Thursday, November 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልብዝኃነት ያላጎለበተው አገራዊ መድረክ

ብዝኃነት ያላጎለበተው አገራዊ መድረክ

ቀን:

በስመ ጥሩ ደራሲ ሐዲስ ዓለማየሁ የተሰየመው በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የሚገኘው የባህል ማዕከል ከተቋቋመ ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ አማተር ከያንያንና ጸሐፊያንን ማበረታታት፣ በባህል ዘርፍ ጥናትና ምርምር በማድረግ ለባህል ጥበቃና ልማት ጉልህ አስተዋጽኦ ማበርከት የተቋቋመባቸው ዋና ዓላማዎች ናቸው፡፡

ተልዕኮውን ለመወጣት እንዲያመቸውም የኪነ ጥበብ፣ የባህላዊና ዘመናዊ ሙዚቃ፣ የቲያትር፣ የግዕዝ ጥናት፣ የሥነ ጽሑፍ፣ የባህል ጉዳዮች እንዲሁም የቤተ መዛግብት ቡድን አቋቁሟል፡፡ የባህል ማዕከሉ ከተቋቋመበት 2004 ዓ.ም. ጀምሮም በየዓመቱ የተለያዩ ጥናትና ምርምሮች ቀርበው ውይይት የሚደረግባቸውን መድረኮች ሲያዘጋጅ ቆይቷል፡፡

ዘንድሮ ለሰባተኛ ጊዜ የተዘጋጀው ዓመታዊ ዓውደ ጥናት ‹‹የጋራ ባህላዊ እሴት ለጠንካራ አገራዊ አንድነት›› በሚል መርህ ነበር፡፡ በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ግንቦት 10 እና 11 ቀን 2011 ዓ.ም. በተዘጋጀው መድረክ የተለያዩ ጽሑፎች ቀርበዋል፡፡

ከቀረቡት ጥናቶች መካከል የኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበር ፕሬዚዳንትና የዘመን መጽሔት ዋና አዘጋጅ በአቶ አበረ አዳሙ ‹‹ኪነ ጥበባት ለትውልድ ቀረፃ የነበራቸውና ሊኖራቸው የሚገባው ንዑድ ሚና›› የተሰኘው አንዱ ነው፡፡

‹‹ኪነ ጥበብ ጨው ነው፣ ኪነ ጥበብ የሌለበት ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊም ሆነ ማኅበራዊ ጉዳይ ይቸካል፤›› የሚሉት አቶ አበረ፣ ኪነ ጥበብ የዓለም ማጣፈጫ መሆኗን በጽሑፋቸው አሳይተዋል፡፡ ኪነ ጥበብ የአገርን ገጽታ በማጠልሸት ወይም በመገንባት ረገድ ትልቅ ሚና እንዳላትም ‹‹አሜሪካ ታላቅ መሆኗን በእያንዳንዱ ሰው ልብ ውስጥ መቅረፅ የቻለችው በኪነ ጥበብ በአማካይነት ነው፡፡ ከአሜሪካ የፊልም ኢንዱስትሪ ሆሊውድ የሚወጡ የፊልም ሥራዎች ዓለምን በእጅጉ ይማርካሉ፤›› በማለት ይገልጻሉ፡፡ ጠንካራው ሆሊውድ አሜሪካ የመንግሥተ ሰማያት ያህል በሰው ልብ ውስጥ ግዝፈት እንዲኖራት ኪነ ጥበብን እንደ መሣሪያ ተጠቅሟል፡፡

ኪነ ጥበብ የአገርን ገጽታ ከመገንባት ባለፈ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳዋ የጎላ ነው፡፡ ለአንድ ተዋናይ በፊልም ሚሊዮኖችን የሚከፍለው ሆሊውድ ዓመታዊ ገቢው ምን ያህል ሊሆን እንደሚችል መገመት ቀላል ነው፡፡ ኢኮኖሚ በምን ያህል መጠን ሊደግፍ እንደሚችልም ግልጽ ነው፡፡ የሙዚቃ ኢንዱስትሪውም እንደዚሁ ጠንካራ ገቢ የሚያስገኝለት መሆኑን እሙን ነው፡፡ ከኪነ ጥበብ ዘርፍ ጠንካራ ገቢ ከሚሰበሰቡ አገሮች ተርታ ህንድም ትጠቀሳለች፡፡ የሆሊውድን ያህል ባይሆንም ጠንካራው ቦሊውድ ህንድ እንድትታወቅ ረድቷታል፡፡ በርካቶች ከህንድ ፊልምና ሙዚቃዎች የተዋወቁት በቦሊውድ ነው፡፡

ከዚህም ባሻገር ኪነ ጥበብ ትውልድ የአንድነትና የአገር ፍቅር ስሜት እንዲኖረው ላቅ ያለ ፋይዳ አላት፡፡ አቶ አበረም ‹‹ትውልዱ በአገር ፍቅር፣ በሰላም፣ በአንድነትና በመተሳሰብ ተከባብሮ እንዲኖር ለማድረግ ኪነ ጥበባት የማይተካ ሚና አላቸው፤›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡ አቶ አበረ የዘፈን ግጥሞችን፣ መጻሕፍትን፣ ፊልሞችንና ተውኔቶችን ማዕከል ያደረገም ትንተና ሰጥተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበር ዋና ጸሐፊና የወሎ ዩኒቨርሲቲ መምህር በአቶ በአካል ንጉሤ ‹‹አርአያ ደምሳሽነትና ልማድ አፍራሽነት በድህረ 83 የአማርኛ ልቦለዶች ውስጥ›› በሚል ጥናታቸው በቡርቃው ዝምታና በሚክሎል የመቻል ሚዛን እንደ ማሳያ በተሰኙ መጻሕፍት የታዘቡትን አብራርተዋል፡፡

በጥናታቸው ከ1983 ዓ.ም. ወዲህ የተጻፉ የኢትዮጵያ ልቦለዶች ውስጥ አርአያ ደምሳሽነትና ልማድ አፍራሽነት ምን መልክ እንዳለው ሁለቱን መጻሕፍት ተንተርሰው ተንትነዋል፡፡ በተስፋዬ ገብረአብ የተደረሰውና በ1992 ዓ.ም. ለንባብ በበቃው የቡርቃው ዝምታ እንዲሁም በሥዩም ገብረሕይወት የተደረሰው በ1995 ለንባብ በበቃው ሚክሎል የመቻል ሚዛን መጽሐፍ ላይ አጥኚው አርአያ ደምሳሽነትና ልማድ አፍራሽነት በስፋት መቀንቀኑን ያስረዳሉ፡፡

በተለይም የቡርቃ ዝምታ የአገርና የአብሮነት ምልክት የሆኑ አርአያዎች እሴታቸውን እንዲያጡ ከመስበኩም በላይ አብሮነትና አገራዊ ታላቅነትን በመነጠል አፍራሽ ታሪክ ሚዛን የደፋበት ነው ብለዋል፡፡ በሚክሎል የመቻል ሚዛንም ጎታች ልምዶች ተተኳሪ ሲሆኑ፣ ወደፊት ለመራመድና ለውጥን ለማምጣት እንደ መስፈንጠሪያነት መቅረቡም በጥናቱ ታይቷል፡፡ መጻሕፍቱ የአርአያ ደምሳሽነትና ልማድ አፍራሽነት ማራመድ ከመሆን አልፈው በታሪክ ሒደት ውስጥ ያጋጠሙ የአርአያ ደምሳሽነትና ልማድ አፍራሽነት መዘገቢያ በመሆንም እንዳገለገሉ ጥናቱ አረጋግጧል፡፡ የሥነ ጽሑፍ ሥራዎች አገራዊ እሴቶች በመጠበቅ አገራዊ አንድነት ለማስጠበቅ ሊኖራቸው ስለሚገባ ሚናም አቶ በአካል በጥናታቸው ዝርዝር ጉዳይ አቅርበዋል፡፡

ኢትዮጵያዊ አንድነት፣ ዘረኝነት፣ ሥነ ጽሑፍና ሙስናን በተመለከተ የአዲስ አበባ ውሾች በተሰኘው ልቦለድ ላይ የሚንፀባረቀውን ማኅበራዊ ሂስ ያስተዋሉትን አቶ የሸዋስ ዓለሙም ዝርዝር ጥናት አቅርበዋል፡፡ በወልዲያ ዩኒቨርሲቲ፣ በማኅበራዊ ትምህርት ክፍል የሥነ ጽሑፍ ፎክሎር መምህሩ አቶ የሽዋሽ፣ የዳንኤል ክብረት ሥራ የሆነውን መጽሐፍ ኢትዮጵያዊነት፣ ዘረኝነትና ሙስናን ለመመርመር በሚያመች መልኩ በኪናዊ ውበት የተቀናበረ ድርሰት በመሆኑ በጥናቱ ተመራጭ ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡

ማኅበራዊ ሒስ በተሰኘው የሥነ ጽሑፍ ንድፈ ሐሳብ የተቃኘው ጥናቱ፣ በፖለቲካ ተቋማት፣ በሃይማኖት ተቋማት፣ በነጋዴው ኅብረተሰብ፣ በፍትሕ ተቋማትና በምሁራን ዘንድ የሚታዩ እንደ ዘረኝነት፣ ሙስናና አድኃሪነት ያሉ ምግባር ብልሹነት የዜጎችን ሰብዓዊነት መንጠፍ፣ ለቀቢፀ ተስፋና ባይተዋርነት እንዲሁም ኢትዮጵያን ለድቀት ያጋለጡ መሆናቸውን ይተቻሉ፡፡

በመድረኩ ሌሎችም ጥናቶች ለውይይት ቀርበዋል፡፡ ‹‹የጋራ ባህላዊ እሴት ለጠንካራ አገራዊ አንድነት›› በሚል መርህ በተዘጋጀው በዚህ መድረክ ላይ ግን የተለያዩ የአገሪቱን ክፍሎች የሚወክሉና በጉዳዩም የተለየ ሐሳብ ሊያነሱ የሚችሉ የሰዎች ስብጥር ያልታየበት መሆኑን ሪፖርተር ታዝቧል፡፡ አገራዊ አንድነት ለመፍጠር በወቅታዊ የአገሪቱ ሁኔታ ላይ ትንታኔዎችን የሚሰጡ የፖለቲካ አዋቂዎችም የተወከሉበት አይመስልም፡፡ ጥናት አቅራቢዎቹ ከታዳሚው ሲወረወሩላቸው ለነበሩ ፖለቲካዊ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት ሲቸገሩም ታይቷል፡፡ አገራዊ አንድነት ለመፍጠር በተዘጋጀው በዚህ መድረክ ጥናት ያቀረቡ አንዳንድ ምሁራንም በጎጠኝነት ሊያስፈርጃቸው የሚችሉ ሐሳቦችን ያንፀባርቁ እንደነበርም ታይቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...