Saturday, December 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናዋስትና የተከለከሉ የደኅንነት ተቋም የቀድሞ ሠራተኞች የአካል ደኅንነታቸው በሚጠበቅበት ቦታ እንዲቆዩ ትዕዛዝ...

ዋስትና የተከለከሉ የደኅንነት ተቋም የቀድሞ ሠራተኞች የአካል ደኅንነታቸው በሚጠበቅበት ቦታ እንዲቆዩ ትዕዛዝ ተሰጠ

ቀን:

ሐሰተኛ ዘገባ አስተላልፈዋል የተባሉ ሚዲያዎች በከባድ ተግሳጽ ታለፉ

እነ አቶ ጌታቸው አሰፋ (አራት ተከሳሾች) ላይ በድጋሚ ትዕዛዝ ተሰጠ

በፌዴራል ዓቃቤ ሕግ የከባድ ሰብዓዊ መብት ጥሰትና የሙስና ወንጀሎች ክስ የተመሠረተባቸው የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት የቀድሞ የተለያዩ ክፍል ሠራተኞች የጠየቁትን ዋስትና ፍርድ ቤት ሳይቀበለው ቀረ፡፡ ዋስትና መከልከላቸውን ተከትሎ በሚቆዩበት ማረሚያ ቤት ጉዳት ሊደርስባቸው እንደሚችል ሥጋታቸውን ለፍርድ ቤቱ በመግለጻቸው፣ የአካል ደኅንነታቸውና የሰብዓዊ መብታቸው በሚከበርበት በቃሊቲ ማረሚያ ቤት እንዲቆዩ ትዕዛዝ ተሰጠ፡፡

ላለፉት ስድስት ወራት በፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ ሥር በሚገኝ ማቆያ ቦታ የከረሙት የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት የቀድሞ ምክትል ዳይሬክተር አቶ ያሬድ ዘሪሁንን ጨምሮ 22 ተከሳሾች ዋስትና ተከልክለው፣ ከግንቦት 9 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ በፌዴራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ቃሊቲ ማረሚያ ቤት እንዲቆዩ ትዕዛዝ ተሰጥቷል፡፡

ተከሳሾቹ ዋስትና መከልከላቸውን ካወቁ በኋላ ለፍርድ ቤቱ በአቶ ቢኒያም ማሙሸትና በአቶ ነጋ ካሴ አማካይነት እንዳስረዱት፣ እጃቸው ከተያዙበት ጥቅምት 30 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ በተለያዩ መገናኛ ብዙኃንና ድረ ገጾች ስለእነሱ በተላለፈው ዘገባ በኅብረተሰቡ ውስጥ ያለው ብቀላ ነው፡፡ ምክንያቱም ሚዲያው አስቀድሞ ወንጀለኛ እንዳደረጋቸው፣ ሚዲያው ባቀረበባቸው መጥፎ ምሥልም ለዕርድ እንዳቀረባቸው አስረድተዋል፡፡ በዚህ ሁኔታ ወደ ቂሊንጦ ማቆያ እስር ቤት ቢላኩ፣ የአካልም ሆነ የሰብዓዊ መብት ጉዳት ይደርስብናል የሚል ሥጋት እንዳላቸውም አክለዋል፡፡ ለዚህም ማረጋገጫ የሚሆነው ከእነሱ ጋር አብረው ታስረው የነበሩና አሁን የክስ መዝገባቸው ተለይቶ ክርክር እያደረጉ የሚገኙት የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች የቀድሞ ሠራተኞች፣ የፌዴራልና የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ባልደረባ የነበሩ ተከሳሾች ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት እንዲቆዩ ተልከው፣ ቀደም ብለው በታሰሩና በእነሱ ላይ ጥሩ ምልከታ በሌላቸው ሌሎች ታሳሪዎች ጉዳት እንደ ደረሰባቸውና ወደ ቃሊቲ ማረሚያ ቤት እንደተቀየሩ ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል፡፡ በመሆኑም በእነሱም ላይ ተመሳሳይ ድርጊት ሊፈጸም እንደሚችልና ሥጋትም ስላላቸው፣ የአካል ደኅንነታቸውና ሰብዓዊ መብታቸው በሚከበርበት ቃሊቲ ማረሚያ ቤት እንዲቆዩ እንዲታዘዝላቸው ጠይቀዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ እስረኞች ስለቆይታቸው ባቀረቡት ጥያቄ ላይ ዓቃቤ ሕግ አስተያየት እንዲሰጥ ጠይቆ፣ ፍርድ ቤቱ በሚያዘው መሠረት የአካል ደኅንነታቸው በሚጠበቅበት ቦታ ቢታሰሩ ተቃውሞ እንደሌለው ገልጿል፡፡

በሌላ በኩል የፌዴራል ፖሊስ ለብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት የቀድሞ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው አሰፋ፣ አቶ አጽብሃ ግደይ፣ አቶ አሰፋ በላይና አቶ ሸሻይ ልዑል መጥሪያ እንዲያደርስ ትዕዛዝ መስጠቱን ፍርድ ቤቱ አስታውሶ ምላሹን ቢጠይቅም ምላሽ የሚሰጥ አካል አልተገኘም፡፡ ዓቃቤ ሕግም ሲጠየቅ እንዲከታተልም ሆነ ሌላ ትዕዛዝ እንዳልተሰጠው ተናግሯል፡፡

ተከሳሾች ግን በጠበቆቻቸው አማካይነት የተቃውሞ አቤቱታ ለፍርድ ቤቱ አቅርበዋል፡፡ የክስ መዝገቡ ባለቤት ዓቃቤ ሕግ መሆኑን የጠቆሙት ጠበቆቹ፣ ፍርድ ቤቱ የሰጠውን ትዕዛዝ ተከታትሎ ውጤቱን ማምጣት ሲገባው፣ የሰጠው ምላሽ አሳማኝ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም ትዕዛዙ ታልፎ ሌላ ትዕዛዝ እንዲሰጥም ጠይቀዋል፡፡ ዓቃቤ ሕግ ያልቀረቡትን እነ አቶ ጌታቸውን ነጥሎ ለመክሰስ ወይም ክሱን ከሌሎቹ ለመነጠል የሚከለክለው ሕግ ስለሌለ፣ ከመዝገቡ በመለየት የክርክር ሒደቱ በተፋጠነ ሁኔታ እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡

ለጠበቆቹ አቤቱታ ምላሽ የሰጠው ዓቃቤ ሕግ ‹‹ስላልቀረበ ይታለፍ የሚባለው ኤግዚቢት ብቻ ነው›› በማለት ድጋሚ ትዕዛዝ መሰጠቱ እንዲታለፍ መጠየቁ አግባብ እንዳልሆነ አስረድቷል፡፡  

በሌሉበት የተከሰሱትን በሚመለከት ለምስክርና ለተጠርጣሪ ማን መጥሪያ እንደሚያደርስ በሕግ ተደንግጎ እንደሚገኝ ጠቁሞ፣ ዓቃቤ ሕግ ፌዴራል ፖሊስን ተከታትሎ እንዲያቀርብ የሚያደርግበት ሕግም ሆነ አሠራር እንደሌለ በመግለጽ ምላሽ ሰጥቷል፡፡

ሌላው ፍርድ ቤቱ በትዕዛዝ ያስቀረባቸውና ትዕዛዝ ሳይሰጥ በሌሉበት ክስ የተመሠረተባቸው እነ አቶ ጌታቸው አሰፋ (አራት ሰዎች)፣ ‹‹በፌዴራል ፖሊስ በኩል መጥሪያ ደርሷቸው እንዲቀርቡ›› ተብሎ የተሰጠውን ትዕዛዝ፣ ‹‹ታስረው እንዲቀርቡ ታዘዘ›› በማለት ሐሰተኛ ዘገባ ሠርተዋል ያላቸው ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን፣ የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተርና ሸገር ኤፍኤም 102.1 በችሎት ቀርበው ማብራሪያ እንዲሰጡ አድርጓል፡፡ ተቋማቱን ወክለው የቀረቡት ግለሰቦችም ያስተላለፉት ዘገባ የሐሰት መሆኑን አምነው፣ በድጋሚ ተመሳሳይ ስህተት እንደማይሠሩ ቃል በመግባት ፍርድ ቤቱን ይቅርታ ጠይቀዋል፡፡ በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 451 ድንጋጌ መሠረት ሐሰተኛ ዘገባ (ወሬ) ለኅብረተሰቡ ማስተላለፍ እንደሚያስቀጣ ጠቁሞ፣ ያስጠራቸው በሚዲያ ላይ ተፅዕኖ ለመፍጠር አለመሆኑን እንዲገነዘቡ ገልጿል፡፡ ሚዲያ የሰማውንና ያየውን ብቻ በትክክል ጽፎ ለሕዝቡ ማድረስ እንዳለበትም አሳስቧል፡፡ ፍርድ ቤቱ ሕግና ሥርዓት እንደሚያስከብር ገልጾ፣ ገና ከጅምሩ መጥሪያ ሳይደርስና ውጤቱ ተገልጾ ድጋሚ ትዕዛዝ ሳይሰጥ የሐሰት ዘገባ መዘገብ እንደሌለበት አስታውቋል፡፡ በሚመለከተው አካል በወንጀል ሕጉ ድንጋጌ መሠረት ተጣርቶ ይቅረብ ብሎ ትዕዛዝ ከመስጠትና ተጠያቂ ከማድረግ ይልቅ፣ ጠርቶ የሐሳብ ክፍሉን መስማት ተፈልጎ መሆኑን በመንገር በድጋሚ ተመሳሳይ ነገር እንዳይፈጠር በማስጠንቀቅ በብርቱ ምክርና ተግሳጽ እንዳለፋቸው ገልጿል፡፡ ‹‹ሕግን አለማወቅ ከተጠያቂነት አያድንም፤›› ብሏቸዋል፡፡  

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ሠራተኛ የነበሩት አቶ ሰይፈ በላይ፣ በቀረበባቸው ክስ ላይ ባቀረቡት የመጀመርያ የክስ መቃወሚያ ላይ ዓቃቤ ሕግ አስተያየት እንዲሰጥ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

የግራ ቀኙን ክርከር የሰማው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አንደኛ ወንጀል ችሎት በሰጠው ትዕዛዝ፣ የፌዴራል ፖሊስ በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 123 ድንጋጌ መሠረት በሌሉበት ክስ ለተመሠረተባቸው እነ አቶ ጌታቸው (አራት ሰዎች) በአድራሻቸው አፈላልጎ መጥሪያ እንዲያደርስና ቃቤ ሕግም ጉዳዩን ተከታትሎ እንዲያስፈጽም አስታውቋል፡፡

ዓቃቤ ሕግ በዕለቱ እንዲያቀርብ ትዕዛዝ ተሰጥቶት የነበረውን የሲዲ ማስረጃ በሚመለከት ለሁሉም ተከሳሾች በሚደርስ ሁኔታ አባዝቶ እንዲያቀርብ፣ ተከሳሾች በፍርድ ቤት ጥፋተኛ እስከሚባሉ ድረስ ንፁህ ሆነው የመቆጠር ሕገ መንግሥታዊ መብታቸው፣ ክርክሩ እየተደረገ ባለበት በየትኛውም ደረጃ (ከፍርድ በፊትም ሆነ በኋላ) ሰብዓዊ መብታቸው ተጠብቆና የአካል ደኅንነታቸው ተረጋግጦ መያዝ እንዳባቸው ፍርድ ቤቱ በእጅጉ እንደሚያምን ገልጿል፡፡

ሕገ መንግሥቱን ጨምሮ በሌሎች ሕጎችም ያለው ይኸው መሆኑን ጠቁሞ፣ ቀደም ሲል ከነበራቸው የሥራ ኃላፊነት አንፃር ተከሳሾቹ ጉዳያቸውን በአዲስ አበባ ማረሚያ ቤት (ቃሊቲ) ሆነው እንዲከታተሉ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ የተከሳሽ ጠበቆች ዓቃቤ ሕግ በአዋጅ ቁጥር 699/2003 ድንጋጌ መሠረት ስለምስክሮቹ ባቀረበው አቤቱታ ላይ አስተያየታቸውን እንዲያቀርቡ በመንገር፣ ሁሉንም ትዕዛዞች ለመጠባበቅ ለግንቦት 16 ቀን 2011 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡          

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...