Monday, September 25, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የአዲስ አበባ ገቢዎች ባለሥልጣን በዘጠኝ ወራት ከ1,400 በላይ ታክስ አጭበርባሪዎች ዕርምጃ እንደተወሰደባቸው አስታወቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ባለፈው ሳምንት አራት የሴራሚክ አከፋፋዮች እጅ ከፍንጅ ተይዘዋል

በዓመት የአሥር በመቶ የታክስ ገቢ ጉድለት በታክስ ማጭበርበር እንደሚታጣ ይገመታል

የአዲስ አበባ ከተማ ገቢዎች ባለሥልጣን ረቡዕ ግንቦት 7 ቀን 2011 ዓ.ም. ባካሄደው ድንገተኛ የመስክ ኦፕሬሽን አራት ከፍተኛ ግብር ከፋይ የሴራሚክ አከፋፋዮች ያለ ደረሰኝ ግብይት በመፈጸም የታክስ ማጭበርበር ወንጀል ሲፈጽሙ እጅ ከፍንጅ መያዙን፣ በዘጠኝ ወራት ውስጥም በ1,439 ግብር ከፋዮች ላይ ዕርምጃ መውሰዱን አስታወቀ፡፡

ኢኮኖሚው ላይ ተፅዕኖ በሚያሳድሩ ግብር ከፋዮች ላይ በተደረገ የመስክ ቁጥጥር 1,439 ግብር ከፋዮች ያለ ደረሰኝ ግብይት ሲፈጽሙ ስለተደረሰባቸው፣71.5 ሚሊዮን ብር አስተዳደራዊ ቅጣት እንደተጣለባቸው የባለሥልጣኑ የታክስ ሕግ ማስከበር ዘርፍ ምክትል ዳይሬክተር አቶ ታምራት ንጉሤ አስታውቀዋል።

ሐሙስ ግንቦት 8 ቀን 2011 ዓ.ም. ለጋዜጠኞች እንዳስታወቁት፣ በግንባታ ዕቃ አቅርቦት በተሰማሩ በከፍተኛ ግብር ከፋዮች ላይ የተወሰደው ዕርምጃ ለሁለተኛ ጊዜ የተሳካ ኦፕሬሽን የተካሄደበት ነው፡፡ ከጥቂት ሳምንታት በፊት በተክለ ሃይማኖት አካባቢ በተደረገ ኦፕሬሽን ሦስት የግንባታ ብረታ ብረት ነጋዴዎች ያለ ደረሰኝ ሲሸጡ እጅ ከፍንጅ መያዛቸውን ምክትል ዳይሬክተሩ አስታውሰዋል፡፡ 

በካዛንቺስ ኡራኤል አካባቢ ሴራሚክስ፣ ግራናይትና የባኞ ቤት ዕቃዎችን ከሚነግዱ ከፍተኛ ግብር ከፋዮች መካከል ያለ ደረሰኝ ሲነግዱ የተደረሰባቸው አራት ድርጅቶች፣ ዓመታዊ ሽያጫቸው ከሦስት እስከ ሰባት ሚሊዮን ብር እንደሆነ ማሳወቃቸውን ኃላፊው ጠቁመዋል፡፡እነዚህ ከፍተኛ ግብር ከፋዮች ላይ ለአንድ ወር በተካሄደውር ጥናትና ክትትል ያለ ደረሰኝ ሲሸጡ እንደነበር መታወቁን የገለጹት አቶ ታምራትባለሥልጣኑ ከአከፋፋዮቹ100 ሺሕ ብር ግዥ በመፈጸም ጭምር ይህንኑ በማረጋገጡ፣ ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ጋር በተካሄደ ኦፕሬሽን አራቱ አከፋፋዮች እጅ ከፍንጅ እንደተያዙ አስታውቀዋል፡፡

ባለቤቱ ወይም ግብር ከፋዩ ቢንያም ሽብሩ በተባለ ግለሰብ የተወከለው ‹‹አብ ሥራ ሴራሚክ›› ‹‹ልዩ አጨራረስ›› እየተባለ የሚጠራውና ባለቤቱ ወይም ግብር ከፋዩ አመርጋ ወልደ ፃድቅ በሚባል ግለሰብ የሚተዳደረው  ‹‹ሳባ ግራናይትና ሴራሚክስ›› የተባለውና በሳባ ጥላሁን ባለቤትነት የሚተዳደረው አስመጪና አከፋፋይ ድርጅት እንዲሁም ‹‹ፎዚያ ሴራሚክስ›› የተባለውና በእስማኤል ነስሩ የሚተዳደረው አስመጪና አከፋፋይ የንግድ ድርጅት ያለ ደረሰኝ  ግብይት ሲፈጽሙ እጅ ከፍንጅ መያዛቸውን ባለሥልጣኑ አስታውቋል።

በዚህም መሠረት ከአራቱ ድርጅቶች ሁለቱ ባለቤቶችና ስምንት የሽያጭ ሠራተኞች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን አቶ ታምራት ይፋ አድርገው፣ ባልተያዙት ላይም የወንጀል ምርመራ በመጀመሩ በፖሊስ ክትትል ሊያዙ እንደሚችሉ ገልጸዋል።  

ከዚህ ቀደም በተመሳሳይ ኦፕሬሽን ዓመታዊ ሽያጫቸው 70 ሚሊዮን ብር በላይ የሆኑ ሦስት የብረታ ብረት ነጋዴዎች፣ ተክለ ሃይማኖት አካባቢ ያለ ደረሰኝ ሲሸጡ ተደርሶባቸው እጅ ከፍንጅ መያዛቸውን አቶ ታምራት አስታውሰዋል።

ያለ ደረሰኝ በሚደረግ ግብይት በሚፈጸም የታክስና የገቢ ማጭበርበር፣ በአስተዳደራዊና በወንጀል ድርጊቶች እንደሚያስቀጣ በሕግ ተደንግጓል። በዚህም መሠረት ለእያንዳንዱ ያለ ደረሰኝ ለተፈጸመ ግብይት 50 ሺሕ ብር አስተዳደራዊ ቅጣት ሲጣል፣ በፍርድ ቤት በሚረጋገጥ ወንጀል ደግሞ 25 ሺሕ ብር ቅጣት ብሎም ከሦስት እስከ አምስት ዓመታት ለሚደርስ ጊዜ የእስራት ቅጣት ያስከትላል።

በዚህ ዓመት ከከተማው የታክስ ምንጮች ማዘጋጃ ቤታዊ ገቢዎችን ጨምሮ 34.5 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ መታቀዱን ያስታወሱት አቶ ታምራት፣ በዘጠኝ ወራት ውስጥ ሊሰበሰብ ከታቀደው 26.3 ቢሊዮን ብር ውስጥ 25.4 ቢሊዮን ብር ገደማ መሰብሰቡን ገልጸዋል፡፡ በአንፃሩ በዘጠኝ ወራት ውስጥ ከታቀደው የ7.9 ቢሊዮን ብር ቀጥተኛ ያልሆኑ የታክስ ገቢዎች ውስጥ 7.2 ቢሊዮን ብር መሰብሰቡንም አስረድተዋል፡፡

እንደ ተጨማሪ እሴት ታክስ (ቫት) እና ተርን ኦቨር ታክስን በመሳሰሉት ቀጥታ ያልሆኑ ታክሶች ላይ ያለ ደረሰኝ በሚፈጸም ግብይት፣ ትክክለኛ ገቢን ባለማሳወቅና ከዋጋ በታች ሽያጭ በማካሄድና ማጭበርበር በዓመት እስከ አሥር በመቶ የሚገመት ገቢ እንደሚታጣ፣ ዘንድሮም ይኸው መታየቱን ከተሰጠው ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች