Sunday, June 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ኪንና ባህልየቅዱስ ያሬድ ማስታወሻ ከድርሳናት ወደ ሐውልት

የቅዱስ ያሬድ ማስታወሻ ከድርሳናት ወደ ሐውልት

ቀን:

‹‹የመንፈስ ቅዱስን ምግብን የጠገበ፣ ከመጻሕፍት ሁሉ የድርሰትን ትርጓሜዎች ሁሉ ያሰባሰበ፣ ሃሌ ሉያ በሚል ምስጋና የኢትዮጵያ አገርን በጥዑም ማሕሌትና በምርምር ምስጋና ያስጌጠ፣ የመለኮት ቃልን በላይዋ ላይ እንደ ንጹሕ የወርቅ ሻሻቴ ያፈሰሰ፣ ለካህኑ ያሬድ ሰላምታ ይገባል፡፡››

ይህ ኃይለ ቃል በአሥራ አምስተኛው ክፍለ ዘመን የኖረው ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ በስድስተኛው ክፍለ ዘመን የኖረውን ታላቁ ሊቅ ቅዱስ ያሬድ ያወደሰበት፣ የገለጸበት ነው፡፡

ይህም የተገኘው መጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ከተረጐሙት ‹‹ተአምኆ ቅዱሳን›› መጽሐፍ ውስጥ ነው፡፡ በዜማ፣ በቅኔ፣ ትምህርተ መለኮት ሊቅነቱ የሚወሳው ቅዱስ ያሬድ በየዓመቱ ግንቦት በመጣ ቁጥር በተለየ አገባብ የሚዘክረው አክሱም ዩኒቨርሲቲ ነው፡፡ ሊቁ ቅዱስ ያሬድ የተሰወረበትን/ያረፈበትን ግንቦት 11 ቀን ምክንያት በማድረግ ዩኒቨርሲቲው እንደ ወትሮው ሁሉ ዘንድሮ የሁለት ቀን ጉባዔን አካሂዶ ነበር፡፡

- Advertisement -

1,500 ዓመታትን ያስቆጠሩትን የቅዱስ ያሬድ ሥራዎች ለዓለም ለማስተዋወቅ፣ በተለይ በሳይንሳዊ መንገድ እንዲጠኑና መረጃዎቹ በሰነድ እንዲደራጁ ለማድረግ በእንቅስቃሴ ላይ መሆኑን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ፀሐዬ አስመላሽ (ዶ/ር) በጉባዔው መክፈቻ ዕለት ተናግረዋል፡፡ በጉባዔው በተለያዩ ምሁራን ከቀረቡት ጥናቶች መካከል የአቶ ሙሉወርቅ ኪዳነ ማርየም ‹‹ቅዱስ ያሬድና ፍልስፍና››፣ የታሪክ ምሁሩ አድኃና ኃይሌ (ዶ/ር) ‹‹የቅዱስ ያሬድና የግዕዝ ቋንቋ አበርክቶ›› ይገኙባቸዋል፡፡

እንደ አቶ ሙሉ ወርቅ አገላለጽ፣ ቅዱስ ያሬድ ግዕዝን የሥነ ጽሑፍ አገራዊ ቋንቋ ያደረገ በርካታ ድርሰቶችን የደረሰ፣ ዜማን የቀመረ፣ የፍልስፍና ሰው ነው፡፡

‹‹ቅዱስ ያሬድ የሰው የትውልድ ሒደትና ፍልስፍና ያሳየ ሊቅ ነው፤›› ያሉት አቶ ሙሉ ወርቅ፣ በኢትዮጵያውያን መካከል መንፈሳዊ አንድነትን በዜማው የቀዳጀ ዳር እስከ ዳር የዘለቀ ነው ሲሉም አመስጥረዋል፡፡

በዩኔስኮ የዓለም ቅርስ ሆኖ የተመዘገበው የአክሱም መካነ ቅርስ፣ በተጨማሪነት ከማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶች መካከል በቀዳሚነት የሚጠቀሰው የቅዱስ ያሬድ ሥራዎች የሚገለጹበት፣ ራሱ የቀመራቸው ማሕሌቶች ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ከመስከረም እስከ መስከረም የሚገኙት ክብረ በዓላት መገለጫቸው የቅዱስ ያሬድ ሥራዎች መሆናቸውም ይወሳል፡፡

“መጻሕፍቶቻችን ስለ ቅዱስ ያሬድ ምን ይላሉ?” በሚል ርዕስ ከዓመታት በፊት በማኅበራዊ ገጻቸው የጻፉት ቀሲስ አምሳሉ ተፈራ (ዶ/ር)  እንዳመለከቱት፣ እስካሁን በተደረገው ጥናት የኢትዮጵያ ጽሑፎች እስከ ያሬድ መነሳት ድረስ ትርጉሞች (በተለይ ከግሪክ ቋንቋ) ነበሩ። ብሔራዊ ድርሰትን (ሀገር በቀል) በኢትዮጵያ የጀመረ ያሬድ ነው።

ዱስ ያሬድ የምስጋና እና የአምልኮ መግለጫ የሆኑ የዜማ መጻሕፍትን በግዕዝ ቋንቋ ጽፏል። እነዚህም በስፋት የሚታወቁት አምስቱ የዜማ መጻሕፍቱና በታሪክና በትውፊት የተቀበልናቸው ሌሎች መጻሕፍት ናቸው። እነርሱም፥ ድጓ፣ ጾመ ድጓ፣ ምዕራፍ፣ ዝማሬ፣ መዋሥዕት ናቸው፡፡

በቀሲስ አምሳሉ ማብራርያ፣ ከድርሰቶቹ ውስጥ የመጀመርያው ትልቁ የዜማ መጽሐፍ ድጓ ሲሆን በሦስት ዋና ዋና ክፍሎች የተከፈለና በቤተ ክርስቲያን  ከዓመት እስከ ዓመት የሚደርስ ምስጋና ነው። ሁለተኛው ጾመ ድጓ በዐቢይ ጾም የሚደርስ ምስጋና ሲሆን ክፍሉ በዓቢይ ጾም ውስጥ ባሉት ሰንበታት ልክ ነው።

 ምዕራፍ ከመዝሙረ ዳዊት የተውጣጡት ምስጋናዎችን በመስመር በመስመር እየከፈለ የሚደርስ የስብሐተ እግዚአብሔር መጽሐፍ ሲሆን፤ ዝማሬ ደግሞ ማሕሌት ሲቆም የሚደርስ ሆኖ በጊዜ ቅዳሴ ከድርገት በኋላ የሚቀርብ ምስጋና ነው። አምስተኛው መዋሥዕት ካህናት በተዋሥኦ (በመቀባበል) የሚያዜሙት ሲሆን በተለይ በጸሎተ ፍትሐት ጊዜ እና በቀዳም ሥዑር ዕለት የሚደርስ ምስጋና መሆኑን የነገረ ድርሳን መምህሩ አምሳሉ ተፈራ (ዶ/ር) ይገልጻሉ፡፡ ቅዱስ ያሬድ አንቀጸ ብርሃን የተሰኘውን የቅድስት ማርያም ምስጋና ያደረሰው  በአክሱም ጽዮን ክርስቲያን ውስጥ ከታቦተ ጽዮን ፊት ቆሞ ነው፡፡

እንደ ቀሲስ አምሳሉ (ዶ/ር) አገላለጽ፣ ቅዱስ ያሬድ ከስድስቱ ሥራዎቹ በተጨማሪ በትውፊት እንደሚታወቀው  ከዘጠኙ ቅዱሳን መካከል የደረሰላቸው የገድለ አረጋዊ፣ ገድለ ጽሕማ እና ገድለ ይምአታ ናቸው።

ቅዱስ ያሬድ ከድርሰቶቹና ከዜማዎቹ ባሻገር ያሉት ቋሚ መታሰቢያዎች በስሙ የተተከሉ አብያተ ከርስቲያናት በአክሱም፣ በአዲስ አበባና በሌሎችም አካባቢዎች የሚገኙ ናቸው፡፡

በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሥር የሚገኘው የሙዚቃ ትምህርት ቤት በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን በስሙ የተሰየመ ነው፡፡ በዚያው ዘመን በአዲስ አበባ ከተማ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታልና በሊቢያ ኤምባሲ መካከል ያለው መንገድም በቅዱስ ያሬድ ስም ተሰይሟል፡፡ ዘንድሮ ወደ ዩኒቨርሲቲ ያደገው ቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ በሥሩ ካቋቋማቸው ኮሌጆች አንዱ የቅዱስ ያሬድ የዜማና የሥነ ጥበባት ኮሌጅ ነው፡፡ በአክሱም የሚገኝ ከፍተኛ መንፈሳዊ ትምህርት ቤትም በስሙ ይጠራል፡፡

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ለታላቁ ኢትዮጵያዊ ሊቅ ሐውልት ለምን አይቆምለትም የሚል ድምፅ ሲስተጋባ ቆይቷል፡፡

የአዲስ አበባው ቅዱስ ያሬድ ቤተ ክርስቲያን ከአፀዱ ባሻገር በሚገኘው አደባባይ ሐውልት ለማቆም ፕሮጀክት ነድፎ እየተንቀሳቀሰ መሆኑ ተሰምቷል፡፡ እንዲሁም የትውልድ ቦታው በሆነችው አክሱምም በመሀል ከተማው (ፒያሳ) ሐውልቱን ለማቆም ባለፈው ሳምንት የመሠረት ድንጋይ ተጥሏል፡፡ የመታሰቢያ ሐውልቱን አንድ ባለሀብት በመደቡት ሁለት ሚሊዮን ብር በጀት የሚሠራ መሆኑ በሥነ ሥርዓቱ ወቅት ተገልጿል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች...

ከባለአንድ ዋልታ ወደ ባለብዙ ዋልታ የዓለም ሥርዓት የመሸጋገራችን እውነታ

በአብዱ ሻሎ አንገት ማስገቢያ እ.ኤ.አ. በፌብሩዋሪ 2022 የሩሲያ መንግሥት በዩክሬን ‹‹ልዩ...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የውጭ ግንኙነት የሺሕ ዘመናት ታሪኳና እሴቶቿን የሚመጥን መሆን ይኖርበታል

(ክፍል አንድ) በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን) እንደ መንደርደሪያ ለዛሬው የግል ትዝብቴንና ታሪክን ላዛነቀው...

ከአገር ግንባታ ጋር የተያያዙ ወሳኝ የቅርብ ታሪካችን አንጓዎች

በታደሰ ሻንቆ በአያሌው የተመረጡና ልጥ የሌላቸው ነጥቦች የተደራጁበት ይህ ታሪክ...