Tuesday, March 5, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊ‹‹እናሸንፋለን እንጂ ሽንፈት አጠገባችን አይቀርብም›› ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)

‹‹እናሸንፋለን እንጂ ሽንፈት አጠገባችን አይቀርብም›› ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)

ቀን:

እሑድ ግንቦት 11 ቀን 2011 ዓ.ም. ምሽት ‹‹ገበታ ለሸገር›› የገቢ ማሰባሰቢያ የእራት ሥነ ሥርዓት ላይ ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ በአንድ አገር ውስጥ የተከማቸ ታላቅ ሀብት ሚስጥሩ ታላቅ ሐሳብ እንጂ ተፈጥሮአዊ ችሮታ አይደለም አሉ፡፡ ታላቅ ሐሳብ የደማቅ አሻራ መነሻ መሠረት ነው ብለው፣ ደማቅ አሻራ አብዝቶ በመስጠት እንጂ በመቀበል የሚገኝ ፍሬ እንዳልሆነ አክለዋል፡፡ ‹‹የጋራ ቤትን ተባብሮ ለመሥራት በቆረጥን ጊዜ ሁሉ፣ በአብሮነትም በጋራ ለመቆም በተነሳን ጊዜ ድል ከፊታችን ትቀርባለች፡፡ እናሸንፋለን እንጂ ሽንፈት አጠገባችን አይቀርብም፤›› ብለዋል፡፡

ንግግራቸውን በተለያዩ ቋንቋዎች ሰላምታ የጀመሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ‹‹በዚህ ታሪካዊ ቦታ ለመሥራት የተሰበሰባችሁ ክቡራትና ክቡራን፣ ዛሬ ለእናንተ የማነሳው አንድ ጉዳይ አለኝ፤›› በማለት አቧራና አሻራን በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ በትውልድ ጉዞ ውስጥ አቧራ ያነሱም አሻራ ያተሙም ሰዎች እንደነበሩ፣ ወደፊትም እንደሚኖሩ አመልክተዋል፡፡ አቧራን ማስነሳት ቀላል እንደሆነና በቶሎም ማዳረስ እንደሚቻል፣ አሻራ ግን የአቧራን ያህል የማይታይና ታይታ የማይገኝበት አድካሚና አሰልቺ መሆኑን አውስተዋል፡፡ ‹‹አቧራ ሲነሳ ጉፍያ ሲያገሳ›› እንደሚባል በማውሳት ያረጀ አንበሳ ያለ የሌለ ድምፁን አሰባስቦ ሲጮህ እንደሚሰማ ገልጸዋል፡፡ አሻራ ግን ትዕግሥትን የሚፈታተን መሆኑን በማስረዳት፣ አሻራን ማስቀመጥ ሲጀመር ፈታኝ ሲፈጸም አስመሥጋኝ የመሆኑን ዘለዓለማዊ እውነትነት ከአክሱም ሐውልቶች፣ ከላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት፣ ከፋሲል ቤተ መንግሥት፣ ከጀጎል ግንብ፣ ከጂማ አባ ጅፋር ቤተ መንግሥት በመጠቃቀስ አሻራ እንጂ አቧራ አይደሉም ብለዋል፡፡

‹‹የዓድዋና የካራማራ ድሎች አሻራ እንጂ አቧራ አይደሉም፡፡ የእነ ፀጋዬ ገብረ መድኅን፣ የእነ ሐዲስ ዓለማየሁ፣ የእነ ገብረ ሕይወት ባይከዳኝ፣ የእነ ጥላሁን ገሠሠ፣ የእነ ዓሊ ቢራ፣ የእነ አበበ ቢቂላ፣ የእነ ምሩፅ ይፍጠር፣ የእነ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ፣ የእነ ደራርቱ ቱሉ ሥራዎችና ድሎች ሁሉ አሻራ እንጂ አቧራ አልነበሩም፣ አይደሉም፤›› ብለዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በዚህ ዘመን አቧራ አስነስተው ስም ለማስጠራት፣ ታሪክ ለመሥራት የሚደክሙ ሰዎች አሉ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ፣ ‹‹ለጊዜው ያደናግራል፡፡ አቧራ ማስነሳት የጉብዝና ምልክት ይመስላል፡፡ ‹ለስሟ መጠሪያ ቁና ሰፋች› እንደተባለውም፣ ለጊዜው ስምን ያስጠሩ ይመስላል፡፡ የአቧራና የአቧራ አስነሺዎች ታሪክና ሥራ ግን እንኳን ዘመን ወቅትን አይሻገርም፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

‹‹’ያማ ቀርቶ ሌላ ዘፈን መጥቶ’ እንደሚባለው ፋሽን ሆኖ መጥቶ እንደ ፋሽን ያልፋል፡፡ የአገራችንም ታሪክ ይኼንን ይነግረናል፡፡ መከራና ችግርን ተቋቁመው እዚህ የደረሱልን የአገራችን መኩሪያ ቅርሶች አሻራዎች እንጂ አቧራዎች አይደሉም፡፡ በየዘመኑ የተነሱት አቧራዎች ለጊዜው ታይተው፣ አስደንቀው፣ አደባልቀው፣ አነዋውጠው ሄደዋል፣ አልፈዋል፤›› ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ‹‹እዚህ ቦታ የተሰበሰብነው እራት ለመብላት አይደለም፣ አሻራ ለማኖር ነው፡፡ የከፈላችሁት ገንዘብ ለእራት የሚከፈል አይደለም፡፡ በኢትዮጵያ ዕድገትና ሥልጣኔ ላይ አሻራችሁን ለማኖር ነው፡፡ አስቡት ከዛሬ ሰላሳና አርባ ዓመት በኋላ ሁላችንም አርጅተን፣ በዚህ የአዲስ አበባ ተፋሰስ ግራና ቀኝ ደስታን አስቡት እስኪ፤›› በማለት፣ በአምስት ሚሊዮን ብር የሚገኝ እንዳልሆነ ለእራት ሥነ ሥርዓቱ ተሳታፊዎች ማስረዳት ለቀባሪው ማርዳት ነው ብለዋል፡፡

‹‹ልጆቻችን በዚህ የትውልድ ፕሮጀክት ላይ ስማችንን ሲያዩትና የዛሬውን ፎቶግራፋችንን ሲመለከቱ፣ የዚያ ዘመን ትውልድ በወንዞቹ ዳርቻ እየተዝናና በዛፎቹ ሥር ሲያወጋ በቤተ መጻሕፍቱ ውስጥ እያነበበ ይህንን አሻራ የተውለትን አባቶቹንና እናቶቹን ሲያመሠግን ምን ሊሰማው እንደሚችል እስቲ ለአፍታ አስቡት፤›› በማለት የወደፊቱን በምናብ ገልጸዋል፡፡

ለአባቶች ክብር፣ ለልጆች ፍቅር ሲባል የኢትዮጵያውያን የወል ካስማና የአፍሪካ ዋና ከተማና የብዙ ታሪክ ማማ ለሆነችው ለአዲስ አበባ አደይ አበባዋን ለመመለስ ሥነ ሥርዓቱ መዘጋጀቱን ጠቁመው፣ ‹‹ከተማችን ከመስከረም ወፍና ከቢራቢሮዎች ውብ ትዕይንት ከተፋታች ቆይታለች፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹ከተማችን ከተክሎች የተፈጥሮ መዓዛ፣ በስሱ ከሚነፍስ ቀዝቃዛ ንፋስና ቅዝ ብለው ከሚበሩ መንፈስ ጠጋኝ ድንቅ ወፎች ከተኳረፈች ከራርማለች፡፡ ይኼንን ማጣታችን እኛንም ሆነ ልጆቻችንን ያሳጣን ብዙ ነገር አለ፤›› ሲሉ የችግሩን መጠን አመላክተዋል፡፡ አዲስ አበባ የአፍሪካ መዲና ብቻ ከመባል አልፋ የአፍሪካ ውብና ፅዱዋ ከተማ የምትባልበት ጊዜ እንደሚመጣ ተስፋ እንደሚያደርጉ፣ ከባዱ የመጀመርያ ዕርምጃ አንድ ተብሎ መጀመሩን፣ በንፅህና ባህሉና በተግባሩ እንጂ ከተማ በስሙ አይወደድም፣ በግብሩ እንጂ በባዶ ቃሉ አይመሠገንም ብለዋል፡፡

‹‹ለዚህች ታላቅ አገር፣ ለዚህች ታላቅ ከተማ፣ ለዚህ ታላቅ ሕዝብ ገጽታውን፣ ታሪኩንና ደረጃውን የሚለውጥ አሻራ ለማኖር እንኳን በዚህ ታሪካዊ ሥፍራ ተገናኘን፡፡ አቧራው ይጭስ ተውት፡፡ ስለሱ ብዙ አታሰቡ፡፡ እኛ አሻራችንን በክብር እናኖራለን፡፡ በክብርም በዚህች አገር ታሪክ እንታወሳለን፤›› ካሉ በኋላ፣ ሁሉንም ተሳታፊዎች የቀኝ እጃቸውን አውራጣት በማስወጣት ጠረጴዛ ላይ አብረዋቸው አሻራቸውን በማሳረፍ፣ ‹‹አቧራውን አልፈዋለሁ፣ አሻራዬን አኖራለሁ፣ ታሪኬንም እሠራለሁ፤›› በማለት በአንድነት አስተጋብተዋል፡፡

በታላቁ ቤተ መንግሥት በአፄ ምኒልክ የግብር አዳራሽ በተዘጋጀው ‹‹ገበታ ለሸገር›› የእራት ሥነ ሥርዓት ላይ ከ240 በላይ ተሳታፊዎች የተገኙ ሲሆን፣ ከሁለት ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ተገኝቷል፡፡ በነፍስ ወከፍ ለአንድ ገበታ አምስት ሚሊዮን ብር ከከፈሉ ጀምሮ፣ የተለያየ መጠን ያለው የገንዘብ ድጋፍ ያደረጉ የአገር ውስጥና የውጭ ተቋማት ለገቢው አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡ የአዲስ አበባ ወንዞችን ለማልማት ለተመሠረተው ፕሮጀክት 29 ቢሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ መገለጹ ይታወሳል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ቁጥር ሲጨምር የሚኒባስ ታክሲዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱ ሊታሰብበት ይገባል

በአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ከፍተኛ የሚባለውን ድርሻ...

ሃምሳ ዓመታት ያስቆጠረው አብዮትና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውጣ ውረድ

የኢትዮጵያ ሕዝቦች የዴሞክራሲ ለውጥ ጥያቄ የሚነሳው ከፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የተፈጸመው ሕገወጥ ተግባር ምንድነው?

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የዳይሬክተሮች ቦርድ፣...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ላይ ምርመራ እንዲደረግ ውሳኔ ተላለፈ

ፕሬዚዳንቷና ዋና ጸሐፊው ተጠያቂ ሊሆኑ ይችላሉ ተብሏል ከአዲስ አበባ ንግድና...