Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊትኩረት የተነፈገው የቀድሞ ምድር ጦር የጡረታና የሕክምና መብት ጥያቄ

ትኩረት የተነፈገው የቀድሞ ምድር ጦር የጡረታና የሕክምና መብት ጥያቄ

ቀን:

‹‹እየራበን እንዳንበላ፣ እየተጠማን እንዳንጠጣ፣ እየታረዝን እንዳንለብስ፣ የጡረታ መብታችንን ተከለከልን፡፡ እየታመምን እንዳንታከምና ሕክምና እንዳናገኝ ታገድን፡፡ ብንሞትም እንዳንቀበር የዕድር ገንዘባችንንና በሠራዊቱ የግል መዋጮ ገንዘብ የተገነባ ክበባችንን ያለ ምትክና ካሳ የተነጠቅንበት፣ በግዳጅ ላይ የተሰው የጦር አባላት ልጆች ከሚያድጉበት የሕፃናት አምባ በእኩለ ሌሊት ከካምፕ ወጥተው የተጣሉበት፣ በተለያዩ የጦር ሜዳ የአካል ጉዳት የደረሰባቸው የጦር አባላት ከጀግኖች አምባ ወጥተው የተበተኑበትና ለልመና የተዳረጉበት፣ ዓለምን ያሳዘነ የብቀላ ድርጊትና የወንጀል ተግባር ተፈጽሞብናል፡፡›› የሚሉት፣ የቀድሞ የምድር ጦር ሠራዊት አባላት ናቸው፡፡

አባላቱ ከ50 ዓመት በፊት ባቋቋሙት የምድር ጦር ሠራዊት አባላትና በመከላከያ ሚኒስቴር የሲቪል ሠራተኞች መረዳጃ ዕድር አማካይነት ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ኢትዮጵያን በቆላውና በደጋው በቅንነትና በታማኝነት አጥንታቸውን ከስክሰው፣ ደማቸውን አፍስሰው፣ ድንበሯንም ሆነ አንድነቷን ጠብቀው፣ ለአሁኑ ትውልድ አቆይተዋል፡፡ አገሪቱን ከፍ ብሎ በተጠቀሰው መልክ ጠብቀው ቢያቆዩም ያለ ስም ስም እንደተሰጣቸው፣ ለውለታቸው ክብርና ሞገስ ሲገባቸው ጨፍጫፊ፣ አረመኔ፣ የቀድሞ ሥርዓት ናፋቂ፣ ወዘተ እየተባሉ እዚህ ደርሰዋል፡፡

ይህ ሁሉ ስድብ፣ ዛቻና ማስፈራራት እየደረሰባቸው ሳለ በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ለግዳጅ እንዲሠለፉ በተጠሩ ጊዜ ቅሌን ጨርቄን፣ ረሃብ ጥማቴን ሳይሉና የደረሰባቸውን በደልና ግፍ ለታሪክ ትተው ያለማወላወል ጥሪውን ተቀብለው፣ የፍቅርና የአንድነት መለያ የሆነውን ባንዲራቸውን ለብሰው ወደ ግዳጅ በመዝመት የፈንጂ መጥረጊያና የመትረየስ መፈተሻ እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡

ይህም ሆኖ በአጭር ጊዜ ውስጥ ጠላትን ድባቅ መትተው በታሪካዊቷ ባድሜ ላይ በእነሱ ባንዲራ ሰቃይነት ግዳጃቸውን በድል እንደተወጡ ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡ ከዚህ ጦርነት ቀደም ሲልም ሆነ በኋላ ሠራዊቱን በተለያየ ሙያ ከማሠልጠን እስከ ዘላቂ የአገር መከላከያ ዶክትሪን  ዝግጅት ጥናትና ረቂቅ ሥራ ላይ ከፍተኛ ተሳትፎ ማድረጋቸው በወቅቱ በነበሩት የአገር መከላከያ አመራሮች ዘንድ የማይካድ ሀቅ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

‹‹ይህን መሳይ አኩሪ ገደል ፈጽመን ውለታ ሊደረግልን ሲገባ፣ አንገብጋቢ የሆነው መሠረታዊ መብቶቻችን ተጥሶ ውዲቷ አገራችን ልታደርግልን የሚገባው መብቶቻችን ሁሉ ተነፍገናል፡፡ ከተነፈግነውም መብቶች መካከል የጡረታና የሕክምና መብቶች ይገኙበታል፡፡ ከሰባት ሚሊዮን ብር በላይ የዕድራችን ገንዘብ በባንክ እንዲታገድ ተደርጓል፡፡ የነበሩንን ሁለት ክበቦች ተነጥቀናል፤›› ሲሉ አማረዋል፡፡

እንደ ቅሬታ አቅራቢዎቹ አባባል ለደረሰባቸው በደሎች መፍትሔ እንዲሰጣቸው ከ1984 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ለሕዝብ ተወካዮችና ለሚኒስትሮች ምክር ቤቶች፣ እንዲሁም በየወቅቱ ለነበሩ ጠቅላይ ሚኒስትሮች፣ ፕሬዚዳንቶች፣ ለሚኒስትሮች ለተለያዩ የመንግሥት ተቋማት በድምሩ ከ25 በላይ ደብዳቤዎች ቢያቀርቡም የተገኘ ምላሽና መፍትሔ የለም፡፡

ደብዳቤ ከደረሳቸው መንግሥታዊ ተቋማት መካከል የፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት ዳኞች የታገደው የዕድሩ ገንዘብ እንዲለቀቅላቸው መፍረዳቸውን፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ደግሞ ለአገር መከላከያ ሚኒስቴርና ለመንግሥት ሠራተኞች ማኅበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ የዕድሩን ገንዘብ እንዲሁም የጡረታና የሕክምና መብቶቻቸው ላይ ትኩረት ያደረገ ውሳኔና ምክረ ሐሳብ ማቅረቡን ቅሬታ አቅራቢዎቹ አመልክተው፣ ዳኞቹ የፈረዱትን ፍርድ የአገር መከላከያ ሚኒስቴር እንደቀለበሰው አስረድተዋል፡፡

ኮሚሽኑ ለኤጀንሲውና ለአገር መከላከያ ሚኒስቴር ካቀረባቸው ውሳኔና ምክረ ሐሳቦች መካከል የቀድሞ መንግሥት ጦር ሠራዊት አባላት የጡረታ መብት ጉዳይ ሲስተናገድበት ወይም ሲዳኝበት የቆየውና እስካሁን በሥራ ላይ ያለው የ1984 ዓ.ም. መመርያ በስያሜውና በዓላማው ላይ ለቀድሞ መንግሥት ሠራዊት አባላት የጡረታ መብት ተገቢውን ዕውቅና አልሰጠም፡፡ በጡረታ መዋጮ ተመላሽነት ጉዳይ ላይም በወቅቱ በተግባር ላይ በነበሩት የመንግሥት ሠራተኞች የጡረታ አዋጆች የተከበረውን መብት ያሳጣ ወይም የገደበና አድልኦዊ አሠራርን ለረዥም ጊዜ ፈጥሮ የቆየ ስለሆነ የመመሪያው ተፈጻሚነት እንዲቆም እንዲደረግ የሚል ውሳኔ ይገኝበታል፡፡

ከአሥር እስከ 19 ዓመት ያገለገሉትና ከተሰናበቱበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን የጡረታ መብት በአማራጭ ደግሞ የጡረታ መዋጮ ይመለስልን ጥያቄ ሲያቀርቡ የቆዩት የቀድሞ መንግሥት ሠራዊት አባላት ሁለቱንም አጥተው በአረጋዊ ዕድሜያቸው ለተለያዩ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች መጋለጣቸውን ሆኖም የእነሱ የጡረታ መብት ጉዳይ በአሁን ሰዓት በሥራ ላይ ባለው የመንግሥት ሠራተኞች የጡረታ አዋጅ እንዲስተናገዱ ቢደረግ ፍትሐዊ የሆነ ውሳኔ ላይ ለመድረስ እንደማይቻል አመላክቷል፡፡

በዚህም መሠረት የአቤቱታ አቅራቢዎችን የጡረታ ጉዳይ የሚመለከት ልዩ ሕግ እንዲወጣና የአሠራር ማሻሻያ ተደርጎ ዘለቄታ የጡረታ አበል እንዲከበርላቸው ኮሚሽኑ በሰነዘረው ምክረ ሐሳብ ላይ ጠይቋል፡፡ ከዚህም ሌላ ከ1987 ዓ.ም. በፊት የጡረታ መብታቸው የተከበረላቸው የሠራዊቱ አባላት እስካሁን ድረስ ተነፍገው በቆየው ሕክምና የማግኘት መብታቸው ላይ አስፈላጊ የሆነ የአሠራር ማሻሻያ ተደርጎ እንዲከበርላቸው ብሏል፡፡

እንዲሁም እስካሁን ሕክምና ተከልክለው የቆዩ የሠራዊቱን አባላት ለማስተናገድ በሚደረገው ሥራ ሊፈጠር የሚችለውን የሀብት እጥረት ለማቃለልና ለታካሚዎች ተደራሽ አገልግሎት ከመስጠት አኳያ ታካሚዎቹ በየአካባቢያቸው በሚገኙ የመንግሥት ሕክምና ተቋማት አገልግሎት እንዲያገኙ ቢደረግ አማራጭ መፍትሔ መሆኑ በምክረ ሐሳቡ ላይ ተመልክቷል፡፡

ብርጋዴር ጄኔራል ጥላሁን ክፍሌ የቀድሞ የምድር ጦር ሠራዊት አባላትና በመከላከያ የሲቪል ሠራተኞች መረዳጃ ዕድር ሰብሳቢ ናቸው፡፡ እንደ ሰብሳቢው፣ ኮሚሽኑ ከፍ ብሎ የተጠቀሰውን ውሳኔና ምክረ ሐሳብ ለሁለቱም ተቋማት ቢገለጽም የተገኘ መፍትሔ የለም፡፡ በዚህም የተነሳ የሠራዊቱን ጥያቄ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ወይም ለሚኒስትሮች ምክር ቤት እንዲቀርብ ዕድሩ ኮሚሽኑን ከመጎትጎት የቦዘኑበት ጊዜ የለም፡፡

ወደ ተጠቀሱት ምክር ቤቶች ከማምራት ይልቅ ከተሰናባቿ የመከላከያ ሚኒስትር ጋር በአካል ቀርቦ መወያየት የተሻለ ነው የሚል ሐሳብ ኮሚሽኑ ማቅረቡን፣ ይህም ሐሳብ ተቀባይነት በማግኘቱ የተነሳ የካቲት 19 ቀን 2011 ዓ.ም. ከተሰናባቿ የአገር መከላከያ ሚኒስትር ዓይሻ መሐመድ (ኢንጂነር) ጋር ውይይት እንደተደረገ ተናግረዋል፡፡

ተሰናባቹ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽነር አዲሱ ገብረ እግዚአብሔር (ዶ/ር)፣ የዕድሩ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት፣ የመከላከያ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ኮሎኔል ፍሥሐ ዘውዴ፣ የሕግ ክፍሉ ኃላፊ ኮሎኔል ዜናዊ ተሳታፊ በሆኑበት በዚሁ ውይይት የዕድሩን ገንዘብና ክበቦችን በተመለከተ ወደፊት እንዲታይ በተሳታፊዎች ስምምነት መደረጉን ብርጋዴር ጄኔራል ጥላሁን ገልጸው፣ የጡረታና የሕክምና መብቶች ጥያቄ ግን በፍጥነት አዎንታዊ መልስ እንዲሰጥበት ተሰናባቿ ሚኒስትር ለኃላፊዎቹ መመርያ ማስተላለፋቸውን አስረድተዋል፡፡

ይህም ሆኖ ግን የቀድሞ የምድር ጦር ሠራዊት አባላት የጡረታና የሕክምና መብት እስከዛሬ ድረስ ተዳፍኖ እንደቆየ ዕድሩ በተደጋጋሚ ጊዜ ቢያሳስብም እናየዋለን ከማለት በስተቀር መፍትሔ እንዳላገኘ ነው ሰብሳቢው የተናገሩት፡፡

የዕድሩ ሥራ አስፈጻሚ አባል ኮሎኔል ዓለማየሁ ንጉሤ፣ የቀድሞ የምድር ጦር ሠራዊት አባላት ማግኘት የሚገባቸው የጡረታ አበል በጣም ኢምንት መሆኑን ገልጸው፣ ይህንንም እንዳያገኙ የተፈጸመው አካሄድ እጅግ የሚያሳዝንና አሰቃቂ ተግባር መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ታጋዮች ወደ ትግል ከተቀላቀሉበት ጊዜ አንስቶ እስከ ግንቦት 1983 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ለፈጸሙት አገልግሎት እንደ አገልግሎታቸው ዓይነት ታስቦ የማኅበራዊ ድጋፍ ገንዘብ በመንግሥት እንዲሸፈን ሲደረግ፣ የቀድሞ የምድር ጦር ሠራዊት አባላት ግን እንዲህ ዓይነቱ መብት ተነፍጓቸው ማየቱ አካሄዱ ሁሉ ፍትሐዊ አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡

የዕድሩ ምክትል ጸሐፊ አቶ ዘሪሁን ተምትሜ፣ ‹‹አባላቱ በእርጅናና በድህነት ሳቢያ እየተጎሳቆሎ፣ እየተዳከሙና ለጤንነት መታወክና ለሞት እየተዳረጉ ናቸው፡፡ ጥያቄው ጊዜ ሳይወስድ ዕንባቸውን ሊያብስ ይገባል፤›› ብለዋል፡፡

የአገር መከላከያ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ኮሎኔል ፍሥሐ ዘውዴና የሕግ ክፍሉ ኃላፊ ኮሎኔል ዜናዊ  በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ እንዲሰጡን በስልክ ጠይቀናቸው ነበር፡፡ ኮሎኔል ፍሥሐ በሰጡት መልስ፣ ‹‹ጉዳዩ በሒደት ላይ ነው፡፡ ፍፃሜ ሲያገኝ በሕግ አግባብና በሕጉ መሠረት ይፋ ይሆናል፤›› ሲሉ ኮሎኔል ዜናዊ የመለሱት ደግሞ፣ ‹‹ጉዳዩን አላውቀውም፣ መልስም የለኝም፤›› በማለት ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...