ሰላም! ሰላም! እነሆ በሎጂክ ማሰብ አቁመን በሎጎ መባዘናችንን ቀጥለናል። ቡድን የምንወደው ግን ለምን ይሆን? ኳስ እንጂ ሐሳብ የቡድን ሥራ ይፈልጋል እንዴ? እኔ እኮ ግራ ገባኝ እናንተ? ‹‹ቢረታ ሚስቱን ገብቶ መታ፤›› አሉኝ ባሻዬ፡፡ ‹‹ማን ነው እሱ?›› ስላቸው፣ ‹‹ማንነቱ ምን ይሠራልሃል? ዝም ብለህ ከምሳሌው ተማር። ምነው አንተም በማንነት ስም የሚቀነቀን እኔነት አለብህ?›› ብለው ቆጣ አሉ። እኔነት የሰው ልጆች ሁሉ ደካማ ጎን እንደሆነ እያወቁ ባሻዬ ራሳቸው አንዱ የሎጂክ ፀር ሲሆኑ ሳይ ተስፋ ቆረጥኩ። መቼም ዘንድሮ ተስፋ ቆርጦ ተስፋ የሚያስቆርጠን በዝቷል። ቆይ ለምን ብቻቸውን አይቆርጡም? ለምን ሌላውን ጭምር ከእንጀራ ገመዱና ከመኖር ስስቱ ጋር ያቆራርጡታል? እንጃ ዘንድሮስ። ‹ኮሜንት› በቡድን፣ ‹ላይክ› በቡድን፣ ‹ብሎክና ኢግኖርም› በቡድን ሆኗል። ከሁሉ ከሁሉ ግን የሚገርመኝ እያንዳንዷ ጥቃቅን ነገር ሳትቀር እንደ ‹ሳውንድ› ትራክ ፖለቲካዊ አጀንዳ መያዟ ነው። ያውም በመንጋ ፖለቲካ ተቀፍድዳ፡፡
ምን ልበላችሁ በቃ አንዲት እርግብ ከትናንት ወዲያ ተመርቆ በተከፈተው የእከሌ ሕንፃ መስታወት ጋር ተጋጭታ ሕይወቷ አለፈ ሲባል፣ አንዱ ይመጣና፣ ‹‹የሰው አልበቃ ብሏችሁ ደግሞ ምንም የማያውቁትን እንስሳት መግደል ጀመራችሁ?›› ብሎ ኮሜንት ይሰጣል። ያዝ እንግዲህ ይባልልኛል። አንዱ በቀደደው መንቆርቆር ነው። ግር ብለን እንነዳዳለን። የእከሌ ትርፍ አንጀት ፈንድቶ ወደ ሕክምና ጣቢያ ሳይደርስ ሕይወቱ አለፈ ሲባል፣ 28 ዓመት ሙሉ ገዝታችሁ አንድ እንኳ በአቅራቢያችን በፍጥነት የምንደርስበት ሆስፒታል የለም ብሎ አንድ መጀመር ብቻ ነው የሚጠበቅበት። ሌሎቻችን መግተልተል ነው። ደላላው አንበርብር ምንተስኖት ሎጂክ ትተን በሎጎ ማሰብ ጀምረናል አለ ቢባል፣ ለምሳሌ ስንት ምሁር ባለባት አገር በመኃይም ደላላ እንመከር ማለት ብቻ ነው የሚጠበቅባችሁ። ሎጎ ይኑራችሁ እንጂ ተከታዩ ሺሕ ነው!
እናላችሁ የሰሞኑ መብራት መጥፋትና ዝናብ መምጣት ላይ ተደርቦ ይኼ በተነዱበት መነዳትና ያለ ምክንያት ማሰብ በየአቅጣጫው ሲወረኝ፣ እውነቴን ነው የምላችሁ ነገር ሁሉ ይሰለቸኝ ጀምሯል። ለምን የሚሉት ጥያቄ ጠፍቷል፣ ተሰዶብናል። የት? እንዴት? መቼ? ቀብረናቸዋል። አስቡት እስኪ እንደ ደንባራ በቅሎ ቃጭል አንጠልጥሎ ስንሆን። እናማ ተማርኩ አወቅኩ የሚለው ደግሞ ባሰ። በቀደም ከምሁሩ የባሻዬ ልጅ ጋር ቁጭ ብለን አንድ ካፌ ውስጥ ዝናብ እንጠለላለን። አንዱ ድንገት ደርሶ፣ ‹‹ሰው አለው?›› አለን። ወንበሩን መሆኑ ነው። ‹‹የለውም ውሰደው፤›› አለው የባሻዬ ልጅ፡፡ ከዚያ ገና ሳይቀመጥ፣ ‹‹ለነገሩ ዘንድሮ እንኳን ወንበሩ መንበሩስ ምን ሰው አለው ብላችሁ ነው?›› ብሎ ጀመረላችኋ። እንኳን ይህችን የዝንብ ጠንጋራ ቀርቶ የዝንብ ወፈፌም እናውቃለን አልኩና በልቤ፣ ‹‹ቢል ታመጣልን?›› አልኩት አስተናጋጁን። ‹‹ዝናቡ ያባራ እንጂ ቆይ . . .›› ሲለኝ የባሻዬ ልጅ ያ ነገረኛ አሁንም ሳይፈቀድለት፣ ‹‹አዬ እንጃ የዘንድሮ ዝናብስ እንዳያያዙ ከሆነ የሚያባራ አይመስለኝም፤›› ብሎ ብቻውን ሳቀ። አሳሳቁ ታዲያ ቲፎዞ ፍለጋ ስለሚመስል ነገረ ሥራው አላማረኝም፡፡
‹‹ሰው ብርቱ ነው በጎርፍ ውስጥ አረማመድ ያሳምራል፤›› ያለው ገጣሚ ስንኝ ትዝ ብሎኝ ፈገግ ስል ለእሱ የሳቅኩለት መስሎት፣ ‹‹እኔ ምለው ግድ የለም ዛሬ እኔ ልጋብዛችሁ፤›› አለን። ይኼውላችሁ እንግዲህ ገና ለገና ጥርስ ለጥርስ ተለካካን ብለን፣ በአጋጣሚምም በስህተትም ብርጭቋችን ተጋጨ ተብሎ እዚህ ደረጃ ደርሰናል። ፆታዊ ጥቃት ያደረሰ ብቻ ይመስላችኋል አይደል ደፋሪ? የክብር፣ የሐሳብ ነፃነት ተጋፊ፣ የልዩነት ፀሮችም እኮ ከዚያ በላይ ናቸው። የሰውዬውን ሁኔታ መልሼ መላልሼ ሳስበው ስለተበሳጨሁ፣ ‹‹እቸኩላለሁ . . .›› ብዬ በዚያ ዶፍ ውስጥ መሮጥ ጀመርኩ። ለወትሮው ዶፍ ነበር የምንጠለለው። ይኼውላችሁ ዘንድሮ ከሰው መጠለል ጀምረናል። ምን ይደረግ ታዲያ!
መቼስ አንዳንዴ ስሜታዊ እየሆንኩ ጨዋታዬ እንደ ዘመኑ ተቃዋሚዎችና ደጋፊዎች ድርቅ ይላል አይደል። ምንላድርግ ቀልድ ጠፋ። ማለቴ ቀልዱ ሁሉ ያው እንደምታዩት የምር የምኖረው ኑሮ ሆኗል። ቀልድ አሯሯጫችን መሆኑ ቀርቷል። እንደ ሳይንስ ፊክሽን ማለቴ ነው። የዛሬን አያድርገውና በቀደሙት ዘመናት አሁን በእጃችን የጨበጥናቸው ኪሳችን የከተትናቸው፣ ቆፍረን የቀበርናቸው ቴክኖሎጂዎችና የጦር መሣሪያዎች ትናንት ተረት ተረት ነበሩ። ቀልድና ሳይንስ ፊክሽን የሚያመሳስላቸው ይኼው ነው። ትናንት ቀልድና ስላቅ እንደ ዛሬው እያንዳንዳችን የሚያጋጥመን የምኖረው ሀቅ አልነበረም። በአብዛኛው ነው የምላችሁ። ዘመኑ የመረጃና የማስረጃ ነውና ማስረጃዬን ላቅርብ። በቀደም አንድ ቪላ ቤት እያሻሻጥኩ ነበር። የማሻሽጠው ቤት የነበረበት አካባቢ አንድ ቡቲክ ሞቅ አድርጎ በሁለት ሞንታርቦ ሙዚቃ ከፍቷል። መቼም ዘንድሮ ሙዚቃ ቤትና ቡቲክ መለየት ተስኖናል። ይኼኔ ነው ድንገት ጆሮዬ የገባው።
ምን? የአይጥ ዱለትና የጄሶ እንጀራ ሲሸጡ የነበሩ ተጠርጣሪዎች መለቀቃቸው። አሁን ይኼ ታዲያ ቀልድ መሆን አልነበረበትም? ፊክሺኔ መሆን አልነበረበትም? እንዴት በዚህች ድንቅ ምድር አብሮ መብላት፣ አብሮ መኖር፣ አብሮ መሞት በሚሰበክባት አገር እንዲህ ዓይነት ተፋልሶ እንሰማለን? ግን ተፋልሶ አልነበረም እንዴ? እሱም ኑሮአችን ነው። ብቻዬን በግርምት ፈዝዤ እንደቀረሁ ነው ከአላፊ አግዳሚው ከጽንፍ ጽንፍ የሚወነጨፉ አስተያየቶችን የሰማሁት። አንዱ፣ ‹‹እነሱ ሲታሰሩ በከተማው የአይጦች ቁጥር መብዛቱንና የጀሶ ገበያ መቀነሱን ከግምት በማስገባት ይሆናል፡፡ ወይም ለዚህ አመፀኛ ሕዝብ አይጥና ጀሶ ሲያንሰው ይሆናል ተብሎም ሊሆን ይችላል . . .›› ሲል ሌላው፣ ‹‹ሁልሽም በወረፋ በልተሽ አሁን እንትፍ እንትፍ ትያለሽ። አጣርተሽ አትበይም?›› እያለ ይሸልላል። በጣም ያስደነገጠኝ ግን ሦስተኛው አልፎ ሂያጅ ነው፡፡ ‹‹ዘራቸው ይጣራልን ሲል አልሰማሁም መሰላችሁ?›› ይላል? ለዚህ ነው ቀልድ የጠፋብኝ ጎበዝ። ዋ ቁልቁል ማሰብና ቁልቁል ማደግ!
ታዲያላችሁ ኮሚሽኔን ተቀባብዬ በጥንቃቄ ላስቀምጠው ወደ ቤቴ ስጣደፍ ብሄድ ማንጠግቦሽ ቤቱ እንደተዝረከረከ ለጥ ብላ ተኝታለች። ሰዓቴን ሳይ ከቀኑ ስምንት ሰዓት ይላል። እንግዲህ ተመልከቱ ይኼን እያየ እየሰማ ራሱ የኢትዮጵያን ዕድገት የሚጠራጠር አለ? ለነገሩ የእኛ እንቅልፍ በዕድገት የሚረዝም በረሃብ የሚያጥር አይደለም፡፡ እሱ በጥበቡ ሲሠራን በተፈጥሯችን ተኙ ብሎ ፈጥሮናል። ባሻዬ ይኼን አስተሳሰቤን ስለሚጋሩኝ፣ ‹‹የእኛ ጠላታችን ከድህነት ጎን ለጎን የሚቀሰቅሰን ብቻ ነው፤›› ይሉኛል፡፡ ዘንድሮ ደግሞ ቀስቃሽ በአየቅጣጫው የዘመተበት ሁኔታ ነው ያለው (ዕድሜ ለአገራችን የሚዲያ ወሬ የሌለ የሌለ አማርኛ ለምደን፣ ይኼው በጥንቱም በአሁን ጊዜ ሰውም መሳቂያ ሆነን ቀረን) ሁኔታ ብል በአንድ ወቅት በዜና አንድ ሮቦት አይቼ እንደነበር አስታውሳለሁ። ሮቦቷ ሴት ናት። ይገርማል እኮ እናንተ። እንደ ምዕራባውያን ኑሮ ግራ ያጋባን የለ? ተፈጥሮ ፆታ መዳድባ ቦታና ሥፍራ እያቀያየረች ስታዞርብን ከርማ ደግሞ፣ በጎን ሰው ሠራሹን ነገር ሴት ወንድ እያለች ፆታ ታድላለች።
ቆይ ግን ታዳዩና አዳዩ የሚገናኙበት ዘመን ሳይመጣ እንሞት ይሆን? ብቻ ወደ ጀመርኩት ልመለስና ያቺ እንስት ሮቦት ሥራዋ አዛውንቶችን ማጫወት ነው። አንድ ጋዜጠኛ ቃለ መጠይቅ ሲያደርግላት፣ ‹‹እንዲያውም ሥራዬ ማውራት ነው። በወሬ ዕጦት የተጎዱ ሰዎችን እያነጋገርኩ ማጫወት የሕይወቴ ግብ ነው፤›› ስትለው ያለ አስተርጓሚ ገባኝ። ደግሞ ለዚህ አስተርጓሚ ልጥራና ጉድ ልሁን? በቀደም ይኼው እንዲሁ ዓይነት ስለሕይወት ግብ የሚጫወትን ጎልማሳ ቃለ መጠይቅ እያዳመጥኩ አልገባህ ብሎኝ አንድ የሠፈር ልጅ ጠራሁና ምን እንደሚል ንገረኝ እለዋለሁ፣ ‹‹የሕይወቴ ለውጥ የመጣው ሚስቴ የሞተች ቀን ነው ይላል፤›› አይለኝ መሰላችሁ? ሰው እንዴት አካሉ ጎድሎ በቀጥታ ስለለውጥ ያስባል? ባንቀብርም እኮ ሕመሙ ይገባናል። የማይገባቸውማ ይኼው ‹ሙቱ እንሙት፣ ተኙ እንተኛ› እያሉ እያሉ በደንታ ቢስ ፉከራቸው የኢትዮጵያን እናቶች የመኖር ጉጉት ያደበዝዛሉ። ሰው ከታሪኩ ባይማር፣ ሲነገረው ባይገባው፣ ሲጨቀጭቁት ቢደክመው እንዴት ከጎረቤቱ መማር ያቅተዋል?!
በሉ ልንሰነባበት ነው። ብቻ የዚህችን ‹የሕይወቴ ለውጥ› የምትባል ቃላት እንዲህ በትንሽ ትልቁ አፍ መግነን ግርም እያለኝ፣ “ሰው ከሰውነት ወደ ወጥነት ተቀይሯል እንዴ ቆይ? እንዲህ ሕይወቱን መቀመም ትቶ በቅመማ ቅመም ስላቅ ያበደው?” ብዬ ሳልጨርስ ማንጠግቦሽ ትዝ አለችኝ። አስተኛኘቷ ደስ አላለኝም። ከመጮኼ በፊት አንዴ ልሞክራት ብዬ ነካ አደርጋታለሁ፣ ‹‹የቀሰቀሷቸውን ደንበኛ አሁን መነሳት አይችሉም። እባክዎ ከሰዓታት በኋላ እንደገና ይሞክሩ፤›› ብለኝ ተገላብጣ ተኛች። ደህና ከሆንሽስ ብዬ ከባሻዬ ልጅ ጋር ተያይዘን ወደ ግሮሰሪያችን አመራን። ምሁሩ የባሻዬ ልጅ የማንጠግቦሽን ኩመካ ሰምቶ ሲያበቃ፣ “አንዳንዱ እንቅልፍ እኮ ለበጎ ነው አንበርብር። ባንነቃ ባንቀሰቀስ የሚሻለን ጊዜ አለ። ሰሚ የለም እንጂ . . .፤” ሲለኝ፣ “አንዳንዴ ሳምንቱ ቅጣቱ ሲከብድ፣ ምንም አይሳካም ከእሑድ እስከ እሑድ፤” ብሎ አንዱ በአንድ ወቅት ያጨደው መከራ ትዝ አለኝ። ምነው የዘንድሮ ባሰ አልኩ። መነካት በማይገባን ጎናችን እየተነካን፣ መቀስቀስ በሌለብን ሰዓት እየቀሰቀሱን እኛም አቤት እያልን ከእሑድ እስከ እሑድ ከትውልድ እስከ ትውልድ፣ ከዓመት እስከ ዓመት ከሚሊኒየም ሚሊኒየም፣ እንዲሁም እስከ ዛሬ የተባላነው አይበቃም ጎበዝ? እስከ መቼ በእንቅልፍ ላይ እንቅልፍ? እስከ መቼ? እስከ መቼ? ከዓመት እስከ ዓመት፣ ከእሑድ እስከ እሑድ መና ይቀራል? ሌላው ቢቀር ለዕድሜ እንዘን! ሺሕ ዓመት ላይኖር ራሳችንንም አገራችንንም አናሰቃይ፡፡ መሰንበቻውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደነገሩን አቧራ ማስጨሱን ትተን አሻራችንን የሚያስቀርልን መልካም ነገር እንሥራ፡፡ ሰሚ የለም እንጂ ተናግረን ነበረ ብለን መጮህ አለብን እንዴ! መልካም ሰንበት!