Thursday, June 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናየኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ የቀድሞ ኃላፊዎች ከባድ የሙስና ክስ ተመሠረተባቸው

የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ የቀድሞ ኃላፊዎች ከባድ የሙስና ክስ ተመሠረተባቸው

ቀን:

ቀድሞ የኢትዮጵያ መድኃኒት ፈንድና አቅርቦት ኤጀንሲ ይባል የነበረው የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ የቀድሞ ኃላፊዎች፣ ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ ተመሠረተባቸው፡፡

ክስ የተመሠረተባቸው የኤጀንሲው የቀድሞ ኃላፊዎች ዋና ዳይሬክተር የነበሩት አቶ ኃይለ ሥላሴ ቢሆን፣ ምክትል ዋና ዳይሬክተር የነበሩት አቶ የማነ ብርሃን ታደሰ፣ የግዥ ዳይሬክተር የነበሩት አቶ ሙከሚል አብደላ፣ የግዥ ዳይሬክቶሬት የሕክምና መሣሪያዎችና መገልገያዎች የግዥ አስተባባሪ የነበሩት አሸናፊ ሁሴን (ኢንጂነር)፣ የግዥ ትንበያና ግንባታ ዳይሬክተር የነበሩት አቶ ያሬድ ይገዙ፣ የግዥ አስተባባሪ አቶ አንዳርጋቸው ሞግሪያና፣ እንዲሁም የመድኃኒትና መገልገያዎች ግዥ አስተባባሪ አቶ ያለው ሞላ ናቸው፡፡

ተከሳሾቹ የማይገባቸውን ጥቅም ለማግኘትና ለሌላ ሰው ለማስገኘት በማሰብ፣ የተሰጣቸውን ሥልጣንና ኃላፊነት በመጠቀም የመንግሥት ግዥ አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 649/2001 አንቀጽ 52 ድንጋጌንና የማስፈጸሚያ መመርያውን አንቀጽ 25 እና የኤጀንሲው የግዥ መመርያ አንቀጽ 10.3 በመተላለፍ፣ የወንጀል ድርጊቱን እንደፈጸሙ የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ ማክሰኞ ግንቦት 13 ቀን 2011 ዓ.ም. ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 15ኛ ወንጀል ችሎት ያቀረበው ክስ ያስረዳል፡፡

- Advertisement -

አዋጁንና መመርያዎቹን በመተላለፍ ለመከላከያ ሚኒስቴር የመድኃኒት ግዥ ለመፈጸም በኤጀንሲውና በአገር መከላከያ ሚኒስቴር መካከል በተደረገ የዱቤ ሽያጭ ውል መሠረት ግዥው እንዲከናወን ሲደረግ፣ ግልጽ ጨረታ በማውጣት ግዥ መፈጸም ቢኖርባቸውም ያንን አለማድረጋቸውን ክሱ ያብራራል፡፡

የግዥ ዳይሬክተር የነበሩት ተከሳሽ በሕጉ መሠረት የሚፈጸም ግዥ መሆኑን የማረጋገጥ ኃላፊነት እያለባቸው፣ በቀጥታ ሲትረክ ኢንተርናሽናል ከሚባል አቅራቢ ግዥ እንዲፈጸም ሲጠየቁ፣ ዋና ዳይሬክተሩ ግዥው ያለ ውድድር እንዲፈጸም ማድረጋቸውንም ዓቃቤ ሕግ በክሱ ገልጿል፡፡

ሌሎቹም ተከሳሾች የግዥ አፅዳቂ ኮሚቴ ሆነው በመሰየማቸው በአዋጁና በመመርያው መሠረት ግዥው መፈጸሙን የማረጋገጥ ኃላፊነት እያለባቸው፣ ሕጉን ያልተከተለ መሆኑን እያወቁ አቅራቢው ድርጅት ያለ ውድድር ቀጥታ ባቀረበው ዋጋ እንዲገዛ የውሳኔ ሐሳብ ማቅረባቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ገልጿል፡፡ ያለ ውድድር እንዲገዛ ቢደረግ እንኳን፣ የመንግሥትን ጥቅም በማያስጠብቅ ድርድር እንዲደረግ መወሰን፣ ወይም የውሳኔ ሐሳብ ማቅረብ እያለባቸው አለማድረጋቸውንም አክሏል፡፡

በአጠቃላይ ተከሳሾቹ ሕግን ባልተከተለ ሁኔታ የ13,449,110 ብር ግዥ እንዲፈጸም በማድረጋቸው፣ በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን በፈጸሙት የመንግሥትን ሥራ በማያመች አኳኋን መምራት ከባድ የሙስና ወንጀል ተመሥርቶባቸዋል፡፡  

ተከሳሾቹ በተመሳሳይ ሁኔታ አዋጁንና መመርያዎችን በመተላለፍ ያለ ጨረታና ተወዳዳሪ የ1,406,281 ብር ኤር አዲስ አበባ ከሚባል ድርጅት ግዥ እንዲፈጸም በማድረግ፣ የወንጀሉ ዋና ተካፋይ በመሆናቸውና የመንግሥትን ሥራ በማያመች አኳኋን በመምራት ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ ቀርቦባቸዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ ክሱን በችሎት ካነበበላቸው በኋላ ዋስትና እንደማያስከለክላቸው በመግለጽ የዋስትና መብታቸው እንዲከበርላቸው የጠየቁ ቢሆንም፣ የተጠቀሰባቸው የወንጀል ሕግ ዋስትና የሚከለክል መሆኑ ተነግሯቸው፣ ጉዳያቸውን በማረሚያ ቤት ሆነው እንዲከታተሉ ተነግሯቸዋል፡፡ በክሱ ላይ መቃወሚያ ካላቸው ለመጠባበቅ ለግንቦት 19 ቀን 2011 ዓ.ም. ቀጠሮ ተሰጥቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...