Monday, September 25, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹አሁን ያለው ሥልጣኔ ለመጥፋት ቅርብ ነው›› ታፈረ ህሉፍ (ኢንጂነር)፣ ስትራክቸራል መሐንዲስ

ታፈረ ህሉፍ (ኢንጂነር) ስትራክቸራል መሐንዲስ ናቸው፡፡ የድልድይ ግንባታ ላይ ትኩረት ያደረገ የማማከር ሥራ ይሠራሉ፡፡ በኳንተም ፊዚክስና ንድፈ ሐሳቦችን በመመርመር ሥራ ለዓመታት ሲሠሩ ቆይተዋል፡፡ በሪሌቲቪቲ (ሥነ ንፃሬ) ዙሪያ ሁለቱ ንድፈ ሐሳቦች ከማኅበረሰቡ ጋር ያላቸው ቁርኝት እንዲሁም የምርምር ሒደቶች የሚያሳየውን ጽሑፍ ለማሳተም በዝግጅት ላይ ናቸው፡፡ ሳይንሳዊ አስተሳሰብ በአገር ውስጥ ለመፍጠር እሠራለሁ ይላሉ፡፡ የኳንተም ፌዚክስና ሪሌቲቪቲ ጽንሰ ሐሳቦችና ተግባራዊ አንድምታ እንዲሁም ሳይንሱ ከማኅበረሰብ ዕውቀት ጋር እንዴት ይገናኛል የሚለውን በተመለከተ ሻሂዳ ሁሴን አነጋግራቸዋለች፡፡

ሪፖርተር፡- ኳንተም ፊዚክስ ለበርካቶች ረቂቅ ነው፡፡ በኳንተም ደረጃ ጠለቅ ያለ ትምህርትም ከብዙዎች የራቀ ይመስላል፡፡ እርስዎ ከኳንተም ፊዚክስ ጋር እንዴት ተዋወቁ?    

ኢንጂነር ታፈረ፡- እንዳልሽው ኳንተም ፊዚክስ ትንሽ ረቀቅ ይላል፡፡ በኳንተም ፊዚክስ የሚታዩ ከእኛ የቀን ከቀን እንቅስቃሴ ጋር ሊገናኙ የማይችሉ ነገሮች ናቸው፡፡ እኔ ከጽንሰ ሐሳቡ ጋር የተዋወኩት ድሮ ተማሪ ሳለሁ ነው፡፡ የአልበርት አንስታይን ሥራዎች ከአሥረኛ ክፍል ጀምሮ ይመስጡኝ ነበር፡፡ ከአንስታይን የሪሌቲቪቲ ቀመሮች ተነስቼ ዝርዝር ነገሮች እመለከት ነበር፡፡ ተማሪ ሳለሁ ጊዜ ጀምሮ ከዝርዝር ነገሮች በመነሳት ቁጥሮችን ወደ ማምጣት እገባ ነበር፡፡   

ሪፖርተር፡- ቀለል ባለ ቋንቋ ስለኳንተም ፊዚክስ ያብራሩልን?

ኢንጂነር ታፈረ፡- በአንድ አተም ውስጥ የሆነ ዓለም አለ ብሎ ማሰብ ነው፡፡ በአተም ውስጥ ወደ 99.9 በመቶ የሚሆነው ቫኪዩም (ኦና) ነው ያለው፡፡ በዚህ ቫኪውም ዓለም ውስጥ ኤሌክትሮኖች አሉ፡፡ ኳንተም ፊዚክስ የረቂቃኑ ዓለም ክንውን ነው፡፡ ኳንታማዊ ወይም ረቂቅ የሆኑ አካላት በሞገድና ቅንጣት መልክ በሁለትዮሽ አውታር የሚያደርጉት መስተጋብር ነው፡፡ የኳንተም ዓለምና እኛ ያለንበት ሁኔታ ፍፁም የተለያየ ነው፡፡ ለምሳሌ እኔና አንቺ አሁን እዚህ ነው ያለነው፡፡ በዚህ ቅፅበት ውስጥ ሌላ ቦታ የለንም ማለት ነው፡፡ በኳንተም ውስጥ ያለው ዓለም ግን አንድ ቅንጣት በማንኛውም ቦታ በማንኛውም ሰዓት መኖር ይችላል፡፡ ይህን መረዳት ለእኛ ይከብዳል፤ ምክንያቱም ይህ በዕለት ከዕለት እንቅስቃሴችን ያልተለመደ ነው፡፡ ተመራማሪዎችም ኳንተም ፊዚክስን በተወሰነ ደረጃ ለመረዳት እዚህ ዓለም ላይ የምናውቀውን የሐሳብ ቅርፅ ማፍረስ አለብን ይላሉ፡፡

ሪፖርተር፡- በኳንተም ፊዚክስ ጽንሰ ሐሳብ ዓለም የትየለሌ (Infinite) ነች፣ ያለንበትን ዓለም የሚመሳሰሉ ቁጥር ሥፍር የሌላቸው ነገር ግን አንደኛው ከአንዱ ሊገናኙ የማይችሉ ዓለማት አሉ ይባላል፡፡ በአተም ውስጥ የረቀቁ አካላት አሉ ሲሉ ይህንን ሐሳብ በሌላ አገላለጽ እየደገሙት ነው ማለት ነው?

ኢንጂነር ታፈረ፡- ማንኛውም ነገር የተሠራው ከአተም ነው፡፡ አተም ውስጥ ደግሞ ንፁህ አተማዊ ቅንጣቶች አሉ፡፡ ቅንጣት የምንለው ኤሌክትሮን ፕሮቶን የመሳሰሉትን ነው፡፡ በቅንጣት ውስጥ ቁሳዊ ኢነርጂ ቅንጣቶች አሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ ቁሳዊ ያልሆኑ ቅንጣቶች አሉ፡፡ ልክ ፎቶን እንደምንላቸው የብርሃን ቅንጣት ያሉ ማለት ነው፡፡ የብዝኃ ዓለም (መልቲ ዩኒቨርስ) ጽንሰ ሐሳብ ከኳንተም ፊዚክስ ትንበያዎች አንዱ ነው፡፡ ይህ ትንበያ የኳንተም ፊዚክስ ብቻ ሳይሆን የጄኔራል ሪላቲቪቲም (ግዙፍ ንድፈ ሐሳብ) ነው፡፡ ይህን አካላዊ ዓለም ተመራማሪዎች በሁለት ትልልቅ ንድፈ ሐሳቦች ይከፍሉታል፡፡ የመጀመርያው ጄኔራል ሪሌቲቪቲ ነው፡፡ ሁለተኛው ኳንተም (የረቂቁ) ፊዚክስ ነው፡፡ ኳንተም ፊዚክስ የረቂቁ ዓለም ጥናት ሲሆን፣ ጄኔራል ሪሌቲቪቲ ደግሞ ግዙፉን ዓለም የሚያጠና የሳይንስ ዘርፍ ነው፡፡ ሁለቱ ንድፈ ሐሳቦች በሒሳባዊ ሥሌት በተወሰነ ክልል ላይ ተዋህደው ይገለጻሉ፡፡ ከዚህ ዓለምም እዚያ ውስጥ ካሉ ሒሳባዊ ትርጓሜዎች አንዱ ነው፡፡ ኳንተም ፊዚክስን የምንጠቀመው ግን በጄኔራል ሪሌቲቪቲ በኩል ነው፡፡ የመጪው ጊዜ ትልቁ ሥሌት ሊሆን የሚችለው ሁለቱን ንድፈ ሐሳብ እኩል መጠቀም ሲቻል ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ማንኛውንም ነገር ማድረግ ይቻላል፡፡ በብዝኃ ዓለም ጽንሰ ሐሳብ ውስጥ ያለ ትልቁ ጥያቄ በሁለት የተለያዩ ዓለም ላይ የሚገኙ አካላት እንዴት መገናኘት ይችላሉ የሚለው ነው፡፡ የእኛ ዓለም ግዙፍና የ3ዲ ፍጥረት ነው፡፡ እነዚያ ዓለሞች ግን ጨቅላና ረቂቅ፣ ከኤሌክትሮኖችም ያነሰ ነው መጠናቸው፡፡ እኛ የ3ዲ ፍጥረት ነን ስንል ከ3 ዳይሜንሽን ውጪ ማየት አንችልም ለማለት ነው፡፡ አንድ አራተኛ ዳይሜንሽን የሚያይ ሰው ቢኖር ጊዜን እንደ አካል ማየት ይችላል ማለት ነው፡፡      

ሪፖርተር፡- በትይዩ መስመሮች የተደረደሩ ናቸው በሚባሉ ዓለሞች መካከል ግንኙነት መፍጠር አልተቻለም፡፡ ይህንን ዕውን ማድረግ በጣም ከባድና በአንዴም ብዙ ነገሮችን ሊቀይር የሚችል ነው ይባላል፡፡ ይህንን ዕውን ለማድረግ ደግሞ እየተሠራ ነው ብለዋል ቢያብራሩልን፡፡

ኢንጂነር ታፈረ፡- ይኼ አሁን ላይ እጅግ አከራካሪ ጉዳይ ነው፡፡ ፈቃድ ካለ ወይም ቴክኖሎጂው ካለ የግንኙነት መረብ መዘርጋት ይቻላል፡፡

ሪፖርተር፡- ይህንንም በታይም ማሽን ማሳካት የሚቻል ነው ማለት ነው?

ኢንጂነር ታፈረ፡- አዎ ይቻላል፡፡ ስለታይም ማሽን በንድፈ ሐሳብ ደረጃ የተረጋገጠ ተግባራዊ መደረግ የሚችል ንድፈ ሐሳብ አለ፡፡ ስለታይም ማሽን ለማውራት ግን የጊዜን መሠረታዊ ባህሪያት መለየት በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ ጊዜ ብቻውን መኖር አይችልም፡፡ ከሌሎች ገጽታዎች ጋር አብሮ ነው የሚኖረው፡፡ የመጀመርያ ገጽታ ቦታ ነው፡፡ ህዋ ላይ የሚገኙ ማንኛቸውም የሚንቀሳቀሱ ነገሮች በሙሉ በዚህ ቦታና ጊዜ ነው የሚወለዱት፣ የሚፈርሱት ሁሉንም ነገር የሚሆኑት፡፡ እነዚህ ሁሉ ኩነቶች በቦታና ጊዜ ላይ ሲፈራረቁ በራሱ በቦታና ጊዜ ላይ ተፅዕኖ ያሳርፋሉ፡፡ ከዚህ በፊት የነበሩ ንድፈ ሐሳቦች በቦታና ጊዜ ተፅዕኖ ሊደርስበት አይችልም የሚሉ ነበሩ፡፡ ይህንን በጄኔራል ሪሌቲቪቲ ላስረዳሽ፡፡ ጄኔራል ሪሌቲቪቲ የተቀረፀው ይዘት ላይ አይደለም መዋቅራዊ ነው፡፡ በመዋቅሩ ላይ ሁለት ምሰሶዎች አሉ፡፡ መጀመርያው ታይም ስፔስ ሲሆን፣ ሁለተኛው ኃይል ነው፡፡ ናሳዎች ሥሌቱን ሲሠሩ ኢነርጂን በአንድ በኩል ያስቀምጣሉ፡፡ ታይምንም በአንድ በኩል ያደርጋሉ፡፡ የሁለቱ ስብጥር ግራቪቲ (የስበት ኃይል) ነው የሚፈጥረው፡፡ ኢነርጂ በጨመረ ቁጥር ስፔስ ታይም እየጠፋ (ኮላፕስ) እያደረገ ይሄዳል፡፡ ኢነርጂ እጅግ በጣም ጨምሮ የትየለሌ ሲደርስ ሲንጉላሪቲ ይመጣል፣ ቢግ ባግ የሚሉት ነው፡፡ ከቢግ ባንክ ትንሽ ከፍ ሲል ደግሞ ብላክ ሆል ይሆናል፡፡ ስፔስ ታይም ላይ ኢነርጂ በጨመረ ቁጥር ግራቪቲው እጅግ እየጨመረ እፍግታው በጣም ከፍ እያለ ነው የሚሄደው፡፡ በዚህም ጊዜ እየተለጠጠ በጣም እየዘገየ ነው የሚሄደው፡፡ እዚያ አካባቢ አንድ ደቂቃ አሳልፈሽ ወደ መሬት ስትመለሺ ሺሕ ዓመት አልፎ ይሆናል፡፡ ምክንያቱም ጊዜ በራሱ በሌላ ከፍተኛ ተፅዕኖ ውስጥ ነው ያለው፡፡ አሁን ታይም ማሽንን አቅልለን እንየው፡፡ መሬት እንግዲህ አየር ላይ ያለች ኳስ ነች፡፡ አንድ ባቡር መሬትን በሰከንድ ሰባት ጊዜ ቢዞር 420 ዓመት አካባቢ በአንድ ጊዜ ይዞራል ማለት ነው፡፡ ባቡሩ ውስጥ ያለው ሰው ባቡሩ ውስጥ ሰባት ደቂቃ ተጉዞ ቢወርድ 700 ዓመት ዘግይቶ ነው እዚህ የሚደርሰው፡፡ እሱ ሰባት ደቂቃ ብቻ እንዳሳለፈ ነው የሚያስበው፡፡ ጊዜ በተፅዕኖ ውስጥ በሚሆንበት ጊዜ በነገሮች ላይ ያለው ተፅዕኖ ይቀንሳል፡፡ ፍጥነቱ በሰከንድ ሰባት ጊዜ ያህል ሲጨምር በግዙፍ ኤሌክትሮ ማግኔቲክ ሞገድ የሚካሄድ ፍጥነት ነው፡፡ በሰከንድ ሰባት ጊዜ መዞር በጀመረባት አንዷ ደቂቃ ላይ ከ400 ዓመት በኋላ ነው እዚህ የሚደርሰው፡፡ ለእሱ ግን የመተንፈስ ያህል ነው፡፡ ምክንያቱም ውስጥ የነበረው ታይም ተጠቅልሎ አልፏል፡፡ ወደ ህዋ በተጓዝን ቁጥር ታይም ማሽን ጽንሰ ሐሳብ እየታየ ነው፡፡ ነገር ግን ማሽኑን ለመገንባት ግዙፍ ኃይል ያስፈልጋል፡፡ በዓለም ላይ ያለው ትልቁ ችግር ደግሞ የኢነርጂ እጥረት ነው፡፡ ኢነርጂ ለሳይንስ ዕድገት ቁልፍ ነው፡፡   

ሪፖርተር፡- ታይም ማሽን ለመገንባት የተለየ ኃይል ያስፈልጋል እያሉ ነው?

ኢንጂነር ታፈረ፡- መገኘት ያለበት ንፁህ ኃይል ነው፡፡ ልክ እንደ አሁኑ ከኑክሌርና የመሳሰሉ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ይኼ በራሱ ሌላ ስህተት ነው ሚፈጥረው፡፡ ለምሳሌ ወደ መሬት የሚመጣውን የፀሐይ ብርሃን ተጠቅሞ ቴክኖሎጂውን ዕውን ለማድረግ ያለንበት የሥልጣኔ ደረጃ አይፈቅድም፡፡ አራት የሥልጣኔ ደረጃዎች አሉ፡፡ ከአራተኛው የሥልጣኔ ደረጃ እንጀምር፡፡ በዚህ የሥልጣኔ ደረጃ ላይ ሲደርስ ከብዙ ጋላክሲዎች የሚመነጭን ኃይል በአንድ ጊዜ መጠቀም ይቻላል፡፡ ይህ ማንኛውንም ኃይል መጠቀም የሚያስችል ሊጠፋ የማይችል ሥልጣኔ ላይ የሚደረስበት ነው፡፡ ወደ ሌላው ዓለም ሁሉ መጓዝ ይቻላል፡፡ ዘለዓለማዊና ሊጠፋ የማይችል የሥልጣኔ ደረጃ ነው፡፡ በነገራችን ላይ አሁን ያለው ሥልጣኔ ለመጥፋት ቅርብ ነው፡፡ የሰው ሥልጣኔ አንዲት ፕላኔት ላይ ብቻ ነው ያለው፡፡ ይህቺ ፕላኔት ተወርዋሪ ኮከብ ወይም የሆነ ነገር ቢመታት ጠፋች ማለት ነው፡፡ ከ60 ሚሊዮን ዓመታት በፊት ምድር ተመትታ ብዙ እንደ ዳይኖሰር ያሉ ፍጥረቶች ጠፍተዋል፡፡ መሬት ወደ ግግር በረዶ የምትቀየርበት ወይም በከባድ ሙቀት የምትጠፋበት ዕድልም አለ፡፡ ሌሎች ሥልጣኔውን ሊያጠፉ የሚችሉ አጋጣሚዎችም አሉ፡፡ ይህኛው የአራተኛው የሥልጣኔ ደረጃ ተቃራኒ የሆነው የመጀመርያው ሥልጣኔ ነው፡፡ የመጀመርያው የሥልጣኔ ደረጃ ላይ ሰዎች እንደ ጥንታዊ ሰው ይሆናሉ፡፡  በሥልጣኔ ወደ ፊት በመገስገስ ፈንታ አሁን እንዳለው እንደ እኛ አገር በዘርና በሃይማኖት ተከፋፍሎ የመጣላትና ወደ ኋላ የመመለስ ነገር ይታያል፡፡ አንድ በቅርቡ የተሠራ ጥናት እንደሚያሳየው ከ100 ሺሕ ዓመታት በፊት የነበረው የሞራልና የአዕምሮ ንቃት ሁኔታ አሁን ካለው ጋር ብዙም አይለያይም፡፡ ይህም ማለት ለ100 ሺሕ ዓመታት በሙሉ በዚህ ሥልጣኔ ላይ ነው ያለነው፡፡ መሀል ላይ ከክርስቶስ ልደት በፊት 500 ዓመት እጅግ አስገራሚ ጅማሮ ነበር፡፡ ብዙ ምርምሮች ነበሩ በእኛም አገር ጥሩ ሥልጣኔ የነበረበት ወቅት ነበር፡፡

ሌላው ሦስተኛው የሥልጣኔ ደረጃ በሥርዓተ ፀሐይ ውስጥ የሚገኝን ኃይል ሙሉ ለሙሉ መጠቀም የሚያስችለው ነው፡፡ ይህ የበቃ ሥልጣኔ ስለሆነም ራሱን መከላከል ይችላል፡፡ በዚህ ጊዜ ዕውን ሊሆኑ የሚችሉ ቴክኖሎጂዎች አሉ፡፡ ሁለተኛው የሥልጣኔ ደረጃ ደግሞ ፕላኔቷ ላይ ያለውን ኃይል ሁሉ መጠቀም ነው፡፡ መሬት ከሐፀይ የምታገኘውን ኢነርጂ በተፈለገው ልክ መጠቀም ማለት ትልቅ ነገር ነው፡፡ አሁን ያለንበት የሥልጣኔ ደረጃ ኃይልን የመጠቀም ሳይሆን የማፍረስ ነገር የሚታይበት ነው፡፡ ይህንን ደረጃ ተመራማሪዎች ዜሮ የሥልጣኔ ደረጃ ነው ብለው ያስቡታል፡፡ ፕላኔቷን በሚጎዳ መልኩ የበሰበሰ ተክል ነዳጅ ብለን ከመሬት እያወጣን እንጠቀማለን፡፡ የመጨረሻው የሥልጣኔ ደረጃ ከአያሌ ጋላክሲዎች የሚገኙ ኢነርጂዎችን መጠቀም ነው፡፡ ወደ ሌላ ዓለም የሚያስገባን የጠፈር ዋሻ (ዋርም ሆል)ን መጠቀም የሚቻልበት ደረጃ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በቅርቡ በሚታተመው መጽሐፍዎ ሳይንሱን ከአገረ ሰብ ዕውቀት ጋር እንዴት እንደሚገናኝ ያሳየሁበት ነው ብለዋል፡፡ በሁለቱ መካከል ያለው ግንኙነት ምን ይመስላል?

ኢንጂነር ታፈረ፡- የብዝኃ ዓለም ንድፈ ሐሳብ በሳይንስ ቢረጋገጥም ዕውቀቱ ግን ቀድሞ ማኅበረሰብ ውስጥ ነበር፡፡ በተለይ በእኛ አገር ውስጥ በጣም ብዙ ነገሮች ይታወቃሉ፡፡ አንዳንዶቹ ሐሳቦች እንደ Form of Ideas ነበሩ፡፡ ከሁለት ዓመታት በፊት አንድ መሪ ጌታ አግኝቼ ነበር፡፡ ስለ ረቂቅነት ብዙ ይታወቃል፡፡ ከሙታን መንፈስ ጋር በተገናኘ ብዙ ይባላል፡፡ ከትይዩ ዩኒቨርስ ጋር በተገናኘም እንዲሁ ማኅበረሰቡ የሚያውቀው አለ፡፡ መሪ ጌታውን ባናገርኩበት ወቅት እኛ ከምናውቀው ዓለም ውጪ ሌላ ህቡዕ ህልውና አለ ብለውኛል፡፡ በእነዚህ ህቡዕ ዓለም ውስጥ ረቂቅ ህልውናዎች አሉ ይላሉ፡፡ እነዚህን ረቂቅ ህልውናዎች ሠራዊት እያሉ ይጠሯቸዋል፡፡ በተለምዶ የምናውቃቸው እንደ አንደርብ፣ ምሣብና መንድብ የሚባሉ የተለያዩ ረቂቅ ዓለማት አሉ፡፡ እነዚህ የተወሰኑ ሰዎች የሚያከናውኗቸው ናቸው፡፡ መሪጌታው የነገሩኝ ከረቂቅ ሠራዊቶች ጋር የመነጋገሪያ የማዘዣ ጥበብ እያሉም ነው፡፡ በጥንታዊ አባቶች ዘንድ የሚታወቅ ይዘወተር የነበረ እያሉ ነው ያጫወቱኝ፡፡ ባደጉት አገር በሳይንስ የተገኘው የሐሳብ ፎረም እኛ አገር የነበሩና የታወቁ ናቸው፡፡ ከህቡዕ ህልውናና ከረቂቁ ዓለም ጋር የሚነጋገሩ የጥበብ ባለቤት ነው የሚላቸው፡፡ እነዚህ የጥበብ ባለቤቶች ቃልና ቁስን በመጠቀም ከረቂቅ ህልውና ጋር ይገናኛሉ፡፡ ረቂቅ ህልውናን ለመጥራት በተደጋጋሚ ጊዜ የሚጠቀሙት ቃል አለ፡፡ እንደ መስታወት ያሉ ቁሶችን በመጠቀም ግንኙነት ያደርጋሉም፡፡ 

ሪፖርተር፡- በኳንተም ፊዚክስ ውስጥ እነዚህ ሁሉ ይካተታሉ ማለት ነው?

ኢንጂነር ታፈረ፡- ሦስቱንም ነገሮች ይይዛል፡፡ ረቂቅነትን፣ ትይዩ ዩኒቨርስ እንዲሁም ቴሌ ፖርቴሽንን ይይዛል፡፡ አንድ ቁስ በተመሳሳይ ሰዓት ብዙ ቦታዎች ላይ ይገኛል፡፡ እንዲሁም ደግሞ ሁለት ቅንጣቶች በአጋጣሚ ቢጋጩ ወይም በአጋጣሚ Sincronized ቢሆኑ፣ Coherence ውስጥ ከገቡ፣ በዩኒቨርስ ሌላኛው ጫፍ ላይ አንዷ ብትሄድ አንዷ ላይ የሆነው ነገር ሌላዋም ላይ ይሆናል፡፡ ይኼ የተረጋገጠ ሳይንስ ነው፡፡ ይኼ የቁርኝት ሞገድ ነው የሚሉት፡፡ በነጠላ ኤሌክትሮን ደረጃ ቁርኝት ወይም Coherence ከተፈጠረ ሙሉ አካሉ ወደ ሌላ ቦታ ሊሄድ ይችላል፡፡ ሳይንቲስቶች እኛ ሰዎች ከሆነ ቦታ ኮኸረንሲ ፈጥረን የመጣን ልንሆን እንችላለን ይላሉ፡፡ ከሆነ ቦታ የመጣን ከሆነ እኛ የሚያስጨንቀንና የሚያሳስበን ነገር የሆነ ቦታ ላይ ያለ የሆነ ሰውዬ የሚያሳስበውና የሚያስጨንቀው ጉዳይ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም የተገናኙ ስለሆኑ ነው፡፡ ይኼ በሳይንስ የተረጋገጠ ነው፡፡ አንድን ቁስ እዚህ አስቀምጠውት ገና ከመነሳቱ የሆነ ቦታ ላይ ተከስቷል፡፡ በዚህ መነሻ እየተሠሩ ካሉ ቴክኖሎጂዎች መካከል ኳንተም ኮምፒውተር አንዱ ነው፡፡ አሁን የምንጠቀምባቸው ኮምፒውተሮች በመቶ ዓመታት እንኳ የማይፈቱትን ሥሌት በ15 ደቂቃ ኳንተም ኮምፒውተር መፍታት ይችላል፡፡ ብዙ አገሮች ይህንን ኮምፒውተር አሻሽለው ለመሥራት ጥረት ያደርጋሉ፡፡ ነገር ግን በጣም ከባድ ስለሆነ ማሻሻል የሚችሉት የቅንጣት ያህል ነው፡፡ በየዓመቱ የሚመዘገበው መሻሻል በብርሃን ቅንጣት፣ በአተም ቅንጣት እያለ ነው የሚሄደው፡፡ የዚህ ምርምር መጨረሻ ምናልባት በሁለተኛው የሥልጣኔ ደረጃ ሰዎች በቅጽበት ውስጥ የትም መገኘት የሚችሉበት ይሆናል፡፡ ወይም አንድ ሰው ተኝቶ ሲነቃ ጨረቃ ላይ ሊነቃ ይችላል፡፡

ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ ውስጥ ማኅበረሰቡ ስለኳንተም ሳይንስ የሚያውቀው ነገር ባይኖርም ረቂቅ ህልውና እንዳለ በተወሰነ መንገድ ይገምታል ወይም ያምናል፡፡ ለምሳሌ ደብተራው ሰይጣኑን ካለበት ይጠራል ይባላል፡፡ በአንደርቢ የሚንጋጋው ድንጋይ፣ በደብተራው የሚጠራው ሰይጣን በቴሌፖርቴሽን ነው ወደዚህኛው ዓለም የሚመጣው እያሉን ነው?

ኢንጂነር ታፈረ፡- የድንጋይ አንደርቢን በተፈለገው ቦታና ጊዜ መፍጠር ይቻላል፡፡ ካሉበት ሲንቀሳቀሱ ጊዜ መውሰድ ነበረበት፣ በአየር ላይ ሲወረወሩም ሰው ማየት ነበረበት፡፡ ነገር ግን ይኼ አይፈጠርም፡፡ ከምንም ተነስቶ ነው ሲከሰት የሚታየው፡፡ የጥይት፣ የዓይነ ምድር፣ የጦር አንደርቢም ነበር፡፡ እነዚህ ሁሉ በሳይንስ ነበሩ ማለት አንችልም፡፡ ነገር ግን የቴሌፖርቴሽን ጽንሰ ሐሳብ የሚታዩባቸው እንደ Form of idea ነበሩ፡፡ እነዚህን ሐሳቦች ወደ ጥበብ ሥራ ማስገባት ይቻላል፡፡ በፊልሞችና ድራማዎች ላይ ብናያቸው ጥሩ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የኳንተም ፊዚክስ ትሩፋቶች የሆኑ የምርምር ሥራዎች ምን ያህል አሉ?

ኢንጂነር ታፈረ፡- በጣም ብዙ ናቸው፡፡ ጄኔራል ሪሌቲቪቲና ኳንተም ፊዚክስ ሁለቱ እየተጣመሩ ነው አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች የሚወጡት፡፡ በጣም ብዙ የተለያዩ የቴክኖሎጂ ሥራዎች እየተሠሩ ይገኛሉ፡፡ በዓለም ላይ ጠንካራ ከሚባለው ብረት አሥር ቢሊዮን እጥፍ ጠንካራ የሆነ ቁስ መሥራት ተችሏል፡፡ ከመሬት ከመቶ ሺሕ ኪሎ ሜትር በላይ ርቆ የስፔስ መነኸሪያ ቢገነባ ብረቱ ደግሞ ግዙፍ ዕቃዎችን የሚያመላልስ ሊፍት ይሠራበታል፡፡ ወደ ህዋ ዕቃ ማመላለስ በጣም ውድ ነው፡፡ በሚሊዮን ዶላር ወጪ ይወጣበታል፡፡ በዚህ ብረት የሚሠራው ሊፍት ግን ወጪውን በሳንቲም ቤት ያሳንሳል፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች