Sunday, June 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርኢትዮጵያዊነት ክብርም ፍቅርም ነው

ኢትዮጵያዊነት ክብርም ፍቅርም ነው

ቀን:

በወልደ አማኑኤል ጉዲሶ

የደቡብ አፍሪካውያን የነፃነት አባትና ከበርካታ የዓለም መሪዎችም በታጋይነታቸው፣ በፍቅር አባትነታቸውና በምሕረት ሰጪነታቸው በገሃድ የሚታወቁት ኔልሴን ማንዴላ በሕይወት ዘመናቸው ከተናገሯቸው አብነቶች ሁለቱን እንደሚከተለው ላስነብባችሁ፡፡ ‹‹የነፃነት ትግላችን የሰላም ትግል ነው››፣ ‹‹የነፃነት ጉዟችን የማይቀለበስ ነው፣ በዚህም ጉዟችን ፍርኃትን አናስተናግድም›› የሚሉትን፡፡ እነዚህን አብነቶች ለአንባቢያን በአስተያየቴ መንደርደሪያነት የተጠቀምኩት ያለ ምክንያት አይደለም፡፡

ብዙዎቻችን ዘግይቶም ቢሆን መምጣቱ እንደማይቀር ባለ ሙሉ ተስፋ ሆነን እንጠባበቅ የነበረው ለውጥ በአገራችን ተከስቷል፡፡ ያውም የዓለምን ሕዝብ በሚያስገርምና እንዲያውም ለማመን አስቸጋሪ በሆነ ሁኔታና ፍጥነት እየሄደ፡፡ ለዚህም አስገራሚ ለውጥ እያንዳንዳችን ለራሳችን ወይም በጋራ የምንሰጠው ትርጉም የተለያየ ሊሆን እንደሚችልም ይጠበቃል፡፡ መጠበቅም የነበረበት ወይም ያለበት ነውና፡፡ ከእነዚህም እንደ ፖለቲካዊ ብስለታችንና ብቃታችን እየሰጠናቸው ካሉ ትርጉሞች መካከል አዝጋሚ ለውጥ ነው፣ ጅምላ አብዮት ነው፣ ሥር ነቀል አብዮት ነው፣ ጠጋኝ አብዮት ነው፣ የቀለም አብዮት ነው፣ ወይም መነሻውም ሆነ መድረሻው የማይታወቅ ግራ የሚያጋባ ለውጥ እየሆነ ነው፣ ወዘተ. የሚሉ ይገኙባቸዋል፡፡

 ምንም እንበለው ምን ብቻ ለውጡ በአጭር ጊዜ ‹‹ይሆናል ብለን ያልጠበቅነውና ያላሰብነው›› መሆኑ ብዥታ የፈጠረብን ይመስላል፡፡ ይህ ብዥታ የሕዝቡ ወይስ የመንግሥትም? ለማንኛውም ግን ለውጥ መጥቶልናል አሊያም ‹‹መጥቶብናል›› እንበል? ወይስ ግራ አጋብቶናል እንበል? እስቲ ትንሽ ዘርዘር አድርገን እንመልከት፡፡

  ለውጡን ለአገራችንና ለወገኖቻችን ዘላቂ አብሮነት በአዎንታዊና ገንቢ መንገድ ተቀብለን ማስተናገድና መደገፍ የእያንዳንዳችን ግዴታ መሆኑ ደግሞ የግድ ነው፡፡ ይህ ካልሆነ ለኢትዮጵያችንና ለሕዝባችን መፃዒ ሕይወት የምንሰጠው ክብርና ፍቅር በቀጣይ ትውልዶች ዘንድ አዎንታዊ ተወራራሽነት አይኖረውም፡፡ በዚህ መነሻ በብዙዎቻችን ዘንድ ኢትዮጵያዊነትን ለምን በአዎንታዊነት እንቀበለው የሚለውን ጥያቄ በግሌ ትንሽ ዘርዘር አድርጌ ምላሽ ለመስጠት ላብራራ ነውና ይከተሉኝ!

ኢትዮጵያዊነት ክብር ነው፣ ይህ ባይሆን ኖሮ እስከ ዛሬ ተፈራርተን ሳይሆን ተከባብረን ባልኖርን ነበር፡፡ ኢትዮጵያዊነት ፍቅር ነው፣ ይህ ባይሆን ኖሮ ከሦስት ሺሕ ዓመታት በላይ በአንድነትና በመዋደድ ባልኖርን ነበር፡፡  ኢትዮጵያዊነት አንድነት ነው፣ ይህ ባይሆን ኖሮ እስከ ዛሬ ተበታትነን እንጂ ተመካክረንና ተቻችለን ባልኖርን ነበር፡፡ ኢትዮጵያነት ኩራት ነው፣ ይህ ባይሆን ኖሮ ስለኢትዮጵያዊነት በማንኛውም የዓለም መድረክ በኩራት፣ በልበ ሙሉነትና በድፍረት ባላወራን ነበር፡፡ ኢትዮጵያዊነት ድንቅ ባህል ነው፣ ይህ ባይሆን ኖሮ እሴቶቻችንን እስከ ዛሬ እንደ ዓይናችን ብሌን ተንከባክበን ባልጠበቅንና ባላቆየን ነበር፡፡

ኢትዮጵያዊነት ሰላም ነው፣ ይህ ባይሆን ኖሮ እስከ ዛሬ እርስ በርስ ተባልተን፣ ተዋግተንና ተጨፋጭፈን በተላለቅን ነበር፡፡ ኢትዮጵያዊነት አሸናፊነት ነው፣ ይህ ባይሆን ኖሮ በተደጋጋሚ የመጡብንን ጠላቶች ቀፎው እንደተነካበት ንብ ወጥተን፣ ጠዝጥዘንና አሳፍረን ባልመለስናቸው ነበር፡፡ ኢትዮጵያዊነት ጀግንነት ነው፣ ይህ ባይሆን ኖሮ ነፃነታችንን በአኩሪ ወኔና በውድ የሕይወት መስዋዕትነት ጠብቀን በጥቁር ሕዝቦች ዘንድ አርዓያ ሆነን ባላቆየን ነበር፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ ኢትዮጵያዊነት በምንም በማንም መተካት ወይም መለወጥ የማንችል የእናትነትና የአባትነት ፍቅርና ክብር  ነው፡፡ ይህ የእኔ የኢትዮጵያዊነት አጭር ትርጉም ወይም ትንታኔ ነውና የእርስዎን ካከሉበት የተሟላና የገዘፈ ይሆናል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ቀጣዩ ትውልድም ይህንኑ ያልተዛባና ያልተከለሰ ትርጉም ከእኛ በአግባቡ መረዳት ያስችለዋል፡፡ ይህንን ማድረግ ደግሞ የዜግነትና የኢትዮጵያዊነትም ግዴታ ነው፡፡

ስለኢትዮጵያዊነት ይህንን ትርጉም ሳቀርብ ባለፈ ታሪክ ከሚገባ በላይ መንጠልጠልን ግን ብዙም አልደግፍም፡፡ ታሪክ የሠሩ ቀደምት አባቶቻችን የራሳቸውን ድርሻ በመወጣታቸው ልናከብራቸው፣ ልንወዳቸውና ልናወድሳቸውም ይገባል፡፡ ታሪክን ተውሶ ወይም ገዝቶ በማምጣት የእኛ ነው ማለት አይቻልምና በሁሉም ኢትዮጵያዊ ዜጋ ዘንድ ይህ እንዲረሳም ከቶ አልፈልግም፡፡ ባለታሪኮቹን በገድላቸው እያገዘፉ መሄድንም አልጠላም፣ አከብራቸዋለሁም፡፡ ነገር ግን የዛሬው ወጣት የነገ አገር ተረካቢና ታሪክ ሠሪ ነውና ባለፈ ትረካ ብቻ አዕምሮው ደብዝዞ፣ የራሱን ታሪክ ፈጣሪነት የሚዘነጋ እንዲሆን ፍላጎቴም፣ ምኞቴም አይደለም፡፡ ወጣቱ ያለፈውን ታሪክ ሲያስታውስ እኔስ ምን ሠራሁ? ምንስ ይቀረኛል? የእነ ማን ታሪክ ለእኔ አብነት ሊሆን ይገባል? ወይም ሊሆን ይችላል? . . . የሚሉትን ጥያቄዎች በራሱ እንዲመልስና እንዲመራመር ሰፊ ዕድል መስጠት፣ ወይም መንገድ ማሳየት ከእኛ ከሚጠበቁ የወቅቱ አንገብጋቢ አጀንዳዎች አንዱ መስሎ ይታየኛል፡፡

በኢትዮጵያዊ ቤተሰባዊነት ዙሪያ ተከባብረን፣ ተቻችለንና ተፈቃቅረን የኖርነውን ያህል እነዚህኑ እሴቶቻችንን ለማደፍረስና ትርጉም አልባ ለማድረግ የሚቃጡ፣ ነገር ግን የማይሳካላቸው ግለሰቦችና ቡድኖች መፈጠራቸው ዛሬ ዛሬ የአደባባይ ሚስጥር ሆኗል፡፡ ሕጋዊ መብትን በሕጋዊ መንገድ መጠየቅ እንዳለ ሆኖ፣ ሕገወጦቹ ራሳቸውን አጀግነዋል፡፡ እውነትን መናገር ወንጀለኛና የመንጋ ተጠቂ እያደረገ ነው፡፡ ከእኛ በላይ አዋቂነት ለአሳር፣ ከእኛ በላይ ፍትሕ ሰጪነት ፍትሕ አላዋቂነት ነው የሚሉ ቡድኖችም ተበራክተዋል፡፡ ሽማግሌዎች የሚመክሯቸውን፣ የሃይማኖት አባቶች የሚገስጿቸውን፣ የታሪክ አዋቂዎች የሚተነብዩአቸውን በአጭሩ ሰላም ፈላጊ ኅብረተሰብና ወላጆች የሚለምኗቸው ተማፅኖዎች ተቀባይነት ያገኙ አይመስሉም፡፡ ሁሉም ሰው እንደ ሠለጠነው ዓለም ሁሉንም ነገር መንግሥት በጀመረው ሰላማዊና በፍቅር አገርን ለመገንባት ባለው ፍላጎት የሚያደርጋቸው ሙከራዎች፣ ምናልባትም ለጊዜውም ቢሆን እንደ ፍርኃት ወይም ትኩረት አናሳነት እየተቆጠሩ ያሉ ይመስላሉ፡፡

የዚህ ትርምስ ባለቤቶችና ስትራቴጂስቶች እነማን ናቸው? ብለን ራሳችንን ብንጠይቅ የእኛው ‹‹የምንላቸው ወገኖቻችን›› ናቸው፡፡ እነዚህም ወገኖች ለውጡ ያመጣልን ሳይሆን የመጣብን መዓት አድርገን እንድናይ ብዙ ጥረት አድርገዋል፡፡ አሁንም ልዩ ልዩ ሥልቶችን በመቀየስና በመለዋወጥ ይህንኑ ጥረታቸውን አላቋረጡም፡፡ እንዲያውም በአንዳንድ አካባቢዎች ጉልበተኛ ስፖንሰር የተቀጠረላቸው ወይም አይነኬ ባለሥልጣናት ከጎናቸው ሆነው የሚገፉ ይመስል፣ በኢትዮጵያዊነታችን ባህል ዙሪያ ጥቁር ነጥብ ጥለው የሚያልፉ ጠባሳዎችን አኑረዋል፣ እያኖሩም ናቸው፡፡ እንዳይገፉበትም በርካቶች ሥጋታቸውን በየመድረኩ በይፋ እየገለጹ ናቸው፡፡

ከእኛነት ይልቅ እኔነትን አጉልተው እያዩ የሚውሉና የሚያድሩ ወሮበሎች እየበዙ መጥተዋል፡፡ አንድነት ኃይል መሆኑንና ኃይልም ደግሞ ከፈጣሪ በታች የመንግሥት መሆኑን የዘነጉ ጊዜያዊ ጥቅም ፈላጊ የጎበዝ አለቆች ተራብተዋል፡፡ እንደ ጅምላ ጨራሽ ኑክሌር የጦር መሣሪያ ለሁሉም የመንጋ ውሳኔ ሰጪዎች ‹‹የራሳቸውን ሥርወ መንግሥት›› ያቋቋሙ አስመስለዋል፡፡ አስፈላጊ ከሆነ የሚለምኑ ካልሆነም ተጠያቂነትን በተግባር የሚያሳዩ አካላት የሉም የሚል መደምደሚያ ላይ እንዲደርሱ አብቅቷቸዋል፡፡ በሌላ አነጋገር እነዚህን የጎበዝ አለቆች የሚያስቆማቸው ሕግ እስካሁን በይፋ አላየንም የሚሉ በርካታ ናቸው፡፡ ጊዜያዊ ጥቅም ለማግኘት ሲሉ በሐሰተኛ መረጃ ሥርጭትና ሞቅ ባለ የገንዘብ ጉርሻ በመደለልም፣ በየአካባቢው በርካቶችን በማሠለፍ በሰው ሕይወትና ንብረት ላይ ውድመትና ሕልፈተ ሕይወት እንዲደርስ አድርገዋል፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ የህሊና ጉዳትና ምን ይመጣ ይሆን ሥጋት የዕለት ከዕለት ገጠመኝ ሆኗል፡፡

ተማሪው መማሩን አቁሞ በወንድሙ ላይ ዱላና ገጀራ እንዲያነሳ፣ የሕዝብን ሀብት የጠላት ሀብት አድርጎ እንዲያቃጥልና እንዲያወድም፣ ለዝንተ ዓለም አብረው የኖሩ ሕዝቦች በጠላትነት እንዲፈራረጁ፣ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ባለፉት ዘመናት የተፈጸሙ ድርጊቶችን ወደኋላ አድብቶ በመሄድ በመቀስቀስና ቂም እንዲቋጥሩ በማድረግ፣ አንዱ በሌላው ላይ በማያውቀው ሁኔታ ለበቀል እንዲነሳሳ የማድረግ ሥልት ተጠቅመዋል፡፡

ለውጡን ከልባቸው በመደገፍ በደስታ የተሞሉ፣ ከእስር የተፈቱ፣ ከስደት የተመለሱ፣ የሞት ፍርድ ይቅርታ የተደረገላቸው፣ የፖለቲካ ምኅዳር የጠበባቸው፣ በአገር ውስጥም ሆነ ውጭ አገር የህሊና እስረኛ የሆኑ፣ . . . እነዚህን ጉድጓዶች ማስቆም ባለመቻሉ ሥጋት አለባቸው፡፡ በተለይም ደግሞ የሕግ የበላይነት ያለመኖርና ቢኖርም ያለመከበር ያስከተላቸው መዘዞች፣ ዜጎችን ወደ ከፍተኛ ሥጋት በማስገባት ለውጡ መጣልን ወይስ መጣብን የሚል ጥያቄ እንዲያነሱ አስገድዷቸዋል፡፡ ይህ ብቻም አይደለም፡፡ ለማንም ሳያዳሉ እንደ ዜጋ እውነተኛውን ጭብጥ በአደባባይ መናገር ራስን አደጋ ላይ የሚጥል አጋጣሚ መሆኑም እየተስተዋለ ነው፡፡

ከጎረቤቶቻችን የመን፣ ሶማሊያ፣ ሊቢያ፣ ኢራቅና ሶሪያ መማር የሚገቡን በርካታ ቁም ነገሮች ያሉ ይመስለኛል፡፡ ዜጎቻቸው የአገራቸውን፣ የቤተሰቦቻቸውንና ለዘመናት የለፉበትን ሀብት፣ ክብርና ፍቅር እያዩ ተነጥቀዋል፡፡ እሳት በልቶባቸዋል፡፡ አባት፣ እናት፣ ወንድም፣ እህት፣ ሀብት ንብረታቸው ለሕልፈተ ሞት ተዳርገውና ወድሞ አገር አልባ ሆነዋል፡፡

ከዚህ በላይ እንዴትና ምን አስተማሪ ክስተት ይኖራል? የሚሆን ባይሆንም አንዳንዶቻችን ‹‹ራሳችን ሞተን ካልታየን››  በወገኖቻችን ላይ የምናደርሰው ሞት፣ ሞት መስሎ የማይታየን ሰዎች እየሆንን መጥተናል፡፡ ኢትዮጵያዊነት ክብርና ፍቅር ነው ስንል ከዚህ በላይ አሳፋሪና ኢሰብዓዊነትን የተከተለ ተግባር ከቶ ከየት ሊመጣ ነው? ከላይ በተጠቀሱ ጎረቤት አገሮች የምንሰማቸውንና የምናያቸውን የዕለት ከዕለት ሞት ሥቃይና ስደት ነገ በራሳችንና በወገኖቻችን ብለን ካላገናዘብን ከማን ምን ልንማር ነው?

ከሁሉም በላይ የሕዝብ ያልሆነውን አጀንዳ የሕዝብ እያደረግን በሕዝቦች መካከል ጠላትነትን ማብቀል ለማንም ለምንም የማይጠቅም ጊዜ ያለፈበት አጀንዳ መሆኑን ሁላችንም በትኩረት ልንረዳ ይገባል፡፡ ይህንኑ ሌሎችም እንዲያውቁ ካላደረግን ደግሞ እንዲህ ለሕዝብ የማይጠቅሙ አጀንዳዎች፣ እዚህም እዚያም ሰፊ መድረክ እያገኙ የሚኖረው ጠቀሜታ ጉልህ አይሆንም፡፡

ኢትዮጵያውያን የክብር፣ የውበት፣ የፍቅር፣ የአንድነትና የአብሮነት ኅብረ ቀለም ያለን ሕዝቦች ነን፡፡ ይህ ኅብረ ቀለም እየደመቀ እንጂ እየደበዘዘ መሄድ የለበትም፡፡ ይህ እንዲሆን ደግሞ ሁላችንም የሚበጀን ተደጋግፈንና ተመካክረን ወደኋላ መንሸራተት ሳይሆን ወደፊት መራመድ ነው፡፡ በጽሑፌ መግቢያ ላይ የጠቀስኳቸው አንጋፋው የነፃነት አባት ኔልሰን ማንዴላ ከተናገሯቸው ታሪካዊ አስተምህሮዎች መካከል አንድ ተጨማሪ አባባል ላስነብባችሁ ነው፡፡ ‹‹ጠላቶቻችን አንድ ለአንድ ወይም በቡድን እርስ በርስ  ለሚያጨፋጭፍ የባሰ አፓርታይድ ሥርዓት ይዳረጋሉ ብለውን ነበር፡፡ እኛ ግን በውይይትና በሰጥቶ መቀበል ሰላማችንን አሰፈንን፡፡ ጥላቻን አስወገድን ዕርቅ አወረድን፡፡ ጠንካራ አገር፣ ጠንካራ ሕዝብና መንግሥት ገነባን፤›› ነበር ያሉት፡፡

ይህ ሆኖ እያለ በእኛ ነባራዊ ሁኔታ ከሚያስታርቀን ይልቅ የሚያጣላ ባለመድረክ ሆነ፣ ከባለሙያ ይልቅ ዘመን አመጣሹ ፖለቲካ ተንታኝ ሆነ፣ ልጅ የአባትን ምክርና ግሳፄ አልቀበልም አለ፣ ማመልከቻ ጻፊ ሁሉ በማኅበራዊ ሚዲያ ጋዜጠኛ ሆነ፣ ማኅበራዊ ሚዲያም ዕድገቱ ለለውጥና መሻሻል ሳይሆን ለነውጥ ነው ወደሚያሰኝ ደረጃ ተደረሰ፣ የስም ማጥፋትና ማስጠፋት ወንጀሎች ያለምንም ገደብ የሚሠሩበት ብቸኛ መድረክ ሆኖ ቁጭ አለ፡፡ ማኅበራዊ ሚዲያው ለተጠቃሚው ቁርስ፣ ምሳና እራትም ሆነ፡፡ የዘመቻ ኮማንድ ፖስትም ሆኖ ባለ በሌለ ነገር ደጃዝማች፣ ፊታውራሪ፣ ቀኛዝማችና እልፍኝ አስከልካይ፣ ሥልጣን አስከባሪም ሆነ፡፡ ምን ይህ ብቻ አንዳንዱን ወደ ቀበሮ ጉድጓድ ወይም ሰው ሠራሽ ዋሻ ውስጥ አስገብቶ ንፁህ አየር እንዳያገኝም፣ እንዳይወጣም አድርጓል፡፡ ታዲያ በዚህ ሁኔታ መቀጠል እንዴትና እስከ መቼ!?

ኢትዮጵያውያን የክብር፣ የውበት፣ የፍቅር፣ የአንድነትና የአብሮነት ኅብረ ቀለም ያለን ሕዝቦች ነን፡፡ በዚህ ክብራችንና ፍቅራችን በአንድነትና በኢትዮጵያዊነት ተደምረን እንኑር፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አወዛጋቢው የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ጉዳይ

በኢትዮጵያ የሕገ መንግሥት ማሻሻል ጉዳይ ከፍተኛ የፖለቲካ ውዝግብ የሚቀሰቀስበት...

 መፍትሔ  ያላዘለው  የጎዳና  መደብሮችን  ማፍረስ

በአበበ ፍቅር ያለፉት ስድስት ዓመታት በርካቶች በግጭቶችና በመፈናቀሎች በከፍተኛ ሁኔታ...

የተናደው ከቀደምቱ አንዱ የነበረው የአዲስ አበባ ታሪካዊ ሕንፃ

ዳግማዊ አፄ ምኒልክ በ19ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ መናገሻ ከተማቸውን...

የአከርካሪ አጥንት ሕክምናን ከፍ ያደረገው ‘ካይሮፕራክቲክ’

በአፍሪካ ከጀርባ ሕመም ጋር በተያያዘ በርካታ ሰዎች ለከፍተኛ የአካል...