Thursday, March 23, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ንግድ ባንክ ለቤት መግዣ የሚውል ወለድ አልባ አገልግሎት ይፋ አደረገ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እያደገ በመጣው የወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ውስጥ፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያን በወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎቱ የመኖሪያ ቤት ባለቤት መሆን የሚችሉበትን አዲስ አገልግሎት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ይፋ አድርጓል፡፡

በውጭ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ለትውልደ ኢትዮጵያውያን የባንክ አገልግሎቶችን ማቅረብ የጀመረው ንግድ ባንክ፣ ይህ አገልግሎቱ ሙስሊሙን ማኅበረሰብ ጨምሮ ሌሎች ወለድ የሚታሰብበት አገልግሎት የማይፈልጉ ዳያስፖራዎችም እንደሚጠቀሙበት ይፋ ያደረገው ባለፈው ሳምንት ነበር፡፡

የባንኩ የጥራት ቁጥጥር ፕሬዚዳንት ወ/ሮ እመቤት መለስ አገልግሎቱን በማስመልከት በሰጡት አስተያየት፣ ‹‹ለመኖሪያ ቤት መግዣ የሚውለው ከወለድ ነፃ የዳያስፖራ የፋይናንስ አገልግሎት ከዚህ ቀደም ከቀረቡትና ዳያስፖራውን ከሚመለከቱ የባንክ አገልግሎቶች በተለየ መንገድ ይተገበራል፤›› ብለዋል፡፡

ዳያስፖራው ወዲዓ’ህ የቁጠባ ሒሳብን በመጠቀም ቢያንስ 20 በመቶውን ገንዘብ በእንግሊዝ ፓውንድ፣ በአሜሪካ ዶላር ወይም በዩሮ መቆጠብ ከቻለ፣ የፋይናንስ ጥያቄውን ለባንኩ በማቅረብ መስተናገድ እንደሚችል ባንኩ አስታውቋል፡፡

ግንባታው የተጠናቀቀ ወይም በጅምር ላይ የሚገኝ ቤት ለመግዛት የሚውለው አገልግሎት፣ በውጭ የሚኖሩ ዜጎች የመኖሪያ ቤት ችግራቸውን ለመፍታት የገንዘብ ችግር እንቅፋት እንዳይሆንባቸው ለማገዝና ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር ለዳያስፖራው የተዘጋጀ ከወለድ ነፃ አገልግሎት እንደሆነ ባንኩ ገልጿል፡፡

ለወለድ አልባው የፋይናንስ አገልግሎት የወጡትን መሥፈርቶች ያሟሉና በውጭ የሚኖሩ ዜጎች በንግድ ባንክ ቅርንጫፎች አሊያም በሚኖሩበት አገር ውስጥ በሚገኝ የኢትዮጵያ ኤምባሲ በኩል ቀርበው የወዲዓ’ህ የቁጠባ ሒሳብ ከፍተው መቆጠብ እንደሚችሉ ታውቋል፡፡ ለአገልግሎቱ የሚያስፈልገውን ቅድመ ክፍያ በአንድ ጊዜ ወይም በተለያዩ ጊዜያት በመቆጠብ መክፈል የሚችሉና ለቤት መግዣ የሚውለውን ፋይናንስ እስከ 20 ዓመት በሚደርስ የቆይታ ጊዜ ከፍለው መጨረስ የሚችሉበት አሠራር እንደተመቻቸም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አስታውቋል፡፡

ባንኩ ያቀረበውን ወለድ አልባ የዳያስፖራ የቤት መግዣ የፋይናንስ አገልግሎት በውጭ የሚኖሩ ሙስሊም ኢትዮጵያውያንና ሙስሊም ትውልድ ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ ሌሎችም በዚህ አገልግሎት መጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ መካተት እንደሚችሉ ባንኩ አስታውቋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ወለድ አልባ የባንክ አገልግሎት በአብዛኞቹ ባንኮች እየቀረበና እየተስፋፋ ሲሆን፣ በገንዘብ ተቋማቱ መካከልም የመወዳደሪያ አገልግሎት እየሆነ መምጣቱም ይነገርለታል፡፡ ባንኮች ከወለድ አልባ አገልግሎት ያሰባሰቡት የተቀማጭ ገንዘብ መጠን 30 ቢሊዮን ብር ስለመድረሱ መዘገባችን ይታወሳል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች