Sunday, June 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዓለምአሜሪካና ኢራን በቃላት ጦርነት

አሜሪካና ኢራን በቃላት ጦርነት

ቀን:

ኢራን አቋርጣ የነበረውን የኑክሌር ማበልፀግ ፕሮጀክት ለመቀጠል እንቅስቃሴ መጀመሯ በተለይም በአሜሪካ በኩል ውግዘትን አስከትሎባታል፡፡

ኢራን ከቀናት በፊት የኑክሌር ፕሮጀክቷን እንደምትቀጥል ማሳወቋን ተከትሎ አሜሪካ ዩኤስኤስ አብርሃም ሊንከን የተባለውንና ቦምብ ጣይ፣ የጦር አውሮፕላንና ቁሳቁስ የሚሸከመውን ግዙፍ መርከብ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ባለፈው ሳምንት መላኳ ደግሞ የቀጣናውን ሰላም ይበልጥ ሥጋት ውስጥ ከቶታል፡፡

አሜሪካ ዩኤስኤስ አብርሃም ሊንከን የተባለውን ግዙፍ የጦር መርከብ ወደመካከለኛው ምሥራቅ ከመላኳ ባለፈም፣ ዲፕሎማት ያልሆኑ ዜጎቿ ከኢራቅ እንዲወጡ ማዘዟ ጉዳዩን አክርሮታል፡፡

የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ከኢራን ይመነጫል የተባለውን ግን በግልጽ ያልተቀመጠውን ሥጋት ለመመከት በሚል ወደመካከለኛው ምሥራቅ የጦር መሣሪያ ከመላክ  ባለፈ፣ ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ትራምፕ ‹‹ኢራን ጦርነት ከፈለገች ያበቃላታል›› ብለው በትዊተር ገጻቸው ማስቀመጣቸው ኢራንና አሜሪካን የቃላት ጦርነት ውስጥ እንደተከተተና ውጥረቱን እንዳባባሰ አልጀዚራ ዘግቧል፡፡

በኢራን የሚደገፉ የታጠቁ ቡድኖች በኢራቅ ይገኛሉ፣ ጥቃት ሊያደርሱ ይችላሉ በሚል ሥጋቷን ከገለጸች በኋላ፣ በኢራቅ ዋና ከተማ ባግዳድ ግሪን ዞን በሚባለውና በርካታ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችና የአሜሪካ ሚሽንን ጨምሮ በርካታ ኤምባሲዎች በሚገኙበት አካባቢ ሮኬት መተኮሱም ተሰምቷል፡፡

ለድርጊቱ ኃላፊነት የወሰደ አካል ባይኖርም፣ የኢራንና የአሜሪካ ፍጥጫ በጦርነትና በአይኤስ ስትታመስ ዓመታት ላሳለፈችው ኢራቅ ሌላ ጫና ፈጥሯል፡፡

የኢራቅ መሪዎችም አሜሪካና ኢራን ኢራቅን የጦር አውድማ ሊያደርጓት ይችላሉ ሲሉ ቅድመ ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል፡፡

አሜሪካና ኢራን በቃላት ጦርነት

 

በኢራቅ የሺሃ ሙስሊም መሪ አልሳድር፣ ጦርነት የሚያቀጣጥሉ ነገሮችን እንደሚያወግዙና በአሜሪካና በኢራን መካከል የተጀመረው እሰጥ አገባ ኢራቅን የጦር አውድማ እንዳያደርግ ‹‹ሰላም እንፈልጋለን፣ ኢራቅን የጦር አውድማ የሚያደርግ ሁሉ የኢራቅ ጠላት ነው፤›› ብለዋል፡፡

ኢራቅ በአሜሪካና በኢራን መካከል የተጀመረው የቃላት ውርወራ ዳፋው ለእኔ ነው ብትልም፣ ኢራን የዩራኒየም ክምችቷን ከማሳደግ፣ አሜሪካም በኢራን ላይ ከመዛት አልተቆጠቡም፡፡

ፕሬዚዳንት ትራምፕ ‹‹የኢራን መጨረሻ›› ይሆናል ብለው በትዊተራቸው ባሳወቁ ማግሥት፣ ኢራን የዩራኒየም ክምችቷን በአራት እጥፍ እንደምታሳድግ ገልጻለች፡፡

እንደ አልጄዚራ ዘገባ፣ የትራምፕን ማስጠንቀቂያ ተከትሎ የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መሐመድ ጃቫድ ዛሪፍ ኢራን ዝቅተኛ የዩራኒየም መጠን ያለውን ኑክሌር ክምችቷን በአራት እጥፍ ታሳድጋለች ብለዋል፡፡

‹‹በኢራን ኢኮኖሚ ላይ የሚፈጠር ሽብርተኝነትና ኢራናውያንን ለማጥፋት በሚሰነዘር ዛቻ ኢራን አያበቃላትም፤›› ሲሉ በትዊታቸው ያሰፈሩት ሚስተር ዛሪፍ፣ ‹‹ኢራናውያንን አታስፈራሩ፣ ለማክበር ሞክሩ፣ ይህ ይሠራል፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡

አሜሪካ በመካከለኛው ምሥራቅ ያላትን ፍላጎት ኢራን የማታከብር ከሆነ፣ ትልቅ ጦር ይጠብቃታል የሚሉት ትራምፕ፣ ኢራን ለአሜሪካ አልበገሬ መሆኗንም አልሸሸጉም፡፡ ‹‹ኢራን ዝግጁ ስትሆን›› ለመነጋገር ፈቃደኛ መሆናቸውንም አክለዋል፡፡

ትራምፕ ይኼንን ካሉ ከሰዓታት በኋላ ምላሽ የሰጡት የኢራን ፕሬዚዳንት ሀሰን ሩሃኒ፣ በመነጋገርና በዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንደሚያምኑ፣ ሆኖም አሁን ባለው ሁኔታ ይህ ሊሆን እንደማይችል ገልጸዋል፡፡

‹‹የአሁኑ ሁኔታ ለውይይት አይመችም፡፡ የእኛ ምርጫ ራስን መከላከል ብቻ ነው፤›› ማለታቸውን የኢራን ዜና ኤጀንሲ አስፍሯል፡፡

አሜሪካና ኢራን በቃላት ጦርነት

 

የኢራን ዩራኒየም ማበልፀግ

የኢራን ፋርስ እና ታስኒም ዜና ኤጀንሲዎች ኢራን የዩራኒየም ክምችቷን በአራት እጥፍ እንደምታሳድግ የኢራንን ኑክሌር ኤጀንሲ ቃል አቀባይ ከማልቫንዲን ጠቅሰው ዘግበዋል፡፡

ሚስተር ከማልቫንዲ እንደሚሉት፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አቶሚክ ተቆጣጣሪ እንዲሁም ዓለም አቀፉ አቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ ኢራን ስለጀመረችው እንቅስቃሴ እንዲያውቁ ተደርጓል፡፡

በኢራንና አሜሪካን ጨምሮ በሌሎች አገሮች መካከል ተደርሶ ከነበረው ስምምነት አሜሪካ ራሷን ማግለሏና ለኢራን ተሰጥቶ የነበረውን የገደብ እፎይታ መሰረዙ ኢራን የኑክሌር ማበልፀግ ፕሮጀክቷን እንድትቀጥል አንዱ ምክንያት ነው፡፡

በስምምነቱ መሠረት የኢራን ዝቅተኛ የዩራኒየም ማበልፀግ ክምችት ከ300 ኪሎ ግራም እንዳይበልጥ የሚያደርግ የነበረ ቢሆንም፣ በቅርቡ ከ300 ኪሎ ግራም በላይ የዩራኒየም ክምችት ለማኖር እንደሚያመርቱ ሚስተርከማልቫንዲ አስታውቀዋል፡፡

ኢራን ኃይል ለማመንጨት 3.67 በመቶ ዩራኒየም ማበልፀግ የተፈቀደላት ቢሆንም፣ እ.ኤ.አ. በ2015 የተደረሰውን ስምምነት ቀስ በቀስ እያፈረሰች እንደምትመጣ አስታውቃለች፡፡ ይህ እንዳይሆን ግን የስምምነቱ አጋር የሆኑት እንግሊዝ፣ ቻይና፣ ፈረንሣይ፣ ጀርመንና ሩሲያ አሜሪካ የጣለችውን እገዳ እንድታነሳ ማድረግ ይኖርባቸዋል ተብሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አወዛጋቢው የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ጉዳይ

በኢትዮጵያ የሕገ መንግሥት ማሻሻል ጉዳይ ከፍተኛ የፖለቲካ ውዝግብ የሚቀሰቀስበት...

 መፍትሔ  ያላዘለው  የጎዳና  መደብሮችን  ማፍረስ

በአበበ ፍቅር ያለፉት ስድስት ዓመታት በርካቶች በግጭቶችና በመፈናቀሎች በከፍተኛ ሁኔታ...

የተናደው ከቀደምቱ አንዱ የነበረው የአዲስ አበባ ታሪካዊ ሕንፃ

ዳግማዊ አፄ ምኒልክ በ19ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ መናገሻ ከተማቸውን...

የአከርካሪ አጥንት ሕክምናን ከፍ ያደረገው ‘ካይሮፕራክቲክ’

በአፍሪካ ከጀርባ ሕመም ጋር በተያያዘ በርካታ ሰዎች ለከፍተኛ የአካል...