በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል አብዛኞቹ የተማሪ ሐኪሞች በሥራ ገበታቸው ላይ አልተገኙም
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ቅዳሜ ሚያዝያ 26 ቀን 2011 ዓ.ም. ከሕክምና ባለሙያዎች ጋር ባደረጉት ውይይት ወቅት፣ መሠረታዊ የኢትዮጵያ የጤና ዘርፍ መሠረታዊ ችግሮች አለመነሳታቸውን የኢትዮጵያ ሕክምና ማኅበር አስታወቀ፡፡ በውይይቱ የተነሱ ጥያቄዎችም በአመዛኙ ግለሰባዊ እንደነበሩ የማኅበሩ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ገመቺስ ማሞ አስረድተዋል፡፡
ከውይይቱ በኋላ ሰኞ ሚያዝያ 28 ቀን 2011 ዓ.ም. ጤና ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ ለተነሱ ጥያቄዎች መፍትሔ ተብለው የቀረቡ ምላሾች፣ ማኅበሩ ከወራት በፊት ከሚኒስቴሩ ጋር ሲደራደርባቸው የቆዩና ምላሽ የተሰጠባቸው እንደነበሩ ፕሬዚዳንቱ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
እንደ ማኅበሩ ፕሬዚዳንት ገለጻ በመድረኩ ከተነሱ የሐኪሞች ጥያቄዎች መካከል የሕክምና ተማሪዎች የትምህርት ማስረጃቸውን ለማግኘት መክፈል ስለሚጠበቅባቸው 470 ሺሕ ብር የወጪ መጋራት ገንዘብን በተመለከተ፣ ማኅበሩ ከአራት ወራት በፊት ተደራድሮ ውሳኔ የተሰጠበት ነበር፡፡ የሐኪሞች ምደባን በተመለከተም ማኅበሩ ከሚኒስቴሩ ጋር ተወያይቶ ከወራት በፊት መቋጫ ያገኘ ጉዳይ ነበር ብለዋል፡፡ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በነበረው የውይይት መድረክ ‹‹ማኅበራት ጥያቄ እንዲያነሱ ዕድል ስላልተሰጣቸው ዋና ዋና ጥያቄዎች አልተነሱም፡፡ ይህ ማለት ግን ሐኪሞቹ ያነሷቸውን ጥያቄዎች በሙሉ አንስማማባቸውም ማለት አይደለም፤›› ብለዋል፡፡
ማኅበሩ መሠረታዊ የጤና ችግሮች ብሎ ከሚያምንባቸውና የጠቅላይ ሚኒስትሩን ትኩረት ከሚሹት መካከል፣ ለጤና ክብካቤ የሚውለው የገንዘብ መጠን (Healthcare Financing) አንዱ ነው፡፡ የኢትዮጵያ የጤና ችግር ውስብስብና ጠንካራ በጀት የሚጠይቅ ቢሆንም፣ የሚበጀትለት ግን ከችግሩና ከጫናው አንፃር አነስተኛ እንደሆነ፣ በአመዛኙ በውጭ ድርጅቶች ላይ የተመሠረተና አስተማማኝነት እንደሚጎድለው ዶ/ር ገመቺስ አስረድተዋል፡፡
የሕክምና ትምህርት ጥራትና የትምህርት ቤቶች ቅበላ በአገር ደረጃ ትኩረት የሚሻ ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡ ‹‹በየዓመቱ ሦስት ሺሕ ሐኪሞችን እያስመረቁ ነው፡፡ በዚህ መሀል ግን የትምህርት ጥራቱ ተዘግንቷል፡፡ አንዳንዶቹ የሕክምና ትምህርት ቤቶች መባል አይገባቸውም፤›› ያሉት ዶ/ር ገመቺስ፣ በቂ መምህራንና ላቦራቶሪ ሳይኖራቸው ተማሪዎችን የሚቀበሉ ትምህርት ቤቶች እንዳሉ፣ እነዚህም በጥናት ተለይተው አቅም እንዲኖራቸውና ከሌሎች ጋር እንዲዋሀዱ ጠይቀዋል፡፡
በዚህ ረገድ በተደረጉ ተደጋጋሚ ውይይቶች ምክንያት፣ የሕክምና ትምህርት ቤቶችን የሚቀላቀሉ ተማሪዎች ቁጥር በግማሽ እንዲቀንስ መደረጉ ተገልጿል፡፡ በ28 የሕክምና ትምህርት ቤቶች ሦስት ሺሕ ተማሪዎች ይመዘገቡ እንደነበር፡፡ ከዚህ ዓመት ጀምሮ ግን የተማሪ ቅበላቸውን በግማሽ እንዲቀንሱ መደረጉን ዶ/ር ገመቺስ ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡ በየዓመቱ የሚመረቁ ሐኪሞችን መቀበል የሚችል ተቋም እንዲኖርም ጠይቀዋል፡፡ መድኃኒቶችና ልዩ ልዩ የሕክምና ግብዓቶች እጥረት መንሰራፋቱም፣ መንግሥት ለጤናው ዘርፍ ቅድሚያ ሰጥቶ እንዲሠራ ያስገድደዋል ብለዋል፡፡
መንግሥት ምላሽ ሲሰጥ የሚታየው በማኅበራዊ ሚዲያው ለሚንቀሳቀሱ ቡድኖች ነው ያሉት ዶ/ር ገመቺስ፣ ሕጋዊ መሠረት ኖሯቸው ከሚንቀሳቀሱ ማኅበራት ጋር እንዲወያይና አስፈላጊውን ምላሽ እንዲሰጥም ጠይቀዋል፡፡ ‹‹ጥያቄዎቻችን በሒደት ምላሽ የሚያገኙ ናቸው፡፡ በአንድ ጀንበር ምላሽ ካልተሰጠን አንልም፤›› ብለዋል፡፡ በሌላ በኩል፣ ‹‹ለሕክምናው መዳከም ተጠያቂው መንግሥት ራሱ ሆኖ ሳለ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ‹ምን ሕክምና አለ?› ሲሉ ባለሙያዎችን መውቀሳቸው ብዙዎችን አሳዝኗል፤›› በማለት ቅሬታቸውን ገልጸዋል፡፡
ሐኪሞችን በአንድነት ጨፍልቀው ወቀሱ እንጂ በምን ዓይነት ሁኔታ እየሠሩ እንዳሉ ከግምት እንዳላስገቡ፣ አርዓያነት ያላቸው በሳል ሐኪሞች መኖራቸውን እንደዘነጉና በአጠቃላይ ሁሉንም በደፈናው መውቀሳቸው በርካታ ባለሙያዎችን እንዳሳዘነ ዶ/ር ገመቺስ አስረድተዋል፡፡
ይህ በዚህ እንዳለ ‹ጥያቄያችን አልተመለሰም› ያሉ የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የቅድመና የድኅረ ምረቃ ሐኪሞች ከሥራ መቅረታቸው መነጋገሪያ ሆኗል፡፡ ዕጩ ሐኪሞቹ ከሚያዝያ 28 ቀን 2011 ዓ.ም. አድማ እንደመቱ ከርመዋል፡፡
ረቡዕ ግንቦት 7 ቀን 2011 ዓ.ም. ሆስፒታሉ በሰጠው መግለጫ፣ ሐኪሞቹ አድማውን ሲያደርጉ የቀረበለት ጥያቄም ሆነ ማስጠንቀቂያ የለም ብሏል፡፡ ‹‹የምንደራደረው ከማናየውና ከማንጨብጠው አካል ጋር ነው፤›› ያሉት የሆስፒታሉ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶ/ር ዳዊት ወንድማገኝ፣ በሆስፒታሉ ሥራ ላይ ግን ይህ ነው የሚባል መስተጓጎል እንዳልተፈጠረ ገልጸዋል፡፡
አፋጣኝ ሕክምና ከሚጠይቁ የድንገተኛ ሕሙማንና የድንገተኛ ማዋለጃ ክፍል፣ እንዲሁም ከፅኑ ሕሙማን ማቆያ ውጪ ባሉት ቦታዎች ሐኪሞች እንዳልነበሩ የገለጹ ማንነታቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ ሐኪም፣ በሌሎቹ የሕክምና ክፍሎችም መስተጓጎል እንደነበር ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ አገልግሎቱን የሚሰጡ 90 በመቶ ያህሉ የድኅረ ምረቃ ሐኪሞች በሥራ ምድባቸው ላይ እንዳልነበሩም አክለዋል፡፡
የሆስፒታሉ አስተዳደር አባላት ሐሙስ ግንቦት 8 ቀን 2011 ዓ.ም. የድኅረ ምረቃ ሐኪሞችን ስብሰባ ቢጠሩም፣ ከ1,200 ሐኪሞች መካከል በስብሰባው የተገኙት 55 እንደሆኑና ሌሎቹ፣ ‹‹ጥያቄያችን ሆስፒታሉ ውስጥ ባሉ የአስተዳደር አካላት ደረጃ የሚመለስ አይደለም፤›› ብለው መቅረታቸው ተገልጿል፡፡
ሚያዝያ 26 ቀን 2011 ዓ.ም. ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ውይይት ከተካሄደ በኋላ ጤና ሚኒስቴር ያወጣው መግለጫ፣ ጥያቄያቸውን በአግባቡ እንደማይመልስ ሐኪሞች እየገለጹ ነው፡፡ አንዳንድ ጥያቄዎች የተመለሱ ቢመስሉም፣ በጥሞና ሲታዩ መልስ አይደሉም ያሉ አሉ፡፡
‹‹የሥራ ማቆም አድማ አድርገን አናውቅም፣ አናደርግምም፡፡ በሕግ ስለምንታዘዝ ሳይሆን የምንገዛበት ሞራል አለን፡፡ ሕክምና ሥራ ማቆም የማይፈቅድለት የሥራ መስክ ነው፤›› ያሉት የሕክምና ማኅበሩ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ገመቺስ፣ ‹‹እኛ ስለአድማው የምናውቀው ነገር የለም፤›› ብለዋል፡፡
ለዓመታት ሲታገሉለት የነበረ ጥያቄ ምላሽ በማጣቱ ያላቸው ብቸኛ አማራጭ ሥራ ማቆም ነው በሚል እምነት ሐኪሞቹ አድማ ለመምታት እንደወሰኑ መጠርጠራቸውን ገልጸው፣ ‹‹ይኼም ቢሆን ትክክል አይደለም፤›› ብለዋል፡፡
የሆስፒታሉ አመራሮች በበኩላቸው የሐኪሞች ሥራ የማቆም ዕርምጃ ተቀባይነት ባይኖረውም፣ የሚያነሷቸው ጥያቄዎች ግን አግባብነት እንዳላቸው እንደሚያምኑ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡