ብዙ ትችቶችን ስላስተናገደው የቢራ ማስታወቂያ ባለፈው ሳምንት በዚሁ ዓምድ ሥር አንድ ጽሑፍ ቀርቦ ነበር፡፡ በዚህ ሳምንት አጋማሽ ደግሞ የንግድ ውድድርና ሸማቾች ጥበቃ ባለሥልጣን ማስታወቂያውን ስለማገዱ ተሰምቷል፡፡ ቀደም ብሎ ምንነቱን በማይገልጽ ሁኔታ ለወራት የሰማነው ማስታወቂያ ምን ይሆን? ብለን በጉጉት ስንጠብቅ ከቆየን በኋላ፣ መጨረሻው ቢራ ሆኖ መገኘቱ ብዙዎቻችንን ያበሳጨም ያስደመመም ነበር፡፡
ማስታወቂያው ቢራነቱን በማወጅ ማስነገሩን ቢቀጥልም፣ ባለሥልጣኑ ግን ማስታወቂያው ይታገድ በማለት ላወጣው ዕግድም ምክንያት ያለውን አንቀጽ አጣቅሶ ዕርምጃ ወስዷል፡፡ በማስታወቂያው ዙሪያ የተነሱ ትችቶችንና አስተያየቶችን በመንተራስ እንዳይተዋወቅ ውሳኔ መተላለፉ ትክክል መሆኑን የሚያምኑ እንዳሉ ሁሉ፣ ዕርምጃው ምን ያህል ሕጋዊ ነው? የሚለውን ጥያቄ ያነሱም አልጠፉም፡፡
ለማስታወቂያው መታገድ ከሕግ አኳያ የተጠቀሱ ነጥቦች ላይ ከሚከራከሩ ወገኖች በተጨማሪ፣ በባለሥልጣኑ የተጠቀሰውን አንቀጽ በራሳቸው ተርጉመው ሙግት የገጠሙም አልጠፉም፡፡ እንዲህ ያለው ማስታወቂያ ትውልድን ይበርዛል የሚለው መከራከሪያ ነጥብ ላይ ሳይሆን፣ መታገዱ ለምን? የሚል ጥያቄ የሚያነሱቱ፣ አመለካከታቸው የራሳቸው ሆኖ፣ ልቅ ማስታወቂያዎች ተመልካች እንደሚሹ ግን ለሁሉም ግልጽ ሆኗል፡፡
ስለዚህ ዕርምጃው ሌሎችንም ሊያስተምር ይችላል፡፡ አንድ ምርት ወይም አገልግሎት የትውልድን መደበኛ የኑሮ ዘይቤ ሊበርዝ እንደሚችልና ሊያደርስ የሚችለው አደጋም የከፋ እንደሚሆን ከታመነበት በሕግ አግባብ ዕርምጃ መውሰዱ ተገቢ እንደሆነ ያየንበት አጋጣሚ ሊባል ይችላል፡፡ ይህ ማለት ግን የዜጎችን መብት በሚጋፋ መንገድ፣ የማሰብና ሐሳባቸውን የመግለጽ መብታቸውን በሚያሳጣ ሁኔታ መሆን እንደሌለበት መታወቅ አለበት፡፡ ትርጉም ስንሰጥና ስንመዝንም ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል፡፡ ግብታዊነትም ከስሜት መራቅም የመንግሥት በተለይም እንዲህ ያሉትን መልዕክቶች የሚከታተለው አካል ሊያሰምርባቸው የሚገቡ ጉዳዮች ናቸው፡፡
በአንፃሩ ሕግ ሊገዛቸው የሚገባቸው፣ ለአደጋና ጥፋት መንስዔ የሚሆኑ ማናቸውም ተግባራት ጉዳት ከማስከተላቸው በፊት መከላከል፣ ኢትዮጵያ ያሏትን ሕጎች በአግባቡ በመተርጎምና በማስፈጸም ረገድ ያለው ተነሳሽነትና ትጋት የቀዘቀዘ ነው፡፡ ከሰሞኑ ያስተዋልነውም ይህንን ነው፡፡ ሸማቾችና ተገልጋዮች የሚምታቱባቸው መልክዕቶችን በሚገባ አጥንቶ ዕርምጃ ባለመወሰዱ ብዙ ብልሽት እንደተፈጠረ እንረዳለን፡፡ ልጆች ለአልኮል መጠጦች የተሰጡ ስያሜዎችን በየሰፈሩ ጥዑመ ዜማ እተቀባበሉ ሲዘምሩ ታዝበናል፡፡ አደጋ ነው፡፡ መልዕክቶቹ ሕፃናትና ታዳጊዎች ላይ ያነጣጠሩ እስኪመስል ድረስ ሕፃናት በለጋ አዕምሯቸው ሸምድደው የያዙት የመጠጥ ማስታወቂያ ሆኗል፡፡
‹‹ልባም . . .›› ማስታወቂያን የምንተችበት አንዱ ነጥብም ይህ ነው፡፡ ኢንቨስትመንትና ልማቱ ያስፈልጋል፡፡ የማስታወቂያው ዓላማ ግን ለሚፈለገው ምርት የሚመጣጠን መልዕክት ማንገብ እንጂ፣ የአድማጭ ተመልካችን ስሜት የሚነካ መሆን የለበትም፡፡
የመጠጥ ፋብሪካዎች ማስታወቂያ በልክና በአግባቡ እንዲሆን መሻታችን ነገን በማሰብ ነው፡፡ አንድ ምሳሌ እዚህ እንጥቀስ፡፡ ሐይኒከን በውጭ የቴሌቪዥን ጣቢያዎችና ፕሮግራሞች ከሚያስተዋውቅበት ዘዴ መካከል መኪና እያሽከረከረ የነበረውና ከአቻዎቹ ጋር የነበረውን ቆይታ ጨርሶ የሚወጣው ሰው፣ ቢራ እንዲጠጣ ሲጋበዝ ስለማሽከረክር አልጠጣም በማለት በአቋሙ ይጸናና በመኪናው ይፈተለካል፡፡ የተጋበዘው ቢራ የሐይኒከን ነው፡፡ መናገርና መቀባጠር፣ ልባችን፣ ክብራችን ወዘተ. ሳያስፈልግ በሥልጡን መንገድ ሐሳብና ዓላማ እንዲህ ይገለጻል፡፡ መልዕክት ይተላለፋል፡፡
የእኛዎቹ የአልኮል መጠጥ ማስታወቂያዎች ጭራሹኑ የሚጎነጨውን ሳይሆን፣ አፍላዎቹን የነገ ተረኞችን ግብ አድርገው መሠራታቸው ጭምር ነው አሳሳቢው፡፡ የቢራ ፋብሪካዎቹ ዳጎስ ያለ ትርፍ ስላላቸው፣ ከንግዳቸው መካከል ማስተዋወቅ ትልቅ ቦታ ስላለው ጠዋትና ማታ ቢራ ጠጡ እያሉ በማላዘናቸው ልጆች የልጅነት የጨዋታ ዜማቸውን በቢራ ማስታወቂያ መቀየራቸው አደጋ አለው፡፡ እንቦቀቅሎቹ ቢራ እንደ ውኃ በጠጪ ጉሮሮ ሲንደቀደቅ እያዩ ለመጠጣት መመኘታቸው ስለሚያሳስብ ነው ማስታወቂያ በልክ ይሁን የምንለው፡፡
የአነጋጋሪውን ማስታወቂያ ዕግድ የሰሙ ብዙዎች እንዲህ ያለ ሥራ የሚሠራ መሥሪያ ቤት አለ ወይ? ከሚለው ጥያቄያቸው ባሻገር በነካ እጁ ሌሎች ማስታወቂያዎችንም ይፈትሽ ማለታቸው ተገቢ ነው፡፡ ነገሬ ያልተባሉ ግን ደግሞ እንደ ሰሞኑ ቢራ ማስታወቂያ ልብ መስቀሉ ያልተሳካለቸው ማስታወቂያዎችም ሰሚ ተመልካች ቢያገኙ ስንት ጥራዝ ነጠቅ አካሄድ እንዳላቸው ታውቆ፣ ሊታገዱ እንደሚችሉ ማስጠንቀቅ ይገባል፡፡
ከማስታወቂያ አንፃር የንግድ ውድድርና ሸማቾች ጥበቃ ባለሥልጣን ሕግጋት ምን እንደሚሉ ማሳወቁና ማስታወሱም ተገቢ ነው፡፡ እንደ ተገልጋይ ወይም እንደ ማኅበረሰብ ሊታይ የሚገባው ወሳኝ ጉዳይ ግን የማስታወቂያ ባለሙያዎች ነገር ነው፡፡ የማስታወቂያ ባለሙያዎች የሚያስተላልፉት መልዕክት ጨዋነትን የተላበሰ መሆን እንደሚገባው ዕሙን ነው፡፡ ኃላፊነት በተሞላው መንገድ ማስታወቂያዎችን የማሰናዳት ልምድ ኃላፊነትን መወጣት ነው፡፡
በዚህ ጉዳይ ልናነሳው የሚገባን ነገር የአገራችን አልኮል ቀመስ መጠጦች አዲስ በወጣው ሕግ ተሻሽለው ሊቀርቡ ስለመቻላቸው ነው፡፡ ከአልኮል መጠጥ ጋር ተያይዞ የመጠሪያ ስማቸውም ሊያነጋግር የሚችል ነው፡፡ የእስካሁኖቹን ስያሜዎች ማስቀረት ባይቻልም፣ ከዚህ በኋላ ላለው ግን ማሰቡ ተገቢ ነው፡፡ መልካም የሚባሉ እሴቶችንና ታሪካዊ ቦታዎችን፣ የተፈጥሮ ፀጋዎችን፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ የምንታወቅባቸውን ሁሉ የቢራና የአልኮል መጠሪያ ማድረግ የሚደገፍ አይመስለኝም፡፡
በአጠቃላይ ፈር ሊይዙ የሚገባቸውን ጉዳዮች እያዩ ማስተካከል ተገቢ የመሆኑን ያህል፣ ኩባንያዎችን በአግባቡና በሥርዓቱ ሥራቸውን እንዲሠሩ፣ ራሳቸውንም በሚገባ መንገድ መግለጽ አለባቸው፡፡ ቢዝነስና ኢንቨስትመንት የሚያስፈልገንን ያህል ገበያችንን ለማስፋፋትና በውድድር አሸንፎ ለመውጣት ትውልድን መስዋዕት ማድረግ በምንም መለኪያ ለድርድር አይቀርብም፡፡
በጨዋነት ማስታወቂያ መሥራት፣ ማስነገር እየተቻለ፣ ስንት ቴክኖሎጂና ሐሳብ በሞላበት ዘመን ምናለ ቢታሰብበት፡፡ ለነገሩ እጁን አወጣ እንጂ ቢራ መጥመቂያዎች ሁሉ የመንግሥት ፋብሪካዎች አልነበሩም ወይ? ለትውልድ ከታሰበ ሁሉ ነገር በአግባቡ ሊሆን ያስፈልገዋል፡፡