐ ዕድሜ ሳይተርፍህ መሞትህ ነው፤” ይለዋል። ሒሳብ ከተከፈለላት ወይዘሮ ተደርበው የተቀመጡ አዛውንት አስነጠሱ። ደገሙ። ሦስተኛ ማሳረጊያ እንጥሴያቸውን እንዳገባደዱ ቀና ብለው ወደኋላ ወደፊት አማተሩ። ጥቂት ሲያስቡ ቆዩ። እንባ እንባ እንዳላቸው ያስታውቃሉ። “ማነህ ሾፌር አውርደኝ፤” ኮስተር ብለው ቃል ከአንደበታቸው እንደወጣ፣ “ወያላው ለምን ገቡ? አስነጥሰውብን ሊወርዱ ነው የተሳፈሩት?” አላቸው። “እና ላንተ ብዬ ይማርህ ማለት ከረሳ ጋር ልጓዝ?” በጣም ተቆጡ። ወይዘሮዋ ጣልቃ ገባች። “አይ እርስዎ ሰው እኮ ወደ ውስጥ እያስነጠሰና እየሳለ የሌላ ሰው ማድመጥ ትቷል። ይበሉ አርፈው ይቀመጡ፤” አለቻቸው። ካልወረድኩ ብለው ያገነገኑት አዛውንት ወይዘሮዋ እንዳለቻቸው አርፈው ተቀመጡ። ድጋሚም አላስነጠሱብንም። ምናልባት ወደ ጅጊው፣ ወደ ደቦው ተቀላቅለው ንጥሻቸውን ‘ሳይለንት አድርገውት ይሆን? የሚያኖርና የሚምር ሰው የጠፋበት ዘመን ሆነ እኮ ዘመኑ እባካችሁ! 

ወደ መዳረሻችን ተቃርበናል። ጭቅጭቅ ይሁን ውይይት ጎራው ያልለየ ሆይታ ሆይታ ተጀመረ። ሦስተኛው ረድፍ ላይ የተቀመጡ ወጣቶችን ጨምሮ ወዲህ እኔን ሳያካትት፣ “ብለን ብለን በዚህ ዘመን ለአፄዎቹ ልደት ኬክ እንቁረስ እንበል?” እያሉ ‘ወቸው ጉድ’ ሲሉ ድንበር የምጋፋት ቆንጆ፣ “ምን ነውር አለው? አገራቸውን እንቅልፍ አጥተው አገልግለው ላለፉ ይቅርና ለማንም ይቆረስ የለ እንዴ? እንኳንስ ሥራቸው እንደ ፀሐይ የሚያንፀባርቅ ቀርቶ፣ አሉ አይደል እንዴ ሳይሾሙ የተንጠላጠሉ? ላያችን ላይ ማንም እየተነሳ ሲደነፋና ያሻውን ሲያደርግ ጭጭ ብለው የሚያዩ ምን ይባሉ? ገበያውን ሃይ ሳይሉልን ሁለትና ሦስት መቶ ፐርሰት እየተተረፈብን ኬክ የሚቆርሱብን ምን ይደረጉ? መብላት፣ መጠጣትና መልበስ ሲያቅተን ዓይተው እንዳላዩ የሚያልፉን አሉ አይደል? በቃ እንዲህ ነው ማሰብ ያለብን? አለቀ . . . ” አለች በግለትና በቁጣ። “ኧረ ተረጋጊ። ፈጣሪ ምን ጎድሎበት? ማንንስ ፈርቶ? ደግሞ ለእኛ ስሜት? ለለበጣ እኛ አንሰን? ሆሆ . . . ” ብላ ከወዲያ ወይዘሮዋ አገነገነች።

አዛውንቱ በዝምታ ሁሉን ሲታዘቡ ቆይተው አላስችል ስላላቸው ተራቸውን፣ “የእኛ ነገር እኮ ለወሬ ነጋሪም አይመች፤” ብለው ጀመሩ። “ወዲህ የሆዳችንን ጩኸት የጥጋብ ብሥራትና የቁንጣን ርችት ድምፅ ነው ይሉናል። መሸመት አቃተን ብለን ስንሰደድ ‘ድሮም ለአህያ ማር አይጥማት’ እንባላለን። ወዲህ ደግሞ አማራጭ አለኝ ባዩ ትንሽ ትልቁን ጉዳይ ፖለቲካዊ አንድምታ ይሰጥና ሐሳብ በማጨናገፍ ያገኘው ይመስል ችግኝ ዘቅዝቆ መትከል ልመዱ ይለናል። ኧረ በዛ! መረር ስንል መንግሥት ምሬት ለመቀነስ ጠንክሮ እየሠራ እንደሆነ ተገለጸ የሚል ዜና ይሠራብናል። ‘ለምን?’ ስንል አንጀታችሁ እንዳልተፈታ መንግሥት አንጀቱ ይረር ይሉናል። እኛ ከሐሙራቢ ሕግ ልዩ ፍቅር ያለን ይመስል፣ ቆይ ግን አንጀትን በአንጀት ምን ማለት ነው?” ይላሉ። አንድ ወጣት ዘው ብሎ፣ “ይህን ትዝብት በቀጣዩ ምርጫ እንዳይረሱት አደራ . . . አንድ ዓመት ነው የቀረው ደርሷል፤” አላቸው። “ከተደራደርን በኋላ እናስብበታለን፤” ብለው ታክሲያችን ከመቆሟ ዘለው ወርደው ሮጡ። ግን ዘንድሮ የምናስብበት ነገር አልበዛም? አሁን አሁንማ የምንነጋገርበት ርዕስ ራሱ አልግባባ እያለ መዳረቅ በዝቷል፡፡ መዳረቅ ሲበዛ ደግሞ መደናቆር ይከተላል፡፡ የሆነስ ሆነና የት ሄደን ተንፈስ እንበል? ልብ አድርቁ በዝቶ ተደነጋገርን እኮ! መልካም ጉዞ . . .

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት