በትግራይ ክልል ውቅሮ ከተማ ከአሥር እስከ 14 ቢሊዮን ወጪ ሊጠይቅ የሚችል የአሚዩዝመንት ፓርክ ግንባታ መጀመሩን ሳባዊ ሪዞርትና አሚዩዝመንት ፓርክ የተሰኘ ኩባንያ አስታውቋል፡፡
ኩባንያው በመቐለ ከተማ የፓርኩን ግንባታ በተመለከተ በጠራው አገር አቀፍ የውይይት መድረክ ላይ እንዳስታወቀው፣ ፓርኩ በአምስት ምዕራፎች ገንብቶ ለማጠናቀቅ መታሰቡንና የምዕራፍ አንድ ግንባታውም በአሁኑ ወቅት 65 በመቶ ተጠናቋል። ከኩባንያው ኃላፊዎች ማብራሪያ ማወቅ እንደተቻለው፣ ፓርኩ በሦስት ምዕራፎች የሚካሄዱ የሆቴል ግንባታዎችን ጨምሮ በርካታ የመሠረተ ልማት አውታሮችን አካቷል።
በውይይቱ ወቅትም ስለፓርኩ ዝርዝር ይዘቶች የሚያብራሩ ሦስት ጽሑፎች ለታዳሚው ቀርበዋል። ከአቅራቢዎቹ መካከል የፓርኩን የንግድ አዋጭነት የሚያማክሩት አቶ ፋንቱ ጉላ አንዱ ናቸው፡፡ አቶ ፋንቱ ፓርኩ ምን ምን የመዝናኛ ዓይነቶችን እንደሚያካትትና እያንዳንዱ ምዕራፍ ምን ያህል ወጪ እንደሚጠይቅም ለሪፖርተር አብራርዋል፡፡
ፓርኩ ሙሉ በሙሉ ተገንብቶ ሲጠናቀቅ 27 ሔክታር የሚያካልል ሲሆን፣ በምዕራፍ አንድ ግንባታውም በ900 ሚሊዮን ብር ወጪ ባለ ሦስትና ባለ አምስት ኮከብ ሆቴሎች የተካተቱበት የግንባታ ሥራ እንደተጀመረ ተገልጿል። መካከለኛና ከፍተኛ ገቢ ያለውን ተጠቃሚ ማዕከል በማድረግ የሚካሄደው የሆቴሎቹ ግንባታ፣ 350 ክፍሎች የሚኖሩት ባለ አምስት ወለል ሕንፃ ጽሕፈት ቤቱን አካቶ የሚካሄደው የግንባታ ሥራም ተጀምሯል። ሰፊ መናፈሻ፣ ቢራ ፋብሪካዎች ምርቶቻቸውን የሚሸጡበት ክፍት ቦታ ወይም ቢር ጋርደን፣ ከአሥር በላይ ሙሽሮችን በአንድ ጊዜ የሚያስተናግድ ፏፏቴ ያለው መናፈሻ፣ መለስተኛ ስፋት ያላቸው አዳራሾችና ሌሎችም የአገልግሎት መስጫ ግንባታዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ አቶ ፋንቱ ገልጸዋል፡፡
በምዕራፍ ሁለት የፓርኩ ግንባታ ሥራም ዋናውና ትልቅ ዓለም አቀፍ ደረጃ የሚኖረው የአሚዩዝመንት ፓርክ ግንባታ መካሄድ ይጀምራል። በዚህ ግንባታ ሒደት እንደ ዲዚኒላንድ ዓይነት ለሁሉም ዕድሜና ፆታ የሚመቹ የውኃ ላይ መጫወቻዎች፣ የቤት ውስጥና የውጪ ጨዋታዎች ተካተዋል። በዓባይ ወንዝ አምሳያ ሰው ሠራሽ ወንዝ ታላቁ የህዳሴውን ግድብ ንድፍን ጨምሮ፣ ዓባይ ከኢትዮጵያ ወጥቶ የሚያልፍባቸውን አገሮች የሚያሳይ ምስልና፣ የግብፅ ፒራሚዶችን ጨምሮ ይገነባል። በአገር ውስጥና በውጭ የሚገኙ ብርቅዬ ዛፎች፣ ረዣዥም የእግር ጉዞ ለማድረግ የሚመቹ የእግረኛ መንገዶች፣ ከየትኛውም ዓለም የሚመጣ ቱሪስት በድንኳን ማረፍ የሚችልባቸው ቦታዎችና በርካታ ተያያዥ ግንባታዎች በ1.5 ቢሊዮን ብር ወጪ እንዲገነቡ መታቀዱ ተገልጿል፡፡
በምዕራፍ ሦስት የፓርኩ ሥራ ሒደት በ4.2 ቢሊዮን ብር በአብዛኛው የሕንፃ ግንባታ እንደሚከናወን ይጠበቃል፡፡ በአሥር ብሎክ፣ 15 ፎቆች በአጠቃላይ 1,500 አፓርታማዎች የቤት ውስጥ መገልገያዎቻቸው ተሟልቶላቸው ለሽያጭና ለኪራይ አገልግሎት የሚውሉ ሲሆን፣ የትምህርት ቤት፣ ሆቴል፣ ሙሉ የመዝናኛና የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራ፣ ቢዝነስ ሴንተር በግዙፉ ፕሮጀክት ውስጥ መካተታቸውን የቢዝነስ ጥናት አቅራቢው አስታውቀዋል፡፡
በምዕራፍ አራት ግንባታ ሒደትም ወደ መዝናኛው ለሚመጣ ተጠቃሚ እንደ አቅሙ ሸምቶ የሚሄድበት የሚሊኒየም አዳራሽን ዓይነት ሰፋፊ የገበያ አዳራሾችና የኤግዚቢሽን ማዕከሎች፣ የቢዝነስ ሴንተሮችና በአካባቢው የሚመረቱ ምርቶችን በቀጥታ ገበሬው አምጥቶ የሚሸጥበት ሥፍራ የተዘጋጀለት ሲሆን፣ ከቢዝነስ ጋር የተያያዙ ሌሎች ግንባታዎችም በዚህ ምዕራፍ እንዲገነቡ ዕቅድ መያዙን አስቀምጠዋል፡፡
በምዕራፍ አምስት የፕሮጀክቱ ክፍል፣ ሙሉ በሙሉ በባለቤቱ ሐሳብ አመንጪነትና በአሚዩዝመንት ፓርኮች ያልተለመደ ተብሎ የተገለጸውና አቶ ፋንቱ ያቀረቡት፣ ትልቋን ኢትዮጵያ በአንድ ማዕከል በማምጣት የአንድ ኢትዮጵያን ተምሳሌት የሚወክል ማሳያ ማዕከል መገንባት ነው። ለዚህም ዩኔስኮ የመዘገባቸው በኢትዮጵያ የሚገኙ ኪነ ሕንፃዎች በተለይም የአክሱም ሐውልት፣ የፋሲል ግንብ፣ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትና ሌሎችም ሕንፃዎች በውስጣቸው ሆቴሎች፣ ሙዚየሞች የስብሰባ አዳራሾች እንደሚገነቡ ጠቅሰው፣ 50 ሎጆችም በኢትዮጵያ ባህልና ቅርስ መሠረት በፕሬዚዳንሺያል ስዊት ደረጃ ለመገንባት ዝግጅቶች እንተጠናቀቁ ገልጸዋል፡፡
አቶ ግርማይ ኃይሌ ከዚህ ሁሉ ፕሮጀክት ጀርባ ያሉ ባለሀብት ናቸው። ተወልደው ያደጉት በውቅሮ ከተማ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት በንግድ ሥራ የሚተዳደሩና የዋው ፈርኒቸር ድርጅት ባለቤት ናቸው፡፡ አቶ ግርማይ የዚህ ሐሳብ አመንጪና ባለቤት ናቸው፡፡ ስለ ፓርኩ አመሠራረትና ሒደት ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ሐሳቡን ከስምንት ዓመታት ጀምሮ ሲያውጠነጥኑት ቆይተዋል፡፡ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ የሚሳተፍበት አገራዊና ታልቋን ኢትዮጵያ በአንድ ማዕከል በማሳየት የአንድነትን ተምሳሌት መገንባት አንዱ ዓላማቸው ሲሆን፣ ሁለተኛው ወደ ኢትዮጵያ የሚመጣ ቱሪስት፣ ውቅሮን እንደልቡ ተዘዋውሮ እንዲመለከትና እንዲዝናናና ያስችለዋል በሚል ሐሳብ ፕሮጀክቱ መጠንሰሱን ገልጸዋል። የፕሮጀክቱ ጥናት ሲጀመር ግን ሌሎች ሐሳቦችም እንደተፈጠሩ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
አቶ ግርማይ እንደሚሉት፣ እንደዚህ ዓይነት ፕሮጀክቶች ለኢትዮጵያ አዲስና ግዙፍ ስለሆኑ የመሳካት ዕድላቸው አነስተኛ ነው ሲባል እንደሚሰሙና እሳቸውም ስለፕሮጀክታቸው ይህንኑ እንደሚጠየቁ ገልጸው፣ “እኛ ዓመታትን የፈጀ ጥናት በማድረግ ለሚገጥሙን ችግሮች መፍቻ ዕቅድ ጭምር ወረቀት ላይ ጨርሰን ነው ወደ ሥራ የገባነው፤“ ብለዋል። በመሆኑም ፕሮጀክቱን ለማሳካት ግንባታው መካሄድ ያለበት ደረጃ በደረጃ እንደሆነ ጥናቱ ማመላከቱን ጠቅሰው፣ የምዕራፍ አንዱ ግንባታም ጥራቱን ጠብቆ በአንድ ዓመት ጊዜ ለሕዝብ ክፍት እንደሚደረግ አስታውቀዋል።
ፕሮጀክቱ የሕዝብ ስለሚሆን በውቅሮ ከተማ ስለፓርኩ ግንባታ ሒደት የተካሄደውን ዓይነት ሕዝባዊ ውይይት፣ በመጪው መስከረም 2012 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከሁሉም ክልሎችና ከፌደራል መንግሥት የተውጣጡ አካላት ሐሳብ የሚሰጡበትና የባለቤትነት ድርሻውንም ለሚመለከታቸው ሁሉ የማከፋፈል ውጥን የተያዘ በመሆኑ ፕሮጀክቱ ዕውን እንደሚሆን ያላቸውን ሐሳብ ገልጸዋል፡፡
የአሚዩዝመንት ፓርኩ በውቅሮ ከተማ በሊዝ በተገኘ መሬት ላይ ግንባታው እየተካሄደ ይገኛል። ፕሮጀክቱን የሚከታተሉ የግንባታ፣ የገንዘብ አፈላላጊ፣ የግዢ አገልግሎት የሚሰጡ ኮሚቴዎች ተዋቅረውለት ሥራውን ተከፋፍለው እያካሄዱት ይገኛሉ፡፡ ለ1,500 ለአካባቢው ማኅበረሰብ አባላት ጊዜያዊና ቋሚ የሥራ ዕድል የፈጠረው ይህ ፕሮጀክት፣ ለፓርኩ ግንባታ የሚውል የውኃ ጉድጓድ ቁፋሮ ተደርጎ እስካሁንም ሁለት ጉድጓዶች ተቆፍረው ለሥራ ዝግጁ ተደርገዋል። ግንባታው ተጠናቆ ሙሉ በሙሉ አገልግሎት መስጠት እስኪጀምርና ወደ ቋሚ አገልግሎት ሰጪነት ከገባም በኋላ ከአሥር ሺሕ በላይ ሠራተኞች የሚያስፈልጉት ፕሮጀክት፣ ከወዲሁ ከግንባታው ትይዩ ሠራተኛ የመመልመልና የማሠልጠን እንቅስቃሴም እያካሄደ እንደሚገኝ ታውቋል፡፡
ወደፊት ፓርኩ በአክሲዮን ድርጅት መተዳደር በሚችልበት መንገድ እንደሚደራጅ ተጠቅሷል። ከባለሙያዎች ስብስብ የቦርድ አመራሮች በተጨማሪ፣ አማካሪ ቡድን እንደሚኖረውም ተገልጿል፡፡ አሚዩዝመንት ፓርኩ ከተጠናቀቀ በኋላ እንደ የአገልግሎት አሰጣጣቸው ልምድ ላላቸው የውጭ አስተዳዳሪዎች የሚሰጥ ሲሆን፣ ይህን የማድረጉ ሒደትም ከስምንት እስከ አሥር ሳምንታት ይፈጃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
አቶ ግርማይ የፋይናንስ ምንጩ ከየት እንደሆነ፣ ምን ያህሉስ እስካሁን እንደተገኘ ከሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ ‹‹ጥናቱ ይህንንም ከመነሻው የመለሰው ጥያቄ ሲሆን፣ ከአገር ውስጥና ከውጭ ባንኮች፣ አብረውን ለመሥራት ከተስማሙ ከአሜሪካ፣ ከእንግሊዝና ከቱርክ ባለሀብቶች የሚገኝ ነው፤›› ካሉ በኋላ በምሳሌነት የጠቀሱትም፣ የመጀመሪያውን ምዕራፍ ግንባታ ለማካሄድ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ብድር መገኘቱን አስታውቀዋል፡፡ ‹‹እነዚህ ባለሀብቶች አብረውን ለመሥራት መንግሥት በፕሮጀክቱ ላይ ያለውን እምነት ጠይቀውን ይህንንም እየጨረስን ሲሆን፣ እሱን እንዳገኘን ተፈራርመን በቀጥታ ወደ ሥራው ስለመግባት የገንዘብ ችግር ይገጥመናል ብለን አናስብም፤›› ብለዋል፡፡