የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሕገወጦች ላይ መረር ያለ ዕርምጃ አወስዳለሁ አለ
በአገር አቀፍ ደረጃ ሕገወጥ የመሬት ወረራ እየተባባሰ መምጣቱ በይፋ ተነገረ፡፡ በተለያዩ የአገሪቱ ከተሞች ውስጥም ሕገወጥ የመሬት ወረራ መባባሱ ተገልጿል፡፡ ይህ በተገለጸ ማግሥት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በተለይ በማስፋፊያ ክፍላተ ከተሞች በተደራጀ መንገድ፣ ለተለያዩ ልማቶች የሚውሉ መሬቶች በወረራ መያዛቸውን አስታውቋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር)፣ ከፀጥታ ተቋማትና ከክፍላተ ከተማ ሥራ አስፈጻሚዎች ጋር ባደረጉት ምክክር ከሁለት ሳምንት በኋላ በሕገወጦች ላይ መረር ያለ ዕርምጃ ይወስዳል ብለዋል፡፡
የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ከፌዴራልና ከክልል ከተውጣጡ የመሬት ዘርፍ ኃላፊዎች ጋር ከግንቦት 5 እስከ ግንቦት 8 ቀን 2011 ዓ.ም. ድረስ በመቐለ ከተማ ባካሄደው ስብሰባ፣ ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ታዜር ገብረ እግዚአብሔር በተለያዩ የአገሪቱ ከተሞች ሕገወጥ የመሬት ወረራ መባባሱን ገልጸዋል፡፡
‹‹በኢትዮጵያ የሚስተዋለውን ሕገወጥ የመሬት ወረራና ሕገወጥ የቤቶች ግንባታ በተመለከተ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ እስከ ወረዳ ኃላፊዎች ድረስ ያሉት መዋቅሮች፣ አገራዊ አጀንዳ አድርገው መንቀሳቀስ አለባቸው፤›› ሲሉ ሚኒስትር ዴኤታው መናገራቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡
ይህ ስብሰባ ከተካሄደ ከሳምንት በኋላ ምክትል ከንቲባ ታከለ በጠሩት የምክክር መድረክ፣ በአዲስ አበባ ከተማ የማስፋፊያ ክፍላተ ከተማ በሆኑት ቦሌ፣ አቃቂ ቃሊቲ፣ ንፋስ ስልክ ላፍቶና የካ ክፍላተ ከተሞች የተደራጀ የመሬት ወረራ መፈጸሙ ተመልክቷል፡፡
‹‹በሚቀጥሉት ሁለት ሳምንታት አልመን እናጣራለን፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ ሕገወጥ ግንባታ የገነቡ እንዲያፈርሱ፣ የማያፈርሱ ከሆነ አስተዳደሩ ያፈርሳል፤›› በማለት የገለጹት ምክትል ከንቲባው፣ ‹‹በተደራጀ መንገድ በተካሄደው የመሬት ወረራ እጁ ያለበት የመንግሥት አመራርም ሆነ ሠራተኛ ከሥራ ገበታ መባረር ብቻ ሳይሆን ተጠያቂም ይሆናል፤›› ብለዋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ በተለያየ ጊዜያት ‹‹ሕገወጥ የመሬት ወረራ›› ሲካሄድ የቆየ ቢሆንም፣ ምክትል ከንቲባው እንዳሉት ባለፉት ሦስት ሳምንታት የተካሄዱት የመሬት ወረራዎች በተደራጀ መንገድ የተካሄዱ ናቸው፡፡
‹‹ባለሀብቶች፣ የመንግሥት አስፈጻሚ አካላት፣ ደላሎችና የፖለቲካ አጀንዳ ያላቸው ጭምር የተሳተፉበት የመሬት ወረራና ሕገወጥ የቤቶች ግንባታ ተካሂዷል፤›› የሚል መረጃ በውይይቱ ወቅት ጎልቶ ተነስቷል፡፡
ግንባታው ሳይካሄድ መከላከል ለምን እንዳልተሠራ የክፍላተ ከተማ ሥራ አስፈጻሚዎች ሲገልጹ፣ ግንባታው የሚካሄደው ለቁጥጥር በማያመች ሰዓትና በበዓላት መሆኑንና የፍርድ ቤት ዕግድን በምክንያትነት አንስተዋል፡፡
‹‹386 ሕገወጥ ቤቶች ከመሠራታቸው በፊት የፍርድ ቤት ዕግድ ወጥቶባቸዋል፡፡ ከተሠሩ በኋላ ለማፍረስ ስንንቀሳቀስ ዕግድ የወጣባቸው በመሆኑ ለመከላከል አስቸጋሪ ሁኔታ ተፈጥሮብናል፤›› ሲሉ የቦሌ ክፍለ ከተማ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጥላሁን ፈቃዱ በውይይቱ ወቅት ተናግረዋል፡፡
ለወረራ ተጋልጠዋል የተባሉ ቦታዎች ኮንዶሚኒየም ቤቶች ሊገነቡባቸው የታቀደባቸው፣ ለተለያዩ ፕሮጀክቶች ግንባታ የተከለሉና የአርሶ አደሮች መሆናቸው ተገልጿል፡፡
ከ1997 ዓ.ም. ጀምሮ የፖለቲካ ትኩሳት በሚኖርባቸው ጊዜያት አግባብ ያለው አካል ሳይፈቅድ የሚያዙ ቦታዎች ቁጥር እንደሚጨምር መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡