Friday, December 8, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ወንጂ ሸዋና መተሐራ ስኳር ፋብሪካዎችን ለመግዛት የተነሳው ኩባንያ 60 ሺሕ ባለአክሲዮኖች ይኖሩታል ተባለ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የፋብሪካዎቹን መሥራች ኩባንያ በከፍተኛ ባለድርሻነት ያሳትፋል

ከተመሠረቱ ከ60 እስከ 70 ዓመታት ያስቆጠሩትን የወንጂ ሸዋና (ወንጂና ሸዋ ስኳር ለየብቻቸው የነበሩ) የመተሐራ ስኳር ፋብሪካዎችን ለድርድር ለመግዛት የተነሳው ኢትዮ ስኳር አክሲዮን ማኅበር፣ የሦስት ቢሊዮን ብር ዋጋ ያላቸውን ሦስት ሚሊዮን አክሲዮኖች ለ60 ሺሕ ባለአክሲዮኖች ለመሸጥ እንቅስቃሴ መጀመሩን አስታወቀ፡፡

አንድ ዓመት ያስቆጠረው ኢትዮ ስኳር አክሲዮን ማኅበር፣ ለስድስት ወራት ያህል ከመንግሥት አካላት ጋር ፋብሪካዎቹን በሚገዛበት አግባብ እየተጻጻፈና እየተደራደረ መቆየቱን የአክሲዮን ማኅበሩ ኃላፊዎች ሐሙስ፣ ግንቦት 8 ቀን 2011 ዓ.ም. ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ወቅት አስታውቀዋል፡፡

ማኅበሩ ከሚያቅፋቸው ባለአክሲዮኖች መካከል 40 ሺሕ ያህሉ በወንጂ ሸዋና በመተሐራ ስኳር ፋብሪካዎች አካባቢ የሚኖሩ ከ11 ሺሕ ያላነሱ ገበሬዎች፣ 20 ሺሕ የፋብሪካ ሠራተኞችና ፋሪካዎቹ በሚገኙባቸው አካባቢዎች ተመድበው የሚሠሩ አሥር ሺሕ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ሠራተኞች ይካተታሉ፡፡ ሌሎች 20 ሺሕ በአገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የሚሳተፉበት እንደሚሆንና በጠቅላላው ከ60 ሺሕ በላይ ባለአክሲዮኖች ድርሻ የሚይዙበት ኩባንያ እንደሚሆን ተገልጿል፡፡

የአክሲዮን ማኅበሩ ፕሬዚዳንት ለማ ጉርሙ (ኢንጂነር)፣ ምክትል ፕሬዚዳንቱ ኤረሲዶ ለኔቦ (ዶ/ር) እንዲሁም ዋና ሥራ አስኪያጁ አቶ ቢተው ዓለሙ በጋራ በሰጡት መግለጫ እንደተጠቀሰው፣ በወንጂ ሸዋና በመተሐራ ለዘመናት የቆየውን የኢንዱስትሪ ባህል ዳግም እንዲያንሰራራ የማድረግ፣ ብሎም ወንጂና መተሐራን የኢንዱስትሪ ማዕከል የማድረግ ዓላማ ተይዟል፡፡

ከስኳር ባሻገር፣ በከረሜላ፣ በአልኮልና በሽቶ ምርቶች ከእነዚህም በተጨማሪ በኢታኖል፣ በሞላሰስ፣ በቁም እንስሳትና በወተት ተዋጽኦ ምርቶችና በመሳሰሉት መስኮችም እንደሚሰማራ የተነገረለት ኢትዮ ስኳር አክሲዮን ማኅበር፣ የረዥም ጊዜ ልምድና ተሞክሮ ባካበቱ፣ አብዛኞቹም በወንጂ ሸዋና መተሐራ አካባቢ ነዋሪ በሆኑ፣ በ24 የስኳር ኢንዱስትሪ ባለሙያዎች መሥራችነት የተቋቋመ ነው፡፡

ይህ አክሲዮን ማኅበር ወንጂ ሸዋንና መተሐራን ከመሠረተው ከሆላንዱ ኤችቪኤ ኩባንያ ጋር በመነጋገርና የመግባቢያ ስምምነት በባለድርሻነት የሚሳተፍበት አጋጣሚ እንደተፈጠረ አቶ ቢተው አብራርተው፣ የአክሲዮን ማኅበሩን 39 በመቶ ድርሻ የመያዝ ዕድል እንደሚኖረው፣ ዓለም አቀፍ ፋይናንስ አቅራቢዎችን በማፈላለግና የውጭ ኢንቨስትመንት በማምጣት እንደሚሳተፍ ገልጸዋል፡፡

መሥራቾቹና ሌሎች ባለሀብቶች የ35 በመቶ ድርሻ እንደሚኖራቸው ሲገለጽ፣ ኢትዮጵያውያን ባለሀብቶች የ25 በመቶ፣ መንግሥትም የአንድ በመቶ ድርሻ በመያዝ ይሳተፉበታል ተብሏል፡፡ የአክሲዮን ማኅበሩ ፕሬዚዳንት አቶ ለማ በበኩላቸው፣ አክሲዮን ማኅበሩን የመሠረቱት ሰዎች በአስተዳደርና በዋና ባለድርሻነት መግባት ዓላማቸው እንደሆነ ሲገልጹ ምክትል ፕሬዚዳንቱ ኤርሲዶ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ሁለቱን ፋብሪካዎች ለመግዛት የሚውለው ዋጋ አክሲዮን ማኅበሩ ለማሰባሰብ ያቀደው ሦስት ቢሊዮን ብር እንዳልሆነ ገልጸዋል፡፡

ምንም እንኳ ላለፉት ስድስት ወራት ማኅበሩ ለመንግሥት የፋብሪካዎቹን ግዥ በድርድር ለመጨረስ ሲንቀሳቀስ ቢቆይም፣ መንግሥት በቅርቡ 13 የስኳር ፋብሪካዎችን ለሽያጭ ማቅረቡ የበለጠ ዕድል እንደሚፈጥራላቸው ኃላፊዎቹ አስታውቀዋል፡፡ በመሆኑም የሁለቱን ፋብሪካዎች ባለቤትነት ላለማጣት የአክሲዮን ሽያጭ ከማካሄድ ባሻገር፣ ከውጭ ፋይናንስ በማምጣት ግዥውን ለመፈጸም የሚያስችል ቅድመ ዝግጅት መደረጉም ተጠቅሷል፡፡

ከወራት በፊት ለወንጂ ሸዋና ለመተሐራ ፋብሪካዎች ግዥ የ11 ቢሊዮን ብር ዋጋ መሰጠቱ ቢገለጽም፣ የኢትዮ ስኳር አክሲዮን ማኅበር ኃላፊዎች ግን ይህ ግምታዊ ዋጋ እንጂ ትክክለኛ ዋጋው ገና በመንግሥት ትመና እየተሠራለት እንደሚገኝ በመገልጽ አስተባብለዋል፡፡

በመጪው ዓመት መጨረሻ የአክሲዮን ሽያጭ ሥራው ተጠናቆ ወደ ሥራ ሊገባ የሚችልበት አግባብ ሊኖር እንደሚችል የሚጠበቀው ኢትዮ ስኳር፣ በተለይም ላለፉት በርካታ አሠርታት ተጎድተው ቆይተዋል ላላቸው የሸንኮራ አገዳ አምራች ገበሬዎችና ሠራተኞች የአክሲዮን ድርሻ አከፋፈል ላይ ለየት ያለ ዘዴ ይከተላል ተብሏል፡፡ ይኸውም ከኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ፣ ከአዋሽ ባንክና ከሕብረት ባንክ ጋር ባደረገው ስምምነት መሠረት በአምስት ዓመታት ውስጥ የሚከፈል ብድር አመቻችቷል፡፡

በመሆኑም ለአንድ አክሲዮን የቀረበውን የአንድ ሺሕ ብር ዋጋ መሠረት በማድረግ ዝቅተኛው አሥር ሺሕ ብር ከፍተኛው 50 ሚሊዮን ብር በተደረገ የአክሲዮን ድልድል፣ በተለይ ዝቅተኛ ድርሻ የሚኖራቸው 40 ሺሕ ባለአክሲዮኖች አሥር በመቶ ከራሳቸው፣ 90 በመቶ ከባንክ በሚመቻችላቸውና በአምስት ዓመታት ውስጥ በሚከፈል ብድር አማካይነት የአክሲዮን ድርሻ ክፍያቸውን መወጣት የሚችሉበት አሠራር ተዘርግቷል፡፡

ይህ ይባል እንጂ በርካታ የሸንኮራ አገዳ አምራቾች ለዓመታት ያደረባቸው ቅሬታ ከፍተኛ እንደሆነ አክሲዮን ማኅበሩ መግለጫ በሰጠበት ወቅት ተገኝተው ከነበሩ የዋቂሚያ ሸንኮራ አገዳ አምራቾች ማኅበር አባላት ለማወቅ ተችሏል፡፡ በተለይ የወንጂ ሸዋ ስኳር ፋብሪካ ከ50 በመቶ ያላነሰውን የአገዳ አቅርቦት የሚያገኘው ከገበሬዎች ሲሆን፣ በኩንታል 60 ብር ሒሳብ አገዳውን እንደሚረከባቸው መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡ ይሁንና 280 ያህል አባላትን ባቀፈው የአገዳ አምራቾች ማኅበር አባል የሆኑት አቶ ያኚ ደቀቦ፣ አቶ ፋጂዮ ባርዮና አቶ ዲጎ ኢርኪሶ በሰጡት አስተያየት መሠረት፣ ከዚህ ገንዘብ ላይ በተለያየ ምክንያት ተቆራርጦ እጃቸው የሚገባው ገንዘብ በኩንታል ከአምስት እስከ 11 ብር ብቻ ነው፡፡ ከሰባት ዓመታት በፊት በኩንታል 16 ብር ይታሰብላቸው ነበር፡፡

‹‹በኩንታል 60 ብሩን ቢሰጡን እንኳ ጥሩ ነበር፡፡ የተጎዳ ሰው መንግሥትን አያምንም፡፡ ምናልባት ኢትዮ ስኳር ተስፋ እየሰጠን ነው፤›› ያሉት አምራቾቹ የወንጂና የመተሐራ ስኳር ፋሪካዎች ባለቤት መንግሥት ቢሆንም፣ እነሱ ግን ‹‹የፋብሪካዎቹ እውነተኛ ባለቤት ማን እንደሆነ ማወቅና ማነጋገር እንፈልጋለን፤›› በማለት ቅሬታዎችን ገልጸዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር ከአሁን በኋላ በአገዳ እርሻ ሥራ መሳተፍ እንደማይፈልጉና የሦስት ዓመት ውላቸውም ዘንድሮ የሚያበቃ በመሆኑ፣ ዳግመኛ አገዳ ማልማት እንደማይፈልጉም አስታውቀዋል፡፡ እስካሁንም 300 ሔክታር መሬት ላይ የበቀለ አገዳ በማጥፋት ወደ አትክልት እርሻ እንደገቡም አምራቾቹ ገልጸዋል፡፡

እንዲህ ካሉ ቅሬታዎች ጋር የሚጋፈጠው ኢትዮ ስኳር አክሲዮን ማኅበር፣ ገበሬዎቹን በአባልነት አካቶና በአምራችነት አሰማርቶ ተጠቃሚ የሚሆኑበትን መንገድ እንደሚከተል ገልጿል፡፡ የወንጂ ሸዋና የመተሐራ ስኳር ፋብሪካዎች በኢትዮጵያ ፋና ወጊና የኢንዱስትሪ መነሻዎች ቢሆኑም፣ ወደኋላ መቅረታቸው ተቀባይነት እንደሌለው የገለጹት አቶ ለማ፣ የፋብሪካዎቹን የገንዘብ ፍሰትና የአስተዳደር ሥርዓት፣ የውሳኔ አሰጣጥና የሰው ኃይል አጠቃቀም ብሎም ሌሎችም የተዛቡ አሠራሮችን በማስተካከል ፋብሪካዎቹ የሚጠበቅባቸውን ምርት እንዲሰጡ በማድረግ ውጤታማ ማድረግ የሚችልባቸው ዕቅዶች መነደፋቸውን አብራርተዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ እስከ አምስት ሚሊዮን ኩንታል የሚገመት ስኳር ከውጭ እያስገባች እንደምትገኝ ገልጸው፣ ኢትዮ ስኳር ከ60 በመቶ በላይ የሸንኮራ ማሳን በማልማት፣ የመፍጨት አቅሙን በዓመት እስከ 1.4 ሚሊዮን ቶን በማድረስ፣ ከ172 ሺሕ ቶን ያላነሰ ስኳር በዓመት ማምረት የሚችልበት አቅም እንደሚኖረው አስታውቀዋል፡፡ ይህ ምርት አሁን ያለውን በእጥፍ የሚያሳድግ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች