Wednesday, May 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ልናገር“ጥቂት ብዙኃን - ብዙኃን ጥቂቶች” ያለቁበት ኩዴታ

“ጥቂት ብዙኃን – ብዙኃን ጥቂቶች” ያለቁበት ኩዴታ

ቀን:

በዕዝራ ኃይለ ማርያም 

ግንቦት 8 ቀን 1981 .ም.  ሌተና ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ወደ  ምሥራቅ ጀርመን ሲሄዱ፣ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ተገኝተው ሸኟቸው፡፡ አውሮፕላኑ ከቀኑ ስድስት ሰዓት ጉዞ ጀመረ፡፡ የመከላከያ ሚኒስትሩ ሜጀር ጄኔራል  ኃይለ  ጊዮርጊስ ሀብተ ማርያም  ከባህር ኃይል ዋና  አዛዥ ሪር  አድሚራል ተስፋዬ ብርሃኑ  ጋር ኢትዮጵያ ሆቴል ምሳ በመብላት ላይ ሳሉ፣ ጄኔራሉ  ለሪር አድሚራሉ  ‹‹በህልሜ  ሁለት ቀያይ  ዓሳ ስውጥ አየሁ››  ይላሉ አድሚራሊም  ሲሳይ  ነው ይሏቸዋል፡፡

ከምሳ  በኋላ የመፈንቅለ መንግሥት መሪዎች መላኪያ ሚኒስቴር  ተሰበሰቡ፡፡  መፈንቅለ  መንግሥት  በመደረግ  ላይ  መሆኑን  የደረሱበት  የደኅንነት ሚኒስትሩ ኮሎኔል ተስፋዬ  ወልደ ሥላሴ ከሻምበል መንግሥቱ  ገመቹ፣ ከሻምበል  ፍቅረ  ሥላሴ ወግደረስ፣  ከኮሎኔል ፍሰሐ ደስታ ከሌሎችም ጋር ተሰባስበው ጄኔራል ኃይለ ጊዮርጊስ ዘንድ መከላከያ ሚኒስቴር በመሄድ የጄኔራሎችን ስብሰባ  እንዲያስቆሙ ያዟቸዋል፡፡

- Advertisement -

ጄኔራሉም ቢሮዋቸው  ደረጃ  ላይ እንደ ደረሱ ከሜጀር ጄኔራል አበራ አበበ  ጋር ተገናኝተው  ስለጄኔራሎቹ ስብሰባ ሕገወጥነት  ይናገራሉ፡፡ የቃላት ልውውጡ  ይካረራል፡፡  ጄኔራል ኃይለ ጊዮርጊስ ሽጉጣቸውን ሊመዙ ሲሉ ጄኔራል አበራ ቀድመዋቸው በሁለት  ጥይት ይመቷቸውና ይሞታሉ፡፡  በህልማቸው  የዋጧቸው ሁለት ዓሳዎች  በዕውን  ጥይቶችሆነዋል፡፡ ይህን ታሪክ  ያገኘሁት  አጥፍቶ መጥፋትከተባለው መጽሐፍ ነው፡፡ እ.ኤ.አ. 1945 (ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት ፍፃሜ) እስከ ግንቦት  ስምንቱ መፈንቅለ መንግሥት ድረስ በ79 አገሮች 311 የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራዎች  ተደርገዋል፡፡ 170ዎቹ የተሳኩ ነበሩ፡፡ በአርጀንቲና በ16  ዓመታት 13 መፈንቅለ  መንግሥቶች ተካሂደዋል፡፡

ደርግ  ንጉሠ  ነገሥቱን  አስወግዶ ሥልጣን የያዘው አፄ ኃይለ  ሥላሴን እንደ ምስጥ ቦርቡሮ ብቻቸውን ካስቀረ በኋላ ነው፡፡ ያለ ደም መፋሰስ  የተካሄደው ይህ መፈንቅለ መንግሥት አዝጋሚው መፈንቅለ መንግሥት በመባል ተወድሷል፡፡ ደርግ አምባገነን በመሆኑ ግጭቶችንና ጦርነቶችን በውይይት ለመፍታት  ከልቡ አልጣረም፡፡ በጦርነት፣ በድርቅ፣ በመፈናቀል፣ በኑሮ  ውድነት፣ በውትድርና  አፈሳና በመሳሰሉት ሕዝቡ  ተማረረ፡፡ በሰሜን ሻዕቢያና ወያኔ በሚያደርጉት የቅብብሎሽ ጦርነት  አገሪቱ ተሽመደመደች፡፡ 60 በመቶ የአገሪቱ  በጀት ለጦርነት ዋለ፡፡ የጦርነቱ መራዘምና  ድል ማጣት አሰለቸ፡፡

ምዕራባውያን ደርግን እንደ  ዱርዬ መንግሥት በማየት ከሰብዓዊ ዕርዳታ  ውጪ ብድርና ዕርዳታ ከለከሉ፡፡ የውትድርና አመራሩ  የአንድ ሰው ዕዝን አስቀርቶ በሦስት ማዕዘን (አዛዥ፣ ወታደራዊ ደኅንነትና፣ ፖለቲካ ኃላፊ) ሆነ፡፡  ወታደራዊ  ደኅንነትና ፖለቲካ ኃላፊዎች፣ በአገሪቱ መሪና የበላይ አካላት ዘንድ ተቀባይነት ያላቸው ካድሬዎች እንጂ በማዕረግ፣  በልምድና በወታደራዊ ዕውቀት ብቃት  ያላቸው አዛዦች አልነበሩም፡፡  አዛዡ ጄኔራል ያለ እነሱ  ለብቻው መወሰን  አይችልም፡፡ በማዕረግም ሆነ፣ በሙያ የአዛዡ አቻ አይደሉም፡፡

በዚህም የተነሳ የመከላከያ ከፍተኛ አመራሮች መፈንቅለ መንግሥት ለማድረግ ተነሳሱ፡፡ ለመሪነት የታጩት ሜጀር ጄኔራል ፋንታ በላይ ሲሆኑ፣ ጄኔራሉ የአየር ኃይልዋና አዛዥ ሆነው በሙያቸው የተከበሩ፣ የታፈሩ፣ የላቀ ሁለንተናዊ ሰብዕናና ወዝ ያላቸው ነበሩ፡፡ የሶቪዬት ኅብረት  አማካሪዎችን ስለሚንቁና አጎብዳጅ (Yes Man) ባለመሆናቸው አማካሪዎቹ  አስጠቁረዋቸዋል፡፡ ኮሎኔል መንግሥቱ ስለሠጉ  ወደ ኢንዱስትሪ ሚንስትርነት አዛውረዋቸው ነበር፡፡

ግንቦት 8 ቀን 1981 .ም.  ኮሎኔል መንግሥቱ ወደ ምሥራቅ ጀርመን ሲጓዙ  የጦር ኃይሎች ኤታ ማጀር ሹም የነበሩት ጄኔራል መርዕድ ንጉሤ  ከፍተኛ የመከላከያ ባለሥልጣናትንና የኃይል አዛዦችን መከላከያ ሚኒስቴር ጠሩ፡፡  ኮሎኔል መንግሥቱን  ለማስወገድ የቀረቡት አማራጮች አንደኛው አውሮፕላኑን በአየር ላይ መምታት ሲሆን፣  ይህም በውስጡ ያሉትን 74 ሰዎች መጨረስ ስለሆነ ቀረ፡፡ ሁለተኛው አማራጭ  በአየር ኃይል አውሮፕላኖች  አስገድዶ ለሁለተኛው አብዮታዊ ሠራዊት ዋና አዛዥ  ለሜጀር ጄኔራል ደምሴ ቡልቶ ማስረከብ ነበር፡፡ በዚህ ሐሳብ  ቢስማሙም አውሮፕላኑ  የኢትዮጵያን ክልል በማለፉ ተግባራዊ አልሆነም፡፡ ግንቦታውያኑ የረባ ዕርምጃ  ሳይወስዱ፣ ስብሰባ ላይ እንዳሉ በአክሻፊዎቹ ቡድን ተከበቡ፡፡ የመፈንቅለ መንግሥቱ  መሪዎች ጄኔራል መርዕድ ንጉሤና ጄኔራል አምሐ ደስታ ራሳቸውን አጠፉ፡፡

ሌሎች ጄኔራሎች እጃቸውን ሰጡ፡፡ ጄኔራል አበራ አበበ ጄኔራል ኃይለ ጊዮርጊስን ከገደሉ  በኋላ ከመከላከያ ሚኒስቴር ዘለው አመለጡ፡፡ ከአንድ ወር በኋላ  ከቤተሰባቸው አንድ ሰው ባደረገው ጥቆማ በተደበቁበት ቤት ተከበው ተገደሉ፡፡  ጄኔራል ፋንታ  በላይ  ለሦስት  ቀናት ኮንቴይነር ውስጥ ከተደበቁ በኋላ ወጥተው ለማምለጥ ሲሞክሩ ተያዙ፡፡ ቃላቸውን በመስጠት ላይ እንዳሉ ግልጽ ባልሆነ መንገድ  ሊያመልጡ ሲሉበሚል  ሰበብ ተገደሉ፡፡ ጄኔራል ቁምላቸው ደጀኔ ለመፈንቅለ መንግሥቱ ድጋፍ ከአስመራ  የሚመጣ ጦር ለመቀበል ከስብሰባው ውጪ ስለነበሩ ሲከሽፍ አመለጡ፡፡ በኋላ አሜሪካ ገቡ፡፡

በጄኔራል ደምሴ የሚመራው የአስመራው መፈንቅለ መንግሥት ሙከራ  ከምሽቱ  አንድ ሰዓት የአስመራ ራዲዮን  በመቆጣጠር፣ የኮሎኔል መንግሥቱን ከሥልጣን መወገድና  የመፈንቅለ መንግሥቱን  ዓላማም አስተዋውቋል፡፡ ሻዕቢያና ወያኔ መፈንቅለ  መንግሥቱን እንዲደግፉ ጥሪ አቅርቧል፡፡ ሻዕቢያ በሁሉም  ግንባሮች ለ15 ቀናት ተኩስ  በማቆም ድጋፉን ሲገልጽ ወያኔ አልደገፈም፡፡ የአዲስ አበባው ከከሸፈ በኋላ የአስመራው በአቋሙ ፀንቶ ቀጠለ፡፡ ኮሎኔል መንግሥቱ ጉብኝታቸውን አቋርጠው ግንቦት 9  ቀን  1981 .ም. ከምሽቱ አንድ ሰዓት አዲስ አበባ ገቡ፡፡ ለመፈንቅለ መንግሥቱ ሙከራ  መክሸፍ በርካታ ምክንያቶች ቢጠቀሱ፣ ሞካሪዎቹ  ስኬታማ የመፈንቅለ መንግሥት  ባህርያት  (ፍጥነት፣  ከባድ  ምት፣  ሚስጥር  መጠበቅ፣  ጥንቃቄ፣  የወቅት ምርጫ. . .) አለመጠቀማቸው ሕይወታቸውን አሳጥቷቸዋል፡፡

የአገሪቱ ዋና ዋና ጄኔራሎች የመፈንቅለ መንግሥቱ ተሳታፊዎች በመሆናቸው፣  በራስ የመተማመን ስሜታቸው ከፍተኛ መሆኑ እንዳዘናጋቸው ይታሰባል፡፡ ተራ ስህተት ኩዴታን ያከሽፋል፡፡ መገናኛ ብዙኃንን ተቆጣጥረው ዓላማቸውን ለሕዝቡ  አላሰረፁም፡፡ የኮሎኔል መንግሥቱ ደጋፊዎችን ፈጥነው በቁጥጥር ሥር በማዋል የመንግሥትን አከርካሪ አጥንት አልሰበሩም፡፡ በጥንቃቄና በማስተዋል የተደራጀ ሎጂስቲክ፣ ኦፕሬሽን (ዘመቻ) አላካሄዱም፡፡

ኮሎኔል መንግሥቱን ከማንም በላይ የሚያውቋቸው ገዲም ጄኔራሎች  የነብር ጭራ አይዙም፣ ከያዙም አይለቁምየሚለው አባባል ተዘንግቷቸዋል፡፡ ፍጥነት፣ ጥንቃቄ፣ ከባድ ምት፣ መገናኛ ብዙኃንን ተቆጣጥሮ  ዓላማን በማስረፅ በኩል ዳተኛ ሆነዋል፡፡ አንዳንዴ ሳስበው እነዚያን የመሰሉ የጦር ፀያሄ ፍኖቶች መዘናጋት ይገርመኛል፡፡ ‹‹ያሸነፉ ዕለት አምቧቻሪ ዘምበል ያለ ዕለት ምሶ ቀባሪ  አይጠፋም›› እንዲሉ፣ የአዲስ አበባው ከከሸፈና ኮሎኔል መንግሥቱም አዲስ አበባ ከገቡ በኋላ ታማኝነቱን ለማሳየት የሚሯሯጠው በዛ፡፡

የአስመራውም እስከ ግንቦት 10 ቀን 1981 ዓ.ም. ድረስ ተፍገምግሞ ከሸፈ፡፡ አክሻፊዎቹ ጄኔራል ደምሴን ጭካኔ በተሞላው ነውረኛ ድርጊት ገደሉ፡፡ የአስመራውን ያከሸፈው 102ኛው አየር ወለድ ነው፡፡ ይህ ጦር ደካማ እየተባለ በእነ ጄኔራል ደምሴ ቡልቶ ዘለፋ  ይደርስበት ነበር፡፡ ጄኔራል ደምሴን ጨምሮ 12 ጄኔራሎችን፣ አራት ኮሎኔሎችንና  ሁለት ሻለቆችን በአሰቃቂ ሁኔታ ተገደሉ፡፡ በርካታ መኮንኖችም ታሰሩ፡፡  በቁጥጥር  ሥር ከዋሉት መፈንቅለ መንግሥት ሞካሪዎች ውስጥ ንፁኃን ነበሩበት፡፡ የጦር ፍርድ ቤት  ተቋቁሞ መታየት ጀመረ፡፡ ፍርድ ቤቱ ሰኞ ግንቦት 13 ቀን 1982 .ም. ውሳኔ  ለመስጠት ቀጠሮ የያዘ ቢሆንም፣ ቀጥታ በኮሎኔል መንግሥቱ በተጻፈ ቁራጭ ወረቀት  ትዕዛዝ የፍርድ ቀኑ ከመድረሱ በፊት፣ ቅዳሜ ግንቦት 11 ቀን ማታውኑ 12 ጄኔራሎች ቤተ መንግሥት ውስጥ አሰቃቂና ዘግናኝ ግድያ ተፈጸመባቸው፡፡

በመፈንቅለ መንግሥቱ ሙከራ የመከላከያ ሚኒስትር፣ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታ ማጆር ሹም፣ የአየር ኃይል ዋናና ምክትል አዛዥ፣ የፖሊስ ሠራዊት ዋና አዛዥ  እንዲሁም በኤርትራ ከፍተኛ ልምድ  ያላቸው ጄኔራሎች ተገደሉ፡፡ አገሪቱ ካሏት 90  ጄኔራሎች ውስጥ 28 ጄኔራሎች (ሰላሳ በመቶ) ዋናዎቹ የጦር አበጋዞች አለቁ፡፡ ደርግ  የመፈንቅለ  መንግሥት  ሞካሪዎቹን  ጥቂት ጄኔራሎችይል ስለነበር በወቅቱ በካፌ  ውስጥ ሻይና ቡና ሲታዘዝ ጥቂት ሻይጥቂት ቡናማለት ተለምዶ ነበር፡፡

ያለቁት  ከንጉሡ ዘመን ጀምሮ በምዕራብ አገሮች በታዋቂ ወታደራዊ ተቋማት የተማሩ የአፍሪካ  ጎምቱ ጄኔራሎች ነበሩ፡፡ ደርግም ዕርቃኑን ቀረ፡፡ የቁልቁለት ጉዞውን ተያያዘው፡፡  ጄኔራሎችን በጨረሰ በዓመቱ ወደቀ፡፡ በመፈንቅለ መንግሥቱ የመጀመሪያው ተገዳይ  ጄኔራል ኃይለ ጊዮርጊስ ናቸው፡፡ በህልማቸው የዋጧቸው ቀያይ ዓሳዎችን ባልደረባዎቻቸው የነበሩ ጄኔራሎች በማግሥቱ፣ በሰልስቱና በካንጋሮው የጦር ፍርድ  በተሰጠ ውሳኔ በዓመቱ ዋጡ፡፡ አለቁ፡፡ በደርግ ላይ የተሞከረው መፈንቅለ መንግሥት 30 ዓመታት መዘከሪያ ነው፡፡

እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ!

ማስታወሻ፡ይህን  መጣጥፍ  ለማዘጋጀት  አጥፍቶ  መጥፋት እና  አብዮቱና  ትዝታዬመጻሕፍትን ተጠቅሜያለሁ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል [email protected] አድራሻቸው                                                           ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...