የዓለም ጤና ድርጅት ጅምሩን የሚበረታታ ብሎታል
ዓለም አቀፍ የምግብና መጠጥ ጥምረት (ጥምረት) የዓለም ጤና ድርጅት እ.ኤ.አ. በ2023 ትራንስ ፋትን በኢንዱስትሪ ከሚቀነባበሩ ምግቦች ለማስወገድ ያስቀመጠውን ግብ ለማሳካት እንቅስቃሴ ጀመረ፡፡
በየዓመቱ ከትራንስ ፋት ጋር ተያይዞ በሚከሰቱ የልብና ደም ስር በሽታዎች የሚሞቱ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ሰዎችን ለመታደግ በኢንዱስትሪ ከሚቀነባበሩ ምግቦች ትራንስ ፋትን ማስወገድ ወሳኝ እንደሆነ ያስቀመጠው የዓለም ጤና ድርጅት፣ እ.ኤ.አ. በ2023 ትራንስ ፋትን በኢንዱስትሪ ከሚመረቱ ምርቶች ለማስወገድ ያስቀመጠውን ግብ ጥምረት ለማሳካት ፍላጎት ማሳየቱን የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ቴድሮስ አድሃኖም (ዶ/ር) የሚበረታታ ብለውታል፡፡
ትራንስ ፋትን ከምግብ ለማስወገድ በዓለም አቀፍ ደረጃ ምግብና መጠጥ ከሚያመርቱ 12 ያህል ትላልቅ ኩባንያዎች ኃላፊዎችና ከጥምረት ተወካዮች ጋር የመከሩት ዶ/ር ቴድሮስ፣ ትራንስ ፋትን ከምግብ ማስወድ ከባድ እንዳልሆነም ተናግረዋል፡፡
ኩባንያዎቹ ከሚቀነባበሩ ምግቦች ውስጥ ትራንስ ፋትን ብቻ ሳይሆን ጨው፣ ስኳርና ሳቹሬትድ ፋት እንዲቀነሱም ውይይት ተደርጓል፡፡
የምግብ ይዘት መግለጫ፣ ማስታወቂያና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችንም በተመለከተ የየአገሮች የቁጥጥር ሥርዓት በሚወሰደው ዕርምጃና ኩባንያዎች በተለይ በእናት ጡት ወተት ፋንታ ወይም ጎን ለጎን የሚሰጡ በፋብሪካ የሚቀነባበሩ የወተት ምርቶች ላይ አምራቾች ዓለም አቀፍ የጤና ድርጅት ለዘረጋው ሥርዓት ሙሉ ለሙሉ እንዲገዙ ማስቻል የውይይቱ አካል ነበሩ፡፡
የዓለም ጤና ድርጅት ያስቀመጠውን ትራንስ ፋትን ከምግብ የማስወገድን ግብ ተፈጻሚ ለማድረግ የጥምረትን እንቅስቃሴ እንደሚቆጣጠርና ለገቡት ቃል ዕውንነትም ድጋፍና ክትትል ከማድረግ እንደማይቆጠብ ዶ/ር ቴድሮስ ሳይናገሩ አላለፉም፡፡
ዓለም አቀፍ የምግብና መጠጥ አምራች ኩባንያዎች ጥምረት አባላት፣ በሚያቀነባብሩት ምግብና መጠጥ ውስጥ፣ የትራንስ ፋት መጠን በ100 ግራም ከሁለት ግራም እንዳይበልጥ የማድረጉን ሒደት እስከ 2023 ለማሳካት የወሰኑ ሲሆን፣ ይህም ጤናማ የምግብ አቅርቦትን ያረጋግጣል ተብሏል፡፡
የጥምረት አባላት ብቻ ሳይሆኑ በሁሉም አገሮች የሚገኙ ምግብ፣ ዘይትና ቅባትነት (ስብ) ያላቸው ምግብ ኩባንያዎች ትራንስ ፋትን ከምግብ አቅርቦት ውስጥ ለማስወገድ መሥራት እንዳለባቸው ድርጅቱ እ.ኤ.አ. በ2018 ላይ ጥሪ ማቅረቡ ይታወሳል፡፡
ይህንንም ተከትሎ በዴንማርክ፣ አርጀንቲና፣ ህንድ፣ አሜሪካና በሌሎችም አገሮች ትራንስ ፋትን በፋብሪካ ከሚቀነባበሩ ምግቦች ለማስወገድ እንቅስቃሴ ተጀምሮ ብዙ ለውጦች ተመዝግበዋል፡፡
በኢትዮጵያ በጉዳዩ ላይ ብዙ ጥናት ባይኖርም፣ ትራንስ ፋት በተፈጥሮም ሆነ በሰው ሠራሽ የምግብ ማቀነባበር ሒደት ስለሚኖር ትኩረት ተሰጥቶ ሊሠራበት እንደሚገባ በማሳሰብ የጤና ልማትና ፀረ ወባ ማኅበር ግንዛቤ ለመፍጠርና ፖሊሲ አውጪዎችና ተቆጣጣሪው አካላት ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥተው ደረጃ እንዲያወጡ ለማስቻል እንቅስቃሴ ከጀመረ ወራት ተቆጥረዋል፡፡
የጤና ሚኒስቴርም ከ90 እስከ 95 በመቶ ሽፋን ያለውንና በመንግሥት የሚደጎመውን ፓልም የሚረጋ ዘይት ለጤና ጠንቅ በመሆኑ በሌሎች ፈሳሽ ዘይቶች እንዲተካ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤትን መጠየቁ ይታወሳል፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤትም፣ የንግድ ሚኒስቴር የፓልም ዘይት በፈሳሽ የሚተካበትን ሁኔታ አጣርቶ እንዲያሳውቅ ከወራት በፊት ደብዳቤ ቢጽፍም፣ እስካሁን በፓልም ዘይት አቅርቦት ላይ የታየ ለውጥ የለም፡፡
ትራንስ ፋት ማለት ፈሳሽ የሆነ የምግብ ዘይት ወይም ቅቤ በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ እንዲረጋ ሲደረግ የሚፈጠር የስብ ዓይነት ነው፡፡ የዚህ ዓይነት የለውጥ ሒደት በተፈጥሮ ያለ ሰው ጣልቃ ገብነት በአነስተኛ መጠን የሚከሰት ቢሆንም፣ በፋብሪካ በሚመረትበት ሒደት ፈሳሽ በሆኑ የምግብ ዘይቶች ላይ የሃይድሮጂን ንጥረ ነገር በመጨመር በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ የረጉ ዘይቶች ወይም ቅባቶች እንዲሆኑ ማድረግ ለጤና ጠንቅ ነው፡፡
በሒደት የተዘጋጀ ዘይት ወይም ምግብ መጠቀም ምግቡን ለረዥም ጊዜ ጣዕሙ ሳይቀየር እንዲቆይ የሚያደርግ ቢሆንም፣ እንደ ቅቤ የጠጠሩና የረጉ የምግብ ዘይቶችን መመገብ የደም መጓጎል በማስከተል ደም ወደ ልብ፣ ወደ አንጎል እንዲሁም ወደ ተለያዩ የውስጥ አካል ክፍሎች በተፈለገው መጠን እንዳይደርስ ስለሚያደርግ ለድንገተኛ ልብ ሕመምና ለአንጎል ላይ ደም መፍሰስ በአጠቃላይም ከደም ስር ቱቦዎች ጋር ለተያያዙ ሕመሞች ያጋልጣል፡፡
ትራንስ ፋት በሰውነት ውስጥ የሚገኙትን ጥሩ ኮሌስትሮሎች እንዲቀንሱ በማድረግ በምትካቸው መጥፎ ኮሌስትሮሎች እንዲበዙ ያደርጋል፡፡ እነዚህ ጥሩ የሚባሉት ኮሌስትሮሎች ጠጣር የሆኑ ቅባታማ ምግቦችን ወደ ጉበት በማጓጓዝ እንዲፈጩና ከሰውነት በፈሳሽ መልክ እንዲወገዱ ያደርጉታል፡፡ በአንጻሩ መጥፎ የሚባሉት የኮሌስትሮል ዓይነቶች ያልተፈጨውን ቅባት በደም ውስጥ በማዝቀጥ ደም እንዲጓጉል ያደርጋሉ፡፡
የዓለም ጤና ድርጅትም በየዓመቱ ከትራንስ ፋት ጋር በተያያዙ ሕመሞች የሚሞቱትን ግማሽ ሚሊዮን ሰዎች ለመታደግ ግብ አስቀምጧል፡፡ በልብ ሕመም ከሚሞቱት 35 በመቶ መካከልም 28 በመቶ በትራንስ ፋት ሳቢያ የሚከሰት መሆኑን አመልክቷል፡፡