Tuesday, November 28, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የሕክምና ሙያ ማኅበራትን ያካተተው ዓውደ ርዕይ የሐኪሞች ወቅታዊ ጥያቄዎች የተንፀባረቁበትን ውይይት አስተናግዷል

ተዛማጅ ፅሁፎች

አምስተኛው ኢትዮ ኼልዝ ዓውደ ርዕይና ጉባዔ ከግንቦት 7 እስከ ግንቦት 9 ቀን 2011 ዓ.ም. በሚሊኒየም አዳራሽ ሲካሄድ፣ ትኩረቱን በሕክምና መገልገያዎች፣ በመድኃኒት አቅርቦት እንዲሁም በጤና ክብካቤ አገልግሎት፣ ቴክኖሎጂና ግብዓቶች በማድረግ ነበር፡፡ በዓውደ ርዕዩም 16 የሕክምና ሙያ ማኅበራት ለመጀመርያ ጊዜ ተካተው ነበር፡፡

ፕራና ኤቨንትስ ከኢትዮጵያ ምግብ፣ መድኃኒትና ጤና ጥበቃ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን ጋር በትብብር ያዘጋጁት ይህ ዓውደ ርዕይ፣ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ትብብር የሚፈጥሩበትን መድረክ በማመቻቸት የግሉና የመንግሥት አጋርነትን ማጠናከር ስለሚቻልበት መንገድም አመላክቷል፡፡

ዓውደ ርዕዩ በጤና ሚኒስቴር ዕውቅና የተሰጠው ሲሆን፣ በሕክምና ሙያ ማኅበራት በኩልም አጋርነት ተፈጥሯል፡፡ ዓውደ ርዕዩ አጋርነት ከፈጠረባቸው ማኅበራት መካከል የኢትዮጵያ መድኃኒትና ሕክምና መሣሪያ አምራቾች ማኅበር፣ የኢትዮጵያ የጥርስ ሕክምና ባለሙያዎች ማኅበር፣ የኢትዮጵያ ባዮሜዲካል ኢንጂነሪንግ ማኅበር፣ የኢትዮጵያ ሴት ሐኪሞች ማኅበር፣ የልብ ሕክምና ባለሙያዎች ማኅበር እንዲሁም የኢትዮጵያ ሕዝብ ጤና ላቦራቶሪዎች ማኅበር ተጠቃሽ ናቸው፡፡

ከጤና ሚኒስቴር በተገኘው መረጃ መሠረት፣ በጤና ዘርፉ የመንግሥት አጠቃላይ ወጪ ከጠቅላላው ኢኮኖሚ 11.5 በመቶ የማይበልጥ ሲሆን፣ ከፍተኛው ወጪ የሚሸፍነው ግን ከዕርዳታ የሚገኘው ገንዘብ እንደሆነም ይገልጻል፡፡

በአምስት ዓመቱ የጤና ዘርፍ ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ መሠረት 15.6 ቢሊዮን ዶላር በዝቅተኛው አፈጻጸም ወይም 22 ቢሊዮን ዶላር በከፍተኛው አፈጻጸም ለጤናው ዘርፍ እንደሚያስፈልግ ተቀምጧል፡፡

የመድኃኒት ግዥን ከጊዜ ወደ ጊዜ በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ የመጣ ሲሆን፣ በ2010 ዓ.ም. የነበረው የ500 ሚሊዮን ዶላር ወጪ፣ በ2011 ዓ.ም. ከ800 ሚሊዮን ዶላር በላይ እንደሚሆን ይገመታል፡፡

በዓውደ ርዕዩ መዝጊያ ዕለት ማለትም ግንቦት 9 ቀን 2011 ዓ.ም. በተካሄደ የፓናል ውይይት ተሳታፊ የነበሩት የቀድሞው ጤና ሚኒስቴር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሱሌይማን ሽጉጤ ከሕክምና ጋር ተያያዥነት ያላቸው የፍርድ ቤት ጉዳዮች ላይ እንዲሁም በሕክምና ዙሪያ ሰፋ ያለ ማብራሪያ አቅርበዋል፡፡ ‹‹ሕክምና ላይ ሁሌም ስህተት አለ፡፡ ከስህተታችን ግን ትምህርት እየወሰድን እናልፋለን፤›› በማለት ስለወቅታዊ ጉዳዮች አንስተዋል፡፡ የሕክምና ባለሙያዎች አንዱ የአንዱን ቀዳዳ መድፈን ሲኖርባቸው አሁን እየታየ ያለው ግን ተቃራኒው እንደሆነ በመግለጽ የጤና ባለሙያዎችን ሸንቆጥ አድርገዋል፡፡

ቅዳሜ ሚያዝያ 26 ቀን 2011 ዓ.ም. ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከሕክምና ባለሙያዎች ጋር ስብሰባ ማድረጋቸው የሚታወስ ነው፡፡ በአንፃሩ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ የጤና ባለሙያዎች ከሰሞኑ ሠልፍ እየወጡ ነው፡፡ ይኼንንም በማስመልከት ግንቦት 9 ቀን 2011 ዓ.ም. በኦሮሚያ ክልል ከሚገኙ የጤና ባለሙያዎች ጋር የክልሉ መንግሥት ኃላፊዎች ስብሰባ ያካሄዱ ሲሆን፣ በጤና ባለሙያዎች እየተነሱ ያሉ ጥያቄዎችን ከፌዴራል መንግሥት ጋር በመሆን መፍትሔ ለመስጠት እንደሚሠሩም ተወካዮቹ አስታውቀዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች