ሴቶች በሥልጣን፣ በነፃነትና በመወከል ከወንዶች እኩል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያስችላል የተባለና ለቀጣዮቹ አምስት ዓመታት የሚተገበር ‹‹ሴቶች ልጆች እኩል እንዲታዩ›› ዘመቻ ይፋ ሆነ፡፡
ከዚህ ቀደም አንድ የኔፓል ቤተሰቦች ለምን ሴት ልጃቸውን ትምህርት ቤት እንዳልላኩ ሲጠየቁ፣ ‹‹ሴት ስለሆነች›› ብለው በመመለሳቸው፣ ‹‹ሴት ስለሆንኩ›› (Because I am a girl) በሚል ለአምስት ዓመታት ሴቶችን በትምህርት ለማብቃት በሚሠራባቸው 90 አገሮች ውስጥ ዘመቻ ሲያካሂድ የቆየው ፕላን ኢንተርናሽናል፤ ሴቶች በሥልጣን፣ በውክልናና በፈለጉበት አካባቢና የሥራ ቦታ በነፃነትና ሳይሸማቀቁ የመኖር፣ የመናገርና የመንቀሳቀስ መብታቸው እንዲከበር የሚያስችለውን ‹‹ሴቶች ልጆች እኩል እንዲታዩ›› (Girls get Equal) የተባለውን ዘመቻ በይፋ አስጀምሯል፡፡
የዘመቻውን መጀመር አስመልክቶ በሒልተን አዲስ አበባ ረቡዕ ግንቦት 14 ቀን 2011 ዓ.ም. በተዘጋጀው መድረክ የተገኙት የፕላን ኢንተርናሽናል ዋና ዳይሬክተር ብሪጅት አልበርስትሰን እንዳሉት፣ ሴቶች ልጆች እኩል እንዲታዩ በሚል የተጀመረው ዘመቻ፣ በዓለም በሴቶች በመመራት ትልቁ ዘመቻ ነው፡፡
ከአምስት ዓመት በፊት በኒውዮርክ በተካሄደ የመሪዎች ስብሰባ፣ ሴቶች በሥልጣን እኩል እንዲወከሉ፣ ውሳኔ በመስጠት እንዲሳተፉና ነፃነታቸው ተከብሮ እንዲኖሩ ለማስቻል መሪዎች ቃል መግባታቸውን ያስታወሱት ዳይሬክተሯ ብሪጅት፣ አሁን ባለው አካሄድ ይህ ሁኔታ በቅርብ ዓመታት የሚሳካ ስለማይመስል፣ ፕላን ኢንተርናሽናል ዘመቻውን ታዳጊ ልጃገረዶችን ከማብቃት ጀምሮ ለማካሄድ መነሳቱን ተናግረዋል፡፡
‹‹በዛሬው ዕለት [ስብሰባው በተካሄደበት] 200 ሺሕ ሴቶች ይወለዳሉ፣ እነዚህን ሴቶች ከወንዶች እኩል ለማብቃት አሁን ባለው ፍጥነት ከተሠራ 100 ዓመት ይፈጃል›› ያሉት ብሪጅት፣ በኢትዮጵያ ካቢኔ የሴቶች ውክልና 50 በመቶ፣ በሌሎች የመንግሥት ሥልጣንም በኃላፊነት እየመጡ መሆኑ፤ በኢትዮጵያ ሴት ልጆትን ከታች ጀምሮ ለማብቃትና ከወንዶች እኩል ሆነው አገራቸውን እንዲያገለግሉ ለማስቻል መልካም አጋጣሚ መሆኑንና ፕላን ኢንተርናሽናል የጀመረውን ዘመቻ ለማስፈጸምም ዕድል እንደሚፈጥር አክለዋል፡፡
ሴቶች የመምራት ዕድል እንዲያገኙ መንገድ ማመቻቸት፣ በየቀኑ ከፆታ ጋር ተያይዞ የሚገጥሙ ችግሮችን ለመፍታትና ለሴቶች ፍትሐዊ፣ የተሻለና ሁሉን እኩል የሚያይ ዓለም ለመፍጠር ዘመቻው እንደሚያግዝ በመግለጽም፣ ሴቶች እኩል እስኪታዩና እስኪደመጡ ድረስ ዓለም ልትረጋጋ፣ ሰላሟ ሊረጋገጥና ለሁሉም እኩል ልትሆን እንደማትችልም ተናግረዋል፡፡
በሴቶች ሕፃናትና ወጣቶች ሚኒስቴር የሴቶች ግንዛቤና ተሳትፎ ማስፋፊያ ዳይሬክተር አቶ ስለሺ ታደሰ በበኩላቸው፣ መንግሥት የሴቶችን የፖለቲካ ውክልና እያሳደገ መሆኑና ‹‹ጀግኒት›› የተባለው ሴቶችን የማብቃት ዘመቻ ከዓመት በፊት መጀመሩም የኢትዮጵያ ሴቶችን የወደፊት ሕይወት ብሩህ ያደርገዋል ብለዋል፡፡
‹‹ሴቶች እኩል እንዲታዩ›› የተባለው ዘመቻ ማኅበረሰብ አቀፍ ለውጥ ለማምጣት የሚያስችል ሲሆን፣ ዓላማውም ልጃገረዶችና ሴቶች የሚኖሩበትን አካባቢና ራሳቸውን በተመለከተ ራሳቸው እንዲወስኑ ማስቻል ነው፡፡ በተቀናጀ መልኩ የሚካሄደው ዘመቻም፣ የመወትወት፣ የፖሊሲ፣ የጥናት፣ የገቢ ማሰባሰብ የትብብርና የተግባቦት ሥራ ይኖረዋል፡፡
የሕፃናት ጋብቻ፣ አለመማር፣ አፍላ እርግዝናና የመንገድ ላይ ትንኮሳ እንዲቀር፣ ማኅበረሰቡ ወንዶችም ሆኑ ሴቶች ትክክል ነው ብለው የተቀበሉት ሆኖም ሴቶችን ወደኋላ ያስቀሩ ልማዶች እንዲቀየሩ፣ ቀሴች እንዳይገለሉ፣ በቤት ውስጥና በመንገድ ላይ የሚገጥማቸው ጫና እንዲቀልላቸው የሚያግዝም ነው፡፡
ዘመቻው በአንድ አጀንዳ ላይ ብቻ ያተኮረ ሳይሆን፣ ሴቶች ለራሳቸው ራሳቸው እንዲወስኑ ማለትም ሥልጣን እንዲያገኙ፣ እንዲናገሩ፣ ውሳኔ እንዲሰጡና እንዲመሩ ማስቻልም ነው፡፡
ከዚህ ቀደም የነበረው ‹‹ሴት ስለሆንኩ›› ዘመቻ ዋና ትኩረቱ ሴቶችን ማስተማር ላይ የነበረ ሲሆን፣ ‹‹ሴት ልጆች እኩል እንዲታዩ›› የሚያተኩረው ሴቶች እኩል ሥልጣን፣ እኩል ነፃነት፣ እኩል ውክልና የሚያገኙበት ላይ ነው፡፡
በሴቶች በሚመራውና ልጃገረዶች፣ ሴቶች፣ ወጣቶች ወንዶች የሚሳተፉበት ይህ ዘመቻ ማኅበረሰብ አቀፍ ለውጥ ያመጣል ተብሎ ታምኖበታል፡፡