Saturday, July 13, 2024

በተቃርኖ የተሞላው የፌዴራል ሥርዓት ችግሮች መንስዔዎች

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ብዙ ጊዜ ፌዴራሊዝምንና ፌዴሬሽንን አንድ አድርጎ የመውሰድና እየለዋወጡ የመረዳት ሁኔታዎች በኅብረተሰቡ ዘንድ እንደሚታዩ፣ ነገር ግን ሁለቱም የተለየ ፍቺና ይዘት እንዳላቸውና ፌዴራሊዝም ሐሳብ፣ ትልም፣ ምኞትና ርዕዮተ ዓለም መሆኑ፣ ፌዴሬሽን ግን ስለመዋቅር፣ ተቋማትና በተጨባጭ ስላሉ ክስተቶች የሚያስረዳና አንድ አገር መንግሥት የሚዋቀርበት ሥልት እንደሆነ ይነገራል፡፡ ቅዳሜ ግንቦት 10 ቀን 2011 ዓ.ም. በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የመሰብሰቢያ አዳራሽ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ተዘጋጅቶ በነበረው የውይይት መድረክ ላይ ስለፌዴራል ሥርዓት ተቃርኖዎች፣ መንስዔዎቹና ውጤቶቹ፣ በተለይም የኢትዮጵያ ፌዴሬሽን ላለፉት 27 ዓመታት ይዟቸው ስለቆዩ ተቃርኖዎች የፖለቲካል ሳይንስ ተመራማሪውና በካናዳ ቶሮንቶ ዩኒቨርሲቲ መምህር ሰሚር ዩሱፍ (ዶ/ር) ባቀረቡት የመወያያ ሐሳብ ላይ ሰፊ ትንታኔ ሰጥተዋል፡፡ ለግማሽ ቀን በተካሄደውና ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)ን ጨምሮ በርካታ የኅብረተሰብ ክፍሎች በተሳተፉበት በዚህ ውይይት ላይ፣  ሰሚር (ዶ/ር) የብዙዎችን ቀልብ የሳበና በትኩረት የተከታተሉት ስለኢትዮጵያ ፌዴሬሽን ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ፌዴሬሽን በተቃርኖ የተሞላ ሆኖ መቆየቱንና ለዚህም በርካታ አብነቶችን መጥቀስ እንደሚቻል በመግለጽ የመወያያ ሐሳባቸውን የጀመሩት ሰሚር (ዶ/ር)፣  ሁሉም ኢትዮጵያዊያን የሚያውቋቸውን ሁለት ዓበይት ጉዳዮችን አንስተዋል፡፡ የመጀመርያው በተቋማት ደረጃ ሲሆን፣ በአንድ ወገን ብሔር ተኮር የሆኑ መዋቅሮችና ተቋማት በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች በሰፊው መመሥረታቸው፣ በየክልሎች ሕግ አውጪ፣ አስፈጻሚና ተርጓሚ ተቋማት መቋቋማቸውን፣ እነዚህን የሚገዛ ሕገ መንግሥት አፅድቀዋል፡፡ እያንዳንዱ ክልል የራሱ ሰንደቅ ዓላማና ከባቢያዊ ፖለቲካ እንዲኖረውም መደረጉን፣ በሌላ በኩል የክልሎችን ራስን በራስ የማስተዳደር (Self Rule) ትልም በሚቃረን መንገድ የተማከለ አስተዳደርም ሰፍኖ መቆየቱን፣ እንዲሁም ቁልፍ አጀንዳዎች ከላይ ወደ ታች የሚወርዱበት ሥርዓት ተዘርግቶ፣ በተለያዩ ዘዴዎች የክልሎችን የፖለቲካና ፀጥታ ጉዳይ የሚቆጣጠሩ መረቦች ተዘርግተው መቆየታቸውንና በውጤቱም የፌዴራል ሥርዓት አስኳል የሆነው ራስ ገዝነት በተደጋጋሚ ሲገፋ መኖሩን አስረድተዋል፡፡

ሁለተኛው ተቃርኖ በማለት በማሳያነት ያነሱት በሥነ ልቦና ላይ ያተኮረ ሲሆን፣ የፌዴራል ሥርዓቱ በአንድ በኩል ባህልና ቋንቋ በተለያዩ አካባቢዎች እንዲጎለብቱና እንዲያድጉ ትልቅ ሚና መጫወቱን ነው፡፡ አካባቢያዊ ፖለቲካ አድጎ እንደ አንድ ብሔር፣ ብሔረሰብ ለአብነት መብቃት (Ethnic Empowerment) እንዲመጣ የራሱን ሚና መጫወቱን አክለዋል፡፡ በሌላ በኩል ለባህልና ለቋንቋ መዳበር አበርክቶ (Contribution) እንደነበረው ሁሉ የብሔር ተዋረድ ስሜት እንዲፈጠርም የራሱን ሚና መጫወቱንም ጠቁመዋል፡፡ ይኼም በአገር አቀፍና በክልሎችም በመስተዋሉ ‹የአንድ ብሔር የበላይነት አለ›› የሚል ስሜት እንዲፈጠር ምክንያት ሆኗል ብለዋል፡፡ በክልሎች ደረጃም ‹‹መጤ›› እና ‹‹ነባር›› የሚባል የብሔር ክፍፍል በማምጣት የብሔር ተዋረድ (Ethnic Hierarchical) ስሜት እንዲጎለብት የራሱን ሚና መጫወቱንም ተናግረዋል፡፡ በአጭሩ የኢትዮጵያ ፌዴራል ሥርዓት በተቃርኖዎች የተሞላ ሆኖ መቆየቱን ጠቁመዋል፡፡

በኢትዮጵያ የፌዴራል ሥርዓት ላይ የታዩ ተቃርኖዎች በተለያዩ መንገዶች በምሁራን በርካታ መንስዔዎች ሲቀርብባቸውና ትንታኔ ሲሰጥባቸው መቆየታቸውን የጠቆሙት ተመራማሪው፣ አብዛኞቹ መንስዔዎች የኢሕአዴግ (ሕወሓት) ፖለቲካዊ ፍላጎቶች ላይ የተንተራሱ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ የገዥውን ፓርቲ ፖለቲካዊ አወቃቀርም ተመርኩዘው የተሰነዘሩ ትንታኔዎችም ነበሩ፡፡ ትኩረት ያልተሰጣቸውና ለኢትዮጵያ ፌዴሬሽን ተቃርኖዎች መንስዔ የሆኑ ሁለት ትንታኔዎች መኖራቸውን የገለጹት ሰሚር (ዶ/ር)፣ የመጀመርያው ብሔር (Ethnicity) ስለሚባለው ጽንሰ ሐሳብ ኢሕአዴግ ያለው አመለካከት በሁለት የተቃርኖ ሐሳቦች የታጀለ በመሆኑ፣ ፌዴሬሽኑ በራሱ በተቃርኖ እንዲሞላ ትልቅ ሚና መጫወቱን አስምረውበታል፡፡ ሁለተኛው ደግሞ የአመለካከት ጉዳይ ብቻ ሳይሆን፣ ኢሕአዴግ የወረሳቸው ተቃራኒ የታሪክ ዳራዎችም መኖራቸውን አስታውሰዋል፡፡ እነዚህ ውርስ ዳራዎችም ለፌዴሬሽኑ በተቃርኖ መሞላት የራሳቸው ጉልህ ድርሻ እንዳላቸውም ገልጸዋል፡፡    

ኢሕአዴግ ስለብሔር ያለው አስተሳሰብ በሁለት ተቃራኒ ምልክታዎች የተቃኘ ሆኖ ነው ለረዥም ጊዜ የቆየው፡፡ በአንድ በኩል ብሔርን ጥንት የነበረ (Primordial) በሚል እንደተረዳው፣ ይኼም ማለት ብሔርን ከውጭ ሆኖ ወደ ውስጥ የሚገለጽ፣ የሚበየን፣ ማንም ዓይቶ ሊያውቀው የሚችል፣ ውስጣዊ ወጥነት ያለው፣ በድንበር ተወስኖ ሊቀመጥ የሚችልና እምብዛም ተለዋዋጭነት የሌለው ጽንሰ ሐሳብ አድርጎ እንዳየው አብራርተዋል፡፡

ብሔርን ገና ሕገ መንግሥቱ ሲረቀቅ ጀምሮ ጥንት የነበረ ነው ብሎ ስላመነ፣ ክልሎችንም ያዋቀረው ለአንድ የብሔር ንቃተ ህሊና (Consciousness) የነበራቸው አካባቢዎች የዳበረ የልሂቃን ስብስብ ስለነበሩ፣ በሕገ መንግሥቱ አማካይነት ለብሔር መብቃት ሊያገለግሉ የሚችሉ ግብዓቶችን ሰጥተዋል ብለዋል፡፡ በሌሎች ቦታዎችና የብሔር ንቃተ ህሊና በሌለባቸው አካባቢዎች ልሂቃንን በመሰብሰብ ‹‹እናንተ የዚህ ብሔረሰብ አባሎች ናችሁ›› በማለት እንዲደራጁና አገር አቀፍ ፖለቲካውን እንዲቀላቀሉ በማድረግ የራሱን ሚና መጫወቱን ተመራማሪ አስረድተዋል፡፡ ይኼ አሠራር የሚመነጨውም ከውጭ ሆኖ ወደ ውስጥ የሚበይነውና ብሔር አለ ብሎ የተቸነከረ (Fixed) የብሔር አስተሳሰብ ላይ የተመረኮዘ አሠራር ስለነበረው መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ ይኼ አሠራሩ ከተወሰኑ ጊዜያት በኋላ ኢሕአዴግ ባሰበው መንገድ ብሔርን መገንዘብ ችግር እየተጋረጠበት እንደመጣ መገንዘብ ጀመረ ሲሉ ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም ሙሉ የብሔር መብቶችን ያለ ማወላወል የመገንዘብ ትርክቱን (Discourse) እንደ አጋጣሚ በመጠቀም፣ በርካታ ብሔሮችን በአዲስ መንገድ በማደራጀቱ የክልልነት፣ የወረዳነትና የዞንነት ጥያቄዎች መዥጎድጎድ መጀመራቸውንም ጠቁመዋል፡፡ በዚህ ጊዜ ኢሕአዴግ የከፈተውን የፓንዶራ ሳጥን ወደ መዝጋት መሸጋገሩን፣ ምክንያቱ ደግሞ በአንድ በኩል ለአገር መረጋጋት ተግዳሮቶች ናቸው ብሎ በማሰብ ሲሆን፣ በሌላ በኩል የራሱ ፖለቲካ ፈር ይዞ መሄድ ጋሬጣ ይሆናል ብሎ በመሥጋቱ ነው፡፡ ኢሕአዴግ የፓንዶራ ሳጡን ሲዘጋ በሌላ አስተሳሰብ ላይ ሆኖ ብለው፣ ጥንት ከነበረ አስተሳሰብ ወደ ‹ኢንስትሩመንታሊስት› አስተሳሰብ በመሸጋገር መሆኑን ሰሚር (ዶ/ር) አስረድተዋል፡፡

ብሔርን በ‹ኢንስትሩመንታሊስት› አስተሳሰብ መቀበል ማለት፣ እንዳለ መቀበል ሳይሆን ውስጡ በመግባት በመቀነስ፣ በመለወጥ፣ በማላቀጥ (Manuplate) ለሆነ ዓላማ ለማዋል የሚጠቅም ነው ተብሎ የሚታመን አስተሳሰብ ነው፡፡ ኢሕአዴግም በዚህ አስተሳሰብ በመተማመን፣ ጥንት ከነበረ አስተሳሰብ ወደ ‹ኢንስተሩመንታሊስት› አስተሳሰብ መሸጋገሩን ተመራማሪው ገልጸዋል፡፡ ለዚህ ማሳያነት ብዙ ማቅረብ ቢቻልም የደቡብ ክልል ግን በቂ ማሳያ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ አምስት የነበሩትን ክልሎች ወደ አንድ በመሸብለል ‹‹የደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል›› በማለት በአንድ ክልል እንዲሆኑ ኢሕአዴግ ትልቅ ሚና መጫወቱን ገልጸዋል፡፡ ቆይቶ ባይሳካለትም የተለያዩ ቋንቋዎች ይጠቀሙ የነበሩ ብሔሮችን አንድ ሊያደርግ የሚችል ቋንቋም ፈጥሮ እንደነበር አክለዋል፡፡ በርካታ የነበሩትን የፖለቲካ ፓርቲዎችን ወደ አንድ በማምጣት ኢሕአዴግ የሚባል ፓርቲም እንዲመሠረት ማድረጉን፣ ኢሕአዴግ ከፌዴራል እስከ ክልል መንግሥታት ድረስ ፖለቲካና ፀጥታን የሚዘውሩ ልሂቃንን በመላክ ክልሎችን በቁጥጥር ሥር ለማዋል ጥረት እንዳደረገ፣ ከዚህ መገንዘብ የሚቻለው ብሔር ለሁሉም (Ethnicity for All) ከሚባለው አስተሳሰብ ወደ መቆጣጠር (Containment) ወይም ብሔርን መከላከል መሸጋገሩንም አስገንዝበዋል፡፡

ኢሕአዴግ በመቀጠልም የራስን ዕድል በራስ የመወሰን ጥያቄ የሚያነሱ ልሂቃንን በጠባብነት በመፈረጅ ሲኮንናቸው መቆየቱን፣ ጥንት ከነበረ አስተሳሰብ የተቃናው የብሔር ትንታኔ ያመጣውን ያልታሰበ ውጤት ለመከላከል ሲል ወደ ‹ኢንስተሩመንታሊስት› ወደ ሆነ አስተሳሰብ ብሔርን የመረዳት አዝማሚያ በመሸጋገር ነበር ችግሩን ለመቆጣጠር ጥረት ያደረገው፣ በውጤቱም ፌዴሬሽኑ በተቃርኖ እንዲሞላ ትልቅ ሚና የተጫወተበት መንስዔ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡ የኢሕአዴግ ሌላው ተቃርኖአዊ መንስዔ የሁለት ተቃራኒ ታሪካዊ አዋጆች ሴራ ነው ብለዋል፡፡ የመጀመርያው የተዋረዳዊ አስተዳደር ወራሽ ሲሆን፣ ሁለተኛው ከተማሪዎች ንቅናቄ ጋር አብሮ የተወለደ የብሔር ጥያቄ (National Question) ወራሽ ነው፡፡ ኢሕአዴግ ላለፉት 27 ዓመታት እነዚህን ሁለት ውርሶች በአንድ ላይ አቀናጅቶ ለመሄድ ከፍተኛ ትኩረት ሲያደርግ እንደነበር፣ ተዋረዳዊ አስተዳደር በተቋማት አማካይነት በፖለቲካዊ ባህልና ሌሎች ሲወራረስ ቆይቷል ብለዋል፡፡ በአፄ ኃይለ ሥላሴ ጊዜ የተማከለ አስተዳደር ከባህል መድልዎ ጋር፣ ከማርክስ ሌኒኒስት አስተሳሰብ ጋርና ከፀረ ቅኝ ግዛት አስተሳሰብ ጋር አብሮ ሲዳቀል የብሔር ጥያቄ መወለዱን አስታውሰዋል፡፡

የብሔር ጥያቄ ገና ከመነሻው አብዮታዊ ጥያቄ እንደነበር፣ የኢትዮጵያን የፖለቲካ መሠረቶች አጠቃላይ ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ ጥያቄ መሆኑን፣ በቡድኖች መካከል ያለ ጥያቄ የሚገለባበጥ መሆኑን፣ ኢሕአዴግ ይኼንን ጥያቄ በታሪክ በወረሰው የአመራር ‹ሞዳሊቲ› ሊፈታው ጥረት አድርጎ እንደበር ተመራማሪው አስረድተዋል፡፡ በአንድ በኩል ለብሔር ጥያቄ ያለውን አድናቆት፣ ቀናዒነትና ክብር ሲገለጽ መቆየቱን፣ በሌላ በኩል ደግሞ በታሪክ የወረሰውን የተማከለ አስተዳደር ተግባራዊ ለማድረግ ጥረት ማድረጉን፣ ሁለቱን አብሮ አቀናጅቶ ለመቀጠል ያደረገው ጥረት ግን ፌዴሬሽኑን በተቃርኖ እንዲሞላ ትልቅ ሚና መጫወቱን  ሰሚር (ዶ/ር) አስረድተዋል፡፡

ተቃርኖዎቹ ያመጡትን ውጤት በሚመለከት ተመራማሪው እንዳስረዱት፣ ኢሕአዴግ ‹ኢንስተሩመንታሊስት› በሆነ መንገድ የብሔር መጎልበትና መካረርን ለመከላከል ያደረገው ጥረት አገሪቷ የተረጋጋች፣ ከግጭት የነፃችና የጠራች ለማድረግ ነበር፣ ግን አልተሳካም ብለዋል፡፡ ከውጭ የሚበይነውና የሚቆጣጠረው የብሔርተኝነት አስተሳሰብ ገና ከመነሻው ችግር የነበረበት አስተሳሰብ መሆኑን ገልጸው፣ ብሔር ከውጭ ሆኖ ወደ ውስጥ የሚበየን ጉዳይ አይደለም ብለዋል፡፡ በመስተጋብር የሚወለድ አስተሳሰብ ቢሆንም፣ በዋነኛነት ግን በብሔሩ ውስጥ ያሉ ሰዎች ራሳቸውን የሚረዱበት መንገድ ነው፣ ህሊናዊም (Subjective) ነው፣ አብዛኛው ጥንታዊ የነበረ አይደለም፣ አንድ ጊዜ ከተከፈተም በኋላም በኃይልና በተዋረዳዊ አስተዳደር መቆጣጠር የሚቻል ኃይልም አይደለም ሲሉ አክለዋል፡፡

ይኼንን መረዳት የተቻለው ኢሕአዴግ ባለፈባቸው 27 ዓመታት ውስጥ በተለያዩ ቦታዎች ብሔር ተኮር ግጭቶች ተንሰራፍተው መቆየታቸውን፣ ከዚያም በላይ ተቀናቃኝ ብሔሮች አድገውና ጎልብተው ኢሕአዴግን ራሱን በቅርብ ጊዜ እንዳየነው እንዲፍረከረክና እንዲሰነጣጠቅ ትልቅ ሚና ተጫውተዋል ብለዋል፡፡ አሁን ላለው ለውጥም መምጣት ትልቅ ሚና ተጫውተዋል ሲሉም አስታውቀዋል፡፡ ከዚያም በላይ አሁን ሕግ በማስከበር ጥረት ውስጥ እየገጠመ ያለው ፈተና በአንድ ወይም በሌላ መንገድ፣ ከብዙ ምክንያቶች ውስጥ አንደኛው መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ተፎካካሪ ብሔርተኞች ያበረከቱት አስተዋጽኦም ቀላል እንዳልሆነ፣ መቆጣጠርና በኃይል ማስገበር የሚባለው አስተሳሰብ በአብዛኛው ሳይሳካ እንዲቀር ትልቅ ማሳያ ሆኖ ሊጠቀስ እንደሚችልም አክለዋል፡፡ የተማከለ አስተዳደር ኢትዮጵያ ውስጥ የማይቻልበት ደረጃ ላይ እንዲደርስና ማዕከላዊ መንግሥቱም ከፍተኛ ጉዳት እንዲደርስበት ትልቅ ሚና መጫወቱንም ጠቁመዋል፡፡ በተቃራኒ የብሔር ጥያቄ ጎልብቶ፣ አድጎና ከሮ በአሁኑ ጊዜ ከብሔር ጥያቄነት ወደ ብሔር ትንግርትነት ተሸጋግሯል ብለዋል፡፡ ስለዚህ በስድሳዎቹ የተጀመረው የብሔርተኝነት ጥያቄ የብሔር ትንግርት (National Puzzle) አስተሳሰብ መሻገሩን ተመራማሪው ገልጸዋል፡፡

‹‹ብሔርተኝነትን የጀመረው ኢሕአዴግ አይደለም›› ያሉት ሰሚር (ዶ/ር)፣ ራሱ የዚያ ውልድ ወይም ውጤት ነው ብለው፣ ነገር ግን ራሱን ለማስተዳደር የሞከሩበት መንገድ በጣም የተወሳሰበ ፖለቲካ ውስጥ መግባቱንም ጠቁመዋል፡፡      

ኢሕአዴግና ተቃዋሚ ፓርቲዎች የሚያሳስባቸው ብዙ ነገሮች ቢኖሩም፣ በዋነኛነት የሚያመሳስላቸው ነገር ብሔርተኝነትን አቅልለው የማየት ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡ ኢሕአዴግ ከውኃ ልኩ አያልፍም ያለው ብሔርተኝነት ነው አድጎ ራሱ እንዲፍረከረክ ትልቅ ሚና የተጫወተው ብለው፣ አንዳንድ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ደግሞ የተፈጠረ ጉዳይ (Constructed) ስለሆነ ደምስሰው (አጥፍተው) በእሱ አመጽ ላይ ኢትዮጵያዊነትን ማሳደግ እንደሚችል እምነት እንዳላቸው ጠቁመዋል፡፡ ኢሕአዴግንና ተቃዋሚ ፓርቲዎችን አንድ የሚያደርጋቸው ‹‹አቅላይነታቸው ነው›› ብለዋል፡፡ ብሔርተኝነትን አቅልለው ያያሉ፡፡ በእሳቸው አመለካከት ብሔርተኝነት የተፈጠረ ነው፡፡ ሁሌም የነበረና ተፈጥሯዊ አይደለም፡፡ ነገር ግን ከተፈጠረ፣ ካደገና ከጎለበተ በኋላ ከግምት ውስጥ መግባት ያለበት ጉዳይ ነው ብለው፣ እሱን ሊያቅፍና ሊያስተናግድ የሚችል ሥርዓት መዘርጋት ያስፈልጋል ሲሉ ያሳስባሉ፡፡

አደገኛ ወደ ሆነ ልማድ ሊገባ ስለሚችልም መግራት እንደሚያስፈልግም  ሰሚር (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡ ስለፌዴሬሽንም ሆነ ሌላ ሥርዓት ሲታስብ የመግራት ጉዳይ አምኖ የመቀበልንና የሚካተት ጉዳይን ከግምት ውስጥ ማስገባት እንደሚያስፈልግም አክለዋል፡፡ ስለመግራት ሲታሰብ እስካሁን ብዙ የተሠራው ራስ ገዥነት (Self Rule) ላይ መሆኑንና በብዙ ተቃርኖዎች የተሞሉ እንደነበሩ ጠቁመው፣ በጋራ ገዥነት (Shared Rule) በሚባለው ላይ በመሥራት ሊቀራርቡ በሚችሉ ተቋማት ላይ ባህሎችንና እሴቶችን በማጎልበት ብሔርተኝነትን የመግራት (Disciplined) ሥራ ከመቀበል ጋር አብሮ መሥራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡ ይኼ እንዲሳካ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ትልቅ ሚና እንዳለውም አክለዋል፡፡ ከአሁን በኋላ ብሔተኝነትን መግራትም ሆነ ማስተካከል የሚቻለው በኃይል ሳይሆን፣ ዴሞክራሲያዊ በሆነ ዓውድ ውስጥ ከፍተኛ የሆነና ጥልቅ የሆኑ ውይይቶችን በማካሄድ ጭምር መሆኑን መገንዘብ እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል፡፡

የፌዴራል አስፈላጊነት ኢትዮጵያ ውስጥ ሲወራ ከተለመደው ዓውድ ትንሽ ወጣ ማለት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ ለችግር መፍትሔ የሚሆን የአገረ መንግሥት አወቃቀር ላይ ብቻ ትኩረት አድርጎ ‹‹ይሠራል? አይሠራም?›› ከሚል ጥያቄ ወጣ ብሎ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን መሠረታዊ የፖለቲካ ችግር ምንድነው ብሎ መነሳት እንደሚጠቅም፣ ኢትዮጵያ ውስጥ በርካታ ፖለቲካዊ ችግሮች ሰፍነው ቢቆዩም ችግሮቹን ወደ ሦስት ዝቅ በማድረግ ተመልክተዋቸዋል፡፡ የግለሰብ መብት ጥያቄ፣ የቡድን ጥያቄና አብሮ የመኖር ጥያቄዎች በማለት፡፡

በጣም መሠረታዊ ከሆነው በሕይወት የመኖር ጥያቄ ጀምሮ እያደገ የዴሞክራሲ፣ የሲቪክና የፖለቲካ ጥያቄዎችን ሁሉ የሚያካትት የግለሰብ መብት ጥያቄ ሲሆን ወሳኝ ጥያቄ ነው ብለዋል፡፡ የቡድን ጥያቄ ሁለተኛው ጥያቂ ሲሆን፣ መሠረታዊ ከሆነው የውክልና ጥያቄ ጀምሮ ራስ በራስ የማስተዳደር ጥያቄ (Self Administration)፣ ቋንቋን፣ ኢኮኖሚን፣ የባህልንና የፖለቲካ ጉዳይ የሚመለከት ጥያቄ እንደሆነና ኢትዮጵያ ውስጥ ለ50 እና ለ60 ዓመታት የቆየ መሆኑን ተመራማሪው ተናግረዋል፡፡ የግለሰብ መብትና የቡድን መብት እንዲከር ጥያቄ ሲነሳ የኖረ ቢሆንም፣ እንደ ኢትዮጵያዊ ደግሞ አብሮ የመኖር ሦስተኛ ጥያቄም አለ ብለዋል፡፡ በሦስቱ ጥያቄዎች መሀል አንዳንድ ጊዜ መገናኘት፣ አንዳንድ ጊዜ መለያየትና አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ተቃርኖ መኖሩንም አስረድተዋል፡፡

ፌዴራሊዝም ጥርት ባለና ኅብረ ብሔራዊ (Multi Nationalism) በሆነ መንገድ ኢትዮጵያ ውስጥ ሲተገበር ምናልባት የሚነሱ ጥያቄዎች ሲመለሱ እንደሚችሉ ጠቁመው፣ የግለሰብ ጥያቄ እንዲመለስ ግን መሥራት እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል፡፡ ታዋቂ የፖለቲካ የንድፈ ሐሳብ ሰዎች እንደሚናገሩት፣ የሊበራል አስተሳሰብ ያልሠራባቸው አገሮች ውስጥ ኅብረ ብሔራዊ ፌዴራሊዝም ሲሰፍን፣ የግለሰቦች መብት መፍለቂያ እንደሚሆንም አክለዋል፡፡ ፌዴራሊዝም ግን በራሱ የግለሰብን መብት ላይመልስ እንደሚችል፣ ትክክኛ ፌዴራሊዝም ቢሰፍንና ራስ ገዝነት ላይ ጥሩ ምላሽ ቢሰጥ በጋራ አብሮ መምጣት (Shared Rule) ግን ተጨማሪ ሥራ ካልተሠራ፣ ራስ ገዥነት አለ ስለተባለ ብቻ የአብሮነት ኢትጵያዊነት ስሜት ይለመልማል ማለት እንዳልሆነ ሰሚር (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም ፌዴራሊዝም መጥፎ ነው፣ ጥሩ ነው ሲባል ከመሠረታዊ ጥያቄዎች በመነሳት መገምገም እንደሚያስፈልግ፣ ዝም ብሎ ነጭ ነው፣ ጥቁር ነው ግን መልስ አይሆንም ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -