Tuesday, April 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየለገጣፎ ተፈናቃዮች ለሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔ አቤቱታ አቀረቡ

የለገጣፎ ተፈናቃዮች ለሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔ አቤቱታ አቀረቡ

ቀን:

183 የለገጣፎ ተፈናቃዮች የ70 ሚሊዮን ብር ክስ ሊመሠርቱ ነው

የለገጣፎ ተፈናቃዮች የዜጎችን እኩልነትና ሰብዓዊ መብት ይነካል ባሏቸው የሊዝ አዋጁን መሠረት አድርገው በወጡ ደንብና መመርያዎች ላይ የሕገ መንግሥት ትርጉም ጥያቄ አነሱ፡፡ አቤቱታቸውን ለሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔ አቅርበዋል፡፡ የሊዝ አዋጁን ተከትለው የወጡትና የዜጎችን መብት ይነካሉ የተባሉት የኦሮሚያ ክልል የከተማ መሬትን የመተለከቱ ሕጎች መሆናቸው ታውቋል፡፡

የሕገ መንግሥት ትርጉም ጥያቄ የቀረበባቸው የፌዴራል መንግሥት አዋጅ ቁጥር 721/04፣ የኦሮሚያ ደንብ ቁጥር 182/2008 እና መመርያ ቁጥር 05/2008 ድንጋጌዎችን መሠረት በማድረግ መንግሥት መኖሪያቸው እንዲፈርስ ያስተላለፈው ውሳኔ፣ በሕገ መንግሥቱ የተደነገጉትን መሠረታዊ መብቶች ስለሚነካ እንደሆነ የተፈናቃዮች ጠበቃ አቶ በላቸው ግርማ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ጥያቄ የተነሳባቸው የከተማ መሬትን በሊዝ ለማስተዳደር ተሻሽሎ የወጣ ደንብ ቁጥር 182/2008፣ የኦሮሚያ ክልል የከተማ መሬት ሰነድ አልባና ሕገወጥ ግንባታዎችን ሥርዓት ለማስያዝ የወጣ መመርያ 05/2008 በሕገ መንግሥቱ የተደነገጉትን መሠረታዊ የእኩልነት፣ የመዘዋወር፣ ፍትሕ የማግኘት፣ ንብረት የማፍራት፣ እንዲሁም ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ መብቶች የሚቃረኑ ሆነው በመገኘታቸው እንደሆነ ጠበቃው አስረድተዋል፡፡

የሕገ መንግሥት ትርጉም እንዲሰጥባቸው በአመልካቾች የተነሱት ድንጋጌዎች በአዋጅ ቁጥር 721/2004 አንቀጽ 26፣ በደንብ ቁጥር 182/2008 አንቀጽ 56 ንዑስ አንቀጽ 4፣ በመመርያ ቁጥር 05/2008 አንቀጽ 33 ንዑስ አንቀጽ 4 ሥር የሠፈሩ ድንጋጌዎች መሆናቸው ታውቋል፡፡ መሠረታዊ ችግር ታይቶባቸዋል የተባሉትን ስድስት ነጥቦች የያዘ ዝርዝር ሰነድ ለአጣሪ ጉባዔው የተላከው ግንቦት 2 ቀን 2011 ዓ.ም. መሆኑን ጠበቃው አስረድተዋል፡፡

በአዋጅ ቁጥር 721/2004 በአንቀጽ 26 ንዑስ አንቀጽ 4 ሥር የሠፈረው ‹‹የሚመለከተው የመንግሥት አካል በሕገወጥ መንገድ የተያዘን የከተማ ቦታ የሰባት የሥራ ቀናት የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ በመስጠት ወይም ቦታው ላይ በመለጠፍ የማስለቀቅ ሥልጣን አለው፤›› በሚለው ላይ በፌዴራል ሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 37 ፍትሕ የማግኘት መብትን ዕውቅና ሰጥቶ ሳለ፣ የፌዴራል የሊዝ አዋጁ ሕገወጥ ይዞታ ወይም ለባለንብረቶቹ ምንም ዓይነት ካሳ መክፈል ሳያስፈልግ የማስለቀቅ ሥልጣኑን ሙሉ በሙሉ ለአስፈጻሚ አካል ብቻ መስጠት ከሕገ መንግሥቱ ይቃረናል የሚል መከራከሪያ አቅርበዋል፡፡

በዓለም አቀፍ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ባህላዊ መብቶች ቃል ኪዳን በአንቀጽ 11 ላይ የሚደነግገውን የስምምነቱ አባል አገሮች የማንኛውም ሰው በቂ የመኖሪያ ቤት የማግኘት መብት ማክበር ማስከበር አለባቸው የሚለውን ድንጋጌ ጠቅሰውም፣ ቤታቸው የፈረሰባቸው የለገጣፎ ተፈናቃዮች ጉዳይ ከዚህ አንፃር እንዲታይም ጠይቀዋል፡፡

በለገጣፎ ያለ ፕላን የተሠሩ ተብለው ከወራት በፊት በሺዎች የሚቆጠሩ ቤቶች ሲፈርሱ በርካታ ተፈናቃዮች ሜዳ መውደቃቸው የሚታወስ ነው፡፡ ተፈናቃዮቹ በአካባቢው ድንኳን ጥለውና በየዘመድ ቤቱ ተጠግተው እየኖሩ እንደሚገኙ መዘገባችን ይታወሳል፡፡

ከቤት ንብረታችን ያላግባብ ተፈናቅለናል የሚሉት የለገጣፎ ተፈናቃዮች መንግሥት ተገቢውን ምላሽ እንዲሰጣቸው ሲጠይቁ ቆይተው፣ ሰሞኑን ጉዳዩን ወደ ሕግ መውሰዳቸው ተሰምቷል፡፡

ሁለት መቶ አርባ ተፈናቃዮች ሦስት ጠበቃዎችን ወክለው ጉዳዩ በሕግ እንዲታይ እንቅስቃሴ እንደ ጀመሩ ታውቋል፡፡ ከሦስቱ ጠበቃዎች አንዱ የሆኑት አቶ በላቸው ሌሎቹ ተፈናቃዮች መታወቂያቸው በመጥፋቱ፣ ባለመታደሱና በተለያዩ ምክንያቶች ውክልና መስጠት እንዳልቻሉ ገልጸዋል፡፡

በፍትሐ ብሔር ሕጉ በአንቀጽ 1149 የተቀመጠውን የሁከት ይወገድልኝ ድንጋጌን መሠረት በማድረግ ‹የተወሰደ ይዞታችን ይመለስ፣ የወደመ ንብረታችን ይካስ› የሚል ክስ ሊመሠረቱ መሆኑም ታውቋል፡፡ በጠበቆቹ ከተወከሉ 240 ተፈናቃዮች መካከል 183 ያህሉ የ70 ሚሊዮን ብር ክስ ሊመሠርቱ መሆኑን ጠበቃው ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር የጨረታ ማስታወቂያ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር በገቢ እና በውጭ ንግድ እንዲሁም...

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...