Wednesday, May 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊበግድቦች በተከሰተ ውኃ እጥረት የኤሌክትሪክ ኃይል በፈረቃ ማዳረስ ተጀመረ

በግድቦች በተከሰተ ውኃ እጥረት የኤሌክትሪክ ኃይል በፈረቃ ማዳረስ ተጀመረ

ቀን:

ለሱዳን የሚሄደው የኤሌክትሪክ ኃይል ተቋረጠ

በኃይድሮ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድቦች የገባው የውኃ መጠን በመቀነሱ ምክንያት፣ ከግንቦት 1 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ በፈረቃ ኃይል ማዳረስ መጀመሩ ይፋ ተደገ፡፡ ክረምቱ ቶሎ ስለማይገባ ፈረቃው እስከ ሰኔ 30 ቀን 2011 ዓ.ም. ይቀጥላል ተብሏል፡፡

ዓርብ ግንቦት 9 ቀን 2011 ዓ.ም. የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ስለሺ በቀለ (ዶ/ር) እና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሽፈራው ተሊላ ጉዳዩን አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

- Advertisement -

ሚኒስትሩ እንዳሉት በ2010 ዓ.ም. ክረምት በተለይ ጊቤ ሦስት፣ ቆቃና መልካ ዋከና ግድቦች በቂ ውኃ አልያዙም፡፡ በአንፃሩ ጣና በለስ፣ ተከዜ፣ ፊንጫ፣ ጊቤ አንድና አመርቲ ነሼ ግድቦች የተሻለ ውኃ ይዘው ነበር፡፡

ነገር ግን የበልግ ዝናብ በሚፈለገው መጠን ባለመጣሉ ግድቦቹ የያዙት የውኃ መጠን ቀንሶ፣ ኃይል ለማመንጨት አቅም አንሷቸዋል ሲሉ ሚኒስትሩ የችግሩን ምክንያት አስረድተዋል፡፡

በዚህ መሠረት ከግንቦት 1 ቀን ጀምሮ እስከ ሰኔ 30 ቀን 2011 ዓ.ም. ድረስ ተግባራዊ የሚደረግ የፈረቃ ፕሮግራም ተግባራዊ ተደርጓል፡፡

በአሁኑ ወቅት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች አማካይ የማመንጨት አቅማቸው ወደ 1,400 ሜጋ ዋት ወርዷል፡፡ በተጨማሪ የብሔራዊ ሚቲዮሮሎጂ ትንበያ እንደሚያመለክተው ቀጣዩ ክረምት በቶሎ አይገባም፡፡

አቶ ሽፈራው እንደገለጹት፣ በእነዚህ ምክንያቶች በአገሪቱ ከፍተኛ የኃይል አቅርቦት ክፍተት ተፈጥሯል፡፡ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ችግር በመፈጠሩ በሦስት ምዕራፍ የተከፈለ ፈረቃ ይፋ ተደርጓል፡፡

በዚህ መሠረት ከፍተኛ የኃይል ጭነት ባለባቸው ከንጋቱ 11 ሰዓት እስከ ረፋዱ አምስት ሰዓት 514 ሜጋ ዋት፣ ከቀኑ አምስት ሰዓት እስከ አሥር ሰዓት 530 ሜጋ ዋት፣ ከቀኑ አሥር ሰዓት እስከ ምሽቱ አራት ሰዓት 700 ሜጋ ዋት፣ አማካይ የኃይል አቅርቦት ክፍተት እየተፈጠረ ነው ተብሏል፡፡

በመግለጫው እንደተጠቆመው የተፈጠረውን የኃይል አቅርቦት ክፍተት ለማስተዳደር፣ በአሁኑ ጊዜ በግድቦች ውስጥ ያለውን ውኃ እስከ ሰኔ 30 ቀን 2011 ዓ.ም. ወይም ውኃ ወደ ግድቦች መግባት እስኪጀምር ድረስ ከኤክስፖርት፣ ከምግብ ማቀነባበርያ፣ ከመድኃኒት ፋብሪካዎች፣ ከዩኒቨርሲቲዎችና ከማኅበራዊ አገልግሎት ማለትም ከመጠጥ ውኃና ከመሳሰሉ ምርቶች በስተቀር ለሌሎቹ የፈረቃ ሥርዓት ተበጅቷል፡፡

የመጀመርያው የከፍተኛና የመካከለኛ የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ የሆኑ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ካላቸው የሥራ ባህሪ የተነሳ ለተከታታይ ቀናት የኤሌክትሪክ ኃይል ሳይቋረጥባቸው መሥራት ስላለባቸው፣ 50 በመቶ የሚሆኑት ከግንቦት 7 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ በየአሥራ አምስት ቀናት በፈረቃ ኃይል እንዲጠቀሙ መደረጉ ተጠቁሟል፡፡

ሁለተኛው ከሰብስቴሽን በቀጥታ የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያገኙ የብረታ ብረትና ሌሎች መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች 50 በመቶ የሚሆኑት በ24 ሰዓት ፈረቃ ፕሮግራም እንዲሠሩ ተወስኗል፡፡

ሦስተኛ የድንጋይ ወፍጮዎች በግንቦትና በሰኔ የኤሌክትሪክ ኃይል እንዳይጠቀሙ ተወስኗል፡፡ አራተኛ ለሱዳን የሚቀርበው የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ መጠን መቶ በመቶ እንዲቆም፣ እንዲሁም ለጂቡቲ የሚደረገው የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት 50 በመቶ እንዲቀነስ ተወስኗል፡፡

ሱዳን አሥር በመቶ የሚሆነውን የኃይል ፍላጎቷን ከኢትዮጵያ በምታገኘው ኃይል የሚሸፈን እንደነበር ተገልጿል፡፡ ከዚህ የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭም ኢትዮጵያ በዓመት 182 ሚሊዮን ዶላር ታገኝ ነበር፡፡ የኃይል ሽያጩ በመቋረጡም ኢትዮጵያ ይህንን ገንዘብ ታጣለች፡፡ በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ ኃይል የሚያመነጨው ጊቤ ሦስት ነው፡፡ ጊቤ ሦስት ኃይል ማመንጫ ግድብ ባለፈው ዓመት ከባህር ጠለል በላይ 834 ሜትር ከፍታ ነበረው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ከፍታው ከባህር ጠለል በላይ 818 ሜትር ወርዷል ተብሏል፡፡

በሁለቱ ዓመታት ውስጥ የ16 ሜትር ልዩነት ያለው ሲሆን፣ ኃይል ማምረት የሚቻለው እስከ 800 ሜትር ድረስ ብቻ በመሆኑ፣ ከዚህ በታች ጥቅም ላይ ቢውል በተርባይኖች ላይ ጉዳት ሊያስከትል እንደሚችል ተገልጿል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...