Thursday, June 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ስፖርትየክልል ቡድኖች ፉክክር ለፕሪሚየር ሊጉ ድምቀት ሆኗል

የክልል ቡድኖች ፉክክር ለፕሪሚየር ሊጉ ድምቀት ሆኗል

ቀን:

በመከናወን ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በ25ኛው ሳምንት  መርሐ ግብሩ ፋሲል ከተማን በደረጃ ሰንጠረዡ አናት ሲያስቀምጥ፣ ለረዥም ወራት ደረጃውን ተቆጣጥሮት የቆየው መቐለ 70 እንደርታ በሜዳውና በደጋፊው ፊት በሐዋሳ ከተማ በደረሰበት ሽንፈት ከመሪው ፋሲል ከተማ በአንድ ነጥብ ዝቅ ብሎ  እንዲከተል ግድ ብሎታል፡፡ ተከታዩ ሲዳማ ቡናም በተመሳሳይ ከሁለቱ ቡድኖች ያልተናነሰ የዋንጫ ዕድል እንዳለው ከእንቅስቃሴው መረዳት ይቻላል፡፡

ከሻምፒዮንነቱ ክብር ጎን ለጎን ላለመውረድ የሚደረገውም ፉክክር እንደዚሁ ፕሪሚየር ሊጉ ተጠባቂ እንዲሆን ከማድረጉም በላይ፣ ለቀጣይዎቹ የሊጉ መርሐ ግብር ድምቀት ሆኗል፡፡ ይሁንና አሁን የያዘውን መልክ ይዞ በስኬት መጠናቀቅ ይችል ዘንድ ሊጉን በባለቤትነት የሚያስተዳድረው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ልዩ ጥንቃቄ ካልታከለበት ግን አደጋ እንዳለው ሥጋታቸውን የሚገልጹ አልታጡም፡፡ ምክንያቱም ከሻምፒዮንነቱ ውጪ ሆነው ነገር ግን የመውረድ ሥጋት የሌለባቸው ቡድኖች ለቀሪ ጨዋታቸው የሚሰጡት ትኩረት ወሳኝ እንደሆነ ይታመናል፡፡

የእግር ኳሱ ደረጃ የፉክክሩን ያህል ሚዛን የሚደፋ ባይሆንም በሊጉ የሁለት አሠርታት ዕድሜ የክልል ቡድኖች ለሻምፒዮንነቱ ክብር በብቸኝነት ሲፎካከሩ የዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑ፣ ይህ በተለይም ለአንጋፋዎቹ ቅዱስ ጊዮርጊስና መከላከያ እንዲሁም ኢትዮጵያ ቡና በቀጣይ ይኖረናል ብለው ለሚያስቡት የተፎካካሪነት አቅም ከወዲሁ እንዲያስቡበት የሚያመላክት መሆኑ እየተነገረ ይገኛል፡፡ ምክንያቱም ባለፈው ወደ ጅማ ያቀናው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዋንጫ፣ ዘንድሮ ደግሞ ከሦስቱ ማለትም ፋሲልና መቐለ አልያም ወደ ሲዳማ ቡና ማቅናቱ ከወዲሁ ዕውን የሆነ ይመስላል፡፡

- Advertisement -

ፕሪሚየር ሊጉን ገለልተኛ ሆነው የሚከታተሉ ወገኖች ግን፣ ፉክክሩ ለወትሮ በጥቂት የአዲስ አበባ ክለቦች መካከል የነበረው ዘንድሮ በርከት ብለው በሚገኙት የክልል ክለቦች መሆኑ ካልሆነ፣ በእግር ኳሱ ደረጃ ላይ የመጣ አንዳች ለውጥ እንደሌለ ያምናሉ፡፡ ሆኖም ባለፉት ዓመታት ውድቀቱ ብቻ ሳይሆን፣ በተመልካች ድርቅ ክፉኛ ተመትቶ የቆየው እግር ኳስ በዚህ መልኩ ተመልካች አግኝቶ መመልከት መቻላቸው አንድ ነገር እንደሆነ ይናገራሉ፡፡

በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከእግር ኳስ ዳኝነት ጀምሮ አሁንም በጨዋታ ታዛቢ ዳኝነት እያገለገሉ ይገኛሉ፣ ለደኅንነታቸው ሲሉ ግን ማንነታቸው እንዲገለጽ አይፈልጉም፡፡ የዘንድሮ ፕሪሚየር ሊግ ጠንካራ ጎን የሚሉት ሙያተኛው፣ ‹‹ሊጉ ሲጀመር ከስፖርታዊ ጨዋነት ጋር ተያይዞ ትልቅ ሥጋት ሆኖ የነበረው ሁከትና ብጥብጥ ለጊዜውም ቢሆን ጋብ ማለቱ አንዱ ሲሆን፣ ሌላው ደግሞ የክልል ቡድኖች በአዲስ አበባ ክለቦች ላይ የበላይነት መውሰዳቸው ብቻ ነው፤›› ይላሉ፡፡

አስተያየት ሰጪው ትዝብታቸውን ሲቀጥሉ፣ ‹‹የክልሎቻችን ፉክክር አሁን እንደሚስተዋለው እግር ኳሱን መርህ ያደረገ ከሆነ እሰየው የሚያስብል ነው፡፡ ግን አይደለም፤ ምክንያቱም አንዳንድ ክልሎች ይወክለናል ብለው የሚደግፉት ቡድን ሲያሸንፍም ሆነ ሲሸነፍ፣ ማንነት እንዳሸነፈ አልያም እንደተሸነፈ አድርጎ የመቁጠር አዝማሚያ እየተስተዋለ ነው፡፡ ይህ በእኔ አስተሳሰብ እግር ኳሳዊ መርህን የተከተለ ነው ተብሎ አይወሰድም፡፡ አንዳንዶች ከፉክክሩ እየራቁ ከመጡት የአዲስ አበባ ቡድኖች የክልል ቡድኖች ጥንካሬ አድርገው የሚወስዱ አሉ፣ ይህ በእኔ ስህተት ነው፤›› የሚሉት ሙያተኛው ከብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ጀምሮ በተዋረድ የሚመለከታቸው አካላት ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ትልቅ የቤት ሥራ እንደሚጠብቃቸው ያምናሉ፡፡

‹‹በፕሪሚየር ሊጉ ከሻምፒዮኑ ማን ይሆናል ከሚለው እስከ ወራጁ ቡድን ማንነት አሁን ላይ እንዲህንና እንዲያ ብሎ ለመናገር አዳጋች መሆኑ ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡ እስከ ዛሬ በነበረው ተሞክሮ አሸናፊው ቡደን በዚህ ጊዜ አይደለም፣ ገና ሁለተኛው ዙር እንደተጀመረ ይታወቅ ነበር፣ ይህ በእግር ኳሳዊ ግምገማ እጅጉን ሊበረታታ የሚገባው፣ ፌዴሬሽኑም ሆነ ክለቦች እንዲሁም ሙያተኞች አጠናክረው ሊቀጥሉበት የሚገባ ነው፤›› የሚሉት ሙያተኛው፣ የእሳቸውን የሙያ ባልደረቦች ጨምሮ ዳኞች፣ የመውረድ ሥጋት የሌለባቸው ክለቦችና አሠልጣኞች እንዲሁም የክለብ ደጋፊዎች ማግኘት የሚገባቸውን ውጤት ማግኘት ያለባቸው በሥራቸው ልክ እንዲሆን ይጠይቃሉ፡፡

ፕሪሚየር ሊጉን በ49 ነጥብ የሚመራው ፋሲል ከተማ፣ በ26ኛ ሳምንት ጨዋታው ከሜዳው ውጪ ከወላይታ ድቻ፣ በ27ኛ ሳምንት ጨዋታው ደግሞ በሜዳው ከባህር ዳር ከተማ ይጫወታል፡፡ ሲቀጥል ከሜዳው ውጪ ከአዳማ ከተማ፣ በሜዳው ከቅዱስ ጊዮርጊስና የመጨረሻውን ጨዋታ ደግሞ ከሜዳው ውጪ በወራጅ ቀጣና ከሚገኘው ስሁል ሽረ ጋር ይጫወታል፡፡

ከመሪው በአንድ ነጥብ ዝቅ ብሎ የሚገኘው መቐለ ከተማ በበኩሉ፣ በ26ኛ ሳምንት ጨዋታው ከሜዳው ውጪ ከጅማ አባ ጅፋርና ከኢትዮጵያ ቡና እንዲሁም በ28ኛ ሳምንት ጨዋታው በሜዳው ከደቡብ ፖሊስና ከሜዳው ውጪ ከመከላከያ ጋር እንዲሁም የመጨረሻውን ጨዋታ በሜዳው ከድሬዳዋ ጋር ይጫወታል፡፡

በ46 ነጥብ ከአንደኛውና ከሁለተኛው ርቆ የሚገኘው ሲዳማ ቡና፣ በሜዳው ከደቡብ ፖሊስና ከሜዳው ውጪ ከመከላከያ እንዲሁም በሜዳው ከድሬዳዋ ከተማና ከደደቢት ከተጫወተ በኋላ የመጨረሻውን ጨዋታ በሜዳው ከወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ጋር ይጫወታል፡፡ በሻምፒዮኖቹና በወራጆቹ መካከል ማለትም ፋሲል ከተማ ከወላይታ ድቻና ከስሁል ሽረ በሜዳውና ከሜዳው ውጪ የሚያደርጋቸው ጨዋታዎች ዋንጫውን ለማግኘትና ላለመውረድ የሚደረጉ ጨዋታዎች መሆናቸው ለጨዋታው ፍትሐዊነት ጠቀሜታው የጎላ ይሆናል፡፡

እንደ ፋሲል ከተማ ሁሉ መቐለ ከተማም ከደቡብ ፖሊስና ከመከላከያ ጋር የሚያደርጋቸው ጨዋታዎች የጨዋታውን ፍትሐዊነት የሚያጎለብቱ ሲሆን፣ በሲዳማ ቡና በኩል ያለውም ቢሆን ከደቡብ ፖሊስ፣ ከመከላከያና ከደደቢት ጋር የሚያደርጋቸው ጨዋታዎች የቡድኖቹን በፕሪሚየር ሊጉ የመቆየትና ዋንጫ በማንሳት ባለማንሳት የሚወሰኑ መሆናቸው በተመሳሳይ የጨዋታውን ፍትሐዊነት የሚያረጋግጡ መሆን አለባቸው፡፡

ይሁንና ከነዚህ ቡድኖች በተጓዳኝ የሚገኙት ከሌሎቹ ቡድኖች ጋር ወራጆቹም ሆነ ለሻምፒዮንነት የሚጫወቱት ቡድኖች የሚገጥሟቸው ቡድኖች የጨዋታውን ፍትሐዊነት ከመጠበቅ አኳያ ልዩ ጥንቃቄ እንደሚያስፈልገው እየተነገረ ይገኛል፡፡     

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...