ኮርፖሬሽኑ ግን ሠራተኞች ፈቃደኝነታቸውን አሳይተዋል ብሏል
ስኳር ኮርፖሬሽን ከለውጥ እንቅስቃሴዎቹ መካከል አንዱ በሆነው የወጪ ቅነሳ ሠራተኞች ደመወዛቸውን ጨምሮ የዓመት እረፍት፣ የትርፍ ሰዓት ክፍያና ልዩ ልዩ የጥቅማ ጥቅም ክፍያዎችን በመተው ኮርፖሬሽኑ ከገባበት ቀውስ እንዲወጣ ለማገዝ መስማማታቸውን ቢገልጽም፣ መሠረታዊ የሠራተኞች ማኅበር ግን ሐሰት እንደሆነ አስተባበለ፡፡ በሕግ አግባብ ሠራተኛውን በማይወክሉ የሥራ መሪዎች አማካይነት ስምምነት ተደርጓል ሲልም ኮርፖሬሽኑን ወቅሷል፡፡
ስኳር ኮርፖሬሽን በሥሩ የሚያስተዳድራቸው የስኳር ፋብሪካ ሠራተኞችን የሚወክሉ የሥራ መሪዎችን በመሰብሰብ፣ እያካሄዳቸው ስለሚገኙ የሪፎርም ዕርምጃዎች ሰሞኑን ገለጻ እየሰጠ ነው፡፡ ባለፈው ሳምንት በፊንጫአ፣ በወንጂና በመተሐራ ስኳር ፋብሪካዎችም ስብሰባዎች ተካሂደዋል፡፡ በመተሐራ ብቻ ከ8,000 በላይ ቋሚና ጊዜያዊ ሠራተኞች አሉ፡፡
በስብሰባዎቹ መወያያ ከነበሩ አጀንዳዎች መካከል ሠራተኞች በወጪ ቅነሳ መስክ ሊያደርጉ ስለሚችሏቸው አስተዋጽኦዎች ተደረጉ የተባሉት ይጠቀሳሉ፡፡ ለወጪ ቅነሳ ከሠራተኞች በኩል አስተዋጽኦ እንዲደረግባቸው ሐሳብ ከቀረበባቸው ጉዳዮች መካከል የዓመት እረፍት፣ የትርፍ ሰዓት ክፍያ፣ የምግብና የውሎ አበል ክፍያዎችና ሌሎችም ጥቅማ ጥቅሞችን ለመተው፣ ‹‹ሠራተኞች ፈቃደኛነታቸውን አሳይተዋል፡፡ የተስማማቸውና ፈቃዳቸውን የገለጹትም በራሳቸው አነሳሽነት ነው፤›› ሲሉ የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ወዮ ሮባ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
የወጪ ቅነሳ ሪፎርም ሥራው በኮርፖሬሽኑ እየተከናወኑ ካሉ ዘጠኝ ዋና ዋና የለውጥ ዕርምጃዎች አንዱ ነው ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ የዋናው መሥሪያ ቤት ሠራተኞች የወር ደመወዛቸውን ለመተው ጭምር ጥያቄ ቢያቀርቡም፣ ማኔጅመንቱ ግን ካለው የኑሮ ውድነት አኳያ በሌሎች ጥቅማ ጥቅሞች ላይ የተመሠረተ አስተዋጽኦ ማድረጉ እንደሚሻል በመግለጽ ውይይት ማካሄድ እንደጀመረ ገልጸዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር ውይይቱ ሲደረግም ሆነ ሠራተኞች አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ሲጠየቅ፣ በፈቃዳቸውና በፍላጎታቸው በመሆኑ መስጠት የሚፈልጉ ከሆነ ብቻ በስምምነት እንደሚደረግ ጠቁመዋል፡፡
ዋና ሥራ አስፈጻሚው ይህንን ቢሉም፣ ሪፖርተር ከመተሐራ ስኳር ፋብሪካ አንዳንድ ሠራተኞች የተገለጸለት ቅሬታ ግን ይህንን አያመላክትም፡፡ ሠራተኞች የዓመት እረፍታቸው፣ የትርፍ ሰዓት ክፍያቸውንና ሌሎችም ጥቅማ ጥቅሞቻቸውን መነሻ ያደረገ አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ጥያቄ እየቀረበላቸው የሚገኘው በኮርፖሬሽኑ በኩል እንደሆነ፣ ይህንንም ጥሪ ተቀብለዋል የተባሉት ሠራተኞችን በሕጉ መሠረት የማይወክሉ የሥራ መሪዎች ናቸው በማለት ኮንነዋል፡፡
ሠራተኞቹም ሆነ የሠራተኛ ማኅበሩ አመራር እንደሚሉት፣ በአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ ቁጥር 377/96 መሠረት የዓመት እረፍት ለመተው እንኳንና የሠራተኞች ተወካዮችና ማኅበራት ቀርቶ ባለመብቱ ሠራተኞች ራሳቸው መደራደር እንደማይችሉና በሕግም ተቀባይነት የለውም፡፡ የስኳር ኮርፖሬሽኑ የበታች ኃላፊዎች በተለይም ከቡድን መሪዎች በላይ ወይም ከመደብ 21 በላይ ያሉ ኃላፊዎች ባለፈው ሳምንት ስብሰባ ማካሄዳቸውን፣ ከዚህ በተጨማሪም ፎርማኖችና ከፎርማን በላይ ያሉ የሥራ መሪዎች በተለይ በመተሐራ ስኳር ፋብሪካ ሠራተኞችን ሰብስበው፣ ኮርፖሬሽኑ ስለከሰረ የአንድ ዓመት የዓመት እረፍታችሁን በፈቃደኝነት ስጡ ማለታቸውን ገልጸዋል፡፡
የስኳር ኮርፖሬሽን መሠረታዊ የሠራተኛ ማኅበር ዋና ጸሐፊ አቶ ወርቁ ሌንሲሳ፣ በአሁኑ ወቅት በአሥሩም የስኳር ፋብሪካዎች ውስጥ እየሠሩ ለሚገኙ ሠራተኞች በማኅበሩ አማካይነት መልዕክት መተላለፉን ገልጸዋል፡፡ የሠራተኞች ማኅበር ከኮርፖሬሽኑ ጋር የአንድ ዓመት የዓመት እረፍትን ጨምሮ፣ የትርፍ ሰዓት ክፍያም ሆነ ሌሎች እንደ ምግብ አቅርቦትና አበል ቅነሳም ሆነ መዋጮ ለማድረግ የተደረሰ ምንም ዓይነት ስምምነት እንደሌለ አስታውቀዋል፡፡
የዓመት እረፍት በተለይ በማንኛውም መንገድ ሠራተኞች በራሳቸው ፈቃድና ተነሻሽነት ስምምነታቸውን ቢገልጹ እንኳ በአሠሪና ሠራተኛ ሕግ መሠረት የተደነገገ መብት በመሆኑ ጥያቄው ቀድሞውኑ መቅረብ እንዳልነበረበት አቶ ወርቁ ገልጸው፣ ‹‹መደብ 13 እና ከዚያ በላይ ድልድል የሥራ መሪ ተብለው በኮርፖሬሽኑ ኃላፊዎች የተመደቡት ከአዋጁ ጋር የሚጣረስ ውክልና አላቸው፤›› በማለት፣ ሠራተኞች እንዲወያዩ የተደረገው በአዋጅ በተቀመጠው አግባብ ከሥራ እስከ ማሰናበት የሚደርስና ሠራተኛ የመቅጠር ኃላፊነት የሌላቸው በመሆናቸው፣ የሠራተኛ ማኅበሩ አለመግባባት ውስጥ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
ከሠራተኞች መዋጮ ማድረግ የሚፈልግ በግሉ ፈርሞ መስጠትና በግሉ መወሰን ስለሚችልባቸው ሁኔታዎችና አጠቃላይ የኮርፖሬሽኑን የሪፎርም አጀንዳዎች የሚያመላክቱ ውይይቶች ሲደረጉ መቆየታቸውን የሚገልጹት ዋና ሥራ አስፈጻሚው አቶ ወዮ፣ በአንዳንዶቹ ስብሰባዎች ይህ በተገቢውና በተሟላ መንገድ ለሠራተኞች ባለመገለጹ የተፈጠሩ አለመግባባቶች እንደነበሩ አምነዋል፡፡ ይህም ሆኖ ሠራተኞች ወጪ ቅነሳ ለማድረግ የሚኖራቸው አስተዋጽኦ፣ ከጠቅላላው የሪፎርም አጀንዳ አኳያ የአንድ በመቶ ድርሻ እንደማይዝ አስረድተዋል፡፡