Monday, April 15, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

እየተተራመሱ ማተራመስ አገርን ሰድቦ ለሰዳቢ መዳረግ ነው!

ኢትዮጵያ ውስጥ ለዓመታት የሕዝቡን ውሎና አዳር ከሚረብሹት መካከል በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሱት፣ የመንግሥት አገልግሎት መስጫ ተቋማት ናቸው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ ለዓመታት የመሠረተ ልማት ግንባታዎች መስተጓጎል፣ የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥና ጨርሶ መጥፋት፣ የውኃ ሥርጭት ለቀናት መሰወር፣ የቴሌኮምና ተያያዥ አገልግሎቶች መደነቃቀፍ፣ የማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎቶች ኋላቀር አሠራርና የመሳሰሉት የብዙዎች እሮሮ የሚስተጋባባቸው ናቸው፡፡ በዚህ ባለንበት ጊዜ ደግሞ ለውጡ በመካሄድ ላይ ያለው፣ የለውጡ ዒላማ በሆኑ ታማሚና ጎስቋላ ተቋማት መሆኑ የታወቀ ነው፡፡ ይህ ደግሞ የለውጡን ስኬት ለሚጠብቁ አለመታደል ነው፡፡ ከዚያ ሲብስ ደግሞ ፍርጃ ነው፡፡ ከዚህም ዘለል ሲል እንደ ፖሊስ፣ የሕግ አስከባሪ አካላትና ሌሎች መንግሥታዊ ተቋማትና ፍርድ ቤቶች ጭምር ሌላው ቢቀር ለውጡን ‹‹በቅን ልቦና›› ያገለግሉታል፣ ያራምዱታል፣ ያግዙታል. . . ተብሎ ተስፋ ሲደረግ እያደር ወደኋላ ሲንሸራተቱ ይታያሉ፡፡ ‹‹ቅን ልቦና›› የሚባለው ቢያንስ ቢያንስ ሕዝብ በሰላም ወጥቶ እንዲገባ፣ የቀድሞ አማራሪ ድርጊቶች እንዳይገጥሙት፣ ችግር ቢኖር እንኳ ሕዝቡ ጭምር ተሳታፊ የሚሆንበት ምኅዳር እንዲፈጠር ያመቻቻሉ በሚል ተስፋ ነው፡፡ ነገር ግን እየተተራመሱ የሚያተራምሱ መልካቸውን ቀያይረው ሲመጡ ብዙ ችግሮች እየተፈጠሩ ነው፡፡

አንዳንድ መሠረታዊ የሆኑ ጉዳዮችን ዞር ዞር እያልን ስንታዘብ አገር የሚያተራምሱ፣ አገር የበለጠ እንዲተራመስና እንዲቀጣጠል ደረቅ ሳር፣ ቅጠልና ሙቀት እያገናኙ ሰበቃ የሚፈጥሩ አላዋቂ ድርጊቶች እናስተውላለን፡፡ ፖሊስ ‹‹የሕጋዊነት መሠረት››ን ዘንግቶ ሕጋዊ ግብር፣ ቀረጥ ወይም ኤክሳይዝ ታክስ የሚከፈልበት ዕቃ ወይም ሸቀጥ ያዝኩ ሲል ይሰማል፡፡ ሌላው ቀርቶ ሰባት ግራም ወርቅ በቁጥጥር ሥር አዋልኩ ማለቱን በዜና ዘገባ ስንሰማ በአጠቃላይ ጥፋቱ፣ ስህተቱ ወይም ዕውቀት አጠርነቱ የጋዜጠኞች? ወይስ የፖሊስ አስፈጻሚ አካል? ብለን መደንገጥ ብቻ ሳይሆን ተስፋ እንቆርጣለን፡፡ ሕጋዊውን ከሕገወጡ ለመለየት የሚያስችሉ አሠራሮችና ሕጎች ባሉበት አገር ውስጥ፣ ከግብታዊ ድርጊቶች መታቀብ አለመቻል ለወቀሳ ይዳርጋል፣ ትዝብት ውስጥ ይከታል፡፡ ማንም ሰው በአመዛዛኝ ህሊና ፈር ሊያስይዘው የሚችል ጉዳይን የትርምስ መስንስዔ ማድረግ እንቆቅልሽ ነው፡፡ የረቀቁና ለማመን የሚከብዱ ችግሮችን መፍታት በሚቻልበት በዚህ ሥልጡን ዘመን፣ እዚህ ግባ የማይባሉ ነገሮችን እያወሳሰቡ ትርምስ መፍጠር አገርን ሰድቦ ለሰዳቢ አሳልፎ መስጠት ነው፡፡

መሠረታዊ የአገልግሎት ሰጪ ከሆኑ ተቋማት መካከል አንዱ የሆነው የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተቋምን በምሳሌነት እናንሳ፡፡ ይህ ተቋም ከበፊት ጀምሮ በአገሪቱ ላይ እንዳሻው የሚያዝ ይመስል፣ ተጠቃሚውን ሕዝብ ወይም ደንበኞችን እንዳሻው ያደርጋል፡፡ በውል ላይ የተመሠረተ መብት ያላቸውን ደንበኞች ሳያማክር፣ መጠበቂያ የሌለውን ማብሪያና ማጥፊያ እንደፈለገው ይጫወትበታል፡፡ የኤሌክትሪክ ኃይል ለምን እንደሚጠፋና ለቀናት ተሰውሮ እንደሚቆይ የሚናገር የለም፣ ይቅርታ መጠየቅማ ነውር ነው፡፡ ይህ ለበርካታ ዓመታት እንደሚቀያየሩት ሰዎች እብሪት መጠን የሚከናወን ድርጊት በሚሊዮኖች ላይ ሰቆቃ ሆኖ ቆይቷል፣ አሁንም ቀጥሏል፡፡ መሰንበቻውን በስንት ጩኸት ግንቦት 9 ቀን 2011 ዓ.ም. በተሰጠ መግለጫ ደግሞ፣ ከግንቦት 1 ቀን ጀምሮ ኃይል በፈረቃ ይዳረሳል ተብሎ ለሕዝቡ ተነግሮታል፡፡ በተቋሙ አቆጣጠር አንድ ‹‹ፈረቃ›› እንኳን ሳይሞላና ፈረቃውም ለደንበኞች በቅጡ ሳይገባቸው፣ ፈረቃው ከሦስት ወደ ሁለት ተቀይሯል ተባለ፡፡ አሁንም ፈረቃው የማብራት ይሁን የማጥፋት ግልጽ አይደለም፡፡ ይህ ሁሉ ትርምስ ምንድነው? ሥውሩ ፈረቃ ከስምንት ቀናት በኋላ ግልጽ ቢደረግም፣ አሁንም የተድበሰበሰ ነገር ያለ ይመስል ደግሞ መግለጫው ራሱ ግልጽ አይደለም፡፡

ከላይ በምሳሌ የቀረበው ዓይነት ዝርክርክነቶች በርካታ ናቸው፡፡ እነዚህ ዝርክርክነቶች ሰድቦ ለሰዳቢ ከመዳረጋቸውም ባለፈ፣ ከለውጡ በተፃራሪ ላሉ ኃይሎች ጥሩ የጩኸት ማድመቂያ ሆነዋል፡፡ እንዲህ ዓይነት ትርምስ ውስጥ መዘፈቅ ደግሞ የድክመትን ጥልቀትና ስፋት አለማወቅን ያሳያል፡፡ ድክመቱ በብዙ ሥፍራዎች ያሉ ዝርክርነቶችን ፍንትው አድርጎ ስለሚያሳይ፣ እዚህ ላይ አንድ ነገር ማለት ይገባል፡፡ እዚህ አገር የሄደውና የመጣው እንዳሻው ስም ስለሚሰጥና ስለሚሰይም፣ የሰያሚ ሥልጣንና የመወሰን አስፈላጊነት ሳይለይ 28 ዓመታት የሞላውን የግንቦት 20ን ጥፋት መልሶ ይደግማል፡፡ ግንቦት 20 የሕዝብ በዓል ሆኖ እንዲከበር በሕግ አልተወሰነም፣ መስከረም 2 ቀንም ከሕዝብ በዓልነት በሕግ አልተሰረዘም፡፡ ከሁለት አሠርት ዓመታት በፊት ግንቦት 20 የሚባል መንገድ (ደብረ ዘይት መንገድ) ተሰይሞ ነበር፡፡ በዚያን ጊዜ ነፍስ የሚያውቁና አሁንም በሕይወት ያሉ ያስታውሳሉ፡፡ ዛሬ ያ ስያሜ እንኳን አፍ ውስጥ የስያሜው መዝገብ ውስጥ የለም፡፡ የጠፋው በማግሥቱ ነው፡፡ ዛሬም ተቋም ሳይደራጅና ስያሜ ሳይሰየም የመንገድ ስም መለዋወጥ ውስጥ ተገብቶ፣ አንቱ የሚባል የመንግሥት ተቋምን ጭምር ማስገመት ውስጥ ተገብቷል፡፡ ለተጀመረው ለውጥ ሰላም የመስጠት ትክክለኛነትና ትጋት ከለውጡም ኃይሎች ጭምር ስለሚጠበቅ፣ ከማተራመስና ከመተራመስ መውጣት የግድ ይሆናል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ‹‹ገበታ ለሸገር›› የገቢ ማሰባሰቢያ የእራት ሥነ ሥርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር፣ ‹‹አቧራ›› እና ‹‹አሻራ››ን በተመለከተ ያነሱት ሐሳብ እዚህ ላይ ሊጠቀስ ይገባል፡፡ ‹‹አቧራ ማስነሳት›› ቀላልና አካባቢን ማናወጥ እንደሚበቃው፣ መርገጥና መረጋገጥ ከበቂ በላይ አቧሯ በማስነሳት አቧራው በፍጥነት አካባቢን እንደሚያዳርስ አውስተዋል፡፡ አቧሯ አካባቢውን የሕይወት ሳይሆን የሞት ቀጣና እንደሚያስመስለው፣ ላስነሳው ሰው ‹‹ጨሰ አቧራው ጨሰ›› ተብሎ ቢዘፈንለትም፣ እየባሰ ሲሄድ ግን ዘፋኞቹ ወዳ አልቃሽነት መቀየራቸው አይቀሬ ነው ብለዋል፡፡ ‹‹አሻራ›› ግን ቶሎ እንደማይታይ፣ በቶሎ ወደ ላይ እንደማይነሳና ስም እንደማያስጠራ፣ አሻራን በቀላሉ ጥሎ መሄድ እንደማይቻል፣ ድምፅ እንደሌለው፣ ታይታ እንደማያስገኝ፣ አድካሚና አሰልቺ መሆኑን፣ ሐሜትና ነቀፋ እንደማያስከትል፣ ሌሎች እስከሚረዱ ጊዜ እንደሚወስድ፣ ትዕግሥትን እንደሚፈታተንና በዓለም ላይ የትውልድ አሻራን ያኖሩ ሁሉ ይህ ገጥሟቸዋል ብለዋል፡፡ ይህ መልዕክት መላውን የአገር ሰው የሚመለከት ቢሆንም፣ በመንግሥት ኃላፊነት ላይ ያሉትን ደግሞ ሰርስሯቸው ሊገባ የግድ ይላል፡፡ እየተተራመሱ የሚያተራምሱ በጣም የበዙ በመሆናቸው፣ ከአሻራ ወይም ከአቧራ ምረጡ መባል አለበት፡፡ የመንግሥት ተቋማት በዚህ መሠረት እንዲደራጁ ካልተደረገ የአሁኑ አያያዛቸው ያስፈራል፡፡ እየተተራመሱ ማተራመስ አገርን ሰድቦ ለሰዳቢ መዳረግ መሆኑን ሊያውቁ ይገባል!   

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...

‹‹ደስታ›› የተባለችው አማርኛ ተናጋሪ ሮቦት በሳይንስ ሙዚየም

‹‹እንደ ሮቦት ዋነኛው አገልግሎቴ ውስብስብ የሆኑ የቴክኖሎጂ ውጤቶችንና አሠራሮችን...

በአዲስ አበባ ከ700 ሺሕ በላይ የትራፊክ የደንብ ጥሰቶች መፈጸማቸው ተገለጸ

በአዲስ አበባ 716,624 የትራፊክ የደንብ ጥሰቶች መፈጸማቸውን፣ የአዲስ አበባ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የማፍረስ ዘመቻው በብልሹ አሠራሮች ላይም ይቀጥል!

መንግሥት በኮሪደር ልማት አማካይነት የአዲስ አበባ ከተማን ዋና ዋና ሥፍራዎች በማፍረስ፣ አዲስ አበባን ከኬፕታውን ቀጥሎ ተመራጭ የአፍሪካ ከተማ ለማድረግ መጠነ ሰፊ ሥራ ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡...

ለድጋፍ ብቻ ሳይሆን ለተቃውሞም ማስተንፈሻ ይሰጥ!

በሕዝብ ድምፅ ተመርጦ ሥልጣን የያዘ መንግሥት ዋነኛ ሥራው በሕግ መሠረት የተሰጡትን ኃላፊነቶች በብቃት መወጣት ነው፡፡ የሕዝብን ሰላምና ደኅንነት ማስጠበቅ፣ የአገርን የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነት ማስከበር፣...

የፖለቲካ ምኅዳሩ እንዳይዳፈን ጥንቃቄ ይደረግ!

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ምኅዳር አሁንም ጤና አልባ ሆኖ የተለመደው ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታ ውስጥ ነው የሚገኘው፡፡ ካለፉት ሃምሳ ዓመታት ወዲህ ሊሻሻል ያልቻለው የፖለቲካ ምኅዳር ሰሞኑን አዲስ...