ክፍል ፫
በፈቃዱ በቀለ (ዶ/ር)
ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ ከሁለተኛው የኢትዮጵያና የጣሊያን ጦርነት በኋላ ሥልጣናቸውን እንደገና ሲጨብጡ አንዳንድ የግንባታ ዕርምጃዎችን ቢወስዱም፣ የተከሏቸው ኢንዱስትሪዎች በሙሉ የማደግና የመስፋፋት ባህሪ አልነበራቸውም፡፡ በዚህም ምክንያት የተነሳ በአገር አቀፍ ደረጃ ሰፋ ያለና የተወሳሰበ የውስጥ ገበያ (Home Market) ሊዳብርና ሊያድግ አልቻለም፡፡
ይህ ሁኔታ በጊዜው ብቅ ማለት የጀመረውን የኅብረተሰብ ኃይል ወደ ነጋዴነት ብቻ እንዲያዘነብል ገፋፋው። በዚህ ላይ በየቦታው የቀለጠፈና ዘመናዊ ቢሮክራሲና ሌሎች ለአገር ግንባታ የሚያገለግሉና ሕዝቡን ሊያቅፉ የሚችሉ ተቋማት ባለመገንባታቸው በየክፍለ አገሩ ያለው የሰው ጉልበትና የጥሬ ሀብቶችን በማንቀሳቀሰ ሰፋ ያለ ሕዝቡን የሚጠቅም ግንባታ ማካሄድ አልተቻለም፡፡ የየክፍለ አገሮቹም ገዥዎች የተማሩ ስላልነበሩ በራሳቸው ተነሳሽነት የኢኮኖሚ ፖሊሲዎችን በማውጣትና ትናንሽና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎችን እንዲቋቋሙ በማድረግ ለሰፊው ሕዝብ፣ በተለይም ደግሞ ለወጣቱ የሥራ መስክ መክፈት አልቻሉም። በዚህም ምክንያት የተነሳ በየቦታው በባህል ረገድ ኋላ ቀር ሁኔታ የሚታይበትና ሰፊው ሕዝብም አጋዥ ያልነበረውና በራሱ ኃይል ብቻ ጥሮ ግሮ የሚኖር ነበር። ከአውሮፓ የኅብረተሰብ አገነባብ ታሪክ የምንማረው ነገር ካፒታሊዝም ራሱን እስኪችል ድረስ አብዛኛዎች ነገሮች፣ ማለትም የከተማ ግንባታ፣ የመሠረተ ልማት መስፋፋት፣ የኢንዱስትሪዎች መቋቋምና ድጎማ ማግኘት፣ ልዩ ልዩ ተቋማትና ትምህርት ቤቶችና ዩኒቨርሲቲዎች ይስፋፉና ይገነቡ የነበረው በመንግሥት አማካይነት ነው። በዚህም ረገድ ነው ቀስ በቀስ የገበያ ኢኮኖሚ የሚባለው ነገር ሊያብብ የቻለው። ወደ አገራችን ስንመጣ አገዛዙ የሚመራበትን የኢኮኖሚ ፖሊሲ አለማወቁ ብቻ ሳይሆን፣ በምሁራን ደረጃም ለአገር በሚጠቅም ቲዎሪና ፖሊሲ ነክ ነገር ላይ ምንም ዓይነት ክርክር ስለማይደረግ በአገዛዙ ላይ ጫና ማድረግ አይቻልም ነበር። በመሆኑም ቀስ በቀስ በመንግሥት ላይ ግፊት ሊያደርግና የፖሊሲ መሻሻል እንዲኖር ትምህርት የሚሰጥ ምሁራዊ እንቅስቃሴ አልነበረም። የምዕራብ አውሮፓን የካፒታሊዝም ዕድገትና የማኅበራዊ ሁኔታዎችን መሻሻል ስንመለከት ግን ሁሉም ነገር ይፈልቁ የነበረው በምሁራን አማካይነት ነበር። በተለያዩ ቲዎሪዎችና ፖሊሲዎች ዘንድም የጦፈ ክርክር ስለሚደረግ መንግሥታት በጭፍን አንዱን ፖሊሲ ብቻ ተግባራዊ የሚያደርጉበት ሁኔታ አልነበረም። ወደ አገራችን ስንመጣ ግን በነበረው ምሁራዊ ክፍተትና ውስን የሆነ ፖሊሲ ምክንያት የተነሳ አገዛዙ ሰፋ ብሎ እንዲያስብና አብዛኛውን ሕዝብ የሚጠቅም ብሔራዊ ፖሊሲ እንዲነድፍና ተግባራዊ እንዲሆን አላስቻለውም፡፡ በዚህም ምክንያት የተነሳ በአገራችን ውስጥ ያልተስተካከለ ዕድገት መስፋፋቱ ብቻ ሳይሆን ያለንን የጥሬ ሀብትና የሰው ኃይል በሚገባ መጠቀም አልተቻለም፡፡
በሌላ ወገን ግን ይህ ዓይነቱ የዕድገት ክፍተት እያለ ከ1940ዎቹ መጨረሻ ጀምሮ መታየትና ማደግ የጀመረው በተለያዩ መልኮች የሚገለጸው ባህል ብሔራዊ ስሜታችንን እንዳዳበረውና የኢትዮጵያዊነትን ስሜት እንዳደመቀው ለማንኛችንም ግልጽ ነው። ጣሊያን ድል ከተመታና ከተባረረ በኋላ ነው በተለይም የተለያዩ ሙዚቃዎች ሊዳብሩና ሕዝቡን ሊያስተሳስሩት የቻሉት፡፡ የእነ ጥላሁን ገሠሠ፣ መሐሙድ አህመድና ብዙነሽ በቀለ ወዘተ. የመሳሰሉት ዘፋኞች የዘመናዊነት ውጤቶች ናቸው ማለት ይቻላል። የአገር ባህል ሙዚቃም ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ነው መዳበርና አገርን ማዳረስ የቻለው። በሥነ ጽሑፍ ደረጃም አያሌ ባይባልም ትችታዊ አመለካከት ያላቸው መጽሐፎች በመታተምና በመራባት ለንቃተ ህሊና መዳበር የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማድረግ ችለዋል። የቴአትር ሥራዎችም በመዳበርና በመታየት እስከተወሰነ ደረጃ ድረስ የተወሰነውን የኅብረተሰብ ክፍል ጭንቅላት ማደስ ችለዋል። እነዚህና ሌሎች ባህላዊ ነክ ፈጠራዎች፣ እንደ ምግብ የመሳሰሉት በመስፋፋትና አብዛኛው ሕዝብ እንዲመገበው ማድረግ ቀስ በቀስ ብሔራዊ ሥነ ምግባር እንዲዳብርና በመንፈስ እንድንያያዝ ሊያደርጉን በቅተዋል። ይሁንና ግን በኢኮኖሚው የውስጠ ኃይል ደካማነት የተነሳ በአገሪቱ ውስጥ አጠቃላይ የሆነ የባህል ዕምርታ ሊታይ አልቻለም። እዚያው በዚያው ይኼንን ዓይነቱን ብሔራዊ ባህል የሚቀናቀኑ ነገሮች በመፈጠራቸው ሰፋ ያለ ማኅበራዊ ቅራኔም ይታይ እንደነበር ግልጽ ነው።
ባጭሩ በጊዜው የታየው ኋላ ቀርነት 90 ከመቶ በላይ የሚቆጠረውን ሕዝብ የሚመለከት ነበር። አገዛዙ ከአማራ ብሔረሰብ የተውጣጣ ስለነበር “ለአንድ ብሔረሰብ ያደላል” የሚለው ተራ ቅዠት እንጂ ተጨባጩን ሁኔታ የሚያንፀባርቅ አልነበረም። እንዲያውም ኋላ ቀር የሚባለው ክፍል አብዛኛው የአማራው ግዛት ነበር። በዚህም ምክንያት ነው በወሎና በሰሜኑ አንዳንድ ቦታዎች በተደጋጋሚ ረሃብ ይከሰት የነበረው። በችግር ይሰቃይ የነበረው ጎንደሬው፣ ጎጃሜውም ሆነ የወሎ ሰው ሥራ ለመፈለግ ወደ ደቡቡ ክፍለ አገሮች ነበር የሚያቀናው። ይህ ዓይነቱ የጊዜውን ሁኔታ ያላገናዘበና፣ በተለይም ደግሞ ካፒታሊዝም በዓለም አቀፍ ደረጃ ሲስፋፋ የሚያመጣውን ያልተስተካከለ ዕድገት ሳያጤኑ የትግሬና ዛሬ ኦሮሚያ ተብሎ የሚጠራው በዕድገት ወደ ኋላ የቀረና ጭቆና የሰፈነበት ነበር ብሎ ማራገብ ከእውነተኛው ሁኔታ የራቀ ነበር። አፄ ኃይለ ሥላሴና አገዛዛቸው ለአማራው
ዴሞክራት ሆነው ለሌላው ደግሞ ኢዴሞክራሲያዊ አገዛዝ ሊያራምዱ የሚችሉ አልነበሩም፣ ባህሪያቸውም አይፈቅድም ነበር። በሌላ አነጋገር የዴሞክራሲና የነፃነት ዕጦት፣ ጭቆናና ኋላ ቀርነት ጠቅላላውን ሕዝብና ሁሉንም ክፍለ አገሮች የሚመለከት ነበር። ስለሆነም ነው የየካቲቱ አብዮት የፈነዳውና የመሬት ለአራሹም እስከተወሰነ ደረጃ ድረስ ተግባራዊ ሊሆን የበቃው። በጊዜው አሥራ ስምንት ወራት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ነው በአጠቃላይ ሲታይ አገሪቱን በማዳረስ ከፍተኛ የሆነ ብሔራዊ ባህሪ ያለው ሥራ የተሠራውና፣ ሕዝብን ማደራጀትና መብቱንም አውቆ አዲስ የአሠራርና የአደረጃጀት ሥልት እንዲማር ከፍተኛ ትግል የተደረገው። በጊዜው ሕዝቡም በጎሳው ሳይሆን እንደ አንድ ሕዝብ በመነሳት ነው አዲሲቱ ኢትዮጵያን ለመገንባት ከፍተኛ መስዋዕትነት የከፈለው። ይሁንና ግን ይህንን የማይፈልጉ የውስጥና የውጭ ኃይሎች አንድ ላይ በመጣመር በሕዝባችንና በአብዮቱ ላይ ዘመቻ ከፈቱባቸው። ጉግ ማንጉግን ከኢትዮጵያ ውስጥ ማስወገድ ያስፈልጋል በሚለው ቅስቀሳ የተወናበደው መሳፍንት፣ የሚሊታሪና የሲቪል ብሮክራት፣ እንዲሁም የነፃ አውጪ ድርጅቶች ነን የሚሉና ራሱም የማርክሲዝምን ሌኒንዝም ዓርማ አንግቤያለሁ የሚለው በአንድነት በመነሳትና ከአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝም ድጋፍ በማግኘት አጠቃላይ ጦርነት አወጁ። በዚህ የተወናበደውና ከሥር በሲአይኤ ይገዘገዝ የነበረው የወታደራዊ አገዛዝ ራሱም ጦርነት በማወጅ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን አለቁ። ይህ የእርስ በእርስ መተላለቅ ለወያኔና ለሻዕቢያ የፖለቲካ ክፍተት ፈጠረላቸው። ሥልጣን እንዲጨብጡና ለኢትዮጵያ ሕዝብና ለአገራችን የመቶ ዓመት የቤት ሥራ መስጠት ቻሉ። በዚህ ድርጊታቸው የብልጣ ብልጥ ሥራ የሠሩ መሰሏቸው ነበር። ያልገባቸው ነገር ቢኖር ለራሳቸውም ነው ጉድጓድ የቆፈሩትና ዛሬ ሕዝባቸውን ወደ ከፍተኛ ችግር ውስጥ የከተቱት። አንዳንድ የኦሮሞ ኤሊትም ይህንን ዓይነቱን ድርጊት እየደገመና ድንቁርናውን እያስመሰከረ ነው። እነዚህ ሁሉ ያልገባቸው ነገር ቢኖር የሚያካሄዱት ኢሳይንሳዊ ቅስቀሳና የናሽናሊዝምን ስሜት ማራገብ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ብቻ ሳይሆን በጠቅላላው ጥቁር ሕዝብ ላይም ነው ጦርነት ያወጁት። ተግባራቸውም ቆሜለታለሁ የሚሉትን ሕዝባቸውን የሚጠቅም ሳይሆን የዓረብ አገሮችንና የኢምፔሪያሊስት ኃይሎችን ነው። በዚህ ድርጊታቸውም የሥልጣኔና የዕድገት ህልማችን እንዳለ ይወድማል። ጠቅላላው ሕዝባችን ወደ ዲንጋይ ዘመን እንዲወረወር ይደረጋል። በኢትዮጵያ ምድር ውስጥ የእርስ በእርስ ጦርነት ቢከሰት አገራችንና ሕዝባችን ብቻ ሳይሆኑ የሚጠቁት የአካባቢው አገሮችም በከፍተኛ ደረጃ ይጎዳሉ። አገራችንም የግብፅ፣ የሱዳን፣ የዓረብ አገሮችና የስለላ ድርጅቶች መጫወቻ ትሆናለች። ታሪኳና ባህሏ ይወድማሉ። ይኼንን ዓይነቱን አሉታዊ ውጤት ነው ወያኔዎችና ዛሬ ጊዜው የእኔ ነው ብሎ እዚህና እዚያ የሚራወጠው አንዳንድ የኦሮሞ ኤሊት ግልጽ ሊሆንለት ያልቻለው።
በዚህ ዓይነቱ የታሪክ ወንጀል ሳይንሳዊና ፍልፍናዊ ባህሪ ሳይኖረው ዝም ብለው የኢትዮጵያዊነትን ስሜት የሚያራግቡ ኃይሎችም ተጠያቂዎች ናቸው። አብዮቱ ሊከሽፍ የቻለውና አገራችንም እዚህ ዓይነቱ ደረጃ ላይ ልትደርስ የበቃችው ለአሜሪካ ባደሩና ለሱ በሚሠሩ ኢትዮጵያውያን ኃይሎች ነው። እነዚህ ናቸው ከውስጥ ሆነው አገዛዙን በመገዝገዝ አገራችንን ራቁቷን ያስቀሯት። እነዚህ የድሮ የሠራዊቱ አባላትና አሁንም ለአሜሪካ የሚሠሩ አንዳንድ ግለሰቦች ወጣቱንና ሰፊውን ሕዝብ በማወናበድ በሌላ መልክ ደግሞ ፀረ ኢትዮጵያ ድርጊታቸውን እያጧጧፉት ይገኛሉ። እነዚህ ብቻ ሳይሆኑ ከኢትዮጵያዊነት ይልቅ አሜሪካዊነትን የሚያስቀድሙ በአርባዎቹና በሃምሳዎቹ ዓመታት ዕድሜ የሚገኙ የፖለቲካ መድረኩን በማጣበብ ኢሳይንሳዊና ፍልስፍና አልባ ቅስቀሳ በማድረግ ሕዝብን ግራ እያጋቡ ነው። በአጭሩ በፍልስፍና ላይ የተመረኮዘና ሳይንሳዊ መሠረት ያለው ትግል ስለማይካሄድ ሁሉም በተወሰኑ መፈክሮች ላይ በመሰባሰብ በተለይም ወጣቱን እያሳሳተው ነው። ይኼንን ዓይነቱን ውዥንብርና ለሥልጣን ላይ ለመውጣት የሚደረግ እሽቅድምድሞሽን መልስ ለማሲያዝና ጥራት ያለው ትግል ለማካሄድ በጣም አስቸጋሪ ነው። ማንም የሚሰማም ያለ አይመስለኝም። ሁሉም የመረጠው ዝም ብሎ መደናገርን እንጂ ጥራት ያለውንና ተከታታይ ትግልን ማካሄድ አይደለም። ጥያቄው ከእንደዚህ ዓይነቱ የተዘበራረቀና የተወናበደ ሁኔታ እንዴት መውጣት ይቻላል? የሚለው ነው። ከሁሉም በላይ ከላይ የዘረዘርኩትን በብሔረሰብ አኳያ የሚካሄደውን፣ ከሳይንስና ከፍልስፍና ውጭ የሚደረገውን ትግልና ቅስቀሳ እንዴት መግታት ይቻላል? የሚለው ነው አስቸጋሪው ጉዳይ። በእኔ እምነት የተገለጸለት ኃይል እስከሌለ ድረስ የአገራችን ጉዳይ እጅግ አስቸጋሪ ይሆናል። ስለዚህ ይህንን ሁኔታ ሊያስቀለብስ የሚያስችል ስትራቴጅ መቀየስ የሚያስፈልግ ይመስለኛል።
የብሔረሰብ ወይም የጎሳ፣ የማንነት ጥያቄና የዋና ከተማ ጉዳይ
በመሠረቱ ብሔረሰብ ወይም ደግሞ ጎሳ ሳይንሳዊ መሠረት የለውም። ጽንሰ ሐሳቦቹ ሊገለጹ የሚችሉ አንድ በጣም ውስን የሆነ ተገልሎና በሥራ ክፍፍል ያልተደራጀ ከሆነና በጣም በጠባብ አካባቢ የሚኖር የሰው ስብስብ ከሆነ ምናልባት ጎሳ ወይም ብሔረሰብ ብሎ መጥራ ይቻል ይሆናል። በሶሻል ሳይንስ እንደዚህ ዓይነቱ በባህል፣ በሥራ ክፍፍልና በሌሎች እንደ ሥዕል በመሳሰሉት. . . ወዘተ. የማይገለጽ የሰው ልጅ ያልተነጣጠለ (Undifferentiated) ተብሎ ይጠራል። እንደዚህ ዓይነቱ የሰው ልጅ ደግሞ በአሁኑ የግሎባል ካፒታሊዝም ዘመን በተወሰኑ፣ እንደ ካሜሩን በመሳሰሉ ጫካዎች ውስጥ የሚኖሩ ፒግሚዎች ተብለው በመጠራት የሚታወቁና በፓፕዋ ኖይጊዩኒዋ (Papua Neuguinea) ውስጥ ከዘመኑ ሥልጣኔ ተነጥለው ለሚኖሩ መጠሪያ ሆኖ ሊያገለግል ይችል ይሆናል። ወደ አገራችን ስንመጣ ግን ይህ ዓይነቱን ተነጥሎና በጋብቻ ሳይተሳሰሩና ሳይዋለዱ የሚኖሩ ፈልጎ ማግኘት በጣም አስቸጋሪ ነው። ይህም ማለት በአገራችን የታሪክ ሒደትና በኅብረተሰብ ግንባታ ውስጥ መሰበጣጠሮች፣ መዘዋወሮችና፣ ከአንደኛው ጎሳ መጣ የሚባለው፣ በተለያዩ ምክንያቶች የተነሳ በግለሰብም ሆነ በጥቅል የተወለደበትንና ያደገበትን አካባቢ ጥሎ የሄደው ሌላ ቦታ ሄዶ አዲስ ኑሮ ሲመሠርት በሥራ ወይም በንግድ አማካይነት ግንኙነት ይፈጥራል፣ ይጋባል፣ ይዋለዳልም፣ ይራባልም። በዚህ ምክንያት የተነሳና በአንድ አገር ውስጥ ቀስ በቀስ እያለ በሚዳብረው የሥራ ክፍፍልና ንግድ፣ እንዲህም የከተማ ግንባታና የንግድ እንቅስቃሴ አማካይነት የተነሳ አዲስ ኅብረተሰብዓዊ ግንኙነት (Social Relationship) ይፈጠራል ማለት ነው። አንደኛው አንጥረኛ፣ ሌላው ነጋዴ፣ የተወሰነው ደግሞ የፋብሪካ ሠራተኛ፣ እንዲሁ ደግሞ ሌላው የቢሮ ሠራተኛና ቢሮክራት በመሆንና፣ እንዲሁም በሌላ ሙያ በመሠልጠን ከድሮው ባህላዊ ከሚባለው አስተሳሰብ እየተላቀቀ በመምጣት አዲስ ዓይነት የፍጆታ አጠቃቀምና አነጋገርም ይለምዳል ማለት ነው፡፡ ሥነ ልቦናውም ይቀየራል ማለት ነው። በዚህ መሠረት በአንድ አገር ውስጥ በገቢ ወይም በመደብ (Income or Social Classes) የሚገለጽ የኅብረተሰብ ክፍል በመፍጠር ድሮ በጎሳ መልክ ይታይ የነበረው ግለሰብም ሆነ በጥቅል የሚጠራው እየሟሟ ይሄዳል። የለም በብሔረሰብ ብቻ የሚገለጽ ሰው ነው ያለው የሚባል ከሆነ ደግሞ እንደዚህ ዓይነቱ ግለሰብም ሆነ በጥቅል የሚጠራ ውስጣዊ ኃይል የለውም ማለት ነው። የማሰብ፣ የመፍጠር፣ መሣሪያዎችን የመሥራትና በንግድ አማካይነት የሚገለጽ ተግባርም ሊያዳብር አይችልም ማለት ነው።
ወደ ተጨባጩ የአገራችን ሁኔታ ስንመጣ ከትግራይ በስተቀር ሌሎች ዛሬም መጠሪያችን ይኼኛው ወይም ያኛው ብሔረሰብ ነው ብሎ ራሳቸውን የሚገልጹ ከሌላው ሳይጋቡ አልኖሩም ማለት ይችላል። በተለይም ከ15ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ የክርስትና ሃይማኖት ወደ ደቡብ ክፍል ሲስፋፋ ደብተራዎችና ቄሶች ለአስተማሪነት በመሄድና እዚያው በመኖር ከሌላው ጋር ተጋብተዋል፣ ተዋልደዋልም። እንደዚህም ግራኝ አህመድ ባደረሰው ዕልቂት የተነሳ ከፍተኛ ክፍተት ስለተፈጠረ ኦሮሞዎች ከአንድ ቦታ በመነሳት ተስፋፍተዋል። በአንዳንድ ቦታዎች የነበሩ ሥልጣኔዎችንና ነገሥታትን በመደምሰስ ብዙ ቦታዎችን በቁጥጥራቸው ሥር አውለዋል። ከተቀረውም ሰው ጋር በመጋባት ተዋልደዋል። ይህም ማለት ዛሬ የኦሮሞ ኤሊት ነኝ ብሎ ችግር የሚፈጥረው በሙሉ ከዚህ ወይም ከዚያኛው ብሔረሰብ ጋር ሳይጋባና ሳይዋለድ በንፁህ መልኩ የሚገኝ አይደለም። ዛሬ የፖለቲካውን ሜዳ የሚቆጣጠሩትና ያዙኝ ልቀቁኝ የሚሉት ሁሉ በአባታቸው ወይም በእናታቸው ከአማራ ወይም ከሌላው ብሔረሰብ የሚወለዱ ናቸው። ይሁንና ግን ድርቅ በማለትና የጭቆናንና የመበደልን ዓርማ በማንገብ የኦሮሞ ብሔረሰብ ተሸማቆ እንዲኖር ተደርጓል፣ ተጨቁኗል፣ በቋንቋውም እንዳይናገር ተከልክሎ ነበር ይሉናል። በዚህም መልክ የተረት ተረት በማውራት የፖለቲካ ቴአትር በመሥራት ከሳይንስና ከቴክኖሎጂ፣ እንዲሁም ለሰው ልጅ ዕድገት ከሚጠቀሙ ከባህላዊ ነገሮች እንድንርቅና ለኅብረተሰብ ዕድገት በማይጠቅሙ ነገሮች ላይ ብቻ እንዳንረባረብ እያስገደዱን ነው። ዋና ዓላማቸው ጠቅላላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በእንደዚህ ዓይነቱ ሳይንሳዊ መሠረት በሌለው ነገር ላይ በመጠመድ ደንቁሮ እንዲኖር ለማድረግ ያሰቡ ይመስላል። ተልዕኮአቸውም የአንድ የውጭ ኃይልን ዓላማ ለማሳካት ይመስላል። አገርን መበታተንና ጥሬ ሀብትን ማዘረፍ። ተጨቁነናል የሚሉ ከሆነ ደግሞ እንዴት ማማር እንደቻሉና ወደ አውሮፓና ወደ አሜሪካ በመምጣት የተንደላቀቀ ኑሮ እንደሚኖሩ ሊያስረዱን በፍፁም አይችሉም።
ለማንኛውም ካለን ማረጋገጫ ቀደም ብለው የነበሩና አሁንም በሕይወት የሚኖሩ አንዳንድ የኦሮሞ ብሔረሰብ አቀንቃኞች ሃዘል ብላት ከሚባል ለጀርመን የስለላ ድርጅት ይሠራ ከነበረና የኢትዮጵያ ጠላት ጋር የጠበቀ ግንኙነት እንደነበራቸውና በእሱም እንደሚበወዙ የተረጋገጠ ጉዳይ ነው። ሰውዬው ከሞተም በኋላ ኢትዮጵያን ለመበታተን የሚሠሩና ከአንድ ከሰሜን ጀርመን፣ ኸርማንስቡርግ ከሚባል ከተማ ካለ የፕሮቴስታንት ቤተ ክርስቲያን ማንኛውንም ዕርዳታ እንደሚያገኙ የታወቀ ጉዳይ ነው። ቄሶቹም በየጊዜው ወደ ኢትዮጵያ ይመላለሳሉ። በተለይም ባለፉት 27 ዓመታት ወያኔ ያመቸቻላቸውን ሁኔታ በመጠቀም የኦሮሞን ናሺናሊዝም ሊያግሉት ወይም ሊያሞቁት ችለዋል። በአጭሩ ታሪኩ እንደዚህ ሲሆን፣ የእነዚህ ኤሊቶች ዓላማ ቆመንለታል ለሚሉት ብሔረሰባቸው ሥልጣኔ ማምጣት ሳይሆን የአበባና የቡና ተካይ፣ እንዲሁም ለጀርመንና ለተቀረው የአውሮፓ ገበያ ልዩ ልዩ ፍራፍሬዎችን ተካይና ባርያ አድርጎ ለማስቀረት ነው ዋናው ዓላማቸው። ዓላማቸው ከዚህ ውጭ አይደለም፣ ሊሆንም አይችልም።
ወደ ማንነት ጥያቄም ስንመጣ በጣም አስቸጋሪና ግልጽ ያልሆነ ጉዳይ አለ። ማንነትን በምንድነው የምንገልጸው? ዘለዓለማዊ ወይስ ጊዜያዊ ነው? በቋንቋ፣ በባህል፣ በሥነ ልቦና፣ በምግብ፣ በአለባበስ ወይስ በሌላ ነገር የሚገለጽ? ይኼንን ጉዳይ በቀላሉ ለማስረዳት ያስቸግራል። የማንነትን ወይም የአይደንቲቲን ጥያቄ የሚያነሱ በተለይም የፋሺዝም ወይም የቀኝ ዝንባሌ ያላቸው ሰዎች ናቸው። እነዚህ ዓይነቶች በጀርመን፣ በፈረንሣይና እንዲሁም በአንዳንድ የአውሮፓ አገሮች እያደጉ የመጡና በተለይም ጥቁርን የሚጠሉ ናቸው። ዘራችን ንፁህ ስለሆነና የማሰብ ኃይላችንም ከሌላው የተሻለ ነው ብለው ስለሚያምኑ ከሌላው ጋር በመጋባት ዘራችን መበላሸት የለበትም በማለት ቅስቀሳ ያደርጋሉ፣ በአንዳንድ ቦታዎች ሰው ይደበድባሉ ወይም ይገድላሉ። ከዚህ ስንነሳ በአገራችን ምድር የማንነትን ጥያቄ የሚያነሱ በመሠረቱ ከእነዚህ ናዚዎች የሚለዩበት ነገር የለም። በሌላ ወገን ደግሞ የማንነትን ጥያቄ የሚያነሱ ከሆነ እነሱ ያልፈጠሯቸውን ነገሮች በሙሉ መጠቀም፣ መብላትና መጠጣት የለባቸውም። ይህን የሚያደርጉ ከሆነ ደግሞ ማንነታቸውን ረስተዋል ማለት ነው። ብዙም ሳያስቡ፣ ሳያወጡና ሳያወርዱ የሚናገሯቸው ነገሮች በሙሉ ችግር ከመፍጠር በስተቀር ለመፍትሔ የሚያገለግሉ አይደሉም። ስለዚህ በሳይንስ ከማይደገፍ አስተሳሰብ መላቀቅ አለባቸው። በመሠረቱ የፖለቲካ ዓላማ አለኝ የሚል ግለሰብም ሆነ ድርጅት ከሳይንስ፣ ከቲዎሪና ከፍልስፍና ውጭ ማሰብ የለበትም፡፡ ይህንን በግለሰብ ደረጃ ሊያደርግ ወይም ከጓደኛው ጋር በመሆን ሊያወራ ይችላል፡፡ በሌላ ወገን ግን እንደ መቀስቀሻና ማስተማሪያ መሣሪያ እጠቀማለሁ የሚል ከሆነ መቀጣትና መከልከል ያለበት ነው። ስለሆነም ማንኛውም በብሔረሰብ የተደራጀ የፖለቲካ ዓላማ አለኝ የሚል የግዴታ መከልከል አለበት፡፡ በመሠረቱ በብሔር ደረጃ የተደራጀ ዴሞክራት ሊሆን በፍፁም አይችልም፡፡ ሳይንስን ሊያዳብር አይችልም፣ የማኅበራዊ ጥያቄዎችንም ሊያነሳና እንደ መታገያ ሊያደርግ አይችልም። በአጭሩ በብሔረሰብ የተደራጀ ኃይል የሥልጣኔ ጠንቅ ነው፡፡ የአንድ አገር ሕዝብ እንዳይሰባሰብና በጋራ ታሪክ እንዳይሠራ የሚያግድ ነው፡፡ የተፈጥሮንና የኅብረተሰብን ሕግ የሚፃረር ነው፡፡
ወደ ዋና ከተማ ስንመጣ፣ በመሠረቱ ይህ ነገር ማወዛገብ የለበትም፣ ጉዳዩም ለውይይት መቅረብ ያለበት አይደለም፡፡ በመጀመርያ ደረጃ በአንድ ብሔረሰብ ውስጥ መንደር ካልሆነ በስተቀር ብዙ ነገሮችን ሊያሟላ የሚችል ከተማ ሊመሠረት አይችልም፡፡ በሁለተኛ ደረጃ፣ የከተማ ዕድገት እንደ ኅብረተሰብም ታሪካዊ ሒደት አለው፡፡ በመሆኑም ከተማዎች ከተለያዩ ቦታዎች የመጡ ሰዎች የሚገነቡትና ልዩ ዕምርታን (Melting Points) የሚሰጡት የታሪክ ውጤት ነው፡፡ የከተማዎችን ዕድገት ስንመለከት በተደራጁ ገዥዎች የሚመሠረቱና በሒደት እያደጉ የሚመጡና የአንድ ብሔረሰብ መለያ ሆነው ሊቀሩ የሚችሉ አይደሉም፡፡ ከተማን ከተማ የሚያሰኘው ከተለያየ ቦታ የሚመጡ ሰዎች መጥተው ሲከትሙና የራሳቸውን የባህል ማኅተም ሲያደርጉበት ነው፡፡ በዚህም የተነሳ እንደየ ሁኔታውና እንደ አገዛዞች የማሰብ ኃይል የተነሳ ልዩ ልዩ የኅብረተሰብ ኃይሎች የራሳቸውን የውስጥ ኃይል በማዳበር ከተማዎችን የፈጠራና የልዩ ልዩ ባህል መገናኛዎች ያደርጋሉ፡፡ ከዚህ ስንነሳ አዲስ አበባን የአንድ ብሔረሰብ መኖሪያ ለማድረግ የሚሞከረው ሙከራ ወይም በዲሞግራፊ የሕዝቡን ቁጥር ለመቀየር የሚደረገው ሽር ጉድና አሻጥር የአጭር ጉዞ አመለካከት ነው፡፡ አንድን ሕዝብና የከተማን ዕድገትን ማቀጨጭ ነው፡፡ የሚገርመው ጉዳይ የውጭ ኩባንያዎች ወደ አዲስ አበባ በመምጣትና መሬት በመከራየት አፓርትመንቶች በመሥራት ቅርምት ውስጥ ገብተዋል፡፡ በሌላ ወገን ደግሞ ነዋሪው ሕዝብ እንዲገፋ በመደረግ ላይ ነው፡፡ በአገራችን ምድር ዘረኝነት እየተካሄደ ነው ማለት ይቻላል፡፡
መደምደሚያ
ከላይ ከሞላ ጎደል ለማሳየት እንደሞከርኩት አንድን አገርና ኅብረተሰብ ለመመሥረት ብዙ ውጣ ውረዶችን መጓዝ እንደሚያስፈልግ ነው፡፡ በተለይም ደግሞ በኅብረተሰብና በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ንቃተ ህሊና ወይም ራስን በራስ ማግኘት ከፍተኛውን ሚና ይጫወታሉ፡፡ ከጭንቅላታችን ውጭ የምናደርገው ነገር የለም፡፡ የሰው ልጅ ዕድገት ከታቻ ወደ ላይ ቀስ በቀስ የሚጓዝ ሲሆን፣ አብዛኛውን ጊዜ በደመ ነፍስ የሚደረግ ሒደት ነው፡፡ የሰው ልጅ እንደ ጦጣ ዛፍ ላይ ከመንጠልጠል አልፍፎ አዳኝ ሆኖና አራሽ እስኪሆንና በሥራ ክፍፍልም እስኪያልፍ ድረስ ብዙ ውጣ ውረዶችን አሳልፏል፡፡ ከፍልስፍና ጋር የኋላ ኋላ ደግሞ ከተፈጥሮ ሳይንስና ከሌሎች ዕውቀቶች ጋር የተለማመዱና ጥልቅ ምርምር ማድረግ የጀመሩ ጭንቅላታቸውን ሰብሰብ አድርገው አንድን ማኅበረሰብ ሲመሠርቱ፣ እንደኛ ያለው አገር ደግሞ እስከተወሰነ ደረጃም ድረስ ታሪክ ቢኖረው በውስጣዊ ድክመት የተነሳ ከዝቅተኛው ወደ ከፍተኛው ደረጃ መሸጋገር አልቻለም፡፡ የፖለቲካ ሥልትን በማዳበርና ከውጭ የሚመጣውን በብዙ መልክ የሚገለጸውን አሳሳች ዘዴ መክቶ ለመመልስ ባለመቻል ከውስጥ በተታላይ ኃይሎች በመፈልፈል ለብሔራዊ ነፃነትና እንዲያም ሲል ለኢኮኖሚ ዕድገት ጠንቅ መሆን ተቻለ፡፡ የዚህ ዓይነቱ ክፍተት ለጥራዝ ነጠቅ ኤሊቶች አመቺ ሁኔታ ፈጠረላቸው፡፡
በኅብረተሰብ ግንባታ ውስጥ እንደተረጋገጠው ለጠንካራ ኢኮኖሚ፣ በተለይም ለሳይንስና ለቴክኖሎጂ አትኩሮ የማይሰጥ አገዛዝና ምሁር የመጨረሻ መጨረሻ አገሩን ያስበላል፡፡ ይህ አንደኛው ሲሆን፣ በመሰበጣጠርና በመበታተን የሳይንስና የቴክኖሎጂ ባለቤት መሆን አይቻልም፡፡ የአንድ ሕዝብም በተለያየ መልክ የሚገለጽ ችግር በሳይንስና በቴክኖሎጂ አማካይነት ብቻ ነው ሊፈታ የሚችለው፡፡ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ደግሞ በአገር ደረጃ ነው የሚዳብሩት እንጂ በክልል ደረጃ አይደደለም፡፡ ምክንያቱም ማንኛውም ብሔረሰብ በክልል ደረጃ የሚወሰንና አትድረሱብኝ የሚል ከሆነ የማደግና የመበልፀግ ኃይሉ እጅግ ዝቅተኛ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ወደ ድንጋይ ዘመን እንመለስ ካልተባለ በስተቀር አጠቃላይ ዕድገት ሊመጣ የሚችለው በአገር አቀፍ ደረጃ ብቻ ነው፡፡ የሐሳብ መንሸራሸር ሲኖር፣ የሰው ኃይልና ካፒታል እንዲሁም ዕቃዎች ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ መሽከርከር ሲችሉ ብቻ ነው አንድ ክልልም ሆነ አንድ አገር ሊያድግ የሚችለው፡፡ ስለሆነም እያንዳንዱ ጭንቅላቱ ውስጥ ከተከለው አጉል ጥላቻና ተንኮል፣ እንደዚሁም ቂም በቀል እስካልተላቀቀ ድረስ በማንኛውም ክልልም ሆነ በአገር ደረጃ በፍፁም ዕድገት ሊኖር አይችልም፡፡ ከዚህ ስንነሳ ምርጫችን ሁለት ነው፡፡ ወይ ሥልጣኔ፣ አሊያም የድንጋይ ወይም ደግሞ የኋላ ቀርነቱን ዘመን መምረጥ። መልካም ግንዛቤ!
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡