የዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማኅበር (አይኤኤኤፍ) ከሚያዘጋጃቸው ውድድሮች ሩጫና የሜዳ ተግባራትን የሚያካትተው የዳይመንድ ሊግ ውድድር ይጠቀሳል፡፡ ከውድድሮቹ መካከል በተለይ ምሥራቅ አፍሪካውያኑ ኢትዮጵያውያን ኬንያውያን አትሌቶች ከሚታወቁባቸው ረዥም ርቀት 5000 ሜትር አንዱ ነበር፡፡ ተቋሙ ለሁለተኛ ጊዜ በቻይና ሻንጋይ ባዘጋጀው በዚሁ ውድድር በ5000 ሜትር የቀረቡት ኢትዮጵያውያኑ ያለ ተቀናቃኝ ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ያለውን ደረጃ በመያዝ አጠናቃዋል፡፡ በአሜሪካ ናይኪ አካዳሚ የተሟላ ሳይንሳዊ ሥልጠናውን እየወሰደ የሚገኘው ዮሚፍ ቀጀልቻ ርቀቱን 13፡04፡ 16 በማጠናቀቅ አንደኛ ሲወጣ፣ በአገር ውስጥ በኢትዮጵያውያን አሠልጣኞች የሚሠለጥኑት ሰለሞን ባረጋና ሐጎስ ገብረ ሕይወት 13፡04፡71 እና 13፡04፡83 በማጠናቀቅ ሁለተኛና ሦስተኛ መውጣት መቻላቸው የአይኤኤኤፍ ዘገባ ያመለክታል፡፡