Thursday, June 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
የሳምንቱ ገጠመኝየሳምንቱ ገጠመኝ

የሳምንቱ ገጠመኝ

ቀን:

እኔ እንኳን ላካፍላችሁ የፈለግኩት ባለፈው ሳምንት ውስጥ ስለገጠሙኝ ጉዳዮች ነው፡፡ የመጀመርያው ሰኞ ማለዳ ነው፡፡ ከመገናኛ ወደ ሳሪስ አቦ የሚጓዙት ሃይገር አውቶብሶች ባለመኖራቸው ተሳፋሪዎች በተራ አስከባሪዎች አማካይነት ሠልፍ ይዘን እንጠብቃለን፡፡ በዚህ ባልተለመደ ሁኔታ እየተገረምን ሃይገሮቹ የት ጠፉ እንባባላለን፡፡ ቢያንስ ለሩብ ሰዓት ያህል ባደረግነው ቆይታ አንድም ሃይገር ብቅ ባለማለቱ ረጅም ሠልፍ ሠርተን ተሰላችተናል፡፡

በዚህ መሀል አንድ ሃይገር መጥቶ ሲቆም በሥነ ሥርዓት የሚያስተናግድ ተራ አስከባሪ በመጥፋቱ ሠልፉ ተንዶ ሰው በሰው ላይ ተረባረበ፡፡ ጉልበት ያላቸው ተሳፍረው አቅመ ደካሞች ሜዳ ላይ ሲቀሩ አካባቢውን ጥዬ ታክሲ ፍለጋ ወደ ማዶ ታክሲ መናኸሪያ መጓዝ ጀመርኩ፡፡ በዚህ መሀል አንዱን ተራ አስከባሪ፣ ‹‹ሠልፍ ካስያዛችሁን በኋላ ለምን በሥርዓት አታስተናግዱንም?›› ስለው፣ ‹‹ሥርዓት ማለት ምንድነው? ለምንስ ይጠቅማል?›› እያለ አሾፈብኝ፡፡ ይህንን አሳዛኝ ምላሽ የሰሙ አንድ አዛውንት፣ ‹‹እውነትህን ነው! ድሮስ ግርግር የሚመቸው እኮ ለሌቦች ነው፤›› ብለው ገላገሉኝ፡፡

ታችኛው ታክሲ ተራ ደርሼ የተለመደውን ሠልፍ እንደያዝኩ ሦስት ተራ አስከባሪ መሳዮች መጡና ከመሀል ከመሀል እየከፋፈሉን ወደተለያዩ ታክሲዎች ጠቆሙን፡፡ አገር ሰላም ነው ብለን ስንደርስ የሚያሳፍር ወያላ የለም፡፡ በዚህ መሀል አንድ ታክሲ ከተሸጎጠበት ወጥቶ ‹‹ቦሌ ሳሪስ . . . ›› እያለ ወያላው ሲጣራ ከየአቅጣጫው የሚሯሯጡ ሰዎች ሰፈሩበት፡፡ ንብረቴን ከዘረፋ ለመጠበቅ ዞር ብዬ ስታዘብ ታክሲው የያዘውን ይዞ ሲሸመጥጥ፣ ‹‹ሞባይሌ፣ ቦርሳዬ፣ ሐብሌ . . . ›› የሚሉ ድምፆች ተሰሙ፡፡ ‹‹ግርግር ለሌባ ይመቻል፤›› ማለት ይኼ አይደል? እንደምንም ታግሼ ከተረጋጋ በኋላ ታክሲ አግኝቼ ወደ ሳሪስ ጉዞ ጀምረን አምቼ ስንደርስ ወያላው ሒሳብ መጠየቅ ጀመረ፡፡ አንድ ወጣት ኪሱን ሲዳብስ ባንክ ሊያስገባው የያዘውን ዘጠኝ ሺሕ ብር መገናኛ ግፊያ ላይ መሰረቁን በለቅሶ ቀረሽ ድምፅ ተናገረ፡፡ ታክሲውን አስቁሞ በንዴት ውስጥ ሆኖ በሩጫ ወደ መገናኛ ሲገሰግስ ከንፈራችንን እየመጠጥን ሸኘነው፡፡

ሰኞ ከምሽቱ 12 ሰዓት ላይ ካዛንቺስ ነኝ፡፡ ከካዛንቺስ ወደ ፒያሳ የሚሄደውን ታክሲ ለመሳፈር ሁለት ኮረዶች ከወዲህ ወዲያ እያሉ ይጋፋሉ፡፡ ጠጋ ብዬ ኪሳቸውንና ቦርሳቸውን እንዲጠብቁ ነገርኳቸው፡፡ እየተሳሳቁ ግፊያቸውን ቀጥለዋል፡፡ እኔ ደግሞ እነዚህ ዘናጭ ሴቶች የሌባ ሲሳይ እንዳይሆኑ በሥጋት ውስጥ ሆኜ አያቸዋለሁ፡፡ በዚህ መሀል አንድ ነጭ ሚኒባስ መጥቶ ቆመ፡፡ ወያላው አንገቱን አውጥቶ የሚጋፉትን ያያል፡፡ ሁለቱ ኮረዶች አንድ ሰው መሀላቸው አስገብተው ይጋፋሉ፡፡

በዚህ መሀል አንደኛዋ ሰውየውን ወደ ወያላው ስትጠቁመው እሱ ተንጠራርቶ ከወያላው ጋር ሲጨቃጨቅ ሌላኛዋ ኮቱን ገልብጣ ከኪሱ ውስጥ በካኪ ወረቀት የታሸገ ነገር አውጥታ ዘላ ሚኒባሱ ጋቢና ውስጥ ገባች፡፡ ያችም በፍጥነት ተከተለቻት፡፡ እኔ ወደ እነሱ ስንደረደር ሚኒባሱ በፍጥነት ከአካባቢው ተፈተለከ፡፡ ሰውየው ኪሱን ሲዳብስ ቀሎት ነው መሰል ግራ ተጋብቶ ዓይኑ ሲቁለጨለጭ፣ ‹‹ምን ሆንክ?›› አልኩት፡፡ ‹‹ተዘረፍኩ! ተዘረፍኩ . . . ›› እያለ ሲያለቅስ አንጀቴ ተቃጠለ፡፡ ሴቶቹ ለካ 15 ሺሕ ብሩን ይዘው ጠፍተዋል፡፡

በነጋታው ጠዋት እንደተለመደው ከመገናኛ ወደ ሳሪስ አቦ በሃይገር አውቶቡስ ስንጓዝ አንዱ በሞባይል ስልኩ ያወራል፡፡ ‹‹ኢምፔሪያል አካባቢ ደርሻለሁ፡፡ ከአሥር ደቂቃ በኋላ ሳሪስ ደርሼ 20 ሺሕ ብርህን አፍንጫህ ላይ እወረውርልሃለሁ፡፡ ይኼው በጥሬው ይዤልህ እየመጣሁ ነው ጠብቀኝ . . . ›› እያለ ሲቀደድ ሰዎች እየተገለማመጡ ያዩታል፡፡ በዚህ መሀል አጠገቤ የተቀመጠች ወይዘሮ፣ ‹‹እንዲህ አፋቸውን እየከፈቱ ነው የዘራፊ ሲሳይ የሚሆኑት፡፡ ይገርምሃል ትናንትና አንዱ ከቦሌ ድልድይ ጀምሮ እንዲሁ ስለያዘው ገንዘብ ሲተረተር ጉድ ሠሩት፤›› አለችኝ፡፡

ይኼ አጋጣሚ ምን ይሆን ብዬ፣ ‹‹የት ነው የተዘረፈው?›› በማለት ጥያቄ አቀረብኩላት፡፡ ‹‹ካዛንቺስ!›› አለችኝ፡፡ ‹‹በስንት ሰዓት?›› ስላት፣ ‹‹12 ሰዓት አካባቢ›› አለች፡፡ በጣም ከንክኖኝ፣ ‹‹ምን ዓይነት ሌቦች ናቸው የዘረፉት በዚያ ሰዓት?›› በማለት እንደገና ጥያቄ አቀረብኩላት፡፡ ‹‹ዝንጥንጥ ያሉ የፒያሳ እሳት የላሱ ሴት አራዶች . . . ›› ስትለኝ የትናንትናው ምሽት ትዕይንት ትዝ አለኝ፡፡

ሳሪስ ደርሰን ከሃይገር አውቶቡሱ ስንወርድ ሃያ ሺሕ ብር ይዣለሁ እያለ ሲለፈልፍ የነበረውን ሰው ሦስት ጎረምሶች ከኋላው እያደቡ ሲከተሉት ፍጥነቴን ጨምሬ ተጠጋሁትና ‹‹ተጠንቀቅ ዘራፊዎች እየተከተሉህ ነው፤›› ስለው፣ ‹‹እስኪ ይምጡና ይሞክሩኝ ምላሹን ያገኙታል . . . ›› እያለ ሲፎክር ጎረምሶቹ ቀስ እያሉ ተበታተኑ፡፡ እኔም እየተገለማመጥኩ ወደ ሥራዬ አቀናሁ፡፡ ራሱን መከላከል የሚችል ካለ ደህና፡፡ በባዶ ሜዳ በጉራ የምንወጠር ካለን ግን ከአፋችንም ከድርጊታችንም ጠንቀቅ ብንልስ? ኪስ ውስጥ ያለ ሚስጥርን በነፃ እየሸጥን ራሳችንን ለጉዳት ባናጋልጥስ? ብሔራዊ ደኅንነታችን አስተማማኝ የሚሆነው እኮ የግለሰቦችም ደኅንነት ሲጠበቅ ነው፡፡

(መስፍን ዘ.፣ ከላም በረት)  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በአዲስ አበባ በድምቀት ተከበረ

የአዛርባጃን ኤምባሲ  የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በትላንትናው ዕለት አከበረ። ሰኞ...

የመንግሥትና የሃይማኖት ልዩነት መርህ በኢትዮጵያ

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች የሃይማኖት ተቋማት አዎንታዊ ሚና የጎላ...

ሐበሻ ቢራ ባለፈው በጀት ዓመት 310 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

የአንድ አክሲዮን ሽያጭ ዋጋ 2,900 ብር እንዲሆን ተወስኗል የሐበሻ ቢራ...