‹‹ሰዋዊ›› በሚል ርዕስ ገቢው ለተፈናቀሉ ወገኖች የሚውል የሙዚቃ ኮንሰርት ግንቦት 17 ቀን 2011 ዓ.ም. በቅርቡ በተመረቀው የስካይ ላይት ሆቴል ሊካሄድ ነው፡፡
እስከ 4,000 ሰው የመያዝ አቅም ባለው አዲሱ ሆቴል የተዘጋጀው ይህ ኮንሰርት ‹‹ሰው መሆን ይቅደም›› የሚል ዓላማ አንግቦ የተነሳ ሲሆን ስለፍቅርና ስለአብሮ መኖር ለማወቅ ሰው መሆን ብቻ በቂ ነው የሚለውን መልዕክት በኪነጥበብ ለማስተላለፍ አቅዷል፡፡
ይሳቃል ኢንተርቴይመንት ከሃይነከን ኢትዮጵያ ጋር በጋራ ያዘጋጁት ይህ የሙዚቃ ድግስ ድምፃውያኑ መሐሙድ አህመድ፣ ነፃነት መለሰ፣ ታደለ ገመቹ፣ ሰሎሞን ኃይለ፣ ልጅ ሚካኤል፣ ብስራት ሱራፌል፣ ጃኖ ባንድ፣ አስጌ ዳንዲሾ እና ራሔል ጌቱ የሚሳተፉበት ይሆናል፡፡ ሰዋዊ ማለት ሰው መሆን ማለት ነው የሚሉት አቶ ኢዮብ ዓለማየሁ የይሳቃል ኢንተርቴይመንት ማኔጂንግ ዳይሬክተር፣ ‹‹ሰው ለመርዳት ሰው መሆን በቂ ነው፡፡ ሰው ስንሆን ሌሎች ነገሮች ትርፍ ናቸው፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡
የመግቢያ ዋጋው 600 ብር የሆነው ይህ ኮንሰርት፣ ‹‹ዋጋው ተመጣጣኝ ነው፤ ዓላማውን በጎ አድራጎት ላይ አድርጎ ከመነሳቱ አንፃር ዋጋው የሰውን አቅም ሳይሆን የሰውን ችግር ያገናዘበ ነው፤›› ሲሉ አቶ ኢዮብ ገልጸዋል፡፡
‹‹ከኮንሰርቱ የሚሰበሰበው የቲኬት ሽያጭ መሉ በሙሉ ገቢው ለኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ሲሆን ከቀዬአቸው ለተፈናቀሉ ወገኖቻችን መርጃ የሚውል ይሆናል፤›› ያሉት ደግሞ አቶ ፍቃዱ በሻህ የሃይነከን ኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ሥራ አስኪያጅ ናቸው፡፡ ሰዋዊ ኮንሰርትን በማስመልከት ግንቦት 6 ቀን በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት ገጣሚ ሰናይት ጣፈጡ ከነጋሪት ባንድ ጋር በመሆን በዘር የመከፋፈልን አስከፊ ገጽታ እንዲህ በማለት ገልጻዋለች፡፡
‹‹…ቀስት ተወርውሮ በዱላ ተወግሮ ለሞተው ወንድምህ
ከሸንጎ ፊት ቀርበህ ፍትሕን ልትጠይቅ
ገዳይ ማነው ተብለህ አንተም ስትጠየቅ
ገዳይ ወንድሜ ነው ሟችም ወንድሜ ነው
ብለህ ልትመልስ ነው?
ከቤት ተፈናቅላ ለወጣች እህትህ
ቤት ንብረቷን ትታ ለሸሸች እናትህ
ማን አረገው ሲሉህ ዘር መቁጠር ከጀመርክ
ያኔ አንተም ገዳይ ነህ፣
መድኃኒት ነው ያልነው የዘር በሽታችን
መድኃኒት ነው ያልነው በሽታ የሆነን
ከሕመሙ በላይ ፈውሱ ነው ያቆሰለን፡፡…›