Monday, July 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየጠበበው የአመጋገብ ሥርዓት

የጠበበው የአመጋገብ ሥርዓት

ቀን:

የአመጋገብ ሥርዓት ሲታይ ከቀደሙ ሰዎች በተሻለ ሁኔታ የአሁን ዘመን ሰዎች በቀላሉ ሊመገቧቸው የሚችሉዋቸው ምግቦች ዓይነተ ብዙ ናቸው፡፡ በዓለም ላይ ያሉ ሕዝቦች ምናልባትም ከሉላዊነቱ ጋር በተያያም እጅግ ወደ መመሳሰል፣ ወደ ተቀራራቢና መሠረታቸው ጠባብ ወደ ሆኑ ምግቦች ላይ ሲያጋድሉ ይስተዋላል፡፡

የኢትዮጵያ ብዝኃ ሕይወት ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ፈለቀ ወልደየስ (ዶ/ር) እንደሚሉት፣ ሕዝቦች ወደተወሰኑ ምግቦች ወይም የምግብ ዓይነቶች እንዲሳቡ ከገፋፏቸው በርካታ ምክንያቶች አንዱና ዋነኛው በዓለም ዙሪያ የሚሠሩ ትልልቅ ኩባንያዎች የተወሰኑ ምግቦችን በተመሳሳይ ሁኔታ ለዓለም ሕዝቦች ማቅረባቸው ነው፡፡

በዚህ ሁኔታ የምግብ መሠረት መጥበብ በጎ ጅምር አይዳለም፡፡ ‹‹ብዝኃ ሕይወታችን፣ ምግባችን፣ ጤናችን›› በሚል መሪ ቃል ግንቦት 14 ቀን 2011 ዓ.ም. ለ18ኛ ጊዜ በተከበረው ዓለም አቀፍ የብዝኃ ሕይወት ቀን ላይ ዶ/ር ፈለቀ እንዳብራሩት፣ ጠቃሚ የአመጋገብ ሥርዓት ማጣት እንደ ስኳር በሽታ፣ ከልክ በላይ የሆነ ውፍረትና የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ላሉ በሽታዎች ይዳርጋል፡፡ ባህላዊ መድኃኒቶች ለማግኘትም አሉታዊ ተፅዕኖ ይኖረዋል፡፡

የሰው ልጅ እያጋጠመው ያለው አንዱ ፈታኝ ሁኔታ፣ ጤናማ አመጋገብ በማዳበር ቁጥሩ እየጨመረ ላለው የዓለም ሕዝብ ቀጣይነት ያለው የምግብ ሥርዓት ማቅረብ መሆኑን ገልጸው፣ ዓለም አቀፋዊ የምግብ ምርታማነት ጠቅላላ ከሕዝብ ዕድገት ጋር ሲነጻጸር ከ820 ሚሊዮን የሚበልጡ ሰዎች አሁንም ከፍተኛ የምግብ እጥረት እንዳለባቸው፣ ሌሎች ደግሞ ዝቅተኛ ጥራት ያላቸው ምግቦችን እንደሚጠቀሙ አመልክተዋል፡፡

ከዚህ አኳያ የምግብ ሥርዓታችንን እንዴት ማስፋት ወይም ወደ አዲስ ዓይነት መቀየር ይቻላል? የሚል እሳቤ እንደተያዘ፣ ለዚህም ዕውን መሆን ኢንስቲትዩቱ ማኅበረሰቡንና ባለ ድርሻ አካላትን በማሳተፍ እየሠራ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

ከምግብ መሠረት መጥበብ ባሻገር በብዝኃ ሕይወት ላይ የተከሰቱ ችግሮች አሉ፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ባለፉት 100 ዓመታት ውስጥ 90 በመቶ የሚሆኑ አገር በቀል የሰብል ዝርያዎች ከአርሶ አደሩ ማሳ ላይ መጥፋታቸው ይጠቀሳል፡፡ ከዚህም ሌላ ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ለማዳ እንስሳት ለመመናመንና ለመጥፋት አደጋዎች ተጋልጠዋል፡፡ 50 ከመቶ ያህሉ የለማዳ እንስሳት ንዑስ ዝርያዎች ከምድረ ገጽ ጠፍተዋል፡፡

ከዚህም ሌላ አገር በቀል እንዲሁም ባህላዊና አካባቢያዊ ዕውቀቶችን ጨምሮ በአንድ በተወሰነ አካባቢ የተለያዩ የምግብ ምርታማነት ሥርዓቶች በመመናመን ላይ ናቸው፡፡ በዚህም ምክንያት የግብርና ብዝኃ ሕይወት፣ ባህላዊ መድኃኒትና ምግቦች እንዲሁም አስፈላጊ ዕውቀቶች እየጠፉ መሆኑንም ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡

ከፍተኛ አልኮል መጠጥ፣ አደንዛዥ ዕፅና ትንባሆ ከሚያስከትሉት ችግሮች በተጨማሪ ጤናማ ያልሆነ አመጋገብ ለበሽታ ምክንያት እየሆነ ነው፡፡ አገር በቀል የሰብል ዝርያዎቹ ሊጠፉ የቻሉት አረንጓዴ አብዮት በተባለው መርህ መሠረት ምግብን ለዓለም ሕዝብ በበቂ ሁኔታ ለማቅረብ ሲባል በተወሰኑና በተሻሻሉ ዝርያዎች ላይ በትኩረት በመሠራቱና አገር በቀል ዝርያዎች ምርታማ አይደሉም በሚል የተሳሳተ አመለካከት የተነሳ ለዝርያዎቹ ትኩረት በመነፈጉ ነው፤›› ብለዋል፡፡

በመጥፋት አደጋ ላይ ያሉትና ከምድር ከጠፉት ለማዳ እንስሳት መካከል አብዛኞቹ በቀጥታ ለሰው ልጅ ምግብነት የሚውሉ ሲሆን፣ ከማይውሉት ደግሞ የሰው ልጅ ለምግብነት ለሚያውላቸው እንስሳት በምግብነት የሚያገለግሉ መሆናቸውን ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ጠቅሰዋል፡፡

በአገር ውስጥ ለመጥፋት ወይም ለመመናመን የተቃረቡ የሰብል ዝርያዎች አጠባበቅ ምን ይመስላል ተብሎ ከሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄ ዶ/ር ፈለቀ ሲመልሱ፣ ‹‹በኢንስቲትዩቱ ጂን ባንክ ውስጥ ከ80,000 በላይ የአዝርዕትና የአትክልትና ፍራፍሬ ዝርያዎች በናሙና ደረጃ አሉ፤›› ብለዋል፡፡

ዝርያዎቹን ዝም ብሎ ማስቀመጥ ብቻ ከሆነ በሕይወት የመቆየት ዕድል ላይኖራቸው እንደሚችል፣ በሕይወት የመቆየት ዕድል እንዲኖራቸው ለማድረግ የዕድሳት ሥራ ማለትም እንደገና እንደሚዘሩ፣ መጠናቸውንም የማብዛትና የማሠራጨት ተግባር ይከናወናል፡፡

የየአካባቢው ማኅበረሰቦች ልዩ የሆኑ ዝርያዎች እንዳይጠፉባቸው የማኅበረሰብ የዘር ባንኮች ከ24 በላይ በሆኑ የአገሪቱ ክፍሎች ተቋቁመዋል፡፡ በዚህም የየራሳቸውን ዝርያዎች በመግዛት በባንኮቹ እንዲቀመጥ የሚደረግ ሲሆን፣ የዘር ወቅት ሲደርስ በብድር መልክ ዘሮቹን ወስደው በማሳቸው ላይ ያለማሉ፣ ዘሩ ሲደርስ ይመልሳሉ፣ ይህም ሊጠፉ የተቃረቡ የሰብል ዝርያዎችን ለመጠበቅ አስችሏል፡፡

ከዚህም ሌላ የፎገራ ከብት፣ የሐበሻ ዶሮና በግ ዝርያዎች መካከል በርካታዎች ለመጥፋት የተቃረቡ መሆናቸውን ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ጠቁመው፣ ከአካባቢው ኅብረተሰብ ጋር በመተባበር የተጠቀሱትን እንስሳት ከጥፋት ለመታደግ የሚያስችል ሥራ በመከናወን ላይ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በሐረሪ አካባቢ ከሰው አምልጠው ጫካ የገቡ የፈረስ ዝርያዎች እን
ዳሉና ልዩ ባህሪም እንዳመጡ፣ ልዩ ጀኒተካዊ ይዘትም እንዳላቸው፣ የሰው ቁጥር እየጨመረ መሄድና በአንጻሩ ደግሞ እንስሳት በል የሆኑ የዱር እንስሳት ፈረሶቹን ማጥቃት በመጀመራቸው ቁጥራቸው እንደተመናመነ ነው፡፡

የዘንድሮ ዓለም አቀፍ የብዝኃ ሕይወት ቀን ብዝኃ ሕይወት ለምግብና ጤና መሠረት መሆኑን እንዲሁም የምግብ ሥርዓት ለመቀየርና የሰው ልጅ ጤናን ለማሻሻል የሚረዳ የተፈጥሮ ሀብት እንደሆነ በማሳወቅ ላይ ያተኮረ ሲሆን የበዓሉ ዋና ዓላማም የምግብ ሥርዓትና ጤና በብዝኃ ሕይወትና ጤናማ ሥርዓተ ምህዳር ላይ ጥገኛ በመሆኑ ግንዛቤ እንዲኖር ያለመ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ብዝኃ ሕይወት ኢንስቲትዩት የተቋቋመው በ1968 ዓ.ም. በኢትዮጵያና በጀርመን መንግሥት የትብብር ስምምነት መሠረት የዕፀዋት ጄኔቲክ ሁብት ማዕከል በሚል ስያሜ፣ ኢትዮጵያ በ1986 ዓ.ም. 54ኛዋ አገር ሆና የዓለም አቀፍ የብዝኃ ሕይወት ስምምነት ስትፈርም ይህን ለማስፈጸም ይቻል ዘንድ በዕፀዋት ላይ ብቻ ሲሠራ የቆየውን የዕፅዋት ጀነቲክ ሀብት ማዕከል የእንስሳትና የደቂቀ አካላት እንዲጨምር ተደርጎ ሕይወታዊ ሀብት ጥበቃና ምርምር ኢንቲትዩት በሚል በአዲስ መልክ እንዲቋቋም ተደርጓል፡፡ በ1996 ዓ.ም. በአዲስ መልክ ጥበቃ ላይ እንዲያተኩር ታስቦ የብዝኃ ሕይወት ጥበቃ ኢንስቲትዩት በሚል ስያሜ መቋቋሙ ይታወቃል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...