Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየሕይወት ግርዶሽ

የሕይወት ግርዶሽ

ቀን:

በኢትዮጵያ ከ72 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ የሚኖረው በተጎሳቆሉ አካባቢዎች  ነው፡፡ በእነዚህ አካባቢዎች የውኃ መጠንና የኤሌክትሪክ አቅርቦት እየቀነሰ፣ የውኃ ምንጭ የሆኑት ረግረጋማ ቦታዎች እየነጠፉና ወራሪ አረሞች እየበዙ ነው፡፡ ይህም ከኢትዮጵያ ሕዝብ ከግማሽ በላይ የሚሆነው የተሻሻለ ሕይወት እንዳይኖር አድርጓል፡፡

የደን፣ የአካባቢና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን የደረቅና አደገኛ ውጋጆች ዳይሬክተር አቶ ግርማ ገመቹ፣ ‹‹የሥልጡን ማኅበረሰብ ከተማ ንጹሕ ነው›› በሚል መሪ ቃል ባለፈው ሳምንት በተካሄደው አገር አቀፍ የከተማ አካባቢ ንጽሕና ኮንፈረንስ ላይ እንደገለጹት፣ በርካታ ሕዝብ በሚኖርባቸው ቦታዎች እስከ 1.8 ሚሊዮን ሔክታር መሬት በመጤ አረም ተሸፍኗል፡፡

ከ1996 ዓ.ም. እስከ 2006 ዓ.ም. ድረስ ከነበሩት ረግረጋማ ሥፍራዎች መካከል 70 በመቶ ያህሉ ነጥፈዋል፡፡ ከ92,000 ሔክታር በላይ የሆነውን መሬት የሸፈነው ደን እንደተጨፈጨፈና መሬቱ እንደተራቆተም አቶ ግርማ ተናግረዋል፡፡

በተፈጥሮ የራሷን ቆሻሻ ራሷ የማከም ችሎታ የነበራት ምድር ቆሻሻን በራሷ የማከም አቅሟ እየቀነሰ ሲሆን፣ ለዚህም እንደ ምክንያት የሚነሳው የኦዞን ንጣፍ መሳሳት፣ የአሲዳማ ዝናብ፣ የፕላስቲክና የኑክሌር ዝቃጮች በየአካባቢው መብዛት ነው፡፡

ከተሞች ሰፊ የመሠረተ ልማት አቅርቦት እንደሚያስፈልጋቸው ከእነዚህም አቅርቦት መካከል አንዱና ዋነኛው የደረቅ ቆሻሻ አያያዝ አገልግሎት እንደሆነም አመልክተዋል፡፡ የደረቅ ቆሻሻ መጠን መብዛት፣ የሕዝብ ቁጥርና የኢኮኖሚ ዕድገት ቀጥታ ግንኙነትና ተያያዥነት እንዳላቸው፣ በዚህም የተነሳ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው አገሮች የሚያመነጩት የቆሻሻ መጠን ዝቅተኛ ሲሆን፣ ከፍተኛ ገቢ ያላቸው አገሮች ደግሞ የሚያመነጩት ቆሻሻ ከፍተኛ ነው፡፡

‹‹ቆሻሻ በአግባቡ ተይዞ ጥቅም ላይ ካልዋለ የሰውን ልጅ ጤና ይጎዳል፡፡ የከርሰ ምድርና የገጸ ምድር ውኃን ይበክላል፡፡ በየቤቱ ያለው ቆሻሻ ተለያይነት ከመጨመሩም በላይ አደገኛነቱም ከፍ እያለ መጥቷል፡፡ ከዚህ አኳያ በቀጣይ ከእያንዳንዱ ቤት የሚወጣው ተለያይነት ያለው ቆሻሻ ከፍተኛ የአፈር ብክለትን ያስከትላል፤›› ብለዋል፡፡

በየዓመቱ እስከ 2.9 ሚሊዮን ቶን ደረቅ ቆሻሻ እንደሚመነጭ፣ ከእነዚህም መካከል ከ50 በመቶ ያነሰው ቆሻሻ በአግባቡ የሚወገድ ሲሆን ከ50 በመቶ በላይ የሆነው ግን በወንዝና በወንዝ ዳርቻዎች እንዲሁም ክፍት በሆኑ ቦታዎች ላይ እንደሚጣሉ ተናግረዋል፡፡

ደረቅ ቆሻሻ መመንጨት በየዓመቱ 24 በመቶ እንደሚያድግ፣ ቆሻሻውን ለመሰብሰብ የሚያስችለው ሀብትና የሰው ኃይል ግን በየዓመቱ ከሚያድገው የቆሻሻ መጠን ጋር እንደማይመጣጠን አቶ ግርማ አመልክተው፣ ከእነዚህ ችግሮች ለመላቀቅ የሚያስችሉ ሦስት መሠረታዊ ሁኔታዎች እንደተመቻቹ ተናግረዋል፡፡

ያልተማከለ አስተዳደር መኖሩ፣ የከተማ አስተዳደሮች የቆሻሻ አያያዛቸውን በራሳቸው የማቀድና የመወሰን ኃላፊነት መስጠቱ፣ በከተሞች የደረቅ ቆሻሻ አያያዝና ቁጥጥር ተግባራትን የሚያከናውኑ ተቋማት እየተጠናከሩ መምጣትና ቆሻሻ አይጠቅምም የሚለው አስተሳሰብ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተቀየረ መምጣት ችግሩን እያቃለሉ እንደሚመጡ ገልጸዋል፡፡

እንደ የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ተወካይ አቶ ባህሩ ወልደማርያም አገላለጽ፣ የወንዞችን ውኃ አክሞ ጥቅም ላይ ለማዋል አዳጋች እየሆነ መጥቷል፡፡ ሚኒስቴሩም የችግሩን አሳሳቢነት በመገንዘብ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የአካባቢ ንጽሕና መሠረተ ልማት ጥናትና ግንባታ በማካተት ለተግባራዊነቱ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡ መንግሥትም የችግሩን አሳሳቢነት ከግንዛቤ በማስገባት በዚህ ዓመት የውኃ ልማት ኮሚሽን አቋቁሟል ብለዋል፡፡

በአካባቢ ንጽሕና ዘርፍ ያለውን መጠነ ሰፊ ችግር ለመቅረፍ እንዲቻልም መንግሥት ከዓለም ባንክ በብድር ባገኘው 445 ሚሊዮን ዶላር አማካይነት አዲስ አበባን ጭምር በ23 ከተሞች የከተማ አቀፍ ሳኒቴሽን ፕሮግራም ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ተግባራዊ በመደረግ ላይ እንደሚገኝ ተወካዩ አመልክተዋል፡፡

የፍሳሽ ቆሻሻ እጅግ የተወሳሰበና ለማስወገድም ከፍተኛ በጀትና የቴክኖሎጂ አማራጮችን መጠቀም የሚጠይቅ በመሆኑ፣ የሁሉም ባለድርሻ አካላት ዕገዛና ትብብር በእጅጉ ወሳኝ መሆኑን ተወካዩ ጠቅሰዋል፡፡

በተለይም ከሆስፒታሎች አካባቢ ወይም ከጤና ተቋማት፣ ከኢንዱስትሪዎች ወዘተ የሚወገደው የፍሳሽ ቆሻሻ በተለመደው የፍሳሽ የማጣራት ሒደት አጣርቶ ወደ ወንዝ ለመልቀቅና መልሶ ለመጠቀም የተለያዩ ውስብስብ ሒደቶችን መከተል ይጠይቃል፡፡

የደን፣ አካባቢና የአየር ንብረት ለውጥ ምክትል ኮሚሽነር ወ/ሮ ፍሬነሽ መኩሪያ በኢትዮጵያ እየተመዘገበ ያለው የኢኮኖሚ ዕድገት፣ ፈጣን የከተሞች መስፋፋት፣ የሕዝብ ቁጥር መጨመርና የኑሮ ዘይቤ ለውጥ ማምጣት ከተሞች የሚያመነጩትን ቆሻሻ በመጠንና በዓይነት ይህንን ሊሸከም የሚችል የቆሻሻ አያያዝ ሥርዓትና መሠረተ ልማት በየከተሞቹ እንደሌለ ተናግረዋል፡፡

የጤና ሚኒስትር ዴኤታና የሃይጂን፣ የአካባቢና ጤና ስትሪንግ ኮሚቴ ሰብሳቢ ሊያ ታደሰ (ዶ/ር) የደረቅና የፍሳሽ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ ሥርዓት ላይ ቆሻሻን ከመሰብሰብ ጀምሮ ማጓጓዝ፣ ማስወገድ እንዲሁም መልሶ መጠቀም ላይ በርካታ ችግሮች እንዳሉ ጠቁመው ችግሮቹን ለመፍታትና ክፍተቶችን ለማስተካከል የሚያስችል የተቀናጀ የከተማ ሳኒቴሽንና ሃይጂን ስትራቴጂ በአገር አቀፍ ደረጃ መዘጋጀቱን አስረድተዋል፡፡

ስትራቴጂው ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ወደ አንድ ያመጣ እንዲሁም የተለያየ ዕቅድ፣ ፋይናንስና የቴክኖሎጂ ስልቶችን ይዞ ወደ ሥራ የገባ ሲሆን፣ ሰባት የሚጠጉ ሴክተር መሥሪያ ቤቶችም የሃይጂን፣ አካባቢና ጤና ስትሪንግ ኮሚቴ አቋቁመውና የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመው አስፈላጊውን እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ናቸው፡፡

በመጋቢት 2009 ዓ.ም. የወጣው ስትራቴጂ ሰነድ ወደ አሥር የሚጠጉ ዓላማዎች አሉት፡፡ ከዓላማዎቹም መካከል ዋና ዋናዎቹ በአሁኑ ወቅት ስድስት በመቶ የሆነውን በሜዳ ላይ የመፀዳዳትን ልምድ በማስወገድ በ2020 ዓ.ም. ሙሉ ለሙሉ በሜዳ ላይ ከመፀዳዳት የፀዱ ከተሞች እንዲኖሩ ማስቻል በየትኛውም ከተማ (አነስተኛ ከተሞችን ጨምሮ) የሚኖሩ አባወራዎች 100 ፐርሰንት የተሻሻለ የመፀዳጃ ቤት አገልግሎት ተጠቃሚ መሆናቸውን ማረጋገጥ፣ በመካከለኛና ትልልቅ ከተሞች በሚፈጠረው ደረቅ ቆሻሻ ውስጥ 50 በመቶ ያህሉን እንዲቀንሱ ማድረግና መልሶ መጠቀም ይገኙባቸዋል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...