Thursday, March 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበሱዳን የኢትዮጵያ አምባሳደር በስኳር ፋብሪካ ግንባታ ላይ የመከላከያ ምስክርነታቸውን ሰጡ

በሱዳን የኢትዮጵያ አምባሳደር በስኳር ፋብሪካ ግንባታ ላይ የመከላከያ ምስክርነታቸውን ሰጡ

ቀን:

የገንዘብ ሚኒስትሩ ስለጉዳዩ የሚያውቁት ነገር እንደሌለ በደብዳቤ ገለጹ

የአምባሳደሩን የመጓጓዣ ወጪ የቻሉት ተከሳሽ ናቸው

በኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን ከኦሞ ኩራዝ አምስት ስኳር ፋብሪካ ግንባታ ጋር በተያያዘ የሙስና ወንጀል ክስ በተመሠረተባቸው ወ/ሮ ሳሌም ከበደ፣ በመከላከያ ምስክርነት ተቆጥረው የነበሩት በሱዳን የኢትዮጵያ አምባሳደር ፍርድ ቤት ቀርበው የምስክርነት ቃላቸውን ሰጡ፡፡

የክስ ሒደቱን እያስቻለ በሚገኘው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 15ኛ ወንጀል ችሎት ቀርበው የመከላከያ ምስክርነት የሰጡት፣ አምባሳደር ሽፈራው ጃርሶ ናቸው፡፡

አምባሳደር ሽፈራው ቃለ መሃላ ከፈጸሙ በኋላ በተከሳሿ ጠበቃ በኮርፖሬሽኑ የስኳር ፕሮጀክቶች እንዴት ፋይናንስ እንደሚያደርጉ፣ ግንባታ የሚካሄድበትን ሥርዓትና ደንበኛቸውን ለክስ ያበቃቸው በኦሞ ኩራዝ አምስት ስኳር ፋብሪካ ግንባታ የተፈጸመ ወንጀል ስለመኖሩ እንዲያስረዱ በተያዘ ጭብጥ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

የመከላከያ ምስክሩ ከላይ ለቀረበላቸው ጥያቄ እንዳስረዱት ማንኛውም በቻይና መንግሥትና በቻይና ኩባንያዎች የሚሠሩ ፕሮጀክቶች የሚከናወኑት በድርድር ነው፡፡ የሥራውን ተነሳሽነት በመጀመርያ የቻይና ኩባንያዎች ያቀርባሉ፣ አዋጪነቱ በኢትዮጵያ በኩል ከገንዘብና ኢኮኖሚ ሚኒስቴር (የአሁኑ ገንዘብ ሚኒስቴር) ታይቶ ለስኳር ኮርፖሬሽን ይመራል፡፡ ኮርፖሬሽኑ በሁሉም አቅጣጫ ያለውን አሠራር ያይና ድርድር ካደረገና ስምምነት ላይ ከተደረሰ በኋላ፣ በድጋሚ ወደ ገንዘብ ሚኒስቴር እንደሚላክ አስረድተዋል፡፡

ገንዘብ ሚኒስቴር ከፋይናንስ አፈላላጊው የቻይና ኩባንያ በተያዘው ጉዳይ፣ ጃንዚ ጃንግሊያን ኢንተርናሽናል ኢንጂነሪንግ ካምፓኒ (JJIEC) ስለሚቀርበው የፋይናንስ መጠንና ግንባታ በሚጠናቅቅበት ጊዜ ከገንዘብ ሚኒስቴር ጋር ድርድር ካደረገ በኋላ፣ ውሳኔ ለማስጠት በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ሥር ለተቋቋመው ዓብይ ኮሚቴ (ፕሮጀክቶችን የሚከታተል ኮሚቴ) ተመርቶ እንደሚፀድቅና የሥራውን ክትትል ኮርፖሬሽኑ እንደሚረከብ አስረድተዋል፡፡ ኮርፖሬሽኑ በቦርድ ስለሚመራ ፕሮጀክቱን እየተከታተለ ለቦርዱ በየወሩ ሪፖርት ሲያደርግ፣ ቦርዱ ደግሞ ለዓብይ ኮሚቴው በማቅረብ ውሳኔ እንደሚያሰጥ አክለዋል፡፡

የተመረጠው የቻይና ኩባንያ ለአንድ ዓመት የሚቆይ የመግባቢያ ሰነድ ከቀድሞ የኮርፖሬሽኑ ዋና ዳይሬክተር ከነበሩት አቶ ዓባይ ፀሐዬ ጋር መፈራረሙን አስታውሰው፣ እሳቸው አቶ ዓባይን በ2006 ዓ.ም. ሲተኩ የኩባንያው የውል ጊዜ በመጠናቀቁ ‹‹የአራዝሙልኝ›› ጥያቄ ቀርቦ ሁሉም የሚመለከተው አካል ካወቀውና በኮርፖሬሽኑ የሕግ ክፍል አስተያየት ከሰጠበት በኋላ ውሉ መራዘሙን አስረድተዋል፡፡ በተራዘመለት ጊዜ ውስጥ ኩባንያው ፋይናንሱን ማምጣቱንም አክለዋል፡፡

ፋይናንሱን ያመጣው ኩባንያ ሥራውን ስለመቀጠሉና ራሱ ግንባታውን ስለመቀጠሉ ተጠይቀው፣ ‹‹እሱን አላውቅም›› ካሉ በኋላ፣ ፋይናንስ አፈላልጎ የሚያገኝ ኩባንያ ራሱ ግንባታውን እንደሚያካሂድ ግን ተናግረዋል፡፡ በድርድሩና በአሠራሩ የተጣሰ ሥርዓት ስለመኖሩ ተጠይቀው ‹‹የለም›› ብለዋል፡፡ ኩባንያው ያፈላለገው 85 በመቶ የሚሸፍነውን 550 ሚሊዮን ዶላር በሚመለከት፣ የቴክኒክና የፋይናንስ ድርድር ከማን ጋር እንደተደረገም እንደማያውቁ አምባሳደር ሽፈራው ለችሎቱ ገልጸዋል፡፡

ዓቃቤ ሕግ ድርድሩ ሲደረግ ስለመኖራቸው ጠይቋቸው እንዳልነበሩ፣ ፋይናንሱን ያመጣው ኩባንያ ሲመረጥ ስለማወቃቸውም ጠይቋቸው፣ ‹‹አላውቅም›› ብለዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ በማጣሪያ ጥያቄው ፋይናንሱ እንዴት እንደተገኘ ስለማወቃቸው ጠይቋቸው፣ ‹‹አላውቅም›› ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል በሁለተኛ የመከላከያ ምስክርነት የተቆጠሩት የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሸዴ ሲሆኑ፣ ለፍርድ ቤቱ በደብዳቤ ምላሽ መስጠታቸው በችሎት ተገልጿል፡፡

አቶ አህመድ ምስክርነት በሚሰጡበት ቀን ወደ ውጭ አገር እንደሚሄዱና በመከላከያ ምስክርነት ስለተጠሩበት ጉዳይ ምንም የሚያውቁት ነገር እንደሌለ መግለጻቸውን ፍርድ ቤቱ ገልጿል፡፡

የተከሳሽ ጠበቃ የሚኒስትሩ ምላሽ ሕግን ያላከበረና ሥነ ሥርዓታዊ እንዳልሆነ በማስረዳት፣ የሕግ የበላይነት በሁሉም ዜጎች ሊከበር እንደሚገባው ተናግረዋል፡፡ ሆኖም ግን ቀደም ብለው የመሰከሩላቸው መከላከያ ምስክሮች የሰጡት ምስክርነት በቂ ሆኖ፣ ውሳኔ እንዲሰጥላቸው በመግለጽ አቶ አህመድን እንደማይፈልጓቸው ተናግረዋል፡፡

 አምባሳደር ሽፈራው ጃርሶን ለመከላከያ ምስክርነት እንዲያመጣ ትዕዛዝ ተሰጥቶት የነበረው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ‹‹የትራንስፖርትና የተለያዩ ወጪዎችን አልሸፍንም›› በማለቱ፣ ተከሳሿ የትራንስፖርት 10,000 ብር በመክፈል እንዲመጡ ማድረጋቸው ታውቋል፡፡ ፍርድ ቤቱ መርምሮ ውሳኔ ለመስጠት ለሰኔ 17 ቀን 2011 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡    

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[የምክር ቤቱ አባል ላቀረቡት ጥያቄ በተሰጣቸው ምላሽ አቤቱታቸውን ለክቡር ሚኒስትሩ እያቀረቡ ነው]

ክቡር ሚኒስትር እየሆነ ያለው ነገር ትክክል ነው? ምነው? ምክር ቤቱም ሆነ...

የጉራጌ የክልልነት ጥያቄ ትኩሳት

ቅዳሜ መጋቢት 16 ቀን 2015 ዓ.ም. በጉራጌ ዞን ወልቂጤ...

አይ የእኛ ነገር!

የዛሬው ጉዞ ከጀሞ ወደ ፒያሳ ነው፡፡ መንገዱ ለሥራ በሚጣደፉ፣...

የዓለም ኢኮኖሚ መናጋት ለወቅታዊው የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ችግር ምክንያት ነው?

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ባለፈው ማክሰኞ መጋቢት 16...